​በለማ ሥም የሚመጣ “የተባረከ” ነው? (በመስከረም አበራ) 

ከሁለት አመት ወዲህ የሃገራችን ፖለቲካ ከመቼውም በላይ በሁነት የተሞላ ሆኗል፡፡ ይህ ክስተት ተደላድሎ መምራት የለመደውን ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ እንደ እንግዳ ዶሮ እያንቦጀቦጀው ይገኛል፡፡ ተጀምሮ እስኪጨረስ አቤት ወዴት ባይ ካድሬዎች የሚመሯቸውን የጎሳ ፓርቲዎች አጋር እና አባል ድርጅቶች ብሎ ከፍሎ የሃገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ በማሳጨድ የተካነው ህወሃት መራሹ አስተዳደር የቅቡልነቱን ማጥበቂያ ገመድ የፈተለው በአፈሙዝ ሃይል መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ጠበንጃውን ከክንዱ ሳያርቅም ሆነ አጋር/አባል ላላቸው ሎሉዎቹ ሳያካፍል እንዲሁ ‘የመንግስቴ ባለ እኩል ናችሁ’ እያለ በቀደደው ሲያፈሳቸው ሩብ ምዕተ አመት ተቆጠረ፡፡ 
እነሱም እኩልነታቸውን የሚያመሳክሩት ከባለጠግነቱ ከሚያጠግባቸው ስብ ነውና ይሄን ያህል አጥብቀው የሚጠይቁት ነገር የለም፡፡ ወከልነው የሚሉት ህዝብም ነገራ ነገራቸውን እንደ ትርኢት እያየ፣ በየጓዳው እየበገነ ብዙ አመት ከገፋ በኋላ መንሹ የ1997 ምርጫ መጣ፡፡ የተባለው እውነት የመሰለው ህዝብ ምርጫውን አሳወቀ፣ ‘በቃችሁኝ ገለል በሉልኝ’ ሲል ተናገረ፡፡ ማን ቢሰማ?! መሪው ህወሃትም ሆነ ጌታቸውን አምነው ውጭ የሚያድሩት አባል/አጋር ጭፍራዎቹ ያደረጉትን አድርገው ዲሞክራሲን ገድለው በሰልስት ድንኳኑ የልማት ዘፈን ከፍተው ይጨፍሩ ጀመር፡፡ ልማቱ በራሳቸው ህይወት ላይ እንጅ ሌላ ቦታ ተፈልጎ በመታጣቱ ህዝቡ እጁን ከላያቸው ላይ አነሳ! ህዝብ እና መንግስት ሃዘናቸው እንኳን እስከማይገጥም ድረስ ሌላ እና ሌላ ሆኑ፡፡ 

መንግስትን የሚያስደስተው ጠያቂ፣ ሞጋች፣ አሳቢዎችን አስሮ መግረፍ ህዝብን አምርሮ ያሳዝናል፤ መንግስት “አልምቼ ልሞት ነው” ሲል ህዝብ ሌማቱ ደርቆ ሊሞት ሆነ፤ ገዥ “ታድሼ ልገዛ መጣሁ” ሲል ህዝብ “አይንህን የማላይበት የትልሂድ” ይል ያዘ! ቢብሰው የ1997ቱን ጥይት ረስቶ አደባባይ ተገኘ፣ የዓለምን ጩኽት ጮኸ! አሁን በመስማት የማይታማው ህወሃት/ኢህአዴግ መደንገጥ ጀመረ፡፡ ሲደነግጥ እንደሚያደርገው ተኮሰ፣ ገደለ፣ አሰረ፣ ያሰረውን ሲፈታ አሰለጠነ፣ “አይደገምም” አስባለ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጣ – ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ የለም ተብሎ ግን ተኩሶ አስፋልት ላይ የመድፋቱ ፈሊጥ አልቀረም፡፡ ጥይት እስካላለቀ ድረስም ይህ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በመሳሪያ ጉልበት ላይ ብቻ ተንጠላጥሎ ለሚኖር አስተዳደር መተኮስ ማቆም ማለት እንደ ሳምሶም ፀጉርን ተላጭቶ ማስፈራትን ማጣት፣ ‘የጠላት’ መቀለጃ መሆን ነውና ይህ አይሞከርም፡፡

እስኪነክሱ ማነከስ    

አሮጌውን አካሄዱን ለመተው ጠመንጃን ሙጥኝ ብሎ የመምጣቱ ተፈጥሮው የማይፈቅድለት አገዛዝ ከዚሁ ጎን ለጎን በጭንቅ ጊዜ የመውጫ መንገድ በመዘየድም አይታማም፡፡ በዋናነት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በተነሱ ህዝባዊ አመጾች ተሰቅዞ የተያዘው አገዛዝ የአፈሙዝ አቅሙን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው አካሄዶቹ ብቻ የህዝብን ጩኽት እንደማያስቆሙለት፣ ተረጋግቶ የመግዛቱን ዘመን እንደማይመልሱለት ሳይረዳ አልቀረም፡፡ በጠመንጃ ፊት ቆመው የሚጮሁ እንጅ የሚሸሹ እግሮች የሌላቸውን ብሶተኛ ሰልፈኞችን ማየቱ ይህን ያስረግጥለታል፡፡ ይህ እስኪነክስ ማነከስ የማይቸግረውን ህወሃት መራሽ አስተዳደር ለጊዜው ማንከስን እንዲመርጥ አድርጎታል፡፡

ልክ አስገባለሁ ባለበት አፉ የአዲስ አበባ ተቀናጀ ማስተር ፕላን ያልኩትን ትቻለሁ ብሎ ቆየት ብሎ ደግሞ ዞር ዞር አድርጎ የአፈፃፀም ህግ ብሎ ሊያፀድቅ ሲደገስ የሰነበተበት አሁን ደግሞ መልሶ ዝም ዝም ያለበት አካሄድ ህወሃት ማንነቱን የማይቀይር፣ ራስን ብቻ የመስማት፣ የራስን ፈላጎት ብቻ የማፅናት ዘላለማዊ ማንነት እንዳለው ልብ ላለው ሁሉ አስረጅ ነው፡፡ እንደ እድል ሆኖ አምባገነኑን ስርዓት ሁለት ነብር እንዳየ ያስደነገጡት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተነሱት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች በተመሳሳይ ወቅት በአንድ ላይ አለመከሰታቸው የአማራው ጋብ ሲል ወደ ኦሮሚያ እየተፈናጠረ ነገሮችን መልክ የማስያዙን እስኪነክስ የማነከሱን አካሄድ ቀላል አድርገውለታል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ ከህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የሚመጣውን ነገር ሁሉ ለውትሮው አብዝቶ የሚጠራጠውን፣ አምርሮ የሚቃወመውን አብዛኛውን ዲያስፖራ ሳይቀር ልብ ለማግኘት የሚያስችል ስራ በመስራቱ ረገድ አገዛዙ እየቀናው እንደሆነ የሚያስረዱ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ከሰሞኑ ኦቦ ለማ መገርሳ አባይን ተሻግረው እያሰሙት ያሉት ዲስኩር ኦህዴድን ጨምሮ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከሚታወቁበት የምሬት ፖለቲካ ለየት ያለ መሆኑ ብቻ አያሌ መርሆችን እግር በራስ ለማድረግ በቂ ሆኖ ተወስዶ ብዙ የፖለቲካ ምርኮ ለህወሃት/ኢህአዴግ ገቢ ማስድረጉን ለመገንዘብ ወደ ማህበራዊ ድህረገፅ ጎራ ማለት በቂ ነው፡፡ ኢሳትን ከፍቶ ላዳመጠም በኦህዴድ አሳብሮ፣ በለማ መገርሳ አፈ-ጮማነት ተወስዶ ሳያውቀው ለህወሃት የተማረከው ብዙ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ይህ አስገራሚ ክስተት ህወሃት/ኢህአዴግ ጦረኛ እና ሴረኛ ብቻ ሳይሆን እድለኛም ነው ያስብላል፡፡

