​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-5/: መብት እና ጦርነት

በትላንት ምርኮኞች ክፍል 4 እንደተመለከትነው፣ የሀገር አንድነት የሚረጋገጠው በአስከፊ ጦርነት እና ጭፍጨፋ ነው። ምክንያቱን በግልፅ ለመረዳት የሀገር አመሰራረት ሂደትን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ “ሀገር” ማለት ምን ማለት ነው። የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀው መዝገበ ቃላት “ሀገር/ሃገር/አገር” የሚለው ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” ማለት እንደሆነ ይገልፃል። ስለዚህ፣ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የራሳቸውን ሀገርና መንግስት የሚመሰርቱበት ምክንያት ምንድነው? “Jose Ortega y Gassett” ሀገር፥ መንግስት የሚመሰረትበትን አግባብ እንዲህ አብራርቶታል፡- 

“What real force is it which has produced this living in common of millions of men under a sovereignty of public authority which we know as France, England, Spain, Italy, or Germany? …The State is always, whatever be its form- primitive, ancient, medieval, modern- an invitation issued by one group of men to other human groups to carry out some enterprise in common. That enterprise, be its intermediate processes what they may, consists in the long run in the organisation of a certain type of common life. State and plan of existence, programme of human activity or conduct, these are inseparable terms. The different kinds of State arise from the different ways in which the promoting group enters into collaboration with the others.” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97. 

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የራሳቸውን ሀገርና መንግስት የሚመሰርቱበት ምክንያት የወደፊት አብሮነት ሲኖራቸው – የጋራ የሆነ ዓላማና ግብ ለማሳካት ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ በመጀመሪያ አንዱ ጎሣ፥ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ከጎረቤት ላሉት ነገዶች፥ ጎሣዎች፥ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች የአብሮነት ጥያቄ ያቀርባል። በዚህ መሰረት፣ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የጋራ ዓላማን ለማሳካት ያብራሉ (collaborate) ወይም ግብረ አበር (collaborator) ይሆናሉ። ይህ በሕዝቦች መፈቃቀድ (plebiscite) ላይ የተመሰረተ የሀገር አመሰራረት፥ አንድነት ነው። 

ይሁን እንጂ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ያለው ሀገር የለም። ለምሳሌ፣ ለምን የአሁኗ ኢትዮጲያ በብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የጋራ መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት አልኖራትም? አፄ ሚኒሊክ የሸዋ ንጉስ ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ ለምንድነው ጦራቸውን ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫዎች ያዘመቱት? ይህ በተለይ በአርሲ፣ ዲዚ፣ ከፊቾ፣ ወላይታ እና ሌሎች ሕዝቦች አስከፊ እልቂት አስከትሏል። በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ አንድነት ከሕዝቦች መፈቃቀድ ይልቅ ለምን በጦርነትና እልቂት ላይ የተመሰረተ ሆነ? እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ጉዳዩን ከሁሉን አቀፍ የመብት መርህ አንፃር ማየት ይኖርብናል።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሁሉን አቀፍ የመብት መርህ (Universal Principle of Right) መሰረት፣ እያንዳንዱ ተግባር መብት (ስለዚህ ትክክል) ሊሆን የሚችለው በራሱ ወይም የሚፈፀምበት ዓላማ ከእያንዳንዱና ከሁሉም ተሳታፊዎች ፍላጎትና ምርጫ ጋር አብሮ የሚሄድ ከሆነ ብቻ ነው። ጀርመናዊው ፈላስፋ “Immanual Kant” ይህን መሰረታዊ መርህ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡- 

“Every action is right which in itself, or in the maxim on which it proceeds, is such that it can coexist along with the freedom of the will of each and all in action.” The Science of Right, tran. W. Hastie CH1, Page 2

የእያንዳንዱ ሰው መብት የሌሎችን ነፃነትና መብት በማይገድብ መልኩ መሆን አለበት። በዚህ መሰረት፣ የእያንዳንዱ ሰው መብት የሌሎችን መብት ከማክብር ግዴታ ጋር የተጣመረ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሌሎች ሰዎች መብቱን እንዲያከብሩ የማስገደድ ስልጣን ወይም ፍቃድ አለው። እንደ “Immanual Kant”  አገላለፅ፣ “all right is accompanied with an implied title or warrant to bring compulsion to bear on any one who may violate it in fact” 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ አፄ ሚኒሊክ በመጀመሪያ የሸዋ ንጉስ፣ እንዲሁም ቀጥሎ የኢትዮጲያ ንጉሰ-ነገስት በነበረበት ወቅት የሀገሪቱን አንድነት ለማስከበር በሚል ወደ ምስራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አከባቢዎች ያደረጋቸው ዘመቻዎች ተቀባይት የላቸውም። ምክንያቱም፣ የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ ግዛቱን ለማስፋፋት ያካሄዳቸው ዘመቻዎች በአከባቢው የሚገኙ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ራስን-በራስ የመምራትና የማስተዳደር መብትን ይፃረራል። ራስን በራስ የመምራትና የማስተዳደር መብትን የሚፃረር እንደመሆኑ መጠን መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተቀባይነት ያለው ትክክለኛ ተግባር ነው። 

