​አባዱላ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት (በነጋሽ መሃመድ) 

መስከረም 2003 የምክር ቤቱን የፕላስቲክ መዶሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጨብጡ፤ ያዩ እንዳሚተርኩት፤ በፈገግታ ደምቀዉ መዶሻዋን አገላብጠዉ አይዋት።ከዚያ ቀና፤አይናቸዉን ከፊት ለፊታቸዉ ወደ ተቀመጡት ሹማምንት ወረወሩት እና ፊታቸዉን ቅጭም አደረጉ።
[ይህን ሊንክ በመጫን] አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:43

ሐሰን ዓሊ፤ነጋሶ ጊዳዳ—ሙክታር ከዲር—አባዱላም ሔዱ 

በቅርብ የሚያዉቋቸዉ እንደሚተርኩት ሚናሴ ወልደማሪያም በሚባሉበት ዘመን እንደ ወታደር ለኢትዮጵያ አንድነት ተዋጊ፤ እንደ ተሻናፊ ጦር ምርኮኛ ነበሩ። እንደ ታጋይ አባዱላ ሆኑ። እንደ ፖለቲከኛ የኦሮሞ ብሔረተኛ፤ እንደ ጄኔራል የጦር መሪ ነበሩ። የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ዶክተር ነገሶ ጊዳዳ ዛሬም «ጄኔራል» ነዉ የሚሏቸዉ። ሕጋዊ ምክንያት አላቸዉ። በ1997ቱ የምርጫ ዘመቻ የያኔዉ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና «ጄኔራል ልበልዎት አቶ» ብለዉ ነበር። ሰዉዬዉ ግን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነትን በሕግ ከሚከለክለዉ የጦር ሠራዊት አባልነት ወደ ኦሕዴድ መሪነት፤ ከጄኔራልነት፤ ወደ ኦሮሚያ ርዕሠ-ብሔርነት፤ ከርዕሰ ብሔርነት ወደ ምክር ቤት አፈጉባኤነት ያደረጉትን ፖለቲካዊ ጉዞ «በቃኝ» አሉ። የአባዱላ ዉሳኔ መነሻ፤ የፖለቲካ ጉዟቸዉ ማጣቀሻ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።                          

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ለሁለት ሲከፈል ከሥልጣን የተወገደዉን ኃይል ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ ለማፅደቅ ጊዜ አልፈጀበትም።ቅንጅት የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫ ማሸነፉ ሲነገር ተሰናባቹ ምክር ቤት ገና ወደፊት የሚመሰረተዉ ምክር ቤት የሚመራበትን ደንብ አፅድቋል።

የተቃዋሚዎች ግፊት፤ የሲቢክ ማሕበረሰብ አባላት እንቅስቃሴ ጠንከር፤በርታ፤ ጠጠር ሲል ፀረ-ሽብር ደንብ፤ የበጎ አድራጎት እና የመያዶች ደንብ የሚባሉ ሕጎችን ለማፅደቅ አላመነታም። የኦሮሚያ፤ የአማራ እና የከፊል ደቡብ  መስተዳድሮች ሕዝብ በተከታታይ ሲቃወም ግን «የሕዝብ ዉክልና ተቀብለዋል የሚባሉ አባላት የሚሰበስቡበት ምክር ቤት

Äthiopien | Parlament (DW/Y. G. Egziabher)

የሕዝብን እንቅስቃሴ የሚገድብ ደንብ አፀደቀ።የኦሮሚያ እና የሶማሌ መስተዳድር ግጭት መቶዎችን ሲገድል፤ ሺዎችን ሲያፈናቅል የሕዝብ እንደራሴ የሚባሉት የምክር ቤት አባላት ለመነጋገር እንኳን አልቃጡም።

የዩኒቨርስቲ መምሕር እና የአምደ መረብ ፀሐፊ አቶ ስዩም ተሾመ እንደሚሉት ሕዝብ ሲቃወም፤ ሲበደል  ሲገደል፤ ሲሰደድ ምክር ቤቱም፤ አፈጉባኤዉም ለሕዝብ ምንም አልሰሩም።

አባዱላ ገመዳ ለወከለዉ ሕዝብ ምንም አላደረገም የሚባለዉን ምክር ቤት መምራት የጀመሩት 2003 ነበር።ከሰባት ዓመት በኋላ ሥልጣን ለቀቁ።ሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑበትን ትክክለኛ ምክንያት እራሳቸዉ ወይም ሿሚዎቻቸዉ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በግልፅ አላስታወቁም።የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን አባዱላ ሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት በቅርቡ በሶማሊያና በኦሮሚያ መስተዳድሮች የተቀሰቀሰዉን ደም አፋሳሽ ግጭት የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት አለማስቆሙን በመቃወም ነዉ።አቶ ሥዩምም በዚሕ ይስማማሉ።                          

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት እና የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል  ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚገምቱት ግን አባዱላ በገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥራ-እና አሰራር ቅሬታ ካደረባቸዉ ቆይቷል።                         

