ልዩ ጥቅም ወይስ ልዩ ግዴታ? (በተመሥገን ተሠማ አፍሬ)

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የሚያስችለውን አዋጅ አጽድቆ  ረቂቁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ድንጋጌ መሠረት ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊያገኝ የሚገባውን ልዩ ጥቅምና በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን የአስተዳደር ድርሻ ለመወሰን የወጣ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ክልሉ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ከተጠበቀለት ልዩ ጥቅም ጋር ተጋምዶ በክልሉና በክልሉ ነዋሪ አርሶ አደር ላይ ልዩ ግዴታም ጭምር ጥሏል፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማም በረቂቅ አዋጁ ላይ ልዩ ጥቅም ተብለው የተዘረዘሩት መብቶች በእርግጥም ልዩ ስለመሆን አለመሆናቸው፣ ለኦሮሚያ ክልል በልዩ ሁኔታ የተጠበቁት ግልጋሎቶችና መብቶች የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌና መርሕ በጠበቀ ሁኔታ በአዋጁ ሽፋን ያገኙ ማግኘት አለማግኘታቸው፣ በተጨማሪም የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ  አውጪ አካል በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በነዋሪው ማኅበረሰብ ላይ ልዩ ግዴታን የሚጥል ሕግ  የማውጣት ሥልጣን ስለመኖር ወይም አለመኖሩ ከሕገ መንግሥት ሙያ አኳያ መፈተሸ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከተሰማሩ ምሁራን የሚጠበቅ ዓብይ ተግባር መሆኑን በማመን ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከዚህ የሚከተለውን ሙያዊ አስተያየት አቅርቤያለሁ፡፡

የፌዴራሉን መንግሥት ሕገ መንግሥት ለማስፈጸም ሊወጡ የሚገባቸውን ሕጎች የማውጣት ሥልጣን ለፌዴራሉ መንግሥት ሕግ  አውጪ አካል የተሰጠ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር ይህንኑ ደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ ሥር የተጠበቀውን አዲስ አበባ ከተማ ለኦሮሚያ ክልል ሊሰጠው የሚገባውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ ዝርዝር ሕግ የማውጣቱ ሥልጣን ለፌዴራሉ መንግሥት ሕግ አውጪ አካል የተሰጠ በመሆኑ ክርክር የሚቀርብበት አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ ይህ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለፌዴራሉ መንግሥት ሕግ  አውጪ አካል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አዲስ አበባ ከተማ ለኦሮሚያ ክልል ልትሰጠው የሚገባውን ልዩ ጥቅም የሚደነግግ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ የኦሮሚያ ክልል ለአዲስ አበባ ከተማ ሊከፍል የሚገባውን ልዩ ግዴታም ጭምር በማጣመር አካቶ  ይዟል፡፡  የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሆነ አርሶ አደር ለደረሰበት ጉዳት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመጣጣኝ ካሳ ሊከፈለው እንደሚገባም ጭምር በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ሊያገኝ የሚገባውን ልዩ ጥቅም በመደንገግ ብቻ ሳይወሰን ልዩ ጥቅም ተቀባዩ የኦሮሚያ ክልልና የክልሉ ነዋሪ አርሶ አደር ለልዩ ጥቅም ሰጭው አዲስ አበባ ከተማ ሊከፍሉት የሚገባ ልዩ ግዴታንም  ከልዩ ጥቅሙ ጋር አጋምዶ ደንግጓል፡፡

ይህን ልዩ መብትና ልዩ ግዴታን መሠረት በማድረግ ለፌዴራሉ መንግሥት ሕግ  አውጪ አካል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ድንጋጌን ለማስፈጸም ለዚህ አካል በተሰጠው የማስፈጸሚያ ዝርዝር ሕግ የማውጣት ሥልጣን ወሰን ልክ መሆን ያለመሆኑን እንመልከት፡፡

በተለይም ደግሞ ይህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተገለጸውን ዓይነት ልዩ ግዴታም ጭምር በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚኖረው የክልሉ ማኅበረሰብ ላይ ይጥላል ወይ? የሚለው መከራከሪያ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን በልዩ ጥቅም (መብት) ውስጥ የተገመደ የልዩ ግዴታ ሕግ  የማውጣቱ ሥልጣንስ የማን ነው? ይህ ዓይነቱ ጉዳይስ ሕግ በማውጣት ሊከወን ይችል ይሆን? የሚሉትን ነጥቦች መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡

በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50/3/ ሥር የክልሎች ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት መሆኑንና የዚህ ምክር ቤት ተጠሪነትም ለመረጠው ሕዝብ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የዚሁ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 5 የክልሉ ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ሥር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል መሆኑን አስምሮበታል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ  አውጪ አካል በክልሎች የውስጥ ጉዳይ ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የሌለው መሆኑን ነው፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ የወጣው ረቂቅ አዋጅ የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ሳይሆን የክልሉ ነዋሪ የሆነውን አርሶ አደርም ጭምር በቀጥታ የሚመለከት ነው፡፡ ይህን ሐሳብ ተጨባጭ ለማድረግ በኦሮሚያ ክልልና በክልሉ ነዋሪ አርሶ አደር ላይ ልዩ ግዴታን የጣሉትን የረቂቅ አዋጁን ድንጋጌዎች በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የአዋጁን ተፈጻሚነት ወሰን የሚደነግገው የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 3 አዋጁ በአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ውስጥና እንደ አግባቡ በአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይም ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ስለሆነም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚኖረው የክልሉ ነዋሪ ይህን አዋጅ የመፈጸምና የማስፈጸም ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡

የአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀጽ 8 ደግሞ የከተማው አስተዳደር ከክልሉ ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የሚያገኘው የመጠጥ ውኃ፣ ምንጭ ጉድጓድ የሚቆፍርበት፣ ግድቡ የሚለማበት ወይም የውኃ መስመሩ አቋርጦ የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞችና ቀበሌዎች በአስተዳደሩ ወጭ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ የክልሉን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውኃ የመጠቀምና ከዚህ ለሚገኘው የመጠጥ ውኃ ምንጭ ጉድጓድ የሚቆፍርበት፣ ግድብ የሚያለማበት፣ የውኃ መስመሩ አቋርጦ ወደ ከተማ አስተዳደሩ የሚያልፍበት መሬት ከክልሉ መንግሥት የማግኘት ልዩ መብት አለው ማለት ነው፡፡

የዚህን ድንጋጌ ጽንሰ ሐሳብ በሌላ አቅጣጫ ብናጤነው የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በክልሉ ከሚገኘው የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ ለአዲስ አበባ ከተማ የመስጠት ግዴታና በተለይም ደግሞ ከክልሉ ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የሚገኘውን ውኃ ለማውጣት አዲስ አበባ ከተማ የምንጭ ጉድጓድ የሚቆፍርበት፣ ግድብ የሚያለማበትና ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚገባው ውኃ መስመር አቋርጦ የሚያልፍበት ቦታ የመስጠት ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በከተማው ዙሪያ የሚኖረው አርሶ አደር የመሬት ይዞታው ለዚህ አገልግሎት የሚመረጥ ቢሆን ካሳ ተቀብሎ ይዞታውን መልቀቅ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

