ጎጠኛ ሰው “ዘረኛ” ቢልህ የሆነውን ነገርህ እንጂ ስድብ እንዳይመስልህ! 

ለረጅም አመታት የፌስቡክ ጏደኛዬ የነበረ ፅንፈኛ የትግራይ ብሔርተኛ የሆነው “Ztseat Saveadna Ananya” እኔን ከጀርመኑ ናዚ መሪዎች ጋር እያነፃፀረ “በዘረኝነት” ሲወቅሰኝ ግዜ ከጏደኝነት ሰረዝኩት ወይም “Block” አደረኩት፡፡ምክንያቱም ራሱን ከጎጠኝነት ማውጣት የተሳነው ሰው እኔን “ዘረኛ” እያለ ከተወሸቀበት የአስተሳሰብ ዝቅጠት ውስጥ ሊከተኝ የሚጣጣርን ሰው መጀመሪያ እመክረዋለሁ፣ ካልተቀየረ ደግሞ ከጏደኝነት አስወግደዋለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የቀድሞ ወዳጄ አሁንም የስም ማጥፋት ዘመቻውና ዛቻውን እንደቀጠለ መሆኑን የሁለታችንም ጏደኞች የሆኑ ሰዎች ይነግሩኛል፡፡ 

“እኔ “ታዳጊው Joseph Gobbles” ብየ የምጠራው፤ እርሱ ግን እንደ ሂምለር (Heinrich Himmler)፣ እንደ ኤክማን (Adolf Eichmann) መሆንም የሚቃጣው ወንድም ስዩም ተሾመ ብሎክ አደረገኝ አሉ። እርሱ ቢሆንለት እዚህ ፌስቡክ ላይ ሳይሆን በእውኑ ዛሬውኑ የሚልዮኖች የህይወት ዑደት” block” አድርጎ ቢያድር ደስታው ነበር። …በፅሑፉ ለሚረጫቸው መርዞች ግን አንድ ቀን እርሱና የኢትዮጵያ ሕዝብ (በተለይም የትግራይ ሕዝብ) የሚወራረዱት ሒሳብ እንዳለ እኔም እሱም እናውቀዋለን።” Ztseat Saveadna Ananya, Yesterday at 2:45am. 

በህወሃት/ኢህአዴግ ላይ ትችትና ነቀፌታ በሰነዘርኩ ቁጥር በተደጋጋሚ እኔ በዘረኝነት የሚከሱኝ እና የሚወቅሱኝ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ ውስጥ ግን ስም ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ዛቻና ማስፈራሪያ ጭምር የያዘ ነው፡፡ ይህ በጣም ከመደጋገሙ የተነሳ ምላሽ መስጠት በራሱ ሰልችቶኛል፡፡ ከሁለት አመት በፊት “ለጀርመን አምባሲ የፃፍኩትን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ እነዚሁ ሰዎች ሲያካሂዱት ለነበረው ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻና ዛቻ በዝርዝር ምላሽ ሰጥቼ ነበር፡፡

በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያይ መድረኮች የሚደረጉ ውይይቶች ፅንፈኛ አቋም በሚያራምዱ ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ወድቋል። በትክክለኛ መራጃና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለም። ይህ ዛሬ ላይ የተገለጠልኝ እውነት ሳይሆን በተለያዩ ድረገፆች ላይ ተከታታይ ፅሁፎች እንድፅፍ ያደረገኝ መሰረታዊ ምክንያት ነው። ለምሳሌ፣ በወቅቱ “አብዛኞቹ የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት የሚያንፀባረቁት ሃሳብ ምን ይመስላል?” ብሎ ለመዳሰስ የሞከረ ሰው ምን እያልኩ እንደሆነ ይገነዘባል። 

ምክንያቱም፣ በአብዛኞቹ ልሂቃን ሲሉት የነበረው ነገር፤ “ድሮስ የወያኔ ፖለቲካ፣… ሁሉንም ቦታ እነሱ የተቆጣጠሩት እንግዲህ፣…. ዉጪ ጉዳይ ብትሄድ ደግሞ ጉድ ታያለህ….” የሚል ቆይቶ በሚፈነዳ ቂምና ጥላቻ የታጨቁ ስሜት ሲያንፀባርቁ ነበር። እንዲህ ያለ ጥላቻና ቂም እንኳን አብሬው በኖርኩት የትግራይ ማህብረሰብ ላይ ቀርቶ፣ “መቼም – የትም – በማንም ላይ ቢሆን ይህ እንዲሆን አልፈቅድም። 

በመጠየቅ እውነት ይገኛል፡፡ ባለመጠየቅ ግን ጥርጣሬና አለመተማመን ይሰፍናል። ከዚህ ደግሞ ጭፍን ጥላቻና ዘረኝነት ይወለዳል። ይኼ የእኔ የግል ስብዕናና የሕይወት መርህ ነው። 
እኔ ደግሞ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ “ይሄ ነገር እንዴትና ለምን እንዲህ ሆነ?” ብዬ ከመጠየቅ ወደኋላ ብዬ አላውቅም። አስታውሳለሁ፣ የ14 ዓመት ልጅ እያለሁ በሆነ ጉዳይ ላይ እየተከራከርን ሳለ ድንገት በመሃል አመለጠኝና አባቴን መልስ የሌለው ጥያቄ ጠየኩት። ድንገት “እስኪ ከቻልክ በእግዚያብሄር እና በእየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለውን ልዩነት ንገረኝ?” ስል ጠየኩት። 
በወቅቱ አባቴ በጣም ተቆጣ! ከፊቱ እንድጠፋለት በግልምጫው አባረረኝ። ምን እንዳስቆጣው የገባኝ ግን ከብዙ አመታት በኋላ ነው። ለካስ አባቴ በእምነት ብቻ የተቀበለውን እውነት በምክንያት እንዲያስረዳኝ ነበር የጠየቅኩት። ስለዚህ፣ ምክንያታዊነት መርህ በዝርዝር ሊያስረዳኝ የማይቻለውን ጥያቄ በመጠየቄ ተበሳጨ፥ ተቆጣ፣ እኔም ያንን ጥያቄ መልሼ አላነሳሁበትም። እርግጥ ነው፣ ቁጣና ብስጭት ለጥያቄ መልስ የሚሆኑት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠት ሲሳነን ነው። 

