እስኪ ይህን የኦዲት ሪፖርት ተመልከትና አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለምን እንደታሰሩ ንገረኝ?

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተጠርጥረው የታሰሩት “የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል” በሚል እንደሆነ የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል፡፡ ነገር ግን፣ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ያለውን ሁኔታ ለማጤን መረጃዎችን ሳፈላል በ2003 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ኘሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ያቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት (pdf) አገኘሁ፡፡ ይህ ሪፖርት በውስጡ ከያዛቸው አስገራሚ መረጃዎች ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር (ገ/ኢ/ል/ሚ)  በየወሩ የአፈፃፀም ሪፖርት የሚያቀርበው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን “ብቻ” መሆኑንና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ግን በጭራሽ ሪፖርት እንደማያደርጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ እንዳቁሞ እንደነበር መርዶ ይነግረናል፡፡  

እያንዳንዱ የልማት ፕሮጀክት ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ካልገጠሙ በቀር፣ በተዘጋጀለት የጥናት ሰነድ ላይ በተመለከተው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሊጀመርና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን መሰረት መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ፕሮጀክት ለማወቅ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በ2003 ዓ.ም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ገፅ 28 ላይ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን የማይጠናቀቁ መሆኑን እንዲህ ይገልፃል፦

በኦዲቱ በናሙና ተመርጠው ከታዩት 8 የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች መካከል አምስቱ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳልተጠናቀቁና ተጨማሪ ጊዜ እንደወሰዱ ታውቋል፡፡ እንደዚሁም በውኃ ሀብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር ከሚካሄዱት ኘሮጀክቶች ውስጥ በኦዲቱ ለናሙና የታዩት ሁለት ኘሮጀክቶች የአፈጻጸሙ ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ የከሰም ተንዳሆ የግድብና መስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት እ.አ.አ በ2004 የተጀመረ ሲሆን በወቅቱ 1.669 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ እስከ 2002 ዓ.ም. ብቻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ለገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር መ/ቤት ከቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁንም ሥራው ያልተጠናቀቀና የከሰም ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 69%፣ የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 55% ያህል ብቻ እስከ 2002 በጀት ዓመት የፊዚካል አፈጻጸም መከናወኑን ከውሃ ሃብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ በቃል የተገለጸልን ሲሆን ይህን የሚገልጽ የአፈጻጸም ሪፖርት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው “ፈቃደኛ” ሊሆኑ አልቻሉም፡፡” 

በገፅ 34 ደግሞ ኘሮጀክቱ አዋጪ መሆን/አለመሆኑ ጥናቱ ተጀምሮ ከፍተኛ ወጪ ከተደረገበት በኋላ የተቋረጠ ኘሮጀክት ስለመኖሩ የሚከተለውን በማሳያነት ይጠቅሳል፦  

“ይሁን እንጂ በኦዲቱ ወቅት፣ በግብርና ሴክተር ስር ያለው የእንስሳት ሃብት ልማት ማስተር ፕሮጀክት (በእርዳታ) ጥናት፣ የፕሮጀክት ዝግጅቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ላይ ሲደርስ ተቋርጧል፡፡ ለምን ጥናቱ እንደተቋረጠ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክቱ ረቂቅ ጥናት ቀርቦ አማካሪው በተሰጠው ቢጋር /TOR/ መሰረት ስራውን ባለማከናወኑ ምክንያት በመንግስት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስራው የተቋረጠ መሆኑንና ስራውን እንደገና መልሶ ለማስጀመር ጥረት ተደርጎም እንዳልተሳካ ተገልጿል፡፡ ከፕሮጀክቱ ጠቀሜታ አንጻር የዝግጅት ሂደቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ደርሶ ለጥናት ዝግጅት የሚያስፈልገው ሃብት በ2000 በጀት ዓመት ብር 4‚922‚220፣ በ2001 በጀት ዓመት ብር 23‚480 እና በ2002 በጀት ዓመት ብር 11‚630.00 በድምሩ ብር 4‚957‚330 ወጪ ተደርጎ እንዲቋረጥ መደረጉ ታውቋል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ የወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲባክን ከመደረጉም በላይ ሀገሪቱ ለ20 ዓመታት የምትመራበት ማስተር ፕላን አለመዘጋጀቱ ከኘላኑ ተግባራዊነት የሚገኘውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያሳጣ በመሆኑ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የሚቀርብ ስላለመሆኑ፦

