​እያወቁ ማለቅ፡ የብሔር ግጭት ከበደሌ እስከ ሱማሌ  

የብሔር (የቁጥር) ፖለቲካ 
ትላንት ማታ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በሚገኙ በደጋ እና ጮራ ወረዳዎች በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት መፈፀሙን የሚገልፅ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተለቅቆ ነበር። በእርግጥ እኔ መረጃው የደረሰኝ ማታ 4፡00 ላይ ስለነበር ትክክለኝነቱን ለማረጋገጥ አልቻልኩም። የኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ መብት አቀንቃኝ የሆኑ ሁለት ግለሰቦች በተጠቀሱት ቦታዎች “በአማራና ትግራይ ብሔር ተወላጆች ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው” በማለት ያወጡትን መረጃ በፌስቡክ ገፄ ላይ አጋርቼ ነበር። ይህን ተከትሎ ዛሬ ጠዋት ብዙ ሰዎች መረጃው ስህተት መሆኑንና በገፄ ላይ ማጋራት እንዳልነበረብኝ አስተያየት ሰጥተውኛል። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው የኦሮሚያና አማራ ክልል ኃላፊዎች የሰጡትን መግለጫ እንደ ማሳያ ጠቅሰውልኛል።   

የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊዎች በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች በተነሳው ሁከትና ብጥብጥ የአስራ አንድ (11) ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ገልፀዋል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መግለጫ መሰረት ከሟቾቹ ውስጥ ስምንቱ (8) የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ሲሆኑ ሦስቱ (3) ደግሞ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውን ገልፀዋል። በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ደግሞ ከላይ የተጠቀሰውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በተጠቀሱት አከባቢዎች “በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት ተፈፅሟል” በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቀው መረጃ ስህተት መሆኑን ገልፀዋል። 

ከላይ በፅኁፌ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ትላንት ማታ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ መብት አቀንቃኞች ያወጡት መረጃ በደጋ እና ጮራ ወረዳዎች በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት መፈፀሙን የሚገልፅ ነው። ዛሬ ጠዋት ደግሞ የኦሮሚያና አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊዎች የሰጡት መግለጫ በዋናነት የብሔርተኛ ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የለቀቁት መረጃን ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን፣ በሁለቱ ወረዳዎች ላይ “በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት ተፈፅሟል-አልተፈፀመም” የሚለው አንባጓሮ የብሔር ፖለቲካ ቱርፋት ነው። 

የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃንና የመንግስት ኃላፊዎች በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቀው የአስራ አንድ (11) ሰዎች ህልፈት እንደ ዋዛ የሚታለፍበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። እንደ ብሔር ሳይሆን እንደ ሰው ሞትን በራሳችን ብናስበው የአስራ አንድ (11) ሳይሆን የአንድ (1) ሰው ሞት በቂ ነው። “በህግ ከተደነገገው አግባብ ውጪ ማንም ሰው ቢሆን በሕይወት የመኖር መብቱን ማጣት የለበትም” የሚለውን ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበር እንደ ሰው ማሰብ ይጠይቃል። 

አሁን በሀገራችን ካለው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ የብሔር ፖለቲካ ሰብዓዊነታችንን ከውስጣችን አሟጥጦ ጨርሶታል። የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር መሆኑ ቀርቶ ቁጥር ብቻ ሆኗል። የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃንና ኃላፊዎች ለዜጎቻችን ሕይወት ዋጋና ክብር ከመስጠት ይልቅ በቁጥር ጨዋታ ማለፉን መርጠዋል። ለምሳሌ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው ክስተት ተመልከቱ። የአማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን “በደጋ እና ጮራ ወረዳዎች በተፈፀመው ብሔር-ተኮር ጥቃት የአማራና ትግራይ ተወላጆች እየተገደሉ ነው” አሉ። 

ይህን ተከትሎ የአማራና ኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች “ከተገደሉት አስራ አንድ (11) ሰዎች ውስጥ ስምንቱ (8) ኦሮሞዎች ሲሆኑ አማራዎች ሦስቱ (3) ብቻ ናቸው” የሚል መግለጫ አወጡ። በተለይ የአቶ ንጉሱ ጥላሁን መግለጫ “ስምንት ኦሮሞዎች በተገደሉበት ሦስት አማራ መገደሉ በብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት አለመኖሩን ያሳያል” የሚል አንድምታ አለው። እንደ እኔ፥ አንተ፥ አንቺ፥ እናንተ… በአጠቃላይ እንደ ማንኛውም ሰው የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋና ጉጉት ያላቸው አስራ አንድ (11) ሰዎች ያለ አግባብ ተገድለዋል። እንደ ሀገር የተዘፈቅንበት የብሔር ፖለቲካ ግን ይህን አሳዛኝ ዜና ወደ “8 ± 3” የቁጥር ቀመር ቀይሮታል።