ኦቦ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕረዜዳንት

ጋሪው እና ፈረሱ! 
ከሰሞኑ የተጋጋመው ለለማ መገርሳ የማሸብሸቡ ዝንባሌ የተጀመረው ሰውየው የኦሮሚያ ክልልን ወደ ማስተዳደሩ የስልጣን ሰገነት ከመጡ በኋላ በተለይ “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት” የሚለውን ዜማ ከደራሲዎቹ አብልጠው አሳምረው ማዜማቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ይህ ግራ-ቀኝ ከማየት የቀረው የሚመስለኝ ለኦቦ ለማ የማሸብሸብ ዝንባሌ በቅጡ የመረመረው የማይመስለኝ ግን ደግሞ የሁሉ ስር መሰረት እንደሆነ የሚሰማኝ ነገር አቶ ለማ ወደ ስልጣን የመጡበት ምክንያት ነው፡፡ 

እንደሚታወቀው አቶ ለማ መገርሳ ኦሮሚያ ክልልን ወደ ማስተዳደሩ ስልጣን የመጡት ኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ በተቀጣጠለበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሰውየው በኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ቢሮ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰው ነበሩ፡፡ ይህ የስራ ልምዳቸው የሃገሪቱን ወታደራዊ እና ደህንነት ዕዞችን በነሲብ ከተቆጣጠሩት የህወሃት ሰዎች ጋር ቅርርብም እንደሚፈጥርላቸው እሙን ነው፡፡ 

የሃገሪቱ ፖለቲካ በአያሌው በሚዘወርበት የፀጥታ እና ደህንነት መስሪያ ቤት በክልላቸው እንዲሰሩ መስኩን በሚዘውሩት ህወሃቶች ይሁን የተባሉት ኦቦ ለማ ለዋናዎቹ ሰዎች የአዘቦት ሰው ስላልሆኑ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ሰውየው በዚህ መስሪያ ቤት መስራታቸው ከህወሃት ሰዎች ጋር ቅርርብ ብቻ ሳይሆን ታማኝነትንም እንዳገኙበት በቀውጢ ሰዓት ለኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት መሰየማቸው ምስክር ነው፡፡ የለማ መገርሳን ያህል ንግግር ማሳመር የሚቀራቸውን ኦቦ ሙክታር የስልጣን ጊዜያቸውን እንኳን ሳይጨርሱ ከወንበራቸው ያስነሳቸው በክልላቸው ፈልቶ ይንተከተክ የያዘውን ህዝባዊ ማዕበል ፈር በማስያዙ በኩል የጌቶችን እጅ ከመሆን አንፃር የሚቀራቸው ነገር ስለነበረ ነው፡፡ 

አቶ ሙክታር የኦሮሚያው አመፅ በተነሳ ሰሞን በቴሌቭዥን ብቅ ብለው ሲናገሩ ድንጋጤያቸውን እንኳን ከፊታቸው መደበቅ የማይችሉ ተፈጥሯዊ ቢጤ ነበሩ፡፡ በአንፃሩ በደህንነት መስሪያ ቤት ቆይታቸው ከተፎነታቸው በቅርብ የተጠናው፣ በአፈ ጮማነታቸውም የማይታሙት፣ ማንን እንዴት አድርገው ፀጥ ማድረግ እንዳለባቸው ከቀድሞው መስሪያ ቤታቸው ዘዋሪዎች እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩት አቶ ለማ መገርሳ አሁን ኦሮሚያ ያለችበትን ሁኔታ ለራሳቸውም ለበላይ አሳዳሪዎቻቸውም በሚስማማ መልኩ በመለወጡ ረገድ የተሳካላቸው እንደሚሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው ቦታ በትክክለኛው ሰዓት ለትክክለኛው ሰው ተሰጠ፡፡ 

ለዘመናት የተጠራቀመው ህዝባዊ ቅሬታ፣ ብሶት ያገነፈለው የኦሮሚያ ህዝባዊ አመፅ ኦቦ ለማን ወደ ስልጣን አመጣ እንጅ አሁን እንደሚባው የኦቦ ለማ አልገዛም ባይነት የኦሮሚያን ህዝባዊ ትግልም ሆነ የጨፌ ኦሮሚያ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ካድሬን የጠያቂነት መንፈስ አልፈጠረም፡፡የኦቦ ለማ ወደ ኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት መምጣት በኦሮሚያ የተነሳውን አመፅ ለማርገብ ታስቦ በጌቶች ፈቃድ የተደረገ  እንጅ ብዙዎቻችን እንደምናስበው የለማ መገርሳ መምጣት የጨፌ ኦሮሚያን መነቃቃት የፈጠረ፣ ኦሮሚያ ቄሮዎችን ጉልበት ያበረታ እና የህወሃትን እድሜ ለማሳጠር የመጣ ሁነት አይመስለኝም፡፡ 

በጨፌ ኦሮሚያ የሚገኙ መካከለኛ እና ዝቅተኛ አመራሮች ‘እስከመቼ ታዛዥ ሆነን እንኖራለን?’ የሚለው ጥያቄም ቢሆን ለማ ያመጣው ሳይሆን ከድሮም የነበረ እንደውም ለማ በኢኮኖሚ አብዮት እና ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል ስም ያቀዘቅዘው ዘንድ ከበላዮቹ የተላከበት የቤት ስራው ነው፡፡ እዚህ ላይ ያቀዳደምነው ፈረስ እና ጋሪ መሰለኝ አሁን በእውር ድንብሩ እየነዳ ለማ መገርሳን መሲህ አድርጎ እያስቆጠረን ያለው፡፡ ሲጠቃለል ለማ መገርሳ ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ከህወሃት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አይደለም፡፡ አቶ ሙክታር የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ፣ ለዛውም በዛ ቀውጢ ሰዓት ኦሮሚያን የማስተዳደሩን በትር የሚጨብጥ ሰው ያለ ህወሃት እውቅና በራሱ እና በካቢኔዎቹ ጉብዝና ወይም በጨፌ ኦሮሚያ ምርጫ ወደ ስልጣን መጥቶ የህወሃትን የበላይነት ግንብ አፈራርሶ፣ የአማራን እና የኦሮሞን “የጠብ ግርግዳ” ሊንድ ባህርዳር ተገኘ ብሎ ጮቤ መርገጥ በአምባገነን ወጥመድ ሰተት ብሎ ገብቶ መጨረሻን ከማክፋት ያለፈ ትርፍ የለውም፡፡   

ለለማ ምስጋና ለማምጣት የቸኮለው አብዛኛው ሰው የሚረዳው የለማ ወደ ስልጣን መምጣት ኦህዴድን እምቢተኛ እንዳደረገው ሲሆን ለዚህ እንደ ሁነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ደግሞ ለማ መገርሳ እና ካቢኔው እንደ አባዱላ እና ኩማ ደመቅሳ የህወሃት የጫካ ምርኮኞች ሆነው የህወሃትን የጫካ ዳቦ አለማነጎታቸው ነው፡፡ ምርኮኛ ሆኖ የህወሃትን የጫካ መኖ አለማላቆጥ ብቻውን ዳቦ ካነጎቱት ያነሰ ሎሌ እንደ ማያደርግ ለማሳየት በነአስቴር ማሞ፣ ሙክታር ከድር፣ ሙፈሪያት፣ አለማየሁ አቶምሳ (ነፍስ ይማር)፣ አለማየሁ ተገኑን፣ አለምነው መኮንንን፣ በነዶ/ር ይናገር ደሴን፣ የነ አብዲ ኢሌን ከሁሉ በላይ ደግሞ በነ ሃ/ማርያም ደሳለኝን ታማኝነት ላይ ምርኮኛ ባለመሆናቸው ሳቢያ የመጣ እንከን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ምርኮኛ ሆኖ ዳቦ ባለማነጎቱ ረገድ ደግሞ በለማ መገርሳ እና በቀደምታቸው በአቶ ሙክታር ከድር መሃከል ልዩነት ስለሌለ ለማ ምርኮኛ ባለመሆናቸው ምክንያት አሳዩት የተባለው የአልገዛም ባይ “አነርነት” በአቶ ሙክታት ላይም መታየት ነበረበት፡፡ 

