“ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”፡ ​የኦሮሚያ-ሶማሌ ግጭት ለምን፥ እንዴት፥ በማን ተፈጠረ?

“ኢትዮጲያ፡ በግራ መጋባት ወደ እርስ በእርስ ግጭት” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅኁፍ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮችን ጨምሮ አብዛኞቹ ልሂቅ በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ግራ መጋባት ውስጥ እንዳሉ ለመጠቆም ሞክሬ ነበር። በተለይ በኦሮሚያና ሶማሌ አጎራባች አከባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ብዙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። ግጭቱ ለምን፥ እንዴትና በማን እንደተጀመረና ሀገሪቷ ወደየት እያመራች እንደሆነ ለመረዳት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ሕልውና በሕገ መንግስቱ ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህ ነው የኢህአዴግ መንግስት “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን” በሚል መርህ የሚመራው። በዚህ መርህ የሚመራበት መሰረታዊ ዓላማ የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆችና መብቶች ለማሰከበር ሳይሆን የራሱን ሕልውና ለማረጋገጥ ሲል ነው። 

የሶማሌ ክልል ፕረዘዳንት አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)

ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ “Aristotle” ስለ ፖለቲካዊ ስርዓት ጥልቅ ትንታኔ በሰጠበት “Politics” የተሰኘ መፅሃፉ እንደ ኢህአዴግ ያሉ መንግስታት “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር” በሚል በስልጣን ላይ የሚቆዩባቸው ሁለት ዓይነት ስልቶች እንዳሉ ይገልፃል። እነዚህም ስልቶች የመጀመሪያው የሕገ መንግስቱን አጥፊዎች ማጥፋት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የሕገ-መንግስቱን አጥፊዎች በመፍጠር ነው። ከዚህ በመቀጠል የተጠቀሰውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ እነዚህን ስልቶች ከሀገራችን ነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመለከታለን።  

1ኛ) አጥፊዎችን በማጥፋት “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”

በ1997ቱ ምርጫ ኢህአዴግ ሕገ መንግስቱን በከፊል ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሮ መሬት ወድቆ አፈር ልሶ ነው የተነሳው። ከዚያ በኋላ እንደ ቆሰለ አውሬ አደረገው። በወቅቱ ተቃዋሚዎች በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ እንደጋረጡበት ይታወቃል። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት ተቃዋሚዎችን ልክ እንደ “የሙት መንፈስ” ይፈራቸው ጀመረ። ስለዚህ “በሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የመቀልበስ ሙከራ አድርገዋል” በሚል ሰበብ ዋና ዋና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን ለእስርና ስደት ዳረጋቸው። እንዲህ ያለውን የፖለቲካ እርምጃ “የሕገ መንግስቱን አጥፊዎች ማጥፋት” እንደሆነ “Aristotle” እንደሚከተለው ገልፆታል፡-   

 “…it is evident that if we know the causes which destroy constitutions, we also know the causes which preserve them; for opposites produce opposites, and destruction is the opposite of preservation.” Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 108

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ባሉት አመታት የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሉን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ድምጥማጡን በማጥፋት በቀጣዩ የ2002ቱ ምርጫ 99.6% ማሸነፉ ይታወሳል። በዚህ ረገድ በአብነት የሚጠቀሰው የፀረ-ሽብር አዋጁ ነው። ይህ አዋጅ ከሃሳብ እስከ አተገባበሩ ድረስ የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆችና ድንጋጌዎች ይጥሳል። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥…ወዘተ የተከሰሱት በፀረ-ሽብር አዋጁ ነው። ከሞላ ጎደል ሁሉም የተከሰሱት “እንደ ኦነግ፥ ግንቦት7፥ ኦብነግ፥ የኤርትራ መንግስት፥ አልሸባብ ወይም ሌሎች የውጪ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ አሲረዋል” በሚል ነው። 

ከአስር አመት በኋላ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃ ሚዲያና ገለልተኛ የሲቭል ማህበራት በሌሉበት በተካሄደው የ2007ቱ ምርጫ ኢህአዴግ “100% አሸነፍኩ” ብሎ መላው ዓለምን አስገረመ። ይህ ከ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ ለኢህአዴግ መንግስት ህልውና ቀጥተኛ አደጋ የነበረውን የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን ሙሉ በሙሉ ከሀገሪቱ ማጥፋቱን ያረጋገጠ ነበር። ተቃዋሚዎችን ከማጥፋት ጎን ለጎን የኢህአዴግ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ለማረጋገጥ በውሸትና ግነት የተሞሉ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል።  

