ኢህአዴግ እና ሙስና ስጋና ነፍስ ናቸው!

ዛሬ በEthiopian News Network (ENN) የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃ ተከስተ ከአንሙት አብርሃም ጋር ያደረጉትን ውይይት ተመልክቼዋለሁ። ጋዜጠኛ አንሙት በሙስና ችግር እና መንግስት እየተወሰደ ስላለው እርምጃ የችግሩን አሳሳቢነት አፅንዖት ሰጥቶ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የሚኒስትሩ ምላሽ ግን ምንም የተለየ ነገር አልነበረውም። እንደ ሚኒስትሩ አገላለፅ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድና ሥርዓቱን በማ’ጥበቅ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሰጠው ገልፀዋል። ነገር ግን፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከመቼውም ግዜ በተለየ የተስፋፋው በኢህአዴግ ዘመን ነው። ስለዚህ፣ ጥያቄው “ገና ከጅምሩ ችግሩን እንዳይፈጠር ወይም እንዳይስፋፋ ማድረግ የተሳነው መንግስት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይችላል?” የሚለው ነው፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጥናታዊ ፅሁፍን ጨምሮ የተለያዩ ፅሁፎችን ዋቢ በማድረግ ሙስናን ለማስወገድ የሚቻለው የኢህአዴግ መንግስትን ከስልጣን በማስወገድ እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ።

የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ “African Development: Dead Ends and New Beginnings” በሚል ርዕስ ጀምረውት በነበረው ጥናታዊ ፅሁፍ ለሀገር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት መነሻ ስለሆነው ማህበራዊ ልማት ጠቃሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ፅሁፍ “The Neo-Liberal Political Economy and Social Capital” በሚለው የመጀመሪያ ክፍል መደምደሚያ ሃሳብ (Conclusion) ላይ “…ወደ ቁሳዊ ሀብትነት እና ጥቅም ከመቀየራቸው በፊት ልማት እና እድገት መልካም ማህበራዊ እሴቶች፣ ሕጎች እና ልማዶች ናቸው። …ማህበራዊ ልማት ማለት፣ ለተፋጠነ ልማት እና እድገት አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን፣ ልማዶች እና ደንቦችን መፍጠር እና በሕብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፁ ማድረግ ነው። ስለዚህ፣ ማህበራዊ ልማት የሀገር ልማት እንዱ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው…” የሚል ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ እሴቶች” የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያበረታቱና በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እምነቶች፣ መርሆች እና መመሪያዎች ናቸው። ለልማት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ ልማዶች” ደግሞ ለተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ትግል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የአሰራር እና አመራር ሂደቶች ሲሆኑ በአከባቢው ማህብረሰብ ሕጎች መገዛት፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ የፀረ-ሙስና ግድታን መወጣት እና ሥነ-መግባር ከጎደለው ተግባር መቆጠብ እና የመሳሰሉት ናቸው። ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ ደንቦች” ደግሞ የማህብረሰቡ አባላት፣ መንግስት ወይም ሌሎች አካላት፣ ለእድገቱ ተፃራሪ በሆኑ ተግባራት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚያግዱ እና ማዕቀብ የሚጥሉ ማህበራዊ ሕጎችን ናቸው።

በዚህ ፅኁፍ ትኩረት የምናደርግበት ሙስና እና ብልሹ አሰራር በልማድና ደንብ መልክ በማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ በግልፅ ከመንፀባረቃቸው በፊት በቅድሚያ በአመለካከት ደረጃ መስረፅ አለበት። ሰዎች በሙስና ውስጥ ከመዘፈቃቸው በፊት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የማይጠየፍ ወይም የሚፈቅድ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። ኪራይ ሰብሳቢነት የማይገባ ጥቅምን መፈለግ ሲሆን ሙስና ደግሞ የማይገባ ጥቅምን ማግኘት ነው። ስለዚህ፣ የሙስና ተግባር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የመጨረሻ ውጤት ነው።