ይህን የተውሸለሸለ ክርክር ያመጣው የህወሃት ምርኮኛ የመሆኑ ትክክለኛው ቦታ የት የት እንደሆነ መሳት ይመስለኛል፡፡ ህወሃት ታማኝ ሎሎዎችን የሚማርክበት ቦታ ያኔ ድሮ ከደርግ ጋር የተዋጋበት ጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፡፡ለምሳሌ የኦህዴድን ካድሬ “የአማራን ጭራቅነት” እንደላሜ ቦራ ተረት በመተረክ፣ ቀጥሎም ከባለጠግነቱ ትቂት በመቆንጠር፣መንትፎ የሰራውን ፎቅ አይቶ እንዳላየ በማለፍ፣በአዲስ አበባ ዙሪያ መሬቶችን ላይ አቁሞ አቤት ወዴት እስካልክ ድረስ እግርህ የረገጠውን ሁሉ ውረስ በማለት ነው፡፡ የህን ያለው ህወሃት ደግሞ “ከአማራ ጭቆናም” ከድህነትም ነፃ አውጭ ጌታ እንደሆነ ተስማምተው መግዛት መንዳቱን እንደተዋረዳቸው ሲቀጥሉ ኖረዋል፡፡ 

ስብሃት ለለማ መገርሳ የሚያስብለው ሌላው ጉዳይ ሰውየው ገና ወንበሩ ላይ ከመቀመጡ ቀን ጀምሮ ሳያሰልስ የሚዘርፈው “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት” የሚለው ቅኔ ይመስለኛል፡፡ የኢኮኖሚ አብዮቱን ስር መሠረት ለማጤን ትኩረት መደረግ ያለበት ቅኔውን “ተቀበል” እየተባለ በሚሞዝቀው ለማ ላይ ሳይሆን የኢኮኖሚ አብዮቱ ሙዚቃ ራሱ በማን? ለምን? እንዴት? እና መቼ? መጣ ሚለውን በመመርመሩ ላይ  ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የኦሮሚያው እና የአማራ ክልሉ ህዝባዊ ቁጣ ከሚገለጡባቸው መንገዶች አንዱ የኢፈርት ንብረቶች የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በማቃጠል እና በማጥቃት ነበር፡፡ 

ከዚህ ህወሃት የተረዳው ነገር ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በማይዛመድ መልኩ ያመጣውን የኢኮኖሚ የበላይነት ህዝቡ እንዳልወደደው፣ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚው ረገድ የኢፈርትን የንግድ ዝውውር የመጉዳት መጥፎ ዝንባሌ እንዳለው፤ በፖለቲካው ረገድ ደግሞ የህወሃት የበላይነት አንድ ማሳያ መሆኑን ህዝቡ መረዳቱ አለመረጋጋቱን በማባባስ በኩል አደገኛ ውጤት እንደሚኖረው ተገንዝቧል፡፡ ለወትሮው ኢፈርትን ከዲንሾ እና ጥረት ጋር በማመሳሰል ሲቀለድ የነበረው ቀልድ እንደማያዋጣ በመረዳት ሌላ ‘የኢፈርት መሳ’ የሚመስል ማደናገሪያ በኦሮሚያ መታየት እንዳለበት ታስቧል፡፡ 

ለዚህ ማስረጃው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት በተባለው እቅድ ውስጥ በአመፁ ሰዓት የድንጋይ በረዶ ሲወርድበት ነበረውን ሰላም ባስን የመሰለ “ኦዳ ትራንስፖርት” የሚባል እንደሚመጣ ሲወራ መባጀቱ ነው፡፡ ሰላም ባስ እንዲደበደብ ያደረገው ተመሳሳዩ የኦህዴድ ንብረት በኦሮሚያ አለመታየቱ ብቻ የመሰላቸው ነገስታት እውን ኦሮሚያን በኢኮኖሚ አብዮት ለማንደድ አምሯቸው ሳይሆን ሰላም ባስ እንደወትሮው እንደልብ ሽር እንዲል፤ ሁለትም የለማን ኦህዴድ ከቀደምቶቹ ኦህዴድ የተለየ ለማስመሰል “ለእናንተም እነሆ” እንደማለት ያለ ነገር ነው፡፡ ከነ አቶ አባዱላ ገመዳ የመታዘዝ ማንነት ጋር የተፈተለው የዲንሾ ኩባንያን ነገር ከእነሱው ጋር ገፋ አድርጎ አዲስ ከሚመስሉት አቶ ለማ መገርሳ ጋር አዲስ የኢኮኖሚ አብዮት ሙዚቃን መሞዘቁም ለተአማኒነቱ ይረዳል፡፡ የሆነ ሆኖ አቶ ለማ መገርሳም ከ1984 ጀምሮ በኦህዴድ/ኢህአዴግ ቤት ያሉ እና የነበሩ፣የኢኮኖሚ አብዮቱ ሽንገላም የኖረው የማደንዘዣ መውጋት ፖለቲካ ቅጥያ እንጅ በአሮጌው ኢህአዴግ ቤት የተፈጠሩ አዲስ ነገሮች አይደሉም፡፡

የባላጋራን መልክ አለማወቅ…

ኢህዴግ ባላጋራዎቹ ምን ቢበዙ ማንነታቸውን አበጥሮ በማወቅ አይታማም፡፡ በአንፃሩ ኢህአዴግን እንቃወማለን የሚለው ወገን የኢህአዴግን ማንነት በማወቅ በኩል የተካነ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግን ፖለቲካዊ “ማንዋል” በማወቅ የማመሰግነው ኤርሚያስ ለገሰ ሳይቀር ‘ኮካ እና ፋንታ መለየት ያስተማርኳቸው ህወሃቶች ለማ መገርሳን ሃገር እያዞሩ ኢትዮጵያዊነትን በማሰበክ ጊዜ ለማግዛት እስከማሰብ ድረስ በሚደርስ ሴረኝነት መጠርጠር የለባቸውም’ ሲል ገራሞች አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡

የሚገርመው ነገር ግን ከዚህ በስንት እጥፍ በበለጠ ኦኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሴራ ኢፈርትን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት እንዳቆሙ እሱው ራሱ ፅፎ ያስነበበን መሆኑ  ነው፡፡ እንዲህ ያለው የኢህአዴግን የቤታቤት ደንብ አለመረዳት ነው በሚገርም ሁኔታ በአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ በኩል የህወሃትን ፍፃሜ እያስናፈቀን ያለው፡፡ ይህ አካሄድ ከምክንያታዊነቱ ስሜታዊነቱ በልጦ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም በዚህ በኩል የህወሃትን የበላይነት ማብቃት ሚጠብቁ አካላት  ሚያቀርቧቸው ምክንያቶችን ማየቱ አይከፋም፡፡ 