በፅሁፎቼ የማውቀውን በማካፈልና ከዚያም ከማገኘው የሞራል እርካታ በዘለለ አንድም ቀን የተለየ ጥቅም አግኝቼ አላውቅም። በተከታታይ ለማወጣቸው ፅሁፎች ክፍያ ጠይቄም ሆነ ተቀብዬ አላውቅም። እኔ በተለያዩ ድረገፆች ላይ ረጃጅምና ተከታታይ ፅሁፎችን መፃፍ የጀመርኩት ለግል ጥቅም ሳይሆን የማህብረሰቡ ግንዛቤ ለማዳበር የበኩሌን አስተዋፅዖ አበረክታለሁ በሚል እምነት ነው። ለዚህ ደግሞ “በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ የተዛባ አመለካከትን፣ ጭፍን ጥላቻና ዘረኝነት እታገላለሁ” የሚል መርህ ይዤ ነው የተነሳሁት። ይሄ ድንገት ዛሬ ላይ የተገለጠልኝ እውነት ሳይሆን ገና መፃፍ ስጀምር የነበረኝ አቋም ነው። ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያዬን ፅሁፍ (Pdf) “aigaforum” ላይ ሳወጣ የሚከተለውን ጥያቄ በማንሳት ነበር፡- 

“Of course, one cannot evade anti-conceptual arguments altogether as they are the reflections of a low level of comprehension on the subject. And this is archetypal to all underdeveloped nations where social and political problems are barely scrutinized in their entirety. …The political sphere is filled with men whose unthinking loyalty to their belief is what held the whole creaky system together. By and large, the nation’s politics is often framed by thugs who conventionally play the zero-sum game, … It seems idiosyncratic to Ethiopians that we are all thin-skinned to discuss political issues objectively. … Intellectuals also failed to boldly criticize the programs and/or scrutinize the activities of local political groups which makes them liable for the prevalence of the current ‘catch-22 politics’ in Ethiopia.” 

ለጀርመን ኢምባሲ የፃፍኩትን ኢሜል መሰረት በማድረግ እኔን ዘረኛና ለትግራይ ህዝብ ጥላቻ እንዳለኝ አድርጎ ማሰብ ፍፁም ስህተት ነው። በእርግጥ ጥያቄዉን መጠየቄ ስህተት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፣ በግምት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳልይዝ አድርጎኛልና። ከዚህ በተረፈ፣ የአንድን ፅሁፍ ሃሳብ በጭብጡ ሊመዘን ይችል ይሆናል። በአንድና ሁለት ፅሁፍ ግን የፀኃፊውን ሃሳብ፣ አስተሳሰብና አመለካከት ለመመዘን ይከብዳል። ምክንያቱም፣ አንድ ፅሁፍ የራሱ የሆነ ሃሳብ ሊኖረው ይችላል፣ ፅኃፊው ግን ሃሳብ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብ ነው ያለው። 

በአንድ ፅሁፍ መልዕክት የፀኃፊውን አመለካከት መመዘን ስህተት ነው። በመሆኑም፣ በተለያየ አጋጣሚ፣ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ካወጣኋቸው ፅሁፎች ውስጥ የተወሰኑትን በመምረጥ ያለምንም ለውጥ እንደወረዱ አቅርቢያቸዋለሁ። እነዚህንና ሌሎች ፅሁፎቼን ካነበባችሁ በኋላ አሁንም ዘረኛና ጥላቻ አለብህ የምትሉኝ ከሆነ፣ ድፍረት አይሁንብኝና፣ “ዘረኛ” ያላችሁት እኔን ሳይሆን ራሳችሁን እንደሆነ አስቤ እተወዋለሁ። ሙሉ ፅሁፉን ለማንበብ ከዚህ በታች ያለውን ማያያዢያ በመጫን ፅሁፎቹን በPDF ማውረድ ይቻላል፦ “እኔና የጀርመኑ ኢምባሲ የሥራ ማስታወቂያ (Pdf)” 

One thought on “ጎጠኛ ሰው “ዘረኛ” ቢልህ የሆነውን ነገርህ እንጂ ስድብ እንዳይመስልህ! 

 1. My friend you are Amazing person. keep going never give up.never ever.

  2017-10-24 16:45 GMT+03:00 Ethiopian Think Tank Group :

  > Seyoum Teshome posted: “ለረጅም አመታት የፌስቡክ ጏደኛዬ የነበረ ፅንፈኛ የትግራይ ብሔርተኛ የሆነው
  > “Ztseat Saveadna Ananya” እኔን ከጀርመኑ ናዚ መሪዎች ጋር እያነፃፀረ “በዘረኝነት” ሲወቅሰኝ ግዜ
  > ከጏደኝነት ሰረዝኩት ወይም “Block” አደረኩት፡፡ምክንያቱም ራሱን ከጎጠኝነት ማውጣት የተሳነው ሰው እኔን “ዘረኛ”
  > እያለ ከተወሸቀበት የአስተሳሰብ ዝቅጠት ውስጥ ሊከተኝ የሚጣጣርን ሰው መጀመሪያ እመክረዋለሁ፣ ካልተ”
  >

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