“በፕሮጀክት አስፈጻሚ አካላት ስለ ፕሮጀክቶች የስራ አፈጻጸም በየሶስት ወሩ የክትትልና ግምገማ ውጤት ሪፖርት እየተዘጋጀ ለሚ/ር መ/ቤቱ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በአስፈጻሚ መ/ቤቶች እየተዘጋጀ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀርበውን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርትና የግምገማ ውጤት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማይቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስለ ሁኔታው የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክት አስፈጻሚዎች የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት በአሁኑ ወቅት የማይቀርብ መሆኑን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ላለው የፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ዴስክ የአፈጻጸም ሪፖርት ይቀርብና ከመ/ቤቶች ጋር ውይይት ይደረግበት እንደነበርና ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተቋረጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ የሪፖርቱ መቋረጥ የበላይ አካል በገንዘብና ኢኮኖሚ ል/ሚ/ር የተዘጋጀ እና የተገመገመ የፕሮጀክቶችን አጠቃላይ የሥራ ሂደት ሁኔታ የሚያውቅበት እና የሚከታተልበት መንገድ እንደሌለ የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪም ከፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለበላይ አካል ቀርቦ እልባት እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የገ/ኢ/ል/ሚ/ር ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርብለትን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ሆኖ ሳለና ተጠቃሚው ክፍል እንዳይላክ ሳይጠይቅ እንዲቋረጥ መደረጉ አግባብነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

በመጨረሻም በሪፖርቱ ገፅ 36 ላይ ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት ይዘት ወጥነት የሌለውና በፕሮጀክት ክትትል መመሪያው መሰረት ስላለመሆኑ የሚከተለውን ብሏል፦

“የፕሮጀክት ስፈጻሚዎች በጸደቀው የፕሮጀክት ሰነድ መሰረት፣ በፕሮጀክት የድርጊት መርሃ ግብር፣ በክትትልና ግምገማ መመሪያ እንዲሁም በሥምምነቶች መሠረት በትክክል የፕሮጀክቱን የስራ ሂደት፣ ግብዓት፣ ውጤት፣ ስኬት እንዲሁም የፕሮጀክቱን ፋይዳ (impact) በመከታተል በየ3 ወሩ ለ/ገ/ኢ/ል/ሚ/ር ሪፖርት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በኦዲቱ ወቅት እንደታየው፣ በዚህ የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት አቀራረብ በኩል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በጥሩ ተሞክሮ የሚገለጽ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የበጀት ባለሙያ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ እና ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንደተገነዘብነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መ/ቤት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመት ብቻ ሳይሆን በየወሩ ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሌሎች ሴክተሮች የሪፖርት አቀራረብ ሲታይ፣ ከጤና ሴክተር፣ ከትምህርት ሴክተር እና ከግብርና ሴክተር አስፈጻሚዎች ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚቀርበው የፕሮጀክት የፊዚካል እና የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት በሚ/ር መ/ቤቱ በተዘጋጀው የሪፖርት ማቅረቢያ ቅጽ (ፎርማት) መሰረት አለመሆኑ ታውቋል፡፡ የሚቀርበው ሪፖርትም በየሩብ አመቱ መሆን ሲገባው፣ በየ6 ወር ወይም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡” 

3 thoughts on “እስኪ ይህን የኦዲት ሪፖርት ተመልከትና አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለምን እንደታሰሩ ንገረኝ?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