የነዚህ ተከራካሪዎች የንግግር መነሻ ትናንት ዛሬ አይደለም፣ ህወሃትን አጀግነን ማየታችንን እናቁም የሚሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ከማለት ባለፈ ግን ትናንት ዛሬ እንዳልሆነም ሆነ ህወሃትን አጀግነን ማየታችንን የምናቆምበት ተጨባጭ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መለስ ዜናዊን የመሰለ የተሟላ አምባገነን ያጣው ህወሃት መዳከሙ እርግጥ ነው፡፡ ይህ መዳከም መዳከም የሚባው ህወሃት ከራሱ የቀደመ ብርታት ጋር ሲነፃፀር እንጅ ከኦህዴድ ወይ ከበአዴን ጋር ሲነፃፀር አይደለም፡፡ ንፅፅሩ በህወሃት እና በአባል ድርጅቶቹ መሃል ከሆነ የሚያስገምተው ሊያነፃፅር ያሰበውን ሰው ግንዛቤ ነው፡፡ 

የህወሃት ድካም በሚባለው ጉዳይ ላይ ራሱ መረሳት የሌለበት ጉዳይ መለስ ዜናዊ በሚቀያይረው መልኩ የፖለቲካ ማርሹን የሚያሳልጥ አፈ-ጮሌ በመጥፋቱ በፖለቲካዊ መዋቅሩ በኩል አለመናበብ እና ተወሰነ የፕሮፖጋንዳ/የህዝብ ግንኙነት መፋለሶች ታዩ እንጅ የሃገራችንን ፖለቲካ ለመዘወር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ወታደራዊ እና የደህንነት እዙ ከነሙሉ ትጥቁ ዛሬም በህወሃት እጁ ላይ ይገኛል፡፡ ህወሃት ለወትሮው ውልፊት የሚል ሎሌውንም ሆነ በግልፅ የሚቃወመውን አሳቢ ፀጥ የሚያስብለው እንደልቡ በሚያዘው አፈሙዙ፣ በእስርቤቱ፣ በደህንነት መስሪያቤቱን እና በፍርድቤቱ ነው፡፡ ኢህዴግ መዳከም እውን የሚሆነው ቢያንስ ከእነዚህ አንዱን አጥቶ ሲታይ ነው፡፡ ዛሬ ድንገት አነር ሆነ የሚባለው ለማ መገርሳ እውን ህወሃትን የበላይነት ተገዳድሮ ከሆነ፣ ከክልል ክልል ሽር የሚለው ነገርም ከጌቶች ፈቃድ ውጭ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ተጠቅሞ እሱን እና ካቢኔውን ፀጥ ለማድረግ በህወሃት መንገድ ላይ የሚቆመው ማን ነው? 

ጎዳና ላይ እየወጣ ለራሱ ብሶት የሚጮኽው የኦሮሞ ህዝብ ህወሃት ለማን ቢያስር ዝም ስለማይለው ይህን ፈርቶ እጁን ይሰበስባል፣አለያም አሁን ያለው የጨፌ ኦሮሚያ አባል ለማ መገርሳ አንዳች ቢሆን ዝም አይልም  የሚል ተከራካሪ አይጠፋም፡፡ ለዚህ ቀላሉ መልስ የኦሮሞ ህዝብ ጩኽቱ የአፈሙዝ ባለቤቶችን ፈቃድ የሚያስቀይር ቢሆን ከሰውነት ደረጃ ወጥተው እንደ ወንበዴ እጃቸውን በካቴና ታስረው ለታዩት ዶ/ር መረራ የሚኽው ጩኽት ይበረታ ነበር፡፡ ግን በሃገራችን ምድር የህግ ፍፃሜ የሚሆነው ባለጠመንጃው ያለው ነገር ነውና ባለጉልበት ያለው ብቻ ይሆናል፡፡ በተሻለ ሁኔታ ጥርስ እያወጣ እንደሆነ ሲነገርለት ዘመናት የተቆጠሩት የጨፌ ኦሮሚያ መካከለኘኛው እና ዝቅተኛው ካድሬም ቢሆን ከሰሞኑ ባደረገው ስብሰባ ከዚህ በላይ መፈራገጥ በህወሃት ጎራዴ መቀንጠስን እንደሚያመጣ አምኖ በነገስታት ፈቃድ ለማደር መለሳለስ ማሳቱን ዋዜማ ሬዲዮ የውስጥ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡   

ህወሃት እንደመለስ ያለ አምባገነንነቱ በሙሉድምፅ የተረጋገጠ መሪ ለማግኘት የተቸገረ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ፓርቲው ተያይዞ አለመቆም ተያይዞ መሞትን እንደሚያመጣ አሳምረው የሚያውቁት የወንዝ ልጆች ድርና ማግ ሆነው የሰሩ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ “ተዓምረኛው” ለማ መገርሳ ይህንንም ገርስሷል ካልተባለ በቀር! ስለዚህ ህወሃቶች ምን በሃሳብ ቢለያዩ በስንጥቃታቸው ሶስተኛ ወገን ቀርቶ ነፋስ ማስገባት በተለይ በአሁኑ ሰዓት ይዞት የሚመጣውን መዘዝ የማያውቁ ሰዎች አይደሉም፡፡ 

‘ለሁለት ተሰነጠቁ ለሶስት ተተረተሩ’ የሚባለው ወሬ መወራት ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም እነሱ ሁለት ሶስት ጊዜ እየተመላለሱ በራቸውን እየዘጉ ተነጋግረው ሲመለሱ ለተመለካች ያው የድሮዎቹ ናቸው፡፡ በተግባርም ቢሆን የሚያነታርካቸው ነገር ‘በየት ዞረን፣በትኛውን የተሻለ ሎሌ ላይ እምነት ጥለን፣በአፉ ተናግረን የበላይነታችንን ዘላለማዊ እናድርግ’ የሚለው ጉዳይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ጉልበቱን የሚያውቀው ሎሌም ከዚህ ለተለየ ነገር እንደማይፈለግ ያውቀዋል፡፡ ለሎሌ ደግሞ የነገስታትን መንበር ከማፅናት የበለጠ ጉብዝና የለም! በተለይ በኢህአዴግ ቤት ሎሌ የሚለካው በአስቸጋሪ ጊዜ አይኑን በጨው አጥቦ በመቀላመድ ነው፡፡ 

ሁልጊዜ ህወሃትን አጀግነን አንይ አዳንድቀን ለማን የመሰሉ ሎሌዎችም ሊጀግኑ ይችላሉ የሚሉ ተከራካሪዎች ስሜታዊነታቸው በዝቶ ይሰማኛል፡፡ ህወሃትን ማጀገን የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን ህወሃት ራሱ ያበጃጀው የሃገራችን ፖለቲካ ተፈጥሮ በጠመንጃ የሚያስገድደን ምርጫ አልቦ ነገር ነው፡፡ ብጣብልጡ ህወሃት ራሱ ባበጃጀው ቤት፣መሳሪያውን በእጁ እንደታቀፈ ይሸነፋል ማለት ዘበት ነው፡፡ ህወሃትን ማጀገን እንደሌለብን የሚናገሩ ተከራካሪዎች እነሱ የሚያጀግኗቸውን እነ ለማ መገርሳን ደርሰን ነብር አድርገን እንድናይ የሚያደርግ ተጨባጭ ነገር አያሳዩንም፡፡ ዝም ብሎ ኢህአዴግን ማጀኑ መቅረት አለበት ማለት ቂልነቱ ይበዛል፡፡ 

