“ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ”: የኢህአዴግ ጉራ እና ሥራ

ባለፉት እስር አመታት “የሀገራችን ኢኮኖሚ በ11% አደገ፥ ተመነደገ” ሲባል “እሰይ…እንዳፋችሁ ያድርግል!” ብለን ዝም አልን። በGTP-I የእቅድ ዘመን “ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ለመገንባት መሰረት እንጥላለን… በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የማኑፋክቸሪግ ዘርፉ በ25% ማደግ አለበት” ሲሉን “መልካም” ብለን ለውጡን በጉጉት መጠበቅ ጀመርን። እቅዱ ተለጠጠ… ተቀደደ… ሲሉ ከርመው ከአምስት አመት በኋላም “ኢኮኖሚው በ10.6% ብቻ አድጓል” አሉንና ዝም።

ቆይ..ምነው “መዋቅራዊ ለውጥ” ምናምን ብላችሁን ነበር’ኮ፡፡ “ከጠቅላላው የሀገሪቱ የምርት መጠን ውስጥ የኢንዱስትሪው ድርሻ ስንት ሆነ?” ብለን ስንጠይቅ “አይ እንደስትሪው እንኳን ቀድሞ ከነበረበት 12% ወደ 14% ብቻ ነው ያደገው” ብለውን እርፍ። “ይቺም ቂጥ ሆና ለሁለት ተሰነጠቀች” እንደሚባለው የ2% ጭማሪ ለሦስት ተሰነጠቀች። ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ጭማሪ የመጣው ከግንባታው ዘርፍ (Construction sector) ሲሆን የተቀሩት የማምረቻ ዘርፍ (Manufacturing sector) ባለበት ቆሟል፣ የአነስተኛ ማምረቻ ተቋማት (Small-scale manufacturing enterprises) ድርሻ ደግሞ ጭረሽ ቀንሷል (ለዝርዝሩ GTP-I አፈፃፀም ሪፖርትን ይመልከቱ) 

በአንድ ሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ ለመገንባት፤ አንደኛ፡- ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ወደ መካከለኛና ትላልቅ ተቋማት ደረጃ ሲያድጉ፣ ሁለተኛ፡- ትላልቅ የሀገር ውስጥና የውጪ ድርጅቶች በዘርፉ ሰሰማሩ ነው። ላለፉት አስር አመታት ኢኮኖሚው በ11% አደገ እየተባለ የኢንዱስትሪ ክፍለ ኢኮኖሚ ከነበረበት ፈቀቅ ያላለው እነዚህን መሠረታዊ ለውጦች ማምጣት ስላልቻለ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት አመታት “ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ እንገነባለን!” ሲል ኖሮ የኢህአዴግ መንግስት ዛሬ ደግሞ “በቀጣይ አስር አመታት ውስጥ በኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር እናደርጋታለን” ማለት ጀምሯል። ዛሬ ግን ለኢህአዴግ አመራሮች፣ “የኢንዱስትሪ ልማት የሚመጣው በስራ እንጂ በጉራ አይደለም” ብሎ እቅጩን መናገር ያስፈልጋል።

የኢህአዴግ መንግስት “ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እገነባለሁ፣ መዋቅራዊ ለውጥ አመጣለሁ” እያለ መፎከር ከጀመረ አመታት ቢቆጠሩም በዘርፉ የተመዘገበው እድገት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ አመራሮች የተለመደ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ከመንፋት ይልቅ “የኢንዱስትሪ ዘርፉ በሚፈለገው ፍጥነት ለምን አላደገም?” ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ መንግስት ለዘርፉ እድገት ያበረከተውን አስተዋፅዖ ከፓርቲው ሸውራራ አይዲዮሎጂ ውጪ፣ በስነ-ምጣኔ መርህ ላይ ተመስርቶ ማየትና ማስተካከል አለበት፡፡ ላለፉት አስር አመታት የሰማነውን ጉራ ለቀጣይ አስር አመት ብንሰማ ጆራችን ይደነቁራል እንጂ የኢንዱስትሪው አያድግም። ምክንያቱም፣ በቀጣይ አስር አመታት ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ላለፉት አስር አመታት ለምን እንዳላደግ መጠየቅና ማወቅ ያስፈልጋል።

ላለፉት አስር አመታት ለኢትዮጲያ ኢንዱስትሪ እድገት ማነቆ የሆኑ ሦስት መሰረታዊ ችግሮች አሉ። እነሱም፣ 1ኛ፡- የኢህአዴግ መንግስት በቢዝነስ ስራ መሠማራቱ፣ 2ኛ፡- እንደ መንግስት ሥራው አለመስራቱ፣ 3ኛ፡- የግል ተቋማትን አላሰራ ማለቱ ናቸው። የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ችግሮቹን በአጭሩ ለመዳሰስ እሞከራለሁ።

1ኛ፡- የኢህአዴግ መንግስት ቢዝነስ ይሰራል!

