የፀረ-ሽብር ሕጉ ዓላማ ሕዝቡን መሪ-አልባ ማድረግ ነው!

ባለፈው ጓደኛዬ ከአንድ ታዋቂ ምሁር ጋር አስተዋወቀኝና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየን። እኚህ ምሁር ቀድሞ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር የነበሩ ሲሆን አሁን ጡረታ ወጥተዋል። ቦሌ አከባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ለሁለት ሰዓታት ያህል ተወያየን። ውይይታችን በዋናነት ያተኮረው ከኢህአዴግ መንግስት በፊትና በኋላ የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ሚና ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ ያተኮረ ነበር። እኚህ ምሁር ብዙውን ግዜ “The Amhara Hegemony” የምትለዋን አገላለፅ እንደሚያዘወትሩ ስለማውቅ የእኔም ጥያቄ ከዚያ ላይ ነው የጀመረው። “ዶክተር… ይህቺ ‘The Amhara Hegemony’ የሚሏት ነገር ፅንሰ-ሃሳቧ ምንድነው? በቀድሞ ስርዓት ‘የአማራ የበላይነት/አገዛዝ’ አለ ለማለት የቻሉበትን ምክንያት ቢያስረዱኝ?” አልኳቸው።

“በዚያን ግዜ (በደርግና በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን) አብዛኞቹ የአማራ ምሁራን፣ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የአማራ ተወላጅ የሆኑ መምህራን ‘የገብርዔል ማህበር፣ የማሪያም ፅዋ፣…ወዘተ እያሉ በየግዜው እየተገናኙ ተሰብስበው ያወራሉ፥ ይጫወታሉ። ማህበርና ፅዋ ይበሉ እንጂ የሚያወሩት እኮ ስለ ሃይማኖት አይደለም። ምሁራን ከመደበኛ ስራቸው ውጪ ሲገናኙ የሚያወሩት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያው ፖለቲካ ነው። ስለዚህ፣ አብዛኞቹ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ማህበርና ፅዋ እያሉ በየግዜው ይሰበሰቡና ስለ ወቅታዊ ፖለቲካ ያወራሉ። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየት ይሰጣሉ፣ የጋራ ግንዛቤ ይፈጥራሉ። በዚህም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ አቋምና አመለካከት ይይዛሉ። ነገር ግን፣ እንደ እኔ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራን ገና ሶስት-አራት ሆነው መሰባሰብ ሲጀምሩ “ኦነግ” ይባላሉ። በተመሳሳይ፣ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጆች ተሰባስበው መምከር ሲጀምሩ “ወያኔ” ይባላሉ።

በቀድሞ ግዜ የአማራ ምሁራን እንደ እኛ “ጠባብ ብሔርተኛ” ወይም “ገንጣይ ወንበዴ” የሚል ስያሜ አይሰጣቸውም ነበር። ስለዚህ፣ የኦሮሞና ትግራይ ምሁራን እንኳን መደራጀት በጋራ ሰብሰብ ብለው ሻይ-ቡና ማለት አይችሉም ነበር። የአማራ ምሁራን ግን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በይፋ መቃወም እስካልጀመሩ ድረስ በፈለጋቸው ቦታና ሰዓት ተገናኝተው ቢመክሩና ቢዘክሩ ግንኙነታቸው ከኦነግ ወይም ከወያኔ ጋር ይያያዝብናል የሚል ስጋት አልነበረባቸውም። በዚህ ሁኔታ ምሁራን ስለ መጡበት ማህብረሰብ መብትና ነፃነት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ስለሚስፈልገው ለውጥና መሻሻል በጋራ ለመወያየት የሚያስችል ሁኔታ አልነበርም። ምሁራን የሕዝብን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በማንሳትና እርስ-በእርስ በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥና መጠቆም ካልቻሉ መንግስታዊ ስርዓቱ እንደ አፄ ኃ/ስላሴና ደርግ መጨረሻው አያምርም” አሉኝ።

እኔም ከአፋቸው ቀበል አድርጌ “አሁን ካነሱት ሃሳብ አንፃር ከኢህአዴግ መምጣት በኋላ ምን የተለየ ነገር ተፈጠረ?” የሚል ጥያቄ አስከተልኩ። እሳቸውም “ቅድም ያልኩህ ምሁራን በአብዛኛው የአማራ ምሁራን ሀገር ለቅቀው ወጡ። በተመሳሳይ፣ የኦሮሞ ምሁራን እንዲሁ ሀገር ለቅቀው ወጡ” አሉኝ፡፡ “ለምን?” አልኳቸው።

