“እኛ ወደብ መች ቸገረን” ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ከዘመን መጽሔት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገዋል። እስካሁን ድረስ ቃለመጠይቁን በሶስት ተከታታይ ክፍሎች አቅርቧል። በሶስተኛው ክፍል ከቀረበው ውስጥ ዶ/ር አርከበ ከዘመን ለቀረበላቸው “ግንቦት 20 ኤርትራንም ወደብም አሳጥቶናል የሚሉ ወገኖች አሉና ለእነዚህ ወገኖች ምላሽዎ ምንድን ነው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አስገራሚና አነጋጋሪ ሆኖ አግኝተንዋል፡፡ በመሆኑም፣ ጥያቄውንና የተሰጠውን ምላሽ ከመፅሄቱ ድረገፅ ላይ እንደሚከተለው ወስደናል፡፡ ******

ዘመን፡- ግንቦት 20 ኤርትራንም ወደብም አሳጥቶናል የሚሉ ወገኖች አሉና ለእነዚህ ወገኖች ምላሽዎ ምንድን ነው?

ዶክተር አርከበ፡- ስለ ወደብ የሚያነሳ ነገር ግን ስለ ሕዝብ የማያነሳና የማያስብ ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ነው ስለ መሬት የሚያነሳው። አገር ማለት ሕዝብ ነው። ስለሆነም ስለ ሕዝቦች በምናስብበት ጊዜ የኤርትራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ነው መወሰድ ያለበት።

የኤርትራ ሕዝብ ምን ይፈልጋል? ለብዙ ዓመት በጦርነት ውስጥ የቆየ ሕዝብ ነው፤ ከ30 ዓመታት በላይ። ከኢትዮጵያ መገንጠል እንፈልጋለን አሉ። ይሔንን በማየት ኢህአዴግ ጦርነቱ መራዘም የለበትም ብሎ ከድል በኋላ ዓመትም ሳይሞላው ሪፈረንደም እንዲካሔድ አደረገ። በዚያን ወቅት እንደ ኤርትራ ሕዝብ ተመሳሳይ ጥያቄ የነበራቸው ሕዝቦች ነበሩ፤ እንደ ዩጐዝላቪያ ያሉ። እናም የዚያን ጊዜ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፈረንደሙን እንዲመራ ነበር። በዚህም 99 በመቶ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብ ነፃ ኤርትራን እንፈልጋለን አለ። ሕዝቡ ፍላጐቱን በድምፅ አረጋገጠ ማለት ነው። የሕዝቡ ፍላጐት ደግሞ መሟላት አለበት።

ዴሞክራሲ ማለት ለሕዝብ መቆም ማለት ነው። ማነው የመጀመሪያ አገር ኤርትራን እንደ አገር የተቀበለው? የኢትዮጵያ መንግሥት ነበር። ያ ሆኖ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል። ስለዚህ ያንን ያደረግነው ከሰላም፣ ከዴሞክራሲ፣ ከሕዝቦች መብት ማረጋገጥ አንፃር ነውና ይሔ መሆኑ ተገቢ ነው።

ግን ዋናው ነጥብ ምንድንነው “ወደብ ልማት ያመጣል” ብለው የሚያስቡ ሰዎች ስለ ኢኮኖሚ ልማት ምንም የማይገባቸው ሰዎች ናቸው። በአካባቢያችን ሠፋፊ ወደብና የባህር ዳርቻ ያላቸው አገሮች እነማን ናቸው? አንዷ ሶማሊያ ናት። ሁለተኛዋ ማናት? ኤርትራ ናት። ሁለቱንም እንያቸው በጥፋት ሂደት ያሉ አገሮች ናቸው። ሶማሊያ ግን አሁን በተሻለ እንቅስቃሴና መረጋጋት ውስጥ ናት። ኢኮኖሚ ልማት በእነዚህ አገራት የለም።

“እኛ ወደብ መች ቸገረን”

ስለዚህ ልማትና ዕድገትን የሚያመጣው ወደብና የባህር ዳርቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ያለ ማየት አስተሳሰብ ምንጭ ነው። እኛ ወደብ መች ቸገረን፡፡ በጂቡቲና በበርበራ መጠቀም እንችላለን። የኤርትራም ሁኔታ መቀየሩ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ለዘለዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም።

በእኔ ግምት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ። የኤርትራን ወደብ እንጠቀማለን። የኬንያን ወደብ መጠቀም እንችላለን። ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መስመር ለመገንባት ታቅዷል። የሱዳንንም እንጠቀማለን። ቢቻል ወደብ ቢኖረን ጥሩ ነበር ግን የሁሉም መቋጫና መፍትሔ እርሱ ነው ማለት አይደለም። የሚያመጣው መሠረታዊ ለውጥም የለም በእኔ እምነት።

በውጭ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር በሚዲያ ሳይ ነበር። ከተቃዋሚዎች አንዱ “እንዴት ብለን ነው የኢትዮጵያን ውሃ ለጅቡቲ የምንሰጠው?” የሚል ሃሳብ ነው ያነሳው። እነዚህ ሰዎች በእኔ ግምት ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው አይገባኝም።

ውሃ ልከን ገቢ ብናገኝ ምንድን ነው ችግሩ? የኤሌክትሪክ ኃይል ልከን ገቢ እንደምናገኘው ሁሉ ውሃም ልከን ገቢ ብናመጣ ጉዳት የለውም ጥቅም እንጂ፡፡ ውሃ መላክ ነዳጅ ከመላክስ ምን ልዩነት አለው? ምንም ልዩነት የለውም። እና የዚህ ሰው አስተሳሰብ ልማታዊ አስተሳሰብ ነው? ጅቡቲ ያለው ሕዝብ ውሃ እየፈለገ ውሃ የጠማውን ሰው ውሃ መከልከል ተገቢ ነው? በባህላችንስ ይሔ አለ? ስለዚህ የሚነሱ ነጥቦች በጣም አሳፋሪ ናቸው።

እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ዙሪያ የእይታቸው አድማስ መለወጥ አለበት። ጊዜው ግን አልፏቸው ሔዷል። አጀንዳው ተቀይሯል። እያወሩ ያሉት ግን ከአስር ዓመት በፊት የነበረ አጀንዳ ነው። እና ችግሩ የአቋምና የአስተሳሰብ ችግር ነው።