​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-3/፡ አደዋ እና አኖሌ

“የትላንት ምርኮኞች” በሚለው ተከታታይ ፅኁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው መግባባት አለመቻላቸው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ግራ-መጋባትና ያለመተማመን ስሜት መፍጠሩን፣ ይህም ደግሞ በተራው የኢህአዴግ መንግስት ይበልጥ አምባገነን እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ተመልክተናል። በክፍል ሁለት ደግሞ በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ዋናው ምክንያት ሁለቱም ወገኖች “የትላንት ምርኮኞች” መሆናቸው እንደሆነ ተገልጿል። 

በትላንት እሳቤ የወደፊቱን አቅጣጫ ለመወሰን መሞከር ፍጹም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ የሁለቱም ወገኖች አቋምና አመለካከት በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ግንኙነታቸው ከትብብር ይልቅ መጠላለፍ የበዛበት ይሆናል። ብዙውን ግዜ የብሔርተኞች እና የአንድነቶች የፖለቲካ እንቅስቃሴ የዜሮ ድምር (zero sum) ጨዋታ የሚሆነው ለዚህ ነው። ስለዚህ፣ እንዴት ነው ይህን ችግር መቅረፍ የሚቻለው? 
በመሰረቱ ሀገር የሚመሰረተው ትላንት በነበረን ሳይሆን ነገ ሊኖረን በሚችለው ላይ ነው። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ሀገር ትላንት ላይ የራሱ የሆነ አኩሪ እና አሳፋሪ ታሪክ አለው። ለምሳሌ፣ ኢትዮጲያ አሁን ያላትን ቅርፅ ይዛ የተፈጠረቸው በአፄ ሚኒሊክ ዘመን እንደሆነ ይታወቃል። ታዲያ በዚህ ዘመን ሀገሪቷ የተመሰረተችው በታሪካዊ ድል ብቻ አይደለም። በምስረታ ሂደቱ ታሪካዊ በደሎችና ጭቆናዎች ተፈፅመዋል። 

“Jose Ortega y Gassett” የተባለው ምሁር “The Revolt of the Masses” በተሰኘው መፅሃፉ በዘመናዊ ስልጣኔ ግንባር ቀደም የሆኑትን እንደ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣…ወዘተ የመሳሰሉ የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት አመሰራረትን አስመልክቶ ጥልቅ ትንታኔ ሰጥቷል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከላይ የተጠቀሱት የአውሮፓ ሀገራት ልክ እንደ ኢትዮጲያ በአኩሪ ድልና አሳፋሪ በደል ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ሁሉም ሀገራት አሁን ካላቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና ሀገራዊ አንድነት በስተጀርባ በጣም አኩሪና አሳፋሪ ታሪክ አላቸው። በአጠቃላይ፣ ከእያንዳንዱ ሀገር ምስረታ በስተጀርባ ታሪካዊ ኩራት እና ፀፀት አለ። ነገር ግን፣ በታሪካዊ ድልና በደል ይመስረቱ እንጂ ለወደፊቱ ግን አንድ ዓይነት ፕሮግራም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ “Jose Ortega y Gassett” ስለ ሀገር አመሠራረት እንዲህ ይላል፦

To have common glories in the past, a common will in the present; to have done great things together; to wish to do greater; these are the essential conditions which make up a people…. In the past, an inheritance of glories and regrets; in the future, one and the same programme to carry out….” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97.  

ከላይ በጥቅሱ እንደተጠቆመው፣ ሀገር የሚመሰረተው ትላንት ላይ የሚያኮሩ የጋራ ታሪኮች (common glories)፣ ዛሬ ላይ ደግሞ የጋራ የሆነ ፍቃድ (common will) ሲኖር፣ በዚህም ትላንት አኩሪ ታሪክ አብሮ መስራት፣ ነገ ደግሞ ታላቅ ታሪክ አብሮ ለመስራት በመፈለግ ነው። ይሁን እንጂ፣ ከትላንት የምንወርሰው ታሪካዊ ገድሎችን ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ በደሎችን ጭምር ነው። እነዚህ በቀድሞ ዘመን የተፈፀሙ ታሪካዊ በደሎች ዛሬ ላይ የጋራ ፍቃድ እንዳይኖረን በማድረግ፣ ወደፊት በጋራ አብሮ የመኖርና ታሪክ የመስራት ፍላጎት የሚያሳጣን ከሆኑስ? 