መሳሪያ ብቻ በሚገዛበት ሃገር ባዶ እጆቹን እያወዛወዘ ከክልል ክልል የሚማስነው ለማ መገርሳ ለህወሃት አስቸግሮ፣ ከቢጤው ግራ-ገብ ብአዴን ጋር ገጥሞ ህወሃት የነፈገንን ነፃነት የሚያመጣልን በዱኣ ይሁን በወዳጃ ግልፅ አይደለም! ጭራሽ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ባህር ዳር ላይ ተገናኝተው የኢፈርቱን ፋና ስፒከር ደቅነነው የሚያወሩት ወሬ ህወሃትን በአፍጢሙ ለመድፋት እንደሆነ እየታሰበ ነው፡፡ ህወሃት ምን ቢዳከም ኦህዴድ እና ብአዴን ያለ እሱ ፈቃድ ባህር ዳር ላይ  ተገናኝተው እሱ ቀድሞ በአእምሮው ፅፎ በአፋቸው ከሚያናግራቸው አጀንዳ ውጭ ያወራሉ ማለት ሶስቱንም ፓርቲዎች አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ሃገርንም አለማወቅ ነው፡፡                 

ህወሃት/ኢህአዴግ ስህተቴን የማርም ፓርቲ መሆኔ ነው ይህን ያህል ያኖረኝ ባይ ነው፡፡ ህወሃት እንደሚለው የሚማር ሳይሆን የተማረ የሚያስመስል ፓርቲ ነው፡፡ ከ1997 ምርጫ ወዲህ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ እንደሚፈልግ በተግባር ስላሳየው ቀድሞ ፓርቲው ሲያራምደው የኖረው በዘር ሸንሽኖ የመግዛት ዘይቤው እንደማያስኬደው አውቆ ባንዲራን ጨምሮ ሲያናንቃቸው የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት ምልክቶችን ቀን ቆርጦ ሳይቀር መዘከር ጀመረ፡፡ለኢትዮጵያዊነት ዘብ መቆሜን ያሳዩልኛል ያለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ያዘ፣ተጓዥ የብሄረሰቦች ቀን በአል ማክበሩን ተያያዘው፡፡ 

በአንድ በኩል እንዲህ ደርሶ የኢትዮጵዊነት ዘበኛ ነኝ እያለ በሌላ ወገን ኢትዮጵያ ሃገራችን ናት ብለው ከትውልድ መንደራቸው ርቀው በጉራፈርዳ የሰፈሩ አማሮችን ጓዛቸውን እንኳን እስኪያዙ ሳይጠብቅ ባዶ እጃቸውን ያፈናቅል ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ ሲባል ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር “ሰዎቹ እኮ ጉራፈርዳን ምዕራብ ጎጃም አስመሰሉት” ነበር መልሳቸው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ኦሮሞዎች ዘመናት ከኖሩበት ኢትዮ-ሶማሌ ክልል እየተፈናቀሉ ነው፡፡ 

ለማ መገርሳ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ‘ኦሮሚያ ለስንትስ ሚሊዮን ህዝብ የምትበቃ ስለሆነች ማንንም የማፈናቀልም ስልጣንም ሆነ ፍላጎት የለንም’ እያሉ በሚደሰኩሩበት ወቅት አማሮች በኤሊባቡር በጎራዴ ይቀሉ፣ በቆንጨራ ይፈለጡ ፤የኢትዮጵያ ሶማሌዎች በአወዳይ ከተማ በጥይት ይረፈረፉ ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ እሳቸውም ሆኑ ጓዶቻቸው ስለኢትዮጵያዊነት መደስኮራቸውን አላቆሙም፤ወሬ ብቻ የሚያጠግበው፣ አፍ ብቻ የሚበቃው ተላላ አድማጭም አላጡም፡፡ 

ባልተለመደ ሁኔታ ከኦህዴድ መሪ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማህሌት መቆሙን ብቻ በቂ አድርጎ በደስታ ከመስከር ምክንያቱንም መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ባለፈው አመት በጎንደር ተደርጎ በነበረው ሰልፍ የጎንደር ህዝብ ለኦሮሞ ህዝብ በደም የተዋሃድኩ ወንድም ነኝ የሚል አንድምታ ያለው መፈክር ሲያሰማ አፀፋውን ከኦሮሞ ህዝብ ማግኘቱን ያወቀው አጀንዳ በመንጠቅ የተካነው ህወሃት/ኢህአዴግ ይህን የህዝብ ዝንባሌ አፈፍ አድርጎ ኦህዴድን እና በበአዴንን ማስተቃቀፍ ይዟል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ መወራቱ ብቻ በስሜት ያሰከረው ፖለቲካውን የሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ብአዴን እና ኦህዴድ የሰፊው ህዝብ ወኪል የመሆን ርጋፊ ብቃት እንደሌላቸው እንኳን ዘንግቶ የሁለት ካድሬዎችን እና ጄሌዎቻቸውን ሆያ ሆየ የህወሃት እጅ የሌለበት አድርጎ  ሲያሟሙቅ ሰነበተ፡፡

በተለይ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አክቲቪስቶች እንደመርገም ጨርቅ ሲቀፋቸው የነበረው ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ ሲነገር ማር ማር ያላቸው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለወትሮው እኛ ኢትዮጵያዊያን በደም የተሳሰርን አንድ ህዝቦች ነን ሲባሉ በአንድነት ስም የህዝቦችን ማንነት ለመጨፍለቅ የምታስቡ አማሮች ሴራ ነው ሲሉ የነበሩ እነዚህ አክቲስቶች ዛሬ የለማን መዝሙር ተከትለው የሚያሸበሽቡት ለምድን ነው? ይህ ሃሳባቸውስ አብሯቸው ይኖራል ወይ? ብሎ አለመመርመር ቀና አሳቢነት ሳይሆን ፖለቲካዊ የዋህነት ነው፡፡ እነዚህ ስለኢትዮጵያዊ አብሮነት ሲነሳ እንደዛር ሲያስጎራቸው የነበሩ አክቲቪስት ተብየዎች ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ ሲወራ የጣፈጣቸው የለማ ጉዞ ሄዶ ሄዶ በማንኛውም የወንዛቸው ልጅ እንዲያዝ አጥብቀው በሚመኙት ስልጣን ላይ እንደሚያርፍ ስለተገነዘቡ ነው፡፡ ይህን ያመጣው ለለማ ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ሊገድላቸው የማለው የዘረኝነት ልክፍታቸው ነው፡፡     

“ሃገር አረጋጉ”

ኦህዴድ እና ብአዴን ሳያዳግሙ የሚታዘዙ ሎሌዎች ቢሆኑም አያጉረመርሙም ማለት አይደለም፡፡ ሎሌ የጉልበቱ ዋጋ በውል ያልተከፈለው ሲመስለው ጓዳ ለጓዳ ሊያጉረመርም ይችላል፡፡ እንደውም እንደሎሌ አጉረምራሚ የለም፡፡ ኦህዴድም ከነአሽከርነቱ ሊያጉረመርም ይችላል፡፡ማጉረምረም ብቻውን ሎሌነትን የማሽቀንጠር ምልክት አይደለም፡፡ ሎሌ ብዙ አጉረምርሞ ትቂት ይደመጣል፡፡ ኦህዴድ ማጉረምረም ጀመረ የተባለው በአባዱላ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ብአዴንም በአያሌው ጎበዜ ዘመን፡፡ ሆኖም ጉርምርምታቸው እምብዛም ያመጣው ነገር አልነበረም፡፡በተለይ መለስ ክንዳቸውን ሳይንተራሱ፣ ህወሃትም እንዲህ እንደዛሬው ከብራቅ በበረታ የህዝብ ጩኽት ግራ ሳትጋባ በፊት የሎሌ ጉርምርምታ ያስገርማት ይሆናል እንጅ ነገሬ ብላ ላታዳምጠው ትችላለች፡፡