ከላይ እንደተገለጸው የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን እና ኃላፊዎች በእንዲህ ያለ የብሔር (ቁጥር) ፖለቲካ ውስጥ ሆነው ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በግልፅ መገንዘብ አይችሉም። ሀገሪቷና ሕዝቦቿ የተጋረጠባቸውን የእርስ በእርስ ግጭትና አለመረጋጋት ከወዲሁ ተገንዝቦ አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት ለእያንዳንዱና ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ዋጋና ክብር መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በየትኛውም ቦታ የሚኖር የማንኛውም ብሔር ተወላጅ መብቱና ነፃነቱ ሲገፈፍ እንደ ሰው በሰውነት፣ እንደ ዜጋ በዜግነት፣ በእኔነት ስሜት መጠየቅና እውነታውን መረዳት፣ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል። 

ሦስቱ የሁከትና ብጥብጥ ኃይሎች 

በዚህ መልኩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መነሻ ምክንያቶቹን በግልፅ መለየትና ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር፣ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አጎራባች ቦታዎች ለተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት እና ሰሞኑን በሰሜንና ደቡብ ኦሮሚያ ለታየው አመፅና ሁከት፣ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአማራና ትግራይ ተወላጆች መካከል፣ እና ሰሞኑን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በአማራና ኦሮሞ ተወላጆች መካከል ለተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት መንስዔዎች ተመሳሳይ ናቸው። 

በአጠቃላይ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለዘመናት በአብሮት በኖሩ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ለተከሰቱትና ወደፊት ለሚከሰቱት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች፣ እንዲሁም በሰውና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት መነሻ ምክንያቱ የሦስት ፖለቲካ ኃይሎች እንቅስቃሴ ነው። እነዚህ ሦስት የፖለቲካ ኃይሎች፤ አንደኛ፡- የኢህአዴግ መንግስት፣ ሁለተኛ፡- የመብት አቀንቃኞች (Activists)፣ እና ሦስተኛ፡- ሦስተኛው ኃይል (The third Power) ናቸው። 

1ኛ) የኢህአዴግ መንግስት

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በማወጣቸው ተከታታይ ፅሁፎች የኢህአዴግ መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሳው የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን የሚያደርገው ጥረት በሀገሪቱ ለሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት ዋና ምክንያት ነው። የኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን የእኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን ተቀብሎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ እንዲሁም ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎችን ለሞት፥ እስራት፥ ስደትና እንግልት ሲዳርግ የተቃዋሚ መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች ህዝባዊ እምቢተኝነት ን (civil disobedience) በስፋት ማቀንቀን እንደጀመሩ ይታወሳል። ባለፉት ሦስት አመታት በኢትዮጲያ እየታየ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በደቡብ አፍሪካ በነበረው የአፓርታይድ ስርዓት እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሦስት ያጋጠመ ፖለቲካዊ ችግር ነው።

2ኛ) የመብት አቀንቃኞች 

አብዛኞቹ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃንና የመብት አቀንቃኞች ባለፉት ሦስት አመታት በተለይ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ለኢህአዴግ መንግስት ፍፅሞ ተገዢ እንዳይሆን ያላሳለሰ ጥረት አድርገዋል። በዚህ ምክንያት ከ2008 ዓ.ም የመጨረሻ ወር ላይ የሁለቱ ክልሎች አብዛኛው አከባቢ ነዋሪዎች በአመፅና ተቃውሞ ከኢህአዴግ መንግስት ቁጥጥር ውጪ መሆናቸው ይታወሳል። ዛሬ በኢትዮጲያ እየታየ ያለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት  በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የፀረ-አፓርታይድ ትግል ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ እ.አ.አ. በ1986 ዓ.ም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲያውጅ፣ የኢህአዴግ መንግስት በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል። በሁለቱም አጋጣሚዎች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አልቻለም። በደቡብ አፍሪካ 1987 ዓ.ም (እ.አ.አ.) የታየውና ዘንድሮ በኢትዮጲያ እየታየ ያለው አንድና ተመሳሳይ ነው፥ እሱም፡- ሕዝባዊ እንምቢተኝነቱ እየተጠናከረ ሄዶ ከመንግስት የማስተዳደር አቅም በላይ (unmanageable) እየሆነ መጣ። 