በእርግጥ ይሄ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ በግልፅ የሚስተዋል ወቅታዊ ችግር ነው። የኢትዮጲያ ልሂቃን በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ የሚጠላለፉበት ዋና ምክንያት የጋራ የሆነ ፍቃድ (common will) ስለሌላቸው ነው። ይህ ደግሞ ከአሁኗ ኢትዮጲያ አመሰራረት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የአንድነት አቀንቃኞች በአፄ ሚኒሊክ ዘመን የተፈፀመን ታሪካዊ ድል መነሻ ሲያደርጉ ብሔርተኞች ደግሞ በተመሳሳይ ወቅት በተለያዩ ብሔሮች ላይ የተፈፀመውን ታሪካዊ በደል መነሻ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት በሁለቱ ወገኖች መካክል የሰከነ ውይይት ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። 

ችግሩን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዞ ለማየት እንዲስችለን የአደዋ ድል እና የአኖሌ ጭፍጨፋን እንደ ማሳያ መጠቀም እንችላለን። ለምሳሌ፣ በዚህ አመት የካቲት ወር ላይ የአደዋ የድል በዓል በሚከበርበት ሰሞን አንድ ፅሁፍ በፌስቡክ ገፄ ላይ ለጥፌ ነበር። ይህ ፅኁፍ በብሔርተኞች እና አንድነቶች መካከል ሰፊ ክርክር ከማስነሳቱም በላይ ብዙ ወዳጆቼን አስቀይሟል። 

በወቅቱ የነበረው አቋም በጥቅሉ ሲታይ፤ በአብዛኛው በብሔርተኞች ሲንፀባረቅ የነበረው “አፄ ሚኒሊክን ከአደዋ ድል ጋር ለማያያዝ መሞከር በአኖሌ የተፈፀመውን ግፍና በደል እንደመደገፍ ይቆጠራል” የሚል ነው። በተቃራኒው፣ በአንድነቶች ጎራ ሲንፀባረቅ የነበረው “አፄ ሚኒሊክ የአደዋ ጦርነትን የመሩ፣ የሀገሪቱን አንድነትና ነፃነት ያስከበሩ ብልህና ጀግና መሪ ናቸው” የሚል ነው። 

በዚህ ሁኔታ በሁለቱ ወገኖች መካከል ምንም ዓይነት ውይይት ማድረግ አይችልም። በግልፅ ካልተወያዩ ደግሞ መግባባት ሊኖር አይችልም። እርስ-በእርስ መግባባት ከሌላቸው የጋራ የሆነ ፍቃድ (common will) አይኖራቸውም። ዛሬ ላይ መግባባት የሌላቸው ነገ ላይ በጋራ አብሮ የመኖር ሆነ የጋራ ታሪክ የመስራት ፍላጎት ሊኖራቸው አይችልም። በአደዋ ጦርነት የተገኘው የጋራ ኩራት (common glory) በአኖሌ ፀፀት (regret) ይጣፋል። 

በአጠቃላይ፣ ከቀድሞ ዘመን የወረስነው ታሪካዊ ድልና በደል አሁን ለሚስተዋለው የዜሮ ድምር ፖለቲካ መነሻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል። ስለዚህ፣ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ቁልፉ ጥያቄ “አደዋ እና አኖሌን ማስታረቅ ይቻላል ወይ?” የሚለው ነው። መልሱ በአጭሩ “አዎ” ነው። 

በእርግጥ ለብዙዎች አስገራሚ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ የአደዋ ታሪካዊ ድል እና የአኖሌ ታሪካዊ ጭፍጨፋ በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ይህን በንድፈ ሃሳብ ወይም በሌሎች ሀገራት ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ እውነታ የተረጋገጠ ነው። “እንዴት?” የሚለውን በቀጣዩ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።