 ዛሬ የህዝብ ጩኽት ግራ ሲያጋባት ግን አጥብቃ የሎሌዎቿን እርዳታ ፈለገች፡፡ የሚያጉረመርም ሎሌን ለወሳኝ ስራ መላክ ደግሞ እንደማያስተማምን በመረዳቷ “ጩኽታችሁ በፊቴ ነው፣ ድምፃችሁን ሰምቻለሁ፣ እውነት ነው በቁመናችሁ ልክ ስልጣን ያስፈልጋችኋል፤ ለእሱ ግድ የለም መጀመሪያ ግን ሃገር አረጋጉ” በማለት የቀደመ ተረጋግቶ የመግዛት ዘመንን ለመመለስ አድርጉ የተባላችሁትን ካደረጋችሁ የማደርግላችሁን አታውቁም ስትል ኦህዴዶችን እንዳረጋጋች፣ ኦህዴዶችም በሰሞንኛ ጉባኤያቸው ከዚህ በላይ ጌታን መጋፋት መከተፍን እንደሚያመጣ ተስማምተው ይሄው “ሃገር ለማረጋገት” አባይን ዋኝተው ጣናን አቋርጠው ወደ ሌላው የባሰበት ሎሌ ግዛት ተጉዘው “ሃገር ማረጋጋቱን” ተያይዘወታል፡፡ይህን የዘገበው ወሳኝ መረጃዎችን ከውስጥ አወቆች አነፍንፎ ሳያዛባ በማቅረብ የታወቀው ዋዜማ ሬዲዮ ነው፡፡ 

ሱሴ ሱሴ…..!

ሃገር የማረጋጋቱን ስራ በአማራ ክልል የተጀመረው አንደኛው ምክንያት ጌታ ለኦህዴድ ያሰባትን መልካሟን ሃሳብ “ለእኔስ” ለማለቱ ብአዴን ቀዳሚ በመሆኑ ለማ ማለት ኢትዮጵያዊነት እንጅ ኦህዴድነት እንዳልሆነ እንዲታመን በኢትዮጵያዊነት ላይ ጨክኖ በማይጨክነው ህዝብ ምድር ሲቃ እየተናነቀው፣ ኢትዮጵያዊነት እንደሱስ እንደሚያዛጋው መቀላመድ ነበረበት፡፡ እነ ቀመር ዩሱፍን የመሰሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችን አግተልትሎ ወደ አማራ ክልል የመንጎዱ ሌላው ምክንያት በሰላማዊ ሰልፉ የታየው ትክክለኛው የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ እውነተኛ የመፈላለግ ዝንባሌ ውስጥ ጥልቅ ብሎ ዋነኛ አገናኝ፣ የፍቅር ሰው ለመምሰል ነው፡፡ 

ነገሩ ህዝብ ሃያ ምናምን አመት የተሰበከለትን የመነጣጠል ዲስኩር፣ የመባላት ግብዣ የዝሆን ጆሮ ሰጥቶ በፍቅር ሲጠራራ እየተሰማ የተለመደውን የማናከስ ሙዚቃ መክፈት እንደማያስኬድ በመረዳት ግድ ያለውድ የሆነ አካሄድ እንጅ ብዙዎቻችን እንደምናስበው የመነነጣጠል ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞችን የኢትዮጵያዊነት ሱስ አብርሮ ባህርዳር ላይ ጥሏቸው አይደለም፡፡ አንድ ነገር ሱስ የሚሆነው ደጋግመው ሲወስዱት ነው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካን ሲሰብክ እና ሲሰበክ ከኖረው ኦህዴድ፣የልዩነት ፖለቲካን መኖሪያየ ብሎ ከያዘው ግንባር ኢህአዴግ ወግኖ ጥላቻን ሲምግ የኖረ ሰው እንዴት ብሎ ነው ፍቅር የሆነው ኢትዮጵያዊነት ሱሱ የሆነው? የተላከበትን ነገር አሳምሮ ጨርሶ የተዘጋጀለትን አክሊል ለቀበልም ቢሆን ነገሩን ሱስ ደረጃ ማድረስ ራስን ማስገመት ነው፡፡ከአቶ መለስ ጋር ነፍሱ ከስጋው የተለየችውን የአቶ ኃ/ማርያምን ወንበር ለማግኘት ይሄን ያህል መፋተሩ ካድሬ ሆነው ካላዩት ትርጉሙ አይገባም፡፡ 

ማለባበስ ይቅር

ወደ ኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት ከመምጣቱ በፊት በክልሉ የደህንነት መስሪያቤት ውስጥ ሲሰራ የነበረው አቶ ለማ መገርሳ አሁን አሁን ሃጢያቱ ሁሉ የቀረለት ንፁህ መሲህ ተደርጎ እተሞካሸ ይገኛል፡፡ ይህ ትርጉም የሚሰጠው የተሰራ ሃጢያት በቅፅበታዊ የልብ መመለስ ወደ ፅድቅ በሚቀየርበት በመንፈሳዊው ዓለም እንጅ በልብ የተያዘውን በአፍ ከሚወራው ጋር ማመሳከር በማይቻልበት በፖለቲካው ዓለም አይደለም፡፡ በበኩሌ ለለማ መገርሳ ደርሰው ከሚያሸበሽቡት ወገን ለመሰለፍ የምቸገርባቸው ብዙ ነባራዊ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ ሰውየው ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ዘመን ጀምሮ አብረው የመጡ ሰው ከመሆናቸው በተጨማሪ በደህንነት መስሪያቤት በመስራታቸው የእስርቤቱን ቋንቋ ኦሮምኛ በማድረጉ ረገድም ሆነ በአጠቃላይ ፖለቲካችንን ብልሹ በማድረጉ ረገድ ተሳትፎ ያላቸው ሰው ስለሆኑ ድረሶ ለእሳቸው ማሸብሸብ ብዙ መርህ መጠረማመስ መስሎ ይታየኛል፡፡ 

በየእስርቤቱ ለመስማት እንኳን የሚቀፍ ግፍ ለሚሰራ፣ለህዝብ የቆሙ ንፁሃንን ከልጆቻቸው ነጥሎ፣ በቶርቼር (torure) ገላቸውን ለሚበጣጥስ፣ እናትን በልጅ አስከሬን ላይ አስቀምቶ የሚደበድብ ሥርዓት ማገር ሆኖ ሲገለግል የኖረ/እያገለገለ ያለ ሰው፤ ይህ ጥፋት መስሎ ሳይታየው ጭራሽ ለሌላ ስልጣን ጉብ ቂጥ ለሚል ካድሬ ማሸብሸብ መነሻን እና መድረሻን ያለማያውቅ መርህ አልቦነት ነው፡፡ እንዲህ በመርገም ውስጥ ተዘፍቆ ተመችቶት እየኖረ ያለ ሰው ተቀይሮ ደህና ቀን ያመጣልናል ብሎ ጭራ መቁላት የራስን ስራ ተነስቶ ላለመስራት የሚደረግ የሃሞተ ፈሳሶች ከንቱ ዘፈን ነው፡፡ 

ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖበት ሊገድለው እንደደረሰ ሲያወራ እልል የሚባልለት ለማ መገርሳ “ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች” የሚለውን የክልሉን ህገ-መንግስት አስፈፅማለሁ ብሎ ስልጣን ላይ ቂጥ እንዳለ ለማሰብ ያልቻለ ፖለቲካ አውቃለሁ ባይ ሃገር የት ያደርሳል? ለማ ከተመረጠ ጀምሮ እንዲሁ ስለኢትዮጵያዊነት እየቀላመደ መስሎኝ ሰዎች ‘ኦሮሞ ሳትሆኑ እንዴት ብትጠግቡ ኦሮሚያ ምድር ተገኛችሁ’ ተብለው በቆንጨራ የተፈለጡት፡፡ ይህን ፈጥኖ ደርሶ ያላስቆመ ለማ መገርሳ፣ በሚያስተዳድረው ክልል ኦሮሚያ ላይ ነፍስ ማዳን ያልቻለው ለማ መገርሳ በየት ዞሮ ነው ህወሃትን ለማንጓጠጥ የበቃው? 