በዚህ ረገድ ተቃዋሚ ኃይሎችን በግልፅ “ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማት፣ የኒዮ-ሊብራል አጀንዳ አራማኞች፣  የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች፣ ጠባብ ብሔርተኞች፣ የትምክህት ኃይሎች፣ የደርግ ናፋቂዎች…” በማለት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ጥረት ያደርጋል። በሌላ በኩል ራሱን የአዲሲቷ ኢትዮጲያ ፍትህ፥ እኩልነት፥ ሰላምና ልማት ዋስትና እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ለምሳሌ “አስማተኛው የ11% ፈጣንና ተከታታይ እድገት፣ ብዙሃንነትና የብሔሮች እኩልነት፣ የፌደራሊዝም ስርዓት፣ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ደሴት፣….” ነገር ግን፣ ለአስር አመት በ11% የኢኮኖሚ እድገት እና በ100% ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲያደነቁረው የነበረው ሕዝብ በ11ኛ አመቱ ገንፍሎ አደባባይ ወጣ። 

የኢህአዴግ መንግስት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በ2007 ዓ.ም የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡትን ዜጎች በመግደል፣ በመደብደብና በማሰር ለማስቆም ያደረገው ጥረት ጭራሽ ችግሩን ይበልጥ አባባሰው። እንደ “Aristotle” አገላለፅ፣ እዚህ ጋር የኢህአዴግ መንግስት አደጋውን ለመከላከል የስልት ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ይገልፃል፡- 

“In the first place, then, men should guard against the beginning of change, and in the second place they should not rely upon the political devices of which I have already spoken invented only to deceive the people, for they are proved by experience to be useless.” Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 108

ይሁን እንጂ፣ በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ወደ አማራ ክልል ተስፋፋ። በ2008 ዓ.ም የመጀመሪያ አጋማሽ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የወጡትን ዜጎች “ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት፣ የኒዮ-ሊብራል አጀንዳ አራማኞች እና የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች፣ የደርግ ናፋቂዎች… ወዘተ” በሚል በተለመደው መልኩ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት አደረገ። የኢህአዴግ መንግስት የሕዝቡ ጥያቄ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ መሆኑን ተቀብሎ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኢትዮጲያ ሕዝብ ይቅርታ ከጠየቁ በኋላም የተቀየረ ነገር የለም። በመጨረሻ በሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ እርስ-በእርስ የመቀናጀትና የመደጋገፍ አዝማሚያ እያሳየ ሲመጣ አንድ አዲስ ፖለቲካዊ ክስተት ተፈጠረ። 

2ኛ) አጥፊዎችን በመፍጠር “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”

የሶማሌ ክልል ፕረዜዳንት የሆኑት አቶ አብዲ ኢሌ የፌደራሉ መንግስት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተስፋፋውን ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት የክልሉን “ልዩ ፖሊስ” ሊጠቀም እንደሚችል በይፋ ተናገሩ። በመቀጠል ለትግራይ ክልላዊ መስተዳደርና ገዢው ፓርቲ ህወሓት ድጋፍና አጋርነታቸውን አሳዩ። በተቃራኒ የአማራና ኦሮሚያ ክልል መስተዳደሮችን ለፌደራል ስርዓቱ አደጋ የሆነ እንቅስቃሴን መቆጣጠር ተስኗቸዋል በሚል መተቸት ጀመሩ። በመጨረሻም የኦህዴድ/ኢህአዴግ እና የክልሉ ፕረዜዳንትን በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳለው በድፍረት ተናገሩ። 

የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ያነሳውን የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በይፋ ለመቃወምና ሕዝባዊ ንቅናቄውን በኃይል ለማዳፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ፍቃደኝነታቸውን የገለፁት ግለሰብ፥ ፕ/ት አብዲ መሃመድ ኦማር (አብዲ ኢሌ) ማን ናቸው? በኦሮሚያና አማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ከፌደራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጎን ይሰለፋል ያሉት ልዩ ፖሊስ የተቋቋመበት ዓላማና ተግባር ምንድነው? ይህ ኃይል አሁን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አጎራባች አከባቢዎች ለተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት የነበረው ሚና ምንድነው? እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ስለ ልዩ ኃይሉ እና ዋና አዛዡ አመጣጥ ወደኋላ ተመልሰን እንመልከት። 

በመጀመሪያ ደረጃ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የተመሰረተው እ.አ.አ. በ2007 (1999 ዓ.ም) ነው። ልዩ ኃይሉ የተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን (ONLF) በክልሉ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መግታት ነበር። የአሁኑ የሶማሌ ክልል ፕረዜዳንት አብዲ ኢሌ ደግሞ በወቅቱ የልዩ ኃይሉ ዋና አዛዥ ነበሩ። በቀጠይ ጥቂት አመታት ውስጥ በአብዲ ኢሌ የሚመራው የክልሉ ልዩ ኃይል የአማፂያኑን እንቅስቃሴ መግታቱ ይነገርለታል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ልዩ ኃይሉ የተከተለው የውጊያ ስልት ነው። 

አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ባለው ማህብረሰብ ውስጥ ለአማፂያኑ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የተጠረጠሩ ነዋሪዎችን መጨፍጨፍ ነው። የተባበሩት መንግስታት እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት አብዲ ኢሌ የሚመራው ልዩ ኃይል ጦርነት የገጠመው ከአማፂያኑ ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር ነው። በራሱ ሕዝብ ላይ ጦርነትና ሽብር በመክፈት አማፂያኑን ከውስጡ እንዲያስወጣ ማስገደድ። በዚህም በስልጣን ላይ ያለውን የክልሉን መንግስት ሳይወድ በግድ እንዲደግፍና እንዲቀበል አድርጎታል። ይህ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የተካነበት የራስን ሕዝብ በማሸብር ተቀባይነት የማግኘት ስልትን “Aristotle” አጥፊዎችን በመፍጠር ስርዓቱን መጠበቅ መሆኑን ይገልፃል፡- 

“Constitutions are preserved when their destroyers are at a distance, and sometimes also because they are near, for the fear of them makes the government keep in hand the constitution. Wherefore the ruler who has a care of the constitution should invent terrors, and bring distant dangers near, in order that the citizens may be on their guard,… No ordinary man can discern the beginning of evil, but only the true statesman.” Source: Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 109

እ.አ.አ. በ2010 (2002) ዓ.ም አቶ አብዲ ኢሌ በአማፂያኑ ላይ ያስመዘገቡትን “ስኬት” ተከትሎ የክልሉ ፕረዜዳንት ለመሆን በቁ። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም በክልሉ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ ሽብርና ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር “human rights watch” የተባለው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል። እ.አ.አ. ከ2015 (2007/08) ዓ.ም ጀምሮ ግን ከላይ የተጠቀሰውን የውጊያ ስልት በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በሚገኙ አከባቢዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። በዚህ መልኩ የተጀመረው ጥቃት ዛሬ ላይ ከ140ሺህ በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል። ከ200 ንፁሃን ዜጎች ደግሞ  ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የሶማሌ ልዩ ኃይል በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ላይ ሽብርና ጥቃት የጀመረው ልክ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው አመፅና ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት የ2008 አመት መገባደጃ ላይ ነው። የክልሉ ልዩ ኃይል እና ዋና አዛዡ የሶማሌ ክልል ሕዝብን በመጨፍጨፍና በማሸበር የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርንን ከክልሉ ለማስወጣት የተፈጠሩ እንደሆነ ተገልጿል። በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ እየፈፀሙት ያለው ጥቃትና ሽብር መጀመሪያ ከተፈጠሩበት ዓላማ ጋር ፍፁም አንድና ተመሳሳይ ነው። ይኸውም የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጥቃትና ሽብር በመፈፀም የክልሉ ሕዝብ ያነሳውን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማኮላሸት ነው።  

ከዚህ በተጨማሪ፣ የክልሉ ፕረዜዳንት ትላንት ከሀገር ሽማግሌዎችና የክልሉ መንግስት አመራሮች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት በምክንያትነት ያነሷቸው ነገሮች የክልሉ ልዩ ኃይል እና ዋና አዛዡ ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ በግልፅ ይጠቁማል። እነዚህ ምክንያቶች የኢህአዴግ መንግስት ከ1997ቱ ምርጫ ግን የፖለቲካ መሪዎችን፥ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾችን፥ የሃይማኖት መሪዎችን፥…ወዘተ በፀረ-ሽብር አዋጁ ሲከስ የሚጠቀምባቸው “ኦነግ፥ ኦብነግ፥ አልኢተሓድ፥ የኤርትራ መንግስት፥ ሌሎች የውጪ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር፣ …የፌደራል ስርዓቱን በኃል ለማተራመስና አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለማስመለስ…ወዘተ ከሚለው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። 

በአጠቃላይ፣ ላለፉት አስር አመታት በፌደራል መንግስት ስም አዲስ አበባ ተቀምጦ “ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ” የሚል ሰበብ እየፈጠረ የፖለቲካ መሪዎችን፥ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾችን፥ የሃይማኖት መሪዎችን፥…ወዘተ በእስርና ስደት ከሀገር እንዲጠፉ ሲያደርግ የነበረው የፖለቲካ ቡድን ዛሬ ላይ የስልት ለውጥ አድርጏል። በዚህ መሰረት፣ አጥፊዎቹን ከማጥፋት ይልቅ አጥፊዎችን በመፍጠርና የኦሮሞ ሕዝብን በሽብርና ጦርነት በማሸማቀቅ የመብትና ነፃነት ጥያቄ እንዳያነሳ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን (ONLF) ከሶማሌ ክልል እንዲያስወጣ በሚል በመከላከያ ሠራዊትና የፀረ-ሽብር ግብር ኃይል የተደራጀ መሆኑ ይታወቃል። በሶማሌ ክልል ሕዝብ ላይ ሲፈፅም ለነበረው ጥቃት የተከተለው የዉጊያ ስልት፥ ትጥቅና ዓላማን ከእነዚህ አካላት ማግኘቱ ግልፅ ነው። ዛሬ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ተመሳሳይ የውጊያ ስልት፥ በተመሣሣይ ትጥቅና ድጋፍ፣ ለተመሣሣይ ዓላማ ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም።    

 

3 thoughts on ““ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”፡ ​የኦሮሚያ-ሶማሌ ግጭት ለምን፥ እንዴት፥ በማን ተፈጠረ?

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