በተጨማሪም የአዋጁ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 ድንጋጌዎች በቅደም ተከተል የክልሉ መንግሥት ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት የሚውሉ የግንባታ ማዕድናት ማግኛ ስፍራዎችና ለአዲስ አበባ ከተማ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማከሚያ፣ ማስወገጃና መልሶ መጠቀሚያ ቦታዎችን ክልሉ ለከተማ አስተዳደሩ የመስጠት ግዴታን ያካትታል፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች በቀጥታ የክልሉን መንግሥትና  ነዋሪ ሕዝብ የሚመለከቱና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የማዕድን ቦታዎችን ጨምሮ የክልሉን መሬት መጠቀምን፤ በዚህ አጠቃቀም ከይዞታቸው የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ያላቸውን ካሳ የማግኘት መብት የሚመለከቱ በመሆናቸው እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለክልሉ ምክር ቤት እንጂ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ አውጪ አካል አለመሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹ የጋራ ጉዳዮች ሊዳኙ የሚገባቸው በዚህ ሁኔታ በፌዴራሉ መንግሥት ሕግ አውጪ አካል በሚወጡ የአንድ ወገን ሕጎች ሳይሆን የፌዴራሉ መንግሥትና የክልል መንግሥታት ወይም የከተማ አስተዳደሩና የክልሉ መንግሥት በሚያደርጉት ድርድር ወይም ስምምነት ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ሁኔታ በሁለቱ አካላት የተደረገው ስምምነት በሁለቱም ምክር ቤቶች ተቀባይነትን ካገኘ በኋላ በሁለቱም አካላት የሚፈጸም ይሆናል ማለት ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ አውጪ አካል የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊያገኘው የሚገባውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም፣ ይህ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ግን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ ድንጋጌና ጽንሰ ሐሳብ ጋር በሚቃረን ሁኔታ ከልዩ ጥቅሙ ይልቅ ሚዛን የሚደፋው ልዩ ግዴታን በኦሮሚያ ክልልና የክልሉ ነዋሪ በሆነው አርሶ አደር ላይ የሚጥል በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ የክልል አስተዳደሩ ሥልጣን የሆነውን የኦሮሚያ የውስጥ ጉዳይ ሁሉ ያካተተ መሆኑ ገሃድ ነው፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ በክፍል አንድ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ሥር ልዩ ጥቅም ለሚለው ቃል በሰጠው ትርጉም በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉት፣ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተዳድሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ያትታል፡፡ ይህ ትርጉም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ ድንጋጌ ምንም ነገር ሳይጨመር ሳይቀነስ  በቀጥታ የተወሰደ ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ይህ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉት በማለት የደነገገ ሲሆን፣ በተጨማሪም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተዳድሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚለው የሕገ መንግሥቱ ጠቅላላ ሐሳብ በረቂቅ አዋጅ በግልጽ አብራርቶ ሊቀመጥ ይገባው ነበር፡፡ በተለይም ‹‹የመሳሰሉትን›› በሚለው አገላለጽ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው አገልግሎቶችና መብቶች እንዲሁም ‹‹ሁለቱን የሚያስተዳድሩት አስተዳደራዊ ጉዳዮች›› የትኞቹ እንደሆኑ ተለይተውና ግልጽ የሆነ ትርጉም ተሰጥቷቸው አመላካች በሆነ ሁኔታ ሊደነገጉ ይገባ ነበር፡፡

አዋጆች ጠቅላላ የሆኑትን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የሚወጡ በመሆናቸው በሕገ መንግሥቱ የተመለከተውን ጠቅላላ ሐሳብ በግልጽና በዝርዝር መደንገግ ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ረቂቅ ሕግ ‹‹የመሳሰሉት›› የሚለው ሐረግ በአዋጁ ትርጉም ተሰጥቶት በልዩ ጥቅሙ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸው ነገሮች ተዘርዝረው ያልተቀመጡ በመሆናቸው ግጭቶች በተፈጠሩ ቁጥር ትርጉምን የሚሻ ጥቅል ሐሳብ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ጥቅም ፈላጊው አካል ‹‹የመሳሰሉት›› የሚለውን ትርጉም በመጠቀም በዚህ ውስጥ ሊካተት ይገባዋል ብሎ የሚያስበውን መብት ቢጠይቅና ጥቅም ሰጭው አካል ደግሞ ይህ ዓይነቱ ጥቅም በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአዋጁ አልተካተተም የሚል ክርክር ቢያነሳ፣ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚሻ ስለሚሆን ተመልሶ ወደ ተርጓሚው አካል መሔዱ አይቀሬ ነው፡፡

ማስፈጸሚያ ሕጎች የሚወጡት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተመለከቱትን ጠቅላላ ነገሮች በግልጽ በመዘርዘር ለዚህ ጠቅላላ ለሆነው ድንጋጌ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም ሕግ አውጪው አካል በዚህ ረቂቅ ሕግ  የሕገ መንግሥቱን ጠቅላላ ድንጋጌ መተርጎምና በልዩ ጥቅሙ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን የአገልግሎት አቅርቦትና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ቢያንስ ቀሪዎቹን ሊያመላክት በሚችል ሁኔታ መዘርዘር ሲገባው፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ዓረፍተ ነገር በቀጥታ መውሰዱና ልዩ ጥቅሞቹን በደፈናው ልዩ ጥቅሞች በማለት ማለፉ፣ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ ጉልህ ችግር የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የመብት ተቀባዩን አካል ልዩ መብቶች ግልጽና ወጥ በሆነ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ያውካል፡፡

የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 በተደነገገው መሠረት የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ሊያገኝ የሚገባውን የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ ሊነሱ የሚችሉ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ኦሮሚያ ክልል በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀለትን ልዩ ጥቅም መደንገግ  መሆኑን አስቀምጧል፡፡