ኤሊባቡር ላይ ሌሎች ናችሁ ተብለው በአሰቃቂ ሁኔታ ነፍሳቸው ባለፈው ዜጎች ደም በምንም ሁኔታ ለማ መገርሳ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ የዚህ ሲገርም የአቶ ለማ ካቢኔ አባል አቶ አዲሱ አረጋ ኮራ ብለው የአስከሬን ዘር ማንዘር ትግሬ ወይ አደሬ መሆን  የሚፈይደው ነገር ያለ ይመስል ወለጋ ላይ “የሞቱት ሰዎች ዘር ትግሬ አይደለም” እያለ ነገስታትን አለማስቀየሙን ለማጉላት ብቻ ይፋትራል፡፡ ካድሬ ገርሞኝም ስለማያውቅ የምገረመው በአዲሱ ንግግር ሳይሆን ይህንንም እየሰማ የለማን ካቢኔ ልዩ ብፁዕ ለማድረግ በሚቃጣው ፖለቲካ አዋቂ ነኝ ባይ ነው፡፡  

ነገሩን ያደረገው መከረኛው ህወሃት ነው ከተባለም ለማ ህወሃትን አንጓጠጠ የተባለውን ተረት ተረት ፉርሽ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ካድሬ አዲሱ አረጋ እንዳወራው ድርጊቱን የፈፀሙት ያባረሯቸው የኦህዴድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ቢሆኑም ጀግኖ ሊሞት ነው የተባለው የለማ አስተዳደር በብርሃን ፍጥነት ደርሶ የሰዎችን ነፍስ ማዳን ነበረበት፡፡ ይብስ የሚገርመው ለማ መገርሳ በውቢቷ ባህርዳር ተገኝቶ ገዥው ፓርቲ የተለከፈበትን የፕሮፖጋንዳ ጥማት ሲያረካ ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው መከራቸውን የሚያዩ ዜጎች እባካችሁ አንድ በሉን እያሉ የሰሚ ያለህ ይላሉ፡፡ 

እውነት ለማ እንደሚያወራው እና እንደሚዘመርለት የአንድነት ሰባኪ፣ የኢትዮጵያዊ አብሮነት ሱሰኛ፣ ለህዝብ አሳቢ፣ በራሱ እንጅ በጌቶች ሃሳብ የማይነዳ ቢሆን  ቀድሞ ማድረግ ያለበት “ኢትዮ-ሶማሌ ተጉዞ የህዝቦችን አንድነት ሰብኮ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው? ” ወይስ “ባህርዳር ሄዶ የአዞ እንባ ማንባት?” ይሄ ሁሉ እየሆነም ለማ በኢትዮጵያዊነት ሱስ መለከፉን ለሚያምኑት እያወራ ነው፡፡ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ህዝብም እየተከተለው ነው፡፡ እውነቱን እድሜ የሰጠው የሚያየው ይሆናል! የማይካደው ሃቅ ግን በዚህ የፖለቲካ ድራማ ውስጥ ህወሃት/ኢህአዴግ በለማ መገርሳ በኩል ባህር ማዶ የተቀመጡ የጥላቻ ፖለቲካ በሽተኞችን እንዳያንሰራሩ አድርጋ መምታቷ ነው፡፡ ይህ የጋራ ድላችን ነው!  

                                

4 thoughts on “​በለማ ሥም የሚመጣ “የተባረከ” ነው? (በመስከረም አበራ) 

 1. Nigussu Tilahun added 2 new photos.
  November 4 at 6:45pm ·

  ” የአማራ ህዝብ መፈናቀል ለኦሮሞ ህዝብ ህመሙ እና ጉዳቱ ነው ፤ህዝቡም ይህንን ይመስክራል፤ የትኛውም ህዝብ ማንኛውንም ህዝብ አያፈናቅልም፤እንዲህ የሚያደርገን ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው፣ መታገል ያለብን ከፋፋይነትን ነው”

  “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ቢያንስ ሁለት ቋንቋ ትናገራላችሁ ፤እኛ ግን አንድ ብቻ እኛም አፋን ኦሮሞ ብንማር እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም ”

  ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
  ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም
  በመድረኩ ከተናገሩት የአማራ ህዝብ መፈናቀል ለኦሮሞ ህዝብ ህመሙ እና ጉዳቱ ነው ፤ህዝቡም ይህንን ይመስክራል፤ የትኛውም ህዝብ ማንኛውንም ህዝብ አያፈናቅልም፤እንዲህ የሚያደርገን ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው፣ መታገል ያለብን ከፋፋይነትን ነው”

  “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ቢያንስ ሁለት ቋንቋ ትናገራላችሁ ፤እኛ ግን አንድ ብቻ እኛም አፋን ኦሮሞ ብንማር እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም ”

  ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
  ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም
  በመድረኩ ከተናገሩት
  THE ABOVE WAS WHAT THE AMHARA REGION COMMUNICATION HEAD POSTED ON HIS FACEBOOK PAGE AND I COMMENTED THE FOLLOWING አቶ ንጉሡ፤ በጎ ሀሣብ ከየትኛውም አቅጣጫ ከመጣ መቀበል እንደሚኖርብን ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንተና አቶ አዲሡ አረጋ እንዲሁም በአሁኑ ሠአት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች እያደረጋችሁ ያለውን በጎ ሥራ ሳላደንቅ ባልፍ ንፉግነት ነው፡፡ እናም በዚህ በጎ ተግባራችሁ ለፈጠራችሁት በጎ አገራዊ መንፈስ ከልብ የመነጨ አክብሮቴንና አድናቆቴን ላንተና ለአዲሡ አረጋ እንዲሁም ለሁለቱ ክልል ፕሬዜዳንቶች አቀርባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ምናልባት አንተም እንደምታውቀው በአሁኑ ሠአት ኢትዮጵያችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የፖለቲካ ውጥረት ውሥጥ ሆና የህዝቡም መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ሣይመለሡ ንፁሀን ዜጎችም ያለጥፋታቸው ተገለውና እሥር ቤት ታጉረው ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖችም በሀገር ውሥጥና በውጪ በሠላማዊ ትግልና በጦር ሀይል መንግሥትን ለማረቅ እየጣሩ ገዢዎቻችንም በቀደመው የድርቅና አመላቸው ገፍተውበት ወዘተ አገራችን አጣብቂኝ ውሥጥ ትገኛለች፡፡ በዕርግጥ ሀገራችን አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ውጥንቅጥ መሥመር ለማዚያዝ ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የቸብ ቸብ(cermonial) የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ብቻውን ከማሥታገሻነት በዘለለ ዘላቂ የፖለቲካ መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም፡፡ በተለይ ደግሞ ያለ ጥፋታቸው የታሠሩ የህሊና እሥረኞች ጉዳይና ነፃ ምርጫ ቦርድ የማቋቋም፣ የፖለቲካ ምህዳር መሥፋት፣ የሚዲያ ነፃነት፣ የመሠብሠብና የሠላማዊ ሠልፍ ነፃነት፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ወዘተ ጥያቄዎች ሣይመለሡ ህዝቡን በቸብ ቸብ ፖለቲካ ለማሥደሠት መሯሯጡ ችግርን ከማዘግየት በቀር ምንም አይፈይድም(እሡም ቢሆን ከተሣካ ማለቴ ነው)፡፡ ህዝቦችን ለማቀራረብ ማሠቡ የሚደገፍ ቢሆንም ከሥብሠባ ባሻገር መሬት ላይ ሊወርዱ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎች እንዳሉና የህዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊመለሡ እነደሚገባቸው መረሣት የለበትም፡፡ MESKEREM, AS YOU HAVE SAID, IT IS IMPOSSIBLE TO BELIEVE TPLF/EPRDF UNTIL IT ADDRESS ALL PUBLIC INTERESTS OR LOST ITS HEGEMONY IN ALL SPHERES.