“እንዴ…ቀድሞ የነበረው የ“Amhara Hegemony” ኢህአዴግ ከጣ በኋላ በ”Tigray Hegemony” ተተካ። የአማራ ልሂቃን እንደ ቀድሞ ግዜ የገብሬልና የማሪያም ማህበር እያሉ መሰባሰብ ከጀመሩ “ከግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል ለእስርና እንግልት ይዳረጋሉ። እንደ ቀድሞ ስርዓት አሁንም የኦሮሞ ምሁራን በጋራ ተሰባስበው ሲወያዩ “ኦነግ ናችሁ” እየተባሉ ቁም ስቅለቸውን ያያሉ። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ግን ሕወሃት/ኢህአዴግን በይፋ እስካልተቃወሙ ድረስ በየግዜው ተገናኝተው ቢወያዩ ነገሩ ከኦነግና ግንቦት7 ጋር ይያያዝብን ይሆናል የሚል ስጋት የለባቸውም። ኢህአዴግን መቃወም ይቅርና በመንግስት ስራና አሰራር ላይ ጠንከር ያለ ትችትና አስተያየት የሰጡ የአማራና ኦሮሞ ምሁራን ግን የግንቦት7ና የኦነግ የሽብር ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ ተደረሰባቸው ተብለው ወደ እስር ቤት ይወረወራሉ።

የሕወሃት ደጋፊ/አባል የሆኑ ምሁራን የፈላጋቸውን ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይችላሉ። የብኣዴንና ኦህዴድ አባልና አመራሮች እንኳን ይህን የማድረግ ነፃነት የላቸውም። የኢህአዴግ መንግስትን ወይም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ ትችትና ነቀፌታ የሚሰነዝር የብአዴን አባልና አመራር “ትምክህተኛ”፣ የኦህዴድ አባልና አመራር ደግሞ “ጠባብ” የሚል ታፔላ ይለጠፍበታል። ከሕወሃት አባላትና ደጋፊዎች ተፃራሪ የሆነ ሃሳብና አስተያየት ካነሳህና የኢህአዴግ ተቃዋሚ ከሆንክ “ግንቦት7” ወይም “ኦነግ” ትባላለህ፣ የኢህአዴግ አባል ከሆንክ ደግሞ “ትምክህተኛ” ወይም “ጠባብ ብሔርተኛ” ተብለህ በጅምላ ትፈረጃለህ። ስለዚህ፣ ከኢህአዴግ ውስጥ ሆነ ውጪ ያሉ የአማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ስለ ሕዝባቸው መብትና ነፃነት አንዳች ነገር መተንፈስ አይችሉም። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት በተለይ የሕዝቡን ብሶትና ምሬት መረዳት ተስኖታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደፊትም መረዳት የሚችል አይመስለኝም። ስለዚህ፣ ኢህአዴግም እንደ አፄ ኃ/ስላሴ እና ደርግ አገዛዝ መጨረሻ ላይ አወዳደቁ አያምርም።

በመጨረሻም “የተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ሳይቀር ሁሉም የሚከሰሱት በፀረ-ሽብር ሕጉ ነው። ከዚህ አንፃር፣ የፀረ-ሽብር አዋጁን ዓላማና አተገባበር እንዴት ያዩታል?” የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው። እሳቸውም በእርግጠኝነት “የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን መሪ-አልባ ማድረግ ነዋ!” አሉኝ።

“ይሄ ምን ጥያቄ አለው? መንግስት በተግባር የሚያደርገው እኮ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የፈቀደለትን ነው። የብዙሃኑ አስተያየትና አመለካከት የሚቀረፀው ደግሞ ከላይ በጠቀስካቸው ፖለቲከኞች፥ ጋዜጠኞች፥ ፀኃፊያንና በመብት ተሟጋቾች ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ ሕዝብ መብትና ነፃነት በተናገሩ ቁጥር መንግስት እንደ “አልቃይዳ” እያደነ በሽብርተኝነት ወንጀል የሚከሳቸው ከሆነ ሕዝቡ መሪ አልባ ይሆናል። በሕገ-መንግስቱ ላይ የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ የሚገድብ አዋጅ በማውጣት ስለ ሕዝብ መብት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚከራከሩ ሰዎችን ለማሰር፣ ለማሰቃየትና ለማስፈራራት የምትጠቀምበት ከሆነ የአዋጁ ዓላማና ግብ ሕዝቡን መሪ አልባ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሰረት፣ የፀረ-ሽብር ሕጉ ዓላማና አተገባበር በተለይ የኦሮሞና አማራ ሕዝብን መሪ አልባ የሚያደርግ ነው። መሪ-አልባ ሕዝብን እንዴትም፥ ወዴትም ትመራዋለህ! 

One thought on “የፀረ-ሽብር ሕጉ ዓላማ ሕዝቡን መሪ-አልባ ማድረግ ነው!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