​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-2/

የትላንት ምርኮኞች ክፍል አንድ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት በሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን መካከል መግባባት የለም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ልሂቃኑ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ተከፍለው እርስ-በእርስ መጠላለፋቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት አምባገነናዊና ጨቋኝ እየሆነ መጥቷል። በዚህ መሃል የዜጎች ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት ክፉኛ ተገድቧል፡፡ ዛሬ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት ውስጥ የሚደረግ ሆኗል። በመሆኑም፣ ዘላቂ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በቅድሚያ በሀገራችን ፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለው መጠላለፍ ማስቀረት ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ ልሂቃኑ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው የሚጠላለፉበት ምክንያት ምንድነው?
በብሔርተኞች እና የአንድነት አቀንቃኞች መካከል ያለው ልዩነት ፖለቲካዊ ስርዓቱ “በብሔር እኩልነት ወይስ በአህዳዊ አንድነት” ላይ መመስረት አለበት በሚል ነው። ሁለቱም ወገኖች የአመለካከታቸውን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ በአብዛኛው ወደ 19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ በመመለስ ታሪካዊ ማስረጃ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። ነገር ግን፣ በተመሳሳይ ግዜና ቦታ ስለነበሩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እያወሩ ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። 

በተለይ ደግሞ በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመን ስለነበረው አገዛዝ ያላቸው አመለካከት ዋና መለያ ነው። ብዙውን ግዜ ብሔርተኞች የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝን አፍሪካዊ የቅኝ-አገዛዝ ስርዓት እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል። የአንድነት አቀንቃኞች ደግሞ የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ የቅኝ-አገዛዝ ኃይሎችን በማሸነፍ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ተምሳሌት እንደሆነ ይገልፃሉ። በጥቅሉ ብሔርተኞች የአፄ ሚኒሊክን ዘመን ከብሔር ጭቆና ጋር ሲያይዙት አንድነቶች ደግሞ ከሀገራዊ አንድነት ጋር ያያይዙታል። 

በዚህ መሰረት፣ ሁለቱም ወገኖች ስለአንድ ጉዳይ እየተናገሩ እርስ-በእርስ አይግባቡም፥ አይስማሙም። ምክንያቱም፣ አንደኛው ወገን የሚናገረውና የሚያደርገው ነገር በሙሉ የሌላውን ወገን ሃሳብና አመለካከት ውድቅ (nullify) በማድረግ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ የሀገራችን ልሂቃን በሰከነ መንገድ ከመነጋገርና መግባባት ይልቅ እርስ-በእርስ በመዘላለፍና መጠላለፍ ይቀናቸዋል። 

ችግሩ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ የተሰለፉት የፖለቲካ ልሂቃን “የትላንት ምርኮኞች” መሆናቸው ነው። ሁለቱም ወገኖች ትላንት ላይ ቆመው የነገውን መንግስት ለመመስረት የሚታትሩ ናቸው። ብሔርተኞች ሆኑ አንድነቶች ወደፊት በኢትዮጲያ ስለሚያስፈልገው ፖለቲካ ስርዓት እንደ መነሻና ማስረጃ የሚያደርጉት ከ100 ዓመት በፊት የነበረው የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ ነው። 

ብሔርተኞች የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት የብሔር መብትና እኩልነትን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ የተዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦችን መብትና እኩልነት የሚጋፋ መሆኑን ይገልፃሉ። በኢህአዴግ መንግስት የተዘረጋው የብሔር ፖለቲካም በዚህ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በሌላ በኩል የአንድነት አቀንቃኞች የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ የሀገሪቱን አንድነትና ነፃነት ያረጋገጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህ አንድነት ግን በብሔር ፖለቲካ አማካኝነት አደጋ ላይ እንደወደቀ ይገልፃሉ። 

በጥቅሉ ሲታይ ግን የሁለቱም ወገኖች የፖለቲካ አመለካከት ትላንትና በሆነው ላይ እንጂ ነገ መሆን ባለበት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ብሔርተኞች የቀድሞውን በደል እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ፣ አንድነቶች ደግሞ የቀድሞውን ድል እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ። ነገር ግን፣ እንደ “Jose Ortega y Gassett” አገላለፅ ማንኛውም መንግስት የሚመሰረተው ትላንት በሆነው ሳይሆን ነገ ሊሆን በሚችለው ላይ ነው፡-    

 “The State is always, whatever be its form- primitive, ancient, medieval, modern- an invitation issued by one group of men to other human groups to carry out some enterprise in common. State and plan of existence, programme of human activity or conduct, these are inseparable terms. The different kinds of State arise from the different ways in which the promoting group enters into collaboration with the others.” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97.  

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የኢትዮጲያ መንግስታዊ ስርዓት ባለፉት ዘመናት በሆነውና በተደረገው ሳይሆን ነገ ላይ ሊሆንና ሊደረግ በሚችለው ላይ መመስረት ነበረበት። በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ የሚጠዛጠዙት የሀገራችን ልሂቃን የወደፊቱን አቅጣጫ በትላንትው እሳቤ ለመወሰን በመሞከር ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ የትላንትናው መንገድ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አይወስድም። ነገር ግን፣ ምንም ያህል ቢፈጥኑ፥ ቢዘገዩ አንዳቸውም ካሰቡበት አይደርሱም፡፡ ምክንያቱም፣ ሀገርና መንግስት የሚመሠረተው በነገ እንጂ በትላንት እሳቤ አይደለም፡፡ 

በመጨረሻም፣ የሁለቱም መንገድ የተሳሳተ መሆኑ እንዳለ ሆኖ “ለምን እርስ-በእርስ ይጠላለፋሉ?” የሚለውን እንመልከት፡፡ የብሔርተኝነት መንገድ ትክክል ካልሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ የአንድነትን መንገድ መከተል ይመስላቸዋል። በተመሳሳይ፣ የአንድነቶች መንገድ ትክክል ካልሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ የብሔርተኞችን መንገድ መከተል ይመስላቸዋል። ይህ “ጥቁር ወይም ነጭ” በሚል የፍፁማዊነት (infallability) ላይ የተመሠረተ አመለካከት ነው፡፡ የሁለቱም ወገኖች አመለካከት በግትር ፍፁማዊነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የአንዱ ወገን ትክክለኝነት የሚረጋገጠው በራሱ ምክንያት ሳይሆን በሌላው ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ፣ የራስን ሃሳብና አመለካከት ለማረጋገጥ የሌላኛውን መንገድና አካሄድ ውድቅ ማድረግ የግድ ነው። 

በአጠቃላይ፣ በፍፁማዊ የፖለቲካ አመለካከት ለሚመሩ የፖለቲካ ቡድኖች የአንዱ ስኬት ለሌላው ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ፣ የብሔርተኞች ስኬት የሚረጋገጠው በአንድነቶች ውድቀት ነው፡፡ ይህ አንደኛው ወገን ትክክል ሌላኛው ስህተት ስለሆነ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የሁለቱም ወገኖች መንገድና አካሄድ ስህተት ስለሆነ ነው። ምክንያቱም፣ ብሔርተኝነት እና አንድነት የሚያቀነቅኑ ወገኖች በሙሉ የትላንት ምርኮኞች ናቸው። በድጋሜ እንደ ”Jose Ortega y Gassett” አገላለፅ፣ የትላንት ምርኮኞቾ ለህዝብ የሚበጅ መንግስት መመስረት አይችሉም፦

“Not  what we were yesterday, but what we are going to be to-morrow, joins us together in the State.”  The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97.