አንዳንድ የስነ-ምጣኔ ዘርፍ ባለሞያዎች እንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጲያ ውስጥ የግል ተቋማት ድርሻ በጣም ውስን የሆነው ፖለቲካና ቢዝነስ እርስ-በእርስ በመጠላለፋቸው ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ። በሀገራችን ትላልቅ የአገልግሎትና ማምረቻ ተቋማት በመንግስት ይዞታ ስር መሆናቸው እንዳለ ሆኖ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች “Endowment” በሚል ስያሜ የራሳቸው የቢዝነስ ተቋማት አላቸው። በዚህ ምክንያት፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፖለቲካ በተጨማሪ በቢዝነስ እንቅስቃሴ ቀጥተኛ የሆነ የጥቅም ትስስር አላቸው። ለምሳሌ፣ “Tilman Altenburg” የተባሉ የስነ-ምጣኔ ምሁር ከጀርመን የዓለም-አቀፍ ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጲያ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ በሰሩት ጥናት የኢህአዴግ መንግስት ፖሊሲ አውጪዎች በቢዝነስ ዘርፉ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ በመሆናቸው ምክንያት የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ በጣም አስቸጋሪ እንዳደረገው እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል፡-

“Business and politics are still strongly entwined in Ethiopia. State-owned enterprises still dominate many manufacturing industries and service sectors, and party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. Discretionary allocation of public resources lends itself to political capture by interest groups. …Against this background, the main challenge is to make policy decisions more transparent and ensure the accountability of policymakers.” Industrial policy in Ethiopia /Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010.

ከዚህ በተጨማሪ፣ የኢህአዴግ መንግስት የግል ተቋማት በየትኞቹ የኢንደስትሪ ዘርፎች መሰማራት እንዳለባቸው በራሱ ይወስናል። ሆኖም ግን፣ የመንግስት ኤጀንሲዎችና አመራሮች የገበያ ፍላጎቱን የለውጥ ሂደትና የባለሃብቶችን ፍላጎት ለመወሰን ብቃትና ክህሎት የላቸውም። ለምሳሌ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየተገነቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የዚህ ማሳያ ናቸው። በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱ የምርት ዓይነቶች ውስን ከመሆናቸው በተጨማሪ በመንግስት ኃላፊዎች የተወሰኑ ናቸው። ከላይ የተጠቀሰው ጥናት አቅራቢ፣ የኢህአዴግ መንግስት ያለ ቦታው ገብቶ ከሚፈተፍት እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን ስራ በአግባቡ መስራት አለበት በማለት ይመክራል፡-

“Policymakers should acknowledge that private entrepreneurs are better equipped to recognise market trends and take advantage of new opportunities than government agencies. Thus industrial policy should move away from predefining priority sectors and instead focus on skills development and on creating incentives for entrepreneurs in order to develop innovations and disseminate new business models throughout the country.” Industrial policy in Ethiopia /Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010.

2ኛ፡- የኢህአዴግ መንግስት ሥራውን አይሰራም!

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የኢንዱስትሪውን እድገት ለማረጋገጥ የኢህአዴግ መንግስት መደበኛ ሥራ መሆን ያለበት በሰው ኃይል ስልጠና እና ለሥራ ፈጣሪዎችንና ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማበረታታት ነው። ነገር ግን፣ ለምሳሌ አቶ ሰለሞን ዲባባ የተባሉ ፀኃፊ  “Industrial Development in Ethiopia – Background, Challenges and Opportunities” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የትንታኔ ፅሁፍ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ችግር (Lack of skilled manpower) ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ እንደሆነ ይገልፃሉ። ለባለሃብቶችና ሥራ ፈጣሪዎች የሚሰጠው ማበረታቻና ድጋፍ ግልፅነት የጎደለውና አድሏዊ መሆኑን አያይዘው ጠቅሰዋል።  ይጠቅሳሉ።

