የኢህአዴግ ​ለዛ-ቢስ ቃላቶች ክፍል-2: ​ሰላም፥ ልማት፥ ዴሞክራሲ 

ለዛ-ቢስ ቃላቶች በሚለው ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ቅጥ ከመደጋገማቸው የተነሳ ለዛ-ቢስ ከሆኑት ቃላት ውስጥ ጥገኝነት፥ ጠባብነትና ትምክህት የሚሉትን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ በኢህአዴግ መንግስት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው የተነሳ ትርጉም-አልባ ወደ መሆን የተቃረቡትን ሰላም፥ ዴሞክራሲና ልማት የሚሉት ቃላት እንመለከታለን፡፡ 

በመሰረቱ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ የመንግስት መሰረታዊ ዓላማዎች ናቸው። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት የራሱን ስኬት ያለ ቅጥ እያጋነነ፣ የሌሎችን እያጣጣለ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እያጣ ከመምጣቱም በላይ ቃላቱን ለዛ-ቢስ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። 

እነዚህ ሦስት ዓላማዎች በነፃነት ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑም የኢህአዴግ መንግስት ግን ስኬቱን ከዜጎች ነፃነት አንፃር ማየት አይሻም። ከዚያ ይልቅ፣ ከሦስቱ መሰረታዊ ዓላማዎች አንፃር ያስመዘገባቸውን አንኳር ለውጦች በቁጥር ለመለካት ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲን በቁጥር መለካት ክብደትን በሜትር እንደ መለካት ነው። በዚህ ምክንያት፣ የኢህአዴግ መንግስት እንደ ስኬት የሚያቀርባቸው ዘገባዎች፣ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአብዛኛው ትርጉም አልባ ይሆናሉ። ከዚህ አንፃር፣ ሦስቱ ቃላት ከነፃነት ጋር ያላቸውን ቁርኝነት በአጭሩ እንመልከት፡-   

“ሰላም” የሚረጋገጠው ዜጎች በነፃነት ወደ ፈለጉት ቦታ በፈለጉት ግዜ መንቀሳቀስ፣ ለደህንነታቸው ሳይሰጉ በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት ሲችሉ ነው። የፀረ-ሰላም ኃይሎች ዓላማ ደግሞ በሕይወትና ንብረት ላይ ድንገተኛ ጉዳት በማድረስ ይህን የዜጎችን በሰላም የመንቀሳቀስ ነፃነት ወደ ፍርሃት መቀየር ነው። “ሰላም” ማለት በፈለጉት ግዜና ቦታ ያለ ስጋት መንቀሳቀስ መቻል ነው። “ነፃነት” ደግሞ ያለ ማንም አስገዳጅነት በራስ ምርጫና ፍላጎት መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። በአጠቃላይ፣ ሰላም ማለት የዜጎች ነፃነት ነው። 

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚል በመንግስት የሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ የሰላማዊ ዜጎችን ሰላም/ነፃነት መገደብ የለበትም። ሰላም ማለት በራስ ምርጫና ፍላጎት መሰረት በፈለጉት ቦታና ግዜ የፈለጉትን ነገር ማድረግ መቻል እንጂ በኢህአዴግ መንግስት ምርጫና ፍቃድ መሰረት መንቀሳቀስ አይደለም። የኢህአዴግ መንግስት ግን ነፃነቴን ገድቦ ስለ ነፃነት መስበክ ይቃጣዋል፤ ሰላሜን አሳጥቶኝ ስለ ሰላም አስፈላጊነት ያወራል። በዚህ ምክንያት፣ “ሰላም” የሚለው ቃል ለዛና ትርጉሙን አጥቷል። ሌላው ቀርቶ፣ ኢህአዴግ ስለ ሰላም ሲያወራ ሕዝቡን ሰላም ይነሳዋል። 

“ልማት” ማለት በአጭሩ “ሰላም፣ ጤና፣ ትምህርትና መሰረተ-ልማት” ማለት ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ዘላቂ ልማት ሊኖር የሚችለው እነዚህ ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በእኩልነት ተደራሽ ሲሆኑና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው። በኢህአዴግ መንግስት የልማት መርህ መሰረት ግን፣ ማህብረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ግለሰቦች መሰረታዊ ጥቅማቸውን ማጣት አለባቸው። የልማቱ ጥቅምም ሆነ ጉዳቱ ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል እኩል መዳረስ አለበት። 

