“በአሸባሪዎች ህግ” መብትና ነፃነት ወንጀል ነው! 

ለእኔ​ “የሕግ የበላይነት” የሚባለው ነገር ከእነ ጭራሹ ያበቃለት እኮ በሕገ-መንግስቱ ከተደነገጉት 31 ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ 28ቱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መጣሳቸውን የተረዳሁ ዕለት ነው። በዚህ ሀገር “ህገ-መንግስት” የሚባለው ነገር ያበቃለት “ፀረ-ሽብር” የተባለው የአሸባሪዎች ሕግ የወጣ ዕለት ነው። የፀረ-ሽብር ሕጉ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመሸራረፉ እና ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ጋር ተፃራሪ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከዓላማ እስከ አተገባበሩ “አሸባሪ” ነው። 

በእርግጥ ኢትዮጲያ ውስጥ በሽብር ተግባር የተሰማራ ቡድን የለም። ከዚያ ይልቅ፣ በሀገራችን በግልፅ የሚስተዋለው “በፀረ-ሽብር” ስም ሀገርና ሕዝብን የሚያሸብር መንግስት ነው። ምክንያቱም፣ የኢህአዴግ መንግስት በፈለገው ግዜና ቦታ የፈለገውን ሰው በሽብር ወንጀል መክሰስ ይችላል። በመሰረቱ የፀረ-ሽብር ሕጉ የፀደቀበት ዓላማ ህዝቡን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ሳይሆን ንቁ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንዳይኖር ለማድረግ ነው። በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ የፀጥታና ፍትህ አካላት ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው ስራና አሰራር ሲታከልበት ሀገርና ሕዝብን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ከትቷቸዋል።  

ለምሳሌ በፀረ ሽብር ሕጉ መሰረት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ “በአሸባሪነት” ሊያስከስስ ይችላል። ለምሳሌ “የፀረ-ሽብር ሕጉ ይሻሻል!” የሚል መፈክር ይዛችሁ ብትወጡ “አመፅና ሁከትን በማነሳሳት” – “inciting violence and protest” በሚለው አንቀፅ ያስከስሳል። በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንደ አጋጣሚ መንገድ ለተወሰነ ሰከንድ ከተዘጋ  “የሕዝብ አገልግሎትን በማቋረጥ – “disruption of public services’” በሚል ያስከስሳል። “ዜጎች አድማና የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብት አላቸው!” ብሎ በይፋ መናገር “ለአሸባሪዎች የሞራል ድጋፍ በመስጠት – ‘providing moral support or …advice’” በሚለው ያስከስሳል። “ዜጎች በሰላማዊ አድማና ተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ መብታቸውን ማስከበር ይችላሉ” ማለት “አሸባሪነትን በማበረታታት – ‘encouragement of terrorism’” በሚለው አንቀፅ ያስከስሳል። 

የኢትዮጲያ የፀረ-ሸብርተኝነት አወጅ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚሸራርፍና የሕገ-መንግስቱ መርሆች የሚፃረር፤ በዚህም ከአሸባሪዎች ጥቃት የበለጠ ኢትዮጲያኖችን እያሸበረ ያለ አዋጅ ነው። በመሆኑም ለአዲሱ ትውልድ ዋና የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። አብዛኞቹ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች የዚህ ሕግ ሰለባዎች ናቸው። 

በዚህ መሰረት፣ የሀገራችን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድብና የፍርሃትና ስጋት ምንጭ በመሆኑ መሰረታዊ ዓላማውን ስቷል። እንደ “Eliza Manningham Buller” (Pdf) አገላለፅ፡- 

“…What terrorism does is frighten us through its random effect and deter us from behaving normally. But we compound the problem of terrorism if we use it as a reason to erode the freedom of us all. … of law. …[Generally], governments need to pursue a domestic policy that protects the liberties we value and which the terrorist tries to destroy.”

በአጠቃላይ ሽብርን በሌላ የሽብር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በራሱ አሸባሪነት ነው። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በሚል የወጣው የኢትዮጲያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት በመገደቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ሳይሆን የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ ሆኗል። በመሆኑም፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በእውን የእኛ ሳይሆን ፍርሃትና ስጋትን በህዝብ ላይ ለመጫን የሚጥሩ “አሸባሪዎች” ሕግ ሆኗል። 

በአጠቃላይ የአሸባሪዎች ሕግ ዓላማና ግቡ “ፍርሃት” ነው፡፡ በዚህ ህግ መሠረት ራሳቸውን ከፍርሃት ቆፈን ያላቀቁ፣ በዚህም የመብትና ነፃነት ጥያቄ ያነሱ በሙሉ ጥፋተኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ ለጨቋኞች ማስፈራሪያ ተገዢ መሆን ትክክል ነው፡፡ የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበር ሆነ ለማስከበር መሞከር ግን በፀረ-ሽብር ህጉ የሚያስከሰስ ጥፋት ነው፡፡ ምክንያቱም በአሸባሪዎች ህግ የዜጎች መብትና ነፃነት ወንጀል ነው! 

2 thoughts on ““በአሸባሪዎች ህግ” መብትና ነፃነት ወንጀል ነው! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