የቅሬታዉ ዝርዝር ብዙ ነዉ።መስከረም 2003 የምክር ቤቱን የፕላስቲክ መዶሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጨብጡ፤ ያዩ እንዳሚተርኩት፤ በፈገግታ ደምቀዉ መዶሻዋን አገላብጠዉ አይዋት።ከዚያ ቀና፤አይናቸዉን ከፊትለፊታቸዉ ወደ ተቀመጡት ሹማምንት ወረወሩት እና ፊታቸዉን ቅጭም አደረጉ።

የሳቅ ፈገግታቸዉ ምክንያት

Äthiopien Abadula Gemeda und Kang Chang-hee (picture alliance/AP/Yonhap)

ጠመንጃ፤ መትረየስ፤ በትረ መኮንን ሲያገላብጥ የኖረ እጃቸዉ ሳይደክም የእንጨት ጠረጴዛ መወገሪያ መዶሻ እንዲይዝ መገደዱ ሊሆን፤ ላይሆንም ይችላል።

ብዙዎች እንደሚስማሙበት ግን ሰዉዬዉ ከተራ ታጋይነት ባጭር ጊዜ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ መስራችነት፤ ከጄኔራልነት ወደ ርዕሠ-መስተዳድርነት ከርዕሰ መስተዳድርነት ወደ አፈ ጉባኤነት የመገለባበጣቸዉ መሠረት ለአለቆቻቸዉ በተለይ ለቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ለአቶ መለስ ዜናዊ «አቤት» ባይ በመሆናቸዉ ነዉ።                        

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (አነግ) እንደ ሁለተኛ ትልቅ የፖለቲካ ፓርቲ የመሠረተዉን መንግስት ጥሎ ሲወጣ፤ በሁለት እግሩ ለመቆም የሚዉተረተረዉ ኦሕዴድ የኦነግን ክፍተት እንዲሞላ ሲያንደርድሩት ከነበሩት ከፍተኛ መሪዎች አባዱላ አንዱ ነበሩ።

ሐሰን ዓሊ ከተራ አባልነት ወደ ርዕሰ-መስተዳድርነት ሲንቻረሩ መወጣጫ መሠላሉን ከዘረጉት፤ ከርዕሠ-መስተዳድርነት ማማ  ተሽንቀንጥረዉ ከስደት አረሕ ላይ ሲያርፉ-የተዘረጋዉን መሰላል ካጠፉት አንዱ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ፤ ኩማ ደመቅሳ፤አልማዝ መኮ፤ጁነዲን ሳዶ፤ሙክታር ከድር፤ አስቴር ማሞ ሽቅብ ወጥተዉ ሲወርዱ፤ ሲሰደዱ ወይም ሲባረሩ እሳቸዉ ነበሩ።ዘንድሮ ምን አገኛቸዉ? ካልተመቻቸዉ መልቀቅ ይላሉ አንድ የኦሕዴድ አባል።                                   

አቶ ስዩም ተሾመ ደግሞ  በተሰጣቸዉ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን መጠቀም ሥላልቻሉ ነዉ ባይ ናቸዉ።                          

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሚያስተናብራቸዉ አራት የፖለቲካ ማሕበራት ትልቁን አካባቢ የሚያስተዳድረዉ በርካታ የምክር ቤት መቀመጫ ያለዉም የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዉ ድርጅት (ኦሕዴድ) ነዉ።መሪዎቹን ቶሎ በመቀያየርም ኦሕዴድን የሚስተካከል የለም።አቶ ሐሰን ዓሊ፤ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤

Äthiopien | Parlament (DW/Y. G. Egziabher)

አቶ ኩማ ደመቅሳ፤ አቶ ድሪባ ሐርቆ፤ አቶ ዮናታን ዲቢሳ፤ ወይዘሮ አልማዝ መኮ፤ አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ አቶ ሙክታር ከድር፤ አሁን ደግሞ አቶ አባዱላ ገመዳ።በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት በመቃወም ተደጋጋሚ ሕዝባዊ አመፅ የሚደረገዉም ኦሕዴድ በሚያስተዳድረዉ አካባቢ ነዉ።ዶክተር ነጋሶ የኦሕዴድ ለጋነት-አንድ፤ የሌሎቹ የኢሕአዲግ መሪዎች ተፅዕኖ ሁለት ምክንያት አላቸዉ።                             

አቶ ስዩም ተሾመ ደግሞ የኦሮሞን ሕዝብ መሪ አልባ የማድረግ እርምጃ አንዱ አካል ነዉ ይላሉ።

አቶ አባዱላ ከሳቸዉ በፊት የነበሩ፤ ጄኔራሎችን፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፤ርዕሰ-መስተዳድሮችን፤ አፈ ጉባኤዎችን ሲተኩ እንደነበረዉ ሁሉ ዛሬ በተራቸዉ በሌላ መተካታቸዉ እርግጥም ቀላልም ነዉ።የኦሕዴድ-በተናጥል፤ የኢሕአዴግ-በጥቅል የወደፊት ጉዞ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት ማነጋገሩ አይቀርም።አቶ  ስዩም የማይቀረዉን መጠበቅ ይሉታል። 


DW_Amharic
ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

One thought on “​አባዱላ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እዉነት (በነጋሽ መሃመድ) 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