በሌላ በኩል “Tilman Altenburg” ባደረገው ጥናት፣ ከሥራ-ፍቃድ፣ የመስሪያ ቦታ፣ ብድርና የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት አንፃር በመንግስት የሚደረገው ድጋፍና ማበረታቻ አድሏዊና ግልፅነት የጎደለው እንደሆነ ጠቅሷል። በአንፃሩ የኢትዮጲያ ኢንቸስትመንት ኮሚሽን መስሪያ ቤት ደግሞ በኢትዮጲያ ለውጪ ድርጅቶች የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ መሆኑን ለመግለፅ “One-stop government service” እያለ ጉራውን ይቸረችራል። ለምሳሌ የእንግሊዝ የዓለም አቀፍ ንግድ መስሪያ ቤት (Department for International Trade) ለሀገሪቱ ባለሃብቶች ባወጣው መመሪያ መሰረት፣ በኢትዮጲያ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት ወራት እንደሚፈጅና ከውጪ የገቡ ዕቃዎችን ለመረከብ እስከ 75 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ይገልፃል። የእንግሊዝ ባልሃብቶች ወደ ኢትዮጲያ ለመምጣት በቅድሚያ የሚመለከቱት የሀገራቸው መንግስት መመሪያ እንጂ የኢህአዴግን ጉራ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ዝቅተኛ የመሰረተ ልማት ሽፋንና ጥራት፣ እንዲሁም ግልፅነት የጎደለው የታክስ አስተዳደር፣ የተዝረከረከ ቢሮክራሲ፣ …ወዘተ ለኢንዱስትሪው እድገት ማነቆ ናቸው። እነዚህ ማነቆዎች የተፈጠሩት በዋናነት የኢህአዴግ መንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው ሥራና አሰራር መዘርጋት ባለመቻሉ ነው። 

3ኛ፡- የኢህአዴግ መንግስት ሌሎችን አያሰራም!

የኢህአዴግ ፓርቲ በራሱ ቢዝነስ እየሰራ፣ እንደ መንግስት ሥራና አሰራሩን ከማሻሻልና የመሰረተ-ልማትን ጥራትና ተደራሽነት ከማሳደግ አንፃር የሚጠበቅበትን አለመወጣቱ ሳያንስ የግል ተቋማትንና ባለሃብቶችን ጉቦና የፖለቲካ ድጋፍ ይጠይቃል። ለምሳሌ፣ የእንግሊዝ የዓለም-አቀፍ ንግድ መስሪያ ቤት ባወጣው መመሪያ መሰረት፣ በሙስና ረገድ ኢትዮጲያ ከ177 ሀገራት ውስጥ 111ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሷል። ይህ ኢህአዴግ እንደሚለው “በኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር” ሳትሆን የሙሰኞች ሀገር መሆኗን በግልፅ ይጠቁማል። ከሙስና በተጨማሪ፣ “የኢህአዴግ ባለስልጣናት የግል ተቋማትን የፖለቲካ ድጋፍ ካልሰጣችሁን በማለት ቁም-ስቅላቸውን እንደሚያሳያቸው የ”Tilman Altenburg” ጥናት ውጤት ያረጋግጣል፡-

“The government deliberately employs a carrot-and-stick approach that differentiates between economic activities and firms, up to the point where targets for individual firms are sometimes negotiated on a case-by case basis in exchange for public support.” Industrial policy in Ethiopia /Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010.

ስለዚህ፣ እንደ ኢህአዴግ ያለ የራሱን የቢዝነስ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅስ ፓርቲ፣ ሥራና አሰራሩን ለማሻሻል አቅምና ቁርጠኝነት የሌለው መንግስት፣ የግል ቢዝነስ ተቋማትን በሙስናና በፖለቲካ አላላውስ ብሎ ስለ ምን ዓይነት “ኢንዱስትሪ-መር  ኢኮኖሚ” ነው የምታወሩት? በቅድሚያ ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ የሆነውን ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ የሆነው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው!

2 thoughts on ““ኢንዱስትሪ-መር ኢኮኖሚ”: የኢህአዴግ ጉራ እና ሥራ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