ለሀገራችን ማህበራዊ ልማት፣ በተለይ ደግሞ በስፋት የሚስተዋለውን የሙስና ችግር ለመቅረፍ ምቹ የሆኑ አሰራር እና አመራር ሊኖር ይገባል። ለዚህ ደግሞ ለማህብረሰቡ ሕጎች ተገዢ መሆን፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ የፀረ-ሙስና ግድታን መወጣት እና ሥነ-መግባር ከጎደለው ተግባር መቆጠብ ይጠይቃል። በዚህ መሰረት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ማስወገድ፣ ያልተገባ ጥቅምን የሚጠየፍ ማህብረሰብ መፍጠር የግድ ነው። ይህን ለማድረግ ግን በቅድሚያ አሁን ያለው ለሙስና ምቹ የሆነ የሥራ አሰራር ሂደት፣ እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እንዴትና ለምን እንደተፈጠረ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል (Aristotle) “Nicomachean Ethics” በሚለው መጽሐፉ ሰው በግል’ም ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ሊኖሩት ወይም ሊያዳብራቸው የሚገቡ እሴቶች የጥበብ (ዕውቀት) እና የሞራል (ባህሪ) በማለት ለሁለት ይከፍላቸዋል። በግሪክኛ ቋንቋ ሞራል (ethike) የሚለው ስያሜ “ethos” (habit) ከሚለው ጋር ያለውን ተቀራራቢነት በመጥቀስ የሞራል ስነ-ምግባርና መርሆች የባሕሪ ውጤት እንደሆኑ ያስረዳል። ለዕውቀትና ክህሎት ቅድሚያ የሚሰጥ አስተዳደር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር፣ እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ አመራር ባለበት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ሊኖር አይችልም።

ነገር ግን፣ የፖለቲካ መሪዎችና ተወካዮች የሚያወጧቸው ሕጎች፥ ደንቦችና መመሪያዎች እና አተገባበራቸው ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው ከሆነ ለሙስና ምቹ ይሆናል። እንደ አርስቶትል አገላለፅ፣ የመሪዎች ሚና በዕውቀትና በባህሪ የታነፀ ማህብረሰብ መፍጠር ነው። በዚህ መሰረት፣ በኢትዮጲያ ለሚስተዋለው ለሙስና ምቹ የሆነ የሥራ አሰራርና አመራር ሂደት በመዘርጋት እና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በማስረፁ ረገድ ዋናው ተጠያቂ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ነው።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በሀገራችን ለተሰራፋው ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን እና ልማዶችን በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ እንዲሰርፁ ያደረገው ራሱ የኢህአዴግ መንግስት ነው። ስለዚህ፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ እነዚህን ማህበራዊ እሴቶችና ልማዶች ማስወገድ የግድ ነው። ነገር ግን፣ እነዚህን ማህበራዊ እሴቶችና ልማዶች በሕብረተሰቡ ውስጥ በስፋት እንዲሰርፁ ምክንያት የሆነ አካል መልሶ ሊያጠፋቸው ይችላል? በሌላ አነጋገር፣ አሁን ላይ በስፋት ለሚስተዋለው ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ የሆኑት የኢህአዴግ መንግስት አመራሮች ችግሩን መቅረፍ ይችላሉ?
እንደ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Friedrich Nietzsche” አገላለፅ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም፣ ማህበራዊ እሴት ይፈጠራል እንጂ አይቀየርም። እሴት መቀየር ማለት እሴት ፈጣሪዎችን መቀየር ነውና፦

“Valuing is creating: hear it, ye creating ones! Change of values- that is, change of the creating ones. Always doth he destroy who hath to be a creator.” Thus Spake Zarathustra, CH.15. The Thousand and One Goals, Page 34.

ለችግሩ መንስዔ የሆኑት የኢህአዴግ መንግስት አመራሮች ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጡ አይችሉም። ከዚያ ይልቅ፣ የችግሩ መፍትሄ የችግሩን መንስዔዎች ማስወገድ ነው። ምክንያቱም፣ እንደ “Friedrich Nietzsche” አገላለፅ፣ የኢህአዴግ መንግስት አመራሮች የፈጠሯቸውን ለሙስና ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች ለማስወገድ አዲስ ማህበራዊ እሴቶችና ልማዶች መፍጠር ያስፈልጋል። አዲስ ማህበራዊ እሴቶችን መፍጠር በራሱ የቀድሞ እሴት ፈጣሪዎችን ማስወገድ ይጠይቃል። በዚህ መሰረት፣ ሙስናን ለማስወገድ ለሙስና ምቹ የሆነ ማህበራዊ እሴትና ልማድ የፈጠሩትን የኢህአዴግ መንግስት አመራሮች ማስወገድ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ፣ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰውን የሙስና ችግር ለመቅረፍ በመጀመሪያ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እንዲሰርፅ ያደረጉት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከኃላፊነት መወገድ አለባቸው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር መንስዔ የሆነ አመራር በፍፁም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም።

12 thoughts on “ኢህአዴግ እና ሙስና ስጋና ነፍስ ናቸው!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