  Like

 2. እንዲህ አይነት ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጠኝን እና ሀሳቤን የሚከትብልኝን ነበር ሳስብ የነበረው ይሄው አገኘው!

  Liked by 1 person

 3. ከእባብ እንቁላል የዶሮ ጫጩት ሲጠበቅ አይገርምም ?
  አሸናፊ ቶለሣ

  የኦህዴድ ከፍተኛ ካድሬዎች እየነገሩን ያለው ነገር አንደምታው ምንድነው?? ከጀርባዉ ፀሀያማ ነዉ ወይስ ጨፍጋጋ ? ወይስ የለየለት የሞት ድግስ ? ህወሓቶችን በዚህ ደረጃ አለማሰብ እነሱን ካለማወቅ ነው ወይም ከባድ እጅግ ከባድ በጣም ከባድ ልክ ሆነ ብሎ ወንጀል እንደመፈፀም ያህል ከባድ ቸልተኝነት ነዉ ። ይህን የምለዉ በጭፍን ጥላቻ ሳይሆን እግር ለእግር ተከታትዬ እነሱ እንደሚተጉብን በትጋት ሥራቸውን ስለአስተዋልኩ ነው ። ሀገራችንን እና ህዝባችንን ከምናየዉም ከማናየዉም ተጠንስሶልን ከነበረዉ መዐትና መከራ በአምላካችን ተጠብቀን ነዉ እንጂ እንደእነሱ ምኞትና ድርጊት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም ነበር ። ታዲያ ሰሞነኛዉ ሽርጉድ የወያኔን የሴራ ፖለቲካ ነገሬ ብሎ ለሚከታተለው 26 ዐመት ሙሉ ስንሰማ ከኖርነዉ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወሬ በምን ይለያል ? ለምንስ ህዝቡ በሰሞኑ የኦህዴድ ከፍተኛ ካድሬዎች ንግግር የተፈታ ይመስላል? በተራ ወሬ ብቻ እንዴት የተጀመረው መራራ ትግል በቅፅበት ተመልሶ ወደ ወያኔ ጉያ ዉስጥ ተሰነቀረ ። ትናንት በደም የጨቀየዉ የኦሮሞ ለጋ ወጣቶች ደም ሳይደርቅ ገዳይ ለፍርድ ሳይቀርብ በምስኪን እናቶች ፊት በአሰቃቂ ሁኔታ በኦህዴድ የበላይ አመራር መሪነትና ታዛዥነት ግፍ በተፈፅመበት ምድር ዛሬ ነገሩ ተገልብጦ ለፍርድ መቅረብ በሚገባቸዉ ሰዎች የኦሮሞ ህዝብ ትግል ለመመራት እጁን ሰጠ? የባህር ማዶዎቹ ኦህዴድን ወደ ማንቆለጳጰስ የዳዱት ይህችዉ ነች ሩጫቸዉ ? እነ አጅሬም ያደጉበት ጥርሳቸዉን የነቀሉበት ምን ገዷቸዉ ሲታሰር ወደ እኔ ሲፈታ ወደሱ እንደሚባለዉ ዛሬ ማሊያ ቀይረው ከህዝቡ ጋር ያለቅሳሉ ቁስሉን አየነካኩ መሀሉ ገብተዉ እንባ አባሽ ሆነዉ ቁጭ !! ወይ የሰዉ ህሊና !! የጭካኔአቸዉ ጥንካሬ ለነብሳቸዉ ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ራስወዳድነት ምን ቃል ይገልፀዋል ?? እነዚህ ታዲያ እንዴት የለዉጥ መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ምን የሚሉትስ ሂሳብ ነው ?

  ጥያቄዉ በኦሮሞ ህዝብ ያልተወከለዉ ኦህዴድ አይመራንም አልነበረም እንዴ ? ዛሬ ላይ ነገሩን ስመለከተዉ ኦህዴድ በለማ መገርሳ በከል ምርጫዉን መቶ በመቶ ያሸነፈ ሆነ ያዉም በባህር ማዶ ያሉት ሁሉ ድምፅ ሰጥተዉታል ። ይህች ነች የመለስ ዜናዊ ጨዋታ ጊዜዋን ጠብቃ በተጨማሪ ሰዓት የማሸነፊያ ግብ ለህወሓት ። የህዝብ ጥያቄ ሲበረታ ተጠያቂዉ እንዴት ለህዝብ ተቆርቋሪ ሊሆን ይችላል ? ማን ነበር የህዝብ ገዳይና በዳይ? ለማ መገርሳና አጃቢዎቹ ማንን ነው እየረገሙ ያሉት ? ግዑዝ ነገርን ነው ? ወይስ ኦህዴድን ነዉ ? ኦህዴድ ማለት ለማ መገርሳ ነው ለማ መገርሳ ማለት ኦህዴድ ማለት ነዉ :: ይህ ከሆነ ደግሞ ለማ መገርሳ ራሴ ነኝ ጥፋተኛ ማለቱ ነው በዚህ ላይ ምንም ፋላሲ አይታየኝም ። የጥፋተኝነት ስሜት ከተሰማዉ እና ወደ ህሊናዉ ከተመለሰ ራሱን ለውጦ ለሌላ የሥልጣን ዘመን መዘጋጀት ሳይሆን ራስን ለፍርድ ማቅረብ ነዉ ይህ ካልሆነ የድሮው ይቅር ቢባል እንኳ በቅርቡ ለተፈፀመዉ ግድያ ማን ነዉ ተጠያቂዉ ? የኦሮሞ ህዝብ ትግል የእዉነተኛ ለዉጥ ፈላጊ ትግል ከሆነ በመጀመሪያ የታሰሩት የህዝብ ልጆች እነ ዶክተር መረራ እነ በቀለ ይፈቱና የኦሮሞ ህዝብ ትግልን ይምሩ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያ ነፃ ትዉጣ ሊሉ ይገባል ። ዛሬ ላይ የኦሮሞ ህዝብ ትግል በእነ ለማ መገርሳ የተነጠቀ ይመስላል ። ጎበዝ እንደ ባለ አህምሮ ቆም ብለን እናስብ እንጂ በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ ለህዝብ እየታገሉ በወህኒ መከራ እየበሉ ያሉ ዉድ ልጆች እያሉ ዛሬ የህዝብ ልጆች ጥያቄ አይሎና ገፍቶ ለዉጡ የማይቀር መሆኑ ሲታወቅ የህዝብን ልጆች ሲገድሉና ሲያስገድሉ የነበሩ እነ ለማ መገርሳ እንዴት የዚህ ትግል መሪ ይሆናሉ ??? እንደሚሰማዉ ከሆነ ለማመን የሚከበድ ቢሆንም ኦህዴድ ከፈጠረዉ ከህወሓት ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል ቢባል እንኳ ራሱን ችሎ ቆሞ ሊታገል ይችላል እንጂ እንዴት የዚህ ህዝብ ንቅናቄ የትግሉ መሪ ተብሎ ይጠራል? ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ምን በጎ አስተዋጽኦ ነበረዉ , ለምንስ ተቋቋመ ,ማንስ አቋቋመው , ዘመኑን በሙሉ ምንስ ሲሰራ ኖረ, የማንስ ሀሳብ አስፈፃሚ ነበር ? ይህን ሁሉ ቆም ብለን ካሰብን ስሪቱም የተፈጠረበትም አላማ ለእዉነተኛ ኦሮሞ ልጆች መብትና እኩልነት በኦሮሞ ህዝብ የተመሰረተ ድርጅት አይደለም በህወሓት ለኦሮሞ ህዝብ ድርጅት አንመስርትለት ተብሎ የተፈጠረ ነው ይህ