“የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ!”

የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 29 እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ “የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ ነፃነት” እንዳለው ይደነግጋል። በአንቀፅ 30 ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ “የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታን የመግለፅ መብት አለው” ይላል። ነገር ግን፣ ባለፉት አመታት እንደታየው ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና የመብት ተሟጋቾች ለእስርና ስደት ተዳርገዋል። በተመሣሣይ፣ ባለፉት አስርና አስራ አምስት አመታት እንደታዘብነው፣ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ዜጎች ውስጥ የተወሰኑት በሞት፣ በአካል ጉዳትና በእስራት ምክንያት ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል።

በ2015 ዓ.ም (እ.አ.አ.) የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን (CPJ) ባወጣው ሪፖርት መሠረት ኤርትራ በነፃ ሚዲያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ረገድ ከዓለም አንደኛ ናት። ለምሳሌ፣ እ.አ.አ. ከ2010 ጀመሮ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 10 የሚጠጉ ጋዜጠኞች ስታስር፣ 32 የሚሆኑት ደግሞ ከሀገር ተሰድደዋል። ከኤርትራ ቀጥላ ኢትዮጲያ በሁለተኝነት ትከተላለች። በሪፖርቱ መሰረት፣ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለእስር ከተዳረጉት ውስጥ አስር (10) ጋዜጠኞች አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ 57 ጋዜጠኞች ደግሞ ሀገር ጥለው ተሰድደዋል። በሱማሊያና ደቡብ ሱዳን ያለው ደግሞ ከኤርትራና ኢትዮጲያ ጭራሽ የባሰ ነው። ለምሳሌ፣ በሶማሊያ ከ1992 – 2015 (እ.አ.አ.) ባሉት አመታት ውስጥ 42 ጋዜጠኖች ተገድለዋል። በደቡብ ሱዳን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ብቻ 7 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።

እንደ ኤርትራ መንግስት ያለ ሕገ-መንግስት ሀገርና ሕዝብን መምራት አንድ ነገር ነው። እንቆቅልሽ የሚሆነው ግን እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ሀገራት ስራና አሰራር ነው። በአንድ በኩል የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ ነፃነት እና የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታን የመግለፅ መብት በሕገ-መንግስቱ ዋስትና እንደተሰጠው ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሃሳብና አመለካከታቸውን የሚገልፁ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያንና ፀኃፊዎችን፣ እንዲሁም ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ የወጡ ዜጎችንና የሰልፉ አስተባባሪዎችን ለሞት፥ ስደትና እስር ይዳርጋሉ። እንዲህ ያለ “የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” ግራ ያጋባል፡፡

 

“የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” ባለበት ሁሉ የመንግስታቱ ስራና አሰራር አንድ ዓይነት ነው። ሁሉም በሕገ-መንግስታቸው ላይ ዜጎች የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ ነፃነት እና የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታን የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብት አንዳላቸው ይገልፃሉ። ከዚያ ደግሞ እነዚህን ሁለት ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚገድቡ አዋጆች፥ መመሪያዎችና ደንቦች ያወጣሉ። በእንካ-ግን አትንካ ፖለቲካ በነፃነት የመናገርና የመፃፍ፣ እንዲሁም የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብት እንዳለህ ይነገርሃል። ነገር ግን፣ “በዚህ አዋጅ፥ መመሪያ ወይም ደንብ መሰረት ከላይ የተጠቀሱትን ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን ተግባራዊ ማድረግ አትችልም” ይሉሃል።

በፅሁፉ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በኢ.ፊ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 29 እና 30 ላይ በግልፅ ተደንግገዋል። ነገር ግን፣ በ2001 ዓ.ም የወጣው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ እነዚህን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የሚገድብ ነው። ስለዚህ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሞከሩ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፣ ፀኃፊዎችን፣ የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ ለእስራትና ስደት እየተዳረጉ ይገኛሉ። ይህ ግን እንደ ኢትዮጲያ አምባገነን መንግስት ባለበት ሀገር ሁሉ የተለመደ የጭቆና ስልት ነው።

በኢትዮጲያ የማህብረሰቡን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ “Anti-Terrorism Law (2009)” & “Media Law” አለ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጲያ፤ በስዋዚላንድ (Swaziland) ¨Suppression of Terrorism Act (STA)”; በዝምባብዌ (Zimbabwe) “Access to Information and protection of Privacy (2002)” እና “Public Order & Security Act (POSA)”; በአንጎላ (Angola) “State Security Law” እና “Presidential Decree (2014)”፣ እንዲሁም በዩጋንዳ (Uganda) “Public Order Management (Act)”; በዛምቢያ ደግሞ ከቅኝ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ በስራ ላይ ያለው ¨Public Order Act (1955)”፣ …ወዘተ። እነዚህ አዋጆች፥ መመሪዎችና ደንቦች በሙሉ በሀገራቱ ሕገ-መንግስት ላይ የተደነገጉትን ሃሳብና አመለካከትን የመግለፅ ነፃነት እና የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በቀጥታ የሚገድቡ ናቸው።

የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካዊ አስተዳደር የአምባገነናዊ መንግስት (tyranny) ዋና መለያ ባህሪ ነው። የአምባገነናዊ መንግስት ስራና ተግባር የሚመራው በፍርሃት ነው። ሁሉም አምባገነኖች ሀገር የሚመሩት በፍርሃት-በማስፈራራት ነው። ስለዚህ፣ “የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” መሠረታዊ ምክንያቱ የአምባገነኖች ፍርሃት ነው። “አምባገነኖች ለምን ይፈራሉ?” የሚለውን ደግሞ ነገ እንመለስበታለን።