በኢህአዴግ የመሰረተ-ልማት ግንባታ መርህ መሰረት፣ ሀብታም ለሚያቋቁመው የአበባ ፋብሪካ ደሃ ገበሬ ከእርሻ መሬቱ ይፈናቀላል፣ ሀብታም ለሚገነባው ፎቅ ደሃ የከተማ ነዋሪ መኖሪያ ቤት ይፈርሳል። ይህ ለአንዱ ልማት ሌላው ግን ጥፋት ነው። በመሰረታዊ የነፃነት መርህ መሰረት ደግሞ የእኔ መብት የሌላን ሰው ነፃነት መገደብ የለበትም። የባለሃብት ፋብሪካ የማቋቋም መብት አርሶ-አደርን የእርሻ መሬት ማሳጣት የለበትም። ሀብታም የሚገነባው ቤት በደሃ መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ ላይ መሆን የለበትም። የአንዱ ዜጋ በነፃነት የመስራት መብት የሌላውን ዜጋ በነፃነት የመኖርና የመስራት መብት ማሳጣት የለበትም። በዚህ መሰረት፣ የልማታዊ ስራ አግባብነትና የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚለካው ከዜጎች ነፃነት አንፃር ነው። የኢህአዴግ መንግስት ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ ሳልሆን ስለ ልማት ይደሰኩራል። እኔ በነፃነት የመስራትና የመኖር መብቴን ተነፍጌ ሌሎች ሀብትና ንብረት ሲያፈሩ እያየሁ ኢህአዴግ ስለ ልማት ሲያወራ ከመስማት የዘለለ ምን ጸያፍ ነገር አለ? 

“ዴሞክራሲያዊ” ሥርዓት በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተና የዜጎች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ስርዓት ነው። በዚህም፣ የዜጎች አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት፣ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን፣ ኢትዮጲያ ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ፥ ቡድን፥ ማህበር፥ ድርጅት፥…ወዘተ፣ ከኢህአዴግ መንግስት ምርጫና ፍቃድ ውጪ እስከ ተንቀሳቀሰ ድረስ “ከፀረ-ሰላም ኃይሎች” ጎራ ሊመደብ ይችላል። ሌላው ቀርቶ፣ ስለ ሰላም መናገርና መፃፍ በራሱ “ፀረ-ሰላም” ሊያስብል ይችላል። በኢህአዴግ አመለካከት “ለሰላማዊ ሰልፍ” እና “ለትጥቅ ትግል” ጥሪ ያቀረቡ ወገኖች ሁለቱም እኩል “ፀረ-ሰላም” ናቸው። “የአማፂ ቡደን አባል” እና “ስለ አማፂ ቡዱኑ የፃፈ ጋዜጠኛ” እኩል በፀረ-ሽብር ሕጉ ተከሰው ራሳቸውን በማዕከላዊ እስር ቤት ሊያገኙ ይችላሉ። 

የኢህአዴግ መንግስት በሚያከናውነው ማንኛውም የልማት ሥራ ላይ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የሚያነሱ ግነሰቦች” ቡድኖች፥ ማህበራት፥ ድርጅቶች፥ …ብቻ በልማት አግባብነት ላይ ጥያቄ ያነሱ አከላት በሙሉ “ፀረ-ልማት፣ የኒዮ-ሊብራል ተላላኪዎች፣ የኪራይ ሰብሳቢዎች፣…” በሚል የውግዘት መዓት ሊወርድበት ይችላል። እንደ ዜጋ ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ አለመሆኔ ሳያንስ “ፀረ-ልማት” የሚል ተቀፅላ ስም ይሰጠኛል። በአጠቃላይ፣ ኢህአዴግ ከእሱ አቋምና አመለካከት ውጪ ያሉትን በሙሉ “ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ኃይሎች ተላላኪዎች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣…” ስም ያወጣል። 

የኢህአዴግ መንግስት ሰላሜን ያሳጣኝ ሳያንስ “ፀረ-ሰላም” ይለኛል። ከሀገሪቱ ልማት እኩል ተጠቃሚ አለመሆኔ ሳያንሰኝ “ፀረ-ልማት” ብሎ በቁስሌ ላይ እንጨት ይሰዳል። ይህን ባለበት አንደበቱ ደግሞ ተመልሶ ስለ ሀገሪቱ “ሰላምና ልማት” ሊሰብከኝ ይሞክራል። በሰላም ስም ሰላሜን አሳጥቶኝ፣ ከልማት ተጠቃሚ እንዳልሆን ከሌሎች ለይቶ በድሎኝ፣ በደልና ቅሬታዬን ብናገር የሀገሪቱን ሰላም እና ልማት ለማደናቀፍ በሚል አስሮ ያሰቃየኛል። 

One thought on “የኢህአዴግ ​ለዛ-ቢስ ቃላቶች ክፍል-2: ​ሰላም፥ ልማት፥ ዴሞክራሲ 

  1. Their philosophy is based abusing sensitive words to create illusion over the people. and it worked for a lot.
    I for one ask myself once “why i show abhorrence of these words?” and was about to fall into a trap without realizing the words are actually abused.
    Too psychological.

    Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