በሌላ በኩል፣ የሰው ልጅ ሕልውና በሕይወት የመኖር ነፃነት ነው። በተመሳሳይ የሀገርና መንግስት ሕልውና ደግሞ ራስን-በራስ የማስተዳደር ስልጣን ወይም ሉዓላዊነት ነው። በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አደጋ በሕይወት ላይ እንደተቃጣ አደጋ ነው። በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አደጋ ልክ በሰው ሕይወት ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ነው። ስለዚህ፣ የሰው ልጅ ሕይወቱን ለማትረፍ እንደሚያደርገው ሁሉ መንግስትም ሉዓላዊነቱን ለመታደግ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ሊወስድ ይችላል። በዚህ ረገድ የሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ የሚዳኝበት የሞራል ሕግ የለም። 

እዚህ ጋር መነሳት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ፣ “በስተደቡብ፥ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫዎች የሚገኙ የተለያዩ ራስ-ገዝ ጎሳዎች፥ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ወይም ግዛቶች በአፄ ሚኒሊክ በሚመሯት ሀገርና መንግስት ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ፈጥረዋል ወይ?” የሚለው ነው? በእርግጥ የጅማ ሱልጣን አባ ጅፋር፣ የወለጋ ኩምሳ ሞረዳ፣ የወላይታው ካዎ ቶና፣…ወዘተ በአፄ ሚኒሊክ ግዛት ላይ ተጨባጭ የሆነ የሕልውና አደጋ አልፈጠሩም። ስለዚህ፣ የአፄ ሚኒሊክ የግዛት መስፋፋት ወይም ወረራን በሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠ አደጋን ለማስወገድ የተደረገ ነው ማለት አይቻልም። 

ሆኖም ግን፣ በሁሉን አቀፍ የመብት መርህ መሰረት፣ በሕልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ እስካለ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ለምሳሌ፣ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀ ሰው ራሱን ለማዳን በሚያደርገው ጥረት የሌላን ሰው ሕይወት ሊያጠፋ ይችላል። በተመሳሳይ፣ በሉዓላዊነቱ ላይ ቀጥተኛ አደጋ የተጋረጠበት ሀገርና መንግስት ሕልውናውን ለመታደግ በጠላት ላይ ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ምንም ተሳትፎ በሌላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ በሀገር ሉዓላዊዊነት ላይ የተጋረጠን አደጋ ለማስወገድ የሚወሰድ እርምጃ ከሞራል አንፃር የሚዳኝበት ሕግ የለውም። ምክንያቱም፣ በሕልውና ላይ የተቃጣ አደጋን ማስወገድ የግድ አስፈላጊ ወይም አስገዳጅ (Necessity) ነው። በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት ተግባርን የሚዳኝበት የሞራል ሕግ የለም። በመሆኑም፣ በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አደጋን ለማስወገድ የተወሰደ እርምጃን “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ይህን የሞራል ሕግ “Immanual Kant” እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

“‘Necessity has no law’. And yet there cannot be a necessity that could make what is wrong lawful” The Science of Right, tran. W. Hastie CH1, Page 6

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃን በቅድሚያ መጠየቅ ያለባቸው አንድ ጥያቄ አለ። እሱም፡- “አፄ ሚኒሊክ በሚያስተዳድሯት ሀገር ወይም ግዛት ሉዓላዊነት ላይ በተጨባጭ የተጋረጠ አደጋ ነበር ወይ?” የሚለው ነው። ከየትኛውም ወገን ቢሆን፣ በያኔዋ ኢትዮጲያ ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠ አደጋ ከነበረ፣ የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ ይህን አደጋ ለማስወገድ በየትኛውም ራስ-ግዛት ላይ ማንኛውም ዓይነት የኃይል እርምጃ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን፣ በሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠ አደጋ የሌሎችን ሕይወትና ንብረት ለማጥፋት፣ እንዲሁም ራስን-በራስ የማስተዳደር ሉዓላዊ ስልጣን ለመቀማት በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። 

በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው፣ ብሔርተኞች ብሔሮች ላይ ስለተፈፀመው ግፍና በደል ምንም ያህል ማስረጃ ቢያቀርቡ፣ አንድነቶች ደግሞ ስለ ሀገር አንድነት ጥቅምና አስፈላጊነት ምንም ያህል ቢናገሩ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመዳኘት የሚያስችል የሞራል ሕግ የለም። በዚህ መሰረት፣ የኢትዮጲያ ልሂቃን እርስ-በእርስ መግባባት የተሳናቸው “ትክክል” እና “ስህተት” ብሎ እንኳን ለመዳኘት በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ነው። ከዚህ ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችን በፊት ግን፣ “በአፄ ሚኒሊክ ዘመን በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ አደጋ ነበር ወይ? እንዴትና ለምን?” የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር መመለስ ያስፈልጋል። ይህን ደግሞ በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን። 

One thought on “​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-5/: መብት እና ጦርነት

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