3ኛ):- ሦስተኛው ኃይል

ከላይ እንደተገለፀው ድሮ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት የሆነው ዘንድሮ በኢትዮጲያ እየሆነ ካለው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። በአንድ በኩል መንግስታዊ ስርዓቱ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል በእምቢተኝነት  ሕዝቡ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መጣ። ይህን ተከትሎ፣ በሁለቱም ሀገራት የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሚስጥር “ሦስተኛው ኃይል” (The third Force) የተባለ ፀረ-ለውጥ የሆነ የሕቡዕ ድርጅት አቋቋሙ። ይህ ቡድን በደቡብ አፍሪካ “KwaZulu Natal” በተባለው ክልል የፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ብሔር ተወላጆች መካከል እየተፈጠረ ካለው ግጭት ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል የአርስ-በእርስ ግጭት በመፍጠር የነጮች የበላይነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደየት እየሄደች እንደሆነ በቀላሉ መገመት ይቻላል።

እያወቁ ማለቅ፡ ከበደሌ እስከ ሶማሌ

ከላይ የተጠቀሱት የፖለቲካዊ ኃይሎች በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚታየው ግጭትና አለመረጋጋት ያላቸውን አሉታዊ ሚና በግልፅ ለመረዳት እንዲያግዘን ትላንት በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በሚገኙ በደጋ እና ጮራ ወረዳዎች የተከሰተውን ግጭት እንደ ማሳያ ወስደን እንመልከት። ብዙ ሰዎች ትላንት የኦሮሞና አማራ የመብት አቀንቃኞች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የለቀቁትና እኔም በፌስቡክ ገፄ ላይ ያጋራሁት መረጃ ስህተት መሆኑን እንደገለፁልኝ በፅሁፉ መግቢያ ላይ ገልጬያለሁ። በእነዚህ ሰዎች ድጋፍ ችግሩ በተፈጠረበት አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች ጋር ስልክ በመደወል ጉዳዩን ለማጣራት ጥረት አድርጌያለሁ። ሁኔታውን በአካል ተገኝተው ከታዘቡትና ሁኔታውን በቅርበት ከሚከታተሉ የአከባቢው ተወላጆች ያገኘሁት መረጃ፡- 

“አንደኛ፡- በተጠቀሰው ቦታ ሲካሄድ የነበረ ሰላማዊ ስልፍ በተወሰኑ ግለሰቦች አፍራሽ ሚና ወደ ሁከትና ዘረፋ መቀየሩን እና የአከባቢው የፀጥታ ኃይሎች ሁኔታውን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ የስምንት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ሁለተኛ፡- የፖለቲካ ንቅናቄውን ከፊት ከሚመሩት የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) ውስጥ የተወሰኑ ስነ-ምግባር የጎደላቸው ወጣቶች በአከባቢው የሚኖሩ የአማራና ትግራይ ተወላጆችን “ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወጎኖቻችን ገንዘብ አምጡ!” በማለት ያስገድዱ እንደነበር፣ ይሄ ችግር እየተደጋገመ በመሄዱ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሦስት ሰዎች ሞተዋል፣ ሦስተኛ፡- የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ባልሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ውስጥ የኦነግ ባንድራና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ተገኝተዋል…” የሚል ነው። 

ከዚህ በመቀጠል ይህን መረጃ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ፖለቲካዊ ኃይሎች ጋር አያይዘን እንመልከት። ባለፉት ሦስት አመታት የሀገራችን የመብት አቀንቃኞች በአብዛኛው የሀገሪቱ አከባቢዎች ህዝባዊ እምቢተኝነት  (civil disobedience) እንዲሰፍን ያላሳለሰ ጥረት አድርገናል። ሰሞኑን በደጋ እና ጮራ ወረዳ ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበት አግባብ ለዚህ ማሳያ ነው። በብዙሃኑ እምቢተኝነት፣ በፀጥታ ኃይሎች ቸልተኝነት እና በጥቂቶች ወጣቶች ስርዓት አልበኝነት ላይ “ሦስተኛው ኃይል” ጋዝ አርከፍክፎ ክብሪቱን ሲጭር ሰላማዊ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ወዲያው ወደ ሁከት፥ ብጥብጥና እንዲሁም ብሔር-ተኮር ጥቃትና ግጭት ተቀየረ። በዚህ ምክንያት የአስራ አንድ ሰዎች ሕይወት ጠፋ። 

ዛሬ በበደሌ የሆነው በሰሜን ሸዋ ያየነው፣ በሶማሌ ክልል የሆነው ቀጣይ ነው። በቃ…”እያወቁ ማለቅ” ማለት ይሄ ነው። መነሻችን ይሄ ሆኖ መድረሻችን ደግሞ ዕልቂት ነው። የአፓርታይድ ስርዓት ደቡብ አፍሪካን ለአርባ አመታት ሲያስተዳድር ከገደላቸው ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን በላይ በዚህ ቀመር አማካኝነት በአራት አመት አፍሪካ (እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም) ውስጥ ብቻ 14,000 ሰዎችን  ተገድለዋል። አዎ…መድረሻችን እንዲህ ያለ የእርስ በእርስ ዕልቂት ነው። 

3 thoughts on “​እያወቁ ማለቅ፡ የብሔር ግጭት ከበደሌ እስከ ሱማሌ  

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