ሰው ፥ ፍጥነት፥ ዕውቀት፥ የግንዛቤ አድማስ፥…

የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ችሎታ ያለ ገደብ የተሰጠ አይደለም። የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ከቦታ (Space)፣ ግዜ (Time) እና ከምክንያታዊ (rational) ግንዛቤ አንፃር የተገደበ ነው። እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው ልጅ በአንድ ግዜ ሁሉም ቦታ ወይም በሁሉም ግዜ አንድ ቦታ መገኘት (omnipresent) አይችልም።
በዘመናዊ ሥልጣኔ የተገኘው ዋና ነገር “ፍጥነት” (Speed) ነው። ይህም በምድር፣ በህዋ፣ በአየር፣ በውሃ፣…ወዘተ ፈጣን እቅስቃሴ እና ግንኙነት ማድረግ አስችሏል። በዚህ መሰረት፣ ፍጥነት በሥራና አሰራራችን፣ በኑሮና አኗኗራችን ላይ ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ነባራዊ እውነታን የመገንዘብ አቅማችን ውስን አድርጎታል።

በመሰረቱ በሁሉም ቦታ እና ግዜ መገኘት የሚችል ፍጡር ፈጣን ባቡር፣ አውሮፓላን ወይም ኢንተርኔት መጠቀም አያስፈልገውም። የሰው ልጅ እነዚህ የመጓጓዣና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች የፈጠረውና በስፋት የሚጠቀመው በትንሽ ግዜ ብዙ ቦታ ለመገኘት እንዲያስችለው ነው። አሁንም ቢሆን፣ ሰው እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ባገኘው “ፍጥነት” የቦታ እና የግዜ ገደቦችን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ያደረገው ሙከራ ግን በምክንያታዊ ግንዛቤው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። 

ምክንያቱም “ፍጥነት” (Speed) ቦታ፥ ርቀት (Distance) ሲካፈል ለግዜ (Time) ነው። ስለዚህ፣ ፍጥነት ቦታ እና ግዜን ባዶ (nullfy) የሚያደርግ ነው። በእርግጥ በትንሽ ግዜ ብዙ ቦታዎች መገኘት ብዙ ተፈጥሯዊ ግዜን (Cosmic time) እንድንጠቀም ያስችለናል። ይህ ግን በሕይወታችን ወሳኝ የሆነውን ግዜ (Vital time) መስዕዋት በማድረግ የተገኘ ነው። 

ዘመናዊው ሥልጣኔ ያመጣው ፈጣን የግንኙነት ቴክኖሎጂ የሩቁን ቅርብ አድርገን እንድናስብ ያደርገናል። በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ግን ነገሮች በእውን ያሉት ተፅዕኖ በሚያሳርፉበት ቦታ ላይ ነው። በሕይወትህ ላይ ተጨባጭ ተፅዕኖ በሌለው ነገር ላይ ብዙ ግዜ ስታጠፋ የምትኖርበትን እውነታ በጥልቀት ከመገንዘብ ያግዳል። በዚህም፣ ቅርብ ላለው ነባራዊ ሁኔታ ሩቅ፣ ሩቅ ላለው ደግሞ ቅርብ ያደርጋል። ስለዚህ ፍጥነት የሩቁን ተጨባጭ አውነታ ሆነ ያለህበትን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ከመገንዘብ ያግዳል። 

በአንፃሩ በአንድ ነገር ላይ አትኩሮ የተመራመረ ስለ ነገሩ የላቀ ግንዛቤ ይኖረዋል። አንድን ክስተት አዘውትሮ የተከታተለ የክስተቱን መነሻ ምክንያት ይደርስበታል። በአንድ ሃሳብ ላይ በአንክሮ ያሰበ ጥልቅ የሆነ ዕውቀት እንዲጨብጥ ያስችለዋል። በትንሽ ግዜ ብዙ ቦታ ከደረሰ ይልቅ በአንድ ቦታ ብዙ ግዜ የቆየ ሰው ነባራዊ እውነታን በተሻለ መገንዘብ ይችላል። 

በእርግጥ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሰው ለብዙ ነገሮች ትኩረት አይሰጥ ይሆናል። ሆኖም ግን፣ ትኩረት በሰጣቸው የተወሰኑ ነገሮች ላይ ጥልቅ ዕውቀትና ግንዛቤ ይኖረዋል። በተወሰኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሰው በተወሰነ ግዜ ብዙ ነገሮችን ለማወቅ ከሚጥር ሰው የተሻለ ግንዛቤ እና ዕውቀት ይኖረዋል። 

በተወሰነ ግዜ ውስጥ በብዙ ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ ስንሞክር ለምንም ነገር ትኩረት ሳንሰጥ እንቀራለን። ለምሳሌ፣ አልበርት አንስታይን (Albert Einstein) በዓለም ታላቅ ሳይንቲስት የሆነው በሕይወት ዘመኑ ብዙ ነገሮችን በማወቁ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ብዙዎች የዘመኑ ሳይንቲስቶች ትኩረት በነፈጓት ትንሽ ልዩነት ላይ ብዙ ግዜ ሰጥቶ በማስተዋሉ ነው። ይህን “Jose Ortega y Gassett” የተባለው ፀኃፊ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“Einstein’s physics arose through attention to minute differences which previously were despised and disregarded as seeming of no importance.” The Revolt of the Masses (1926), CH.IV: The Increase of Life, Page 17  

ሰው ሰፊ የግንዛቤ አድማስ የሚኖረው በተወሰኑ ነገሮች ላይ ግዜ ሰጥቶ በማስተዋልና በማሰላሰል ነው። “Imagination is more important than knowledge” የሚለው የአልበርት አንስታይን አባባል ይህን ያሳያል። 


የላቀ የግንዛቤ አድማስ የሚገኘው ብዙ መረጃና ዕውቀት በመሰብሰብ ሳይሆን የተወሰኑ ነገሮችን በጥሞና በማስተዋልና በማገናዘብ ነው። ስለዚህ በአንድ ግዜ ብዙ ነገሮችን ለማወቅ ከመጣር ይልቅ የተወሰኑ ነገሮችን በጥሞና ማጤን ይመከራል።