​ኦሮማይ-1፡ በይስሙላ ምርጫ ወደ ለውጥ ማዕበል!

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የተነሳ ሰሞን ባወጣሁት “ኢትዮጲያ የማን ናት”  የሚል ፅሁፍ፤ “የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% ‘አሸነፍኩ’ ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው” ብዬ ነበር። ይህ ዛሬ ላይ በድንገት የተገለጠልኝ እውነት አይደለም። ልክ የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ይፋ እንደተደረገ “100% የምርጫ ቅሌት እንጂ ውጤት አይባልም” በማለት የሚከተለውን ፅፌ ነበር፡- 

“100% የሚባለውን አሰቃቂ ክስተት “የምርጫ ውጤት” በሚል ሰርግና ምላሽ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉትስ አይፈረድባቸውም። በፌዴራልና ክልል ደረጃም ተመሳሳይ አቋም የሚያራምዱ ባለስልጣናት ካሉ ግን በጣም አስገራሚ ነው የሚሆነው ። ይሄ 100% ተብዬ ነገር’ኮ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ሀገሪቱ በዲሞክራሲ ረገድ ያሳየችውን ለውጥና መሻሻል ወደ ኋላ የቀለበሰ፣ ህዝቡ ሰላማዊ ፖለቲካ፣ በሕግ የበላይነት እና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ያለውን እምነት ሽርሽሮ በመናድ ዴሞክራሲን በጭቅላቱ ዘቅዝቆ ያቆመ፣ ልክ እንደ ደርጉ ቀይ-ሽብር ህዝብን በፍርሃት ቆፈን የሚቀፈድድ እጅግ አስቀያሚ ድርጊት ነው።” 

በተለይ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። የኢህአዴግ መንግስት እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። 

በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። በተቃራኒው፣ ከ2008 ዓ፣ም ጀምሮ ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየረና እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለበት የቆመው የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው። 

በ2008 ዓ.ም 3ኛው ማዕበል በሚለው ባወጣሁት ፅሁፍ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በሀገሪቱ ውስጥ የታየው ለውጥ በሀገሪቱ ታላቅ የፖለቲካ ማዕበል እንደሚያስነሳ ገልጬያለሁ። ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት አንዲት እርምጃ መራመድ ተስኖታል። ለኢህአዴግ መንግስት ዛሬም፥ የዛሬ ሁለት አመት ሆነ የዛሬ አስር አመት “ፈተናዎቹ”፤ የመልካም አስተዳደር እና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፡- ትምክህተኝነት፥ ጠባብ ብሔርተኝነት እና አክራሪነት” ናቸው።  

የህዝቡ ጥያቄና እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የመጣ እንደመሆኑ አይቀሬና አስገዳጅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የህዝቡ ኑሮና አኗኗር እየተለወጠ፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ግዴታውን ይበልጥ ያውቃል፥ ይጠይቃል። በልማትና ዴሞክራሲ ረገድ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይበልጥ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መሄዳቸው እርግጥ ነው። 

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየታየ ያለው ተቃውሞ ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቱን ለማስከበር የሚችልበት አማራጭ መንገድ በማጣቱና ብሶትና ምሬቱን የሚተነፍስበት ትንሽ ቀዳዳ ባለመኖሩ የተከሰተ ነው። በአንድ በኩል ህዝቡ በፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየተሰቃየ ነው። በሌላ በኩል፣ ለአስር አመታት የተጠራቀመ ብሶቱንና ምሬቱን የሚያስተነፍስበት ቀዳዳ ሲያጣ፣ አመፅና ተቃውሞ ብቸኛ አማራጭ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ፣ ቀልጣፋ አገልግሎትና ፍትህ ያልሰፈነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የአስተዳደርና ፍትህ ሥርዓቱን ማሻሻል ስለተሳነው እንደሆነ በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሲኖረው ህዝብ ይቆጣል፣ ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀሳል።  

በጅምላ የታሰሩ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል!

ከዚያ በመቀጠል “ኢህአዴግ፡ ከለውጥና ሞት አንዱን ምረጥ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የኢህአዴግ መንግስት ሁለት አማራጮች እንዳሉት ገልጩ ነበር። የመጀመሪያ አማራጭ የሕዝቡን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ በመጓዝ በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ እየተነሳ ያለውን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት በማፈን የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋውን ማጨለም ነው። በዚህ መንገድ የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት መስዕዋት የሚጠይቅ ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት መጨረሻው ውድቀት ይሆናል። 

ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ  የኢህአዴግ መንግስት አካሄድ የፈጠረብኝን ስጋት፤ “አሁን ላይ ይበልጥ እያሳሰበኝ ያለው ነገር፣ ኢህአዴግ ከሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ አለመቻሉ ሳይሆን በዚህ ምክንያት የሀገሪቱ ዜጎች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱ ነው!” በማለት ገልጩ ነበር። ከዚሁ ጋር አያይዤ፣ ከ2008 ዓ.ም ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ከለውጥ እና ሞት አንዱን እንደመምረጥ መሆኑን ጠቅሼ ነበር። ሆኖም ግን፣ በቀጣዩ የ2009 አመት የተካሄደውን “ጥልቅ ተሃድሶ” ከተመለከትኩ በኋላ “ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው” የሚል ፅሁፍ አወጣሁ። ይህ የኢህአዴግ መንግስት ከለውጥ ይልቅ ሞትን እንደመረጠና እንደ ፀጉራም ውሻ ማንም ሳይውቅለት ውስጥ-ለውስጥ እየሞተ እንደሆነ ይጠቁማል። 

One thought on “​ኦሮማይ-1፡ በይስሙላ ምርጫ ወደ ለውጥ ማዕበል!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