ከዓላማው መረዳት የሚቻለው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ውኃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ሕክምና፣ ትምህርት፣ መዝናኛ ወዘተ. የመሳሰሉትን የአቅርቦቶች ግልጋሎት ማግኘትና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም የሚያስችል ልዩ መብት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው  መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ማለትም በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኘውን የአዲስ አበባ ከተማን በማስተዳደር ረገድ የኦሮሚያ ክልል የራሱ ድርሻ ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ፣  ከላይ የተገለጸውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ሥራ ላይ ለማዋል እንዲቻል ለኦሮሚያ ክልል ያስጠበቀውን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ ከደነገጋቸው ድንጋጌዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ በረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት አንቀጽ 4 ሥር የተመለከተው የትምህርት አገልግሎት፣ በአንቀጽ 5 ሥር የተመለከተው የጤና አገልግሎትና በአንቀጽ 6 ሥር የተመለከቱት የባህል፣ ቋንቋና ሥነ ጥበብ አገልግሎቶች ናቸው፡፡

የትምህርት አገልግሎትን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአፋን ኦሮሞ የሚማሩበት የትምህርት ተቋማት በከተማ አስተዳደሩ ወጭ እንደሚደራጅ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49/5/ ድንጋጌ ልዩ ጥቅም የሰጠው ለኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በመሆኑ፣ ይህ የትምህርት አገልግሎትም ለዚሁ ማኅበረሰብ መሰጠት ነበረበት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖረው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአፋን ኦሮሞ የሚማሩባቸውን የትምህርት ተቋማት የማዘጋጀት ኃላፊነት ወትሮውንም ቢሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዴታ በመሆኑ፣ ይህን የአስተዳደር ግዴታውን መወጣት ለኦሮሚያ ክልልና ለነዋሪው ማኅበረሰብ እንደተሰጠ ልዩ ጥቅም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖረው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአፋን ኦሮሞ መማር ፍላጎት ካላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን የመብት ጥያቄ የመመለስ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም ይህ በራስ ቋንቋ የመማር ሕገ መንግሥታዊ መብት ልዩ መብት ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የሌለ ማለት ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአስተዳደር ክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት በቋንቋቸው የሚማሩበት የትምህርት ተቋማት በማዘጋጀት ከአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ሁኔታ ጥቅም የማግኘት መብት የተሰጠውን የኦሮሚያ ክልልንና የክልሉን ነዋሪ ማኅበረሰብ ልዩ ጥቅም በሕገ መንግሥቱ በተረጋገጠው መሠረት ረቂቅ አዋጁ አስጠብቋል ማለት አያስችልም፡፡

ይህ ዓይነቱ ግልጋሎት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለሚገኙት የኦሮሚያ ክልል ዞኖችና ለነዋሪው ማኅበረሰብ በሚኖርበት ቀዬ ሊሰጥ የሚገባው ሲሆን፣ ዓላማውም የከተማ አስተዳደሩንና የክልሉን ነዋሪ በዚህ መንገድ በማስተሳሰር ተቀራርበውና ተረዳድተው የሚሠሩበትን መልካም ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የጤና አገልግሎትም ቢሆን ከትምህርት አገልግሎቱ የተለየ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ነዋሪዎች እንደማንኛውም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በከተማው አስተዳደሩ በሚተዳደሩ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕግ መረጋገጡ እስካሁን በነበረው ሁኔታ ሲከወን የቆየ ተግባር ልዩ መብት ተብሎ መጠቀሱ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ከየትኛውም አካባቢ ወደ እነዚህ የሕክምና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚሔድ የማንኛውም ብሔረሰብ አባላት ተቋማቱ የሚጠይቁትን መሥፈርት ማሟላት እስከቻለ ድረስ ሕክምና አይከለከልም፡፡ የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት ሰብዓዊ መብት በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ለአንድ ብሔረሰብ ብቻ የሚሰጥ ልዩ ጥቅም ተብሎ ሊወሰድም አይገባም፡፡

የጤና አግልግሎት ልዩ ጥቅም ሊሆን የሚችለው ከትምህርት አገልግሎቱ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ የከተማ አስተዳደሩ በዙሪያው ለሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ማኅበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ የሕክምና መስጫ ተቋማትን መገንባትና የሕክምና ቁሳቁሶችንና መድኃኒቶችን ማቅረብና አገልግሎቱን ተጨባጭና ተደራሽ በማድረግ እንጂ በከተማ አስተዳደሩ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት ለዚያውም እንደማንኛውም የክልሉ ነዋሪ በመስጠት ሊሆን አይችልም፡፡

የባህል፣ የቋንቋና የሥነ ጥበብ አገልግሎቶችን የሚመለከቱት ልዩ ጥቅሞችም ቢሆኑ ከላይ ከተመለከተው ሁኔታ የተለዩ አይደሉም፡፡ እነዚህን አግልግሎቶች የተመለከቱት ልዩ ጥቅሞች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለሆነው የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላት የተሰጡ በመሆናቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ለሚገኘው የክልሉ ነዋሪ የተሰጡ ልዩ መብቶች ወይም ጥቅሞች ተደርገው  ሊወሰዱ የሚችሉበት ምንም ዓይነት  ሕገ መንግሥታዊ ምክንያት የለም፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለልዩ ጥቅም ተቀባዩ ክልል ከሰጣቸው ልዩ ጥቅሞች በተነጻጻሪነት የተሻለ ሊባል የሚችለው በአዋጁ ክፍል ሦስት ሥር የኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ልዩ ጥቅምን የሚመለከተው ነው፡፡ በዚህ ክፍል የመሬት አቅርቦት፣ የውኃ አቅርቦት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የሥራ ዕድል፣ የገበያ ቦታ አቅርቦትና የኮንዶሚኒየም ቤት ተጠቃሚነት ልዩ ጥቅሞች ተካተዋል፡፡ ምንም እንኳን ረቂቅ አዋጁ እነዚህን የኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ልዩ ጥቅሞች፣ ለጥቅም ተቀባዩ ክልልና ማኅበረሰብ የሰጠበት አግባብ ‹‹ይደረጋል›› በሚል ያልተቋጨ ድምዳሜ አንጠልጥሎ የተዋቸው በመሆኑ የእነዚህ ልዩ ጥቅሞች ተፈጻሚነት ከፈተና እንደማይጸዳ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ክፍል ሥር የተደነገጉት ልዩ ጥቅሞች ከዚህ በላይ ከዳሰስናቸው ጋር ሲነጻጸሩ የአርቃቂው ክፍል የተሻለ ትጋት የተንጸባረቀባቸው መሆኑን መመስከር ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ረቅቅ አዋጁ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 አማካይነት ለኦሮሚያ ክልል የሰጠውን ልዩ ጥቅም አሟልቶ ያልሰጠና ይልቁንም ለክልሉና ለክልሉ ነዋሪ ኀብረተሰብ ሊረጋገጥ የሚገባውን ልዩ መብት በተለመደው ሁኔታ በብሔረሰብ ግርዶሽ ከልሎ ለማለፍ የሞከረ ነው፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ኦሮሚያ ክልልና የክልሉ ነዋሪ አርሶ አደሮች ካገኙት ልዩ ጥቅም ይልቅ የተጣለባቸው ልዩ ግዴታ ሚዛን ይደፋል፡፡ ልዩ ጥቅም ሰጭው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልዩ ጥቅም ተቀባይ፣ ልዩ ጥቅም ተቀባይ የነበረው የኦሮሚያ ክልል ደግሞ ልዩ ጥቅም ሰጭ በመሆን ቦታቸውን ተቀያይረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የክልሉ አስተዳደር በዚህ ከእምብርቱ ላይ በተመሠረተ የፌዴራል መንግሥት ከተማ ላይ ሊኖረው የሚገባውን የአስተዳደር ድርሻ እንኳን አላገኘም፡፡ ይህ ዓይነቱን መብት አዋጁ የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም በደፈናው አልፎታል፡፡

በመሆኑም ሕግ አርቃቂው የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሆነ ሕግ አውጪው የፌዴራል መንግሥቱ ፓርላማ ረቂቅ አዋጁን በጥንቃቄ በመፈተሽ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ልዩ ጥቅም ሳይሸራረፍና ልዩ ግዴታ በላዩ ላይ ሳይሸረብበት ለጥቅም ተቀባዩ የኦሮሚያ ክልል በመስጠት ለአዲስ አበባ ከተማ ሁለንተናዊ ዕድገት ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባዋል እላለሁ፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን በታማኝነት በመወጣት በተንሻፈፉ ሕጎች ሳቢያ ሊከሠት የሚችለውን አገራዊ ቀውስ ከወዲሁ ሊከላከል እንደሚገባም በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ፡፡


ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ
አዘጋጁ፡- ጸሐፊው ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ሕግ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው temesgent1998@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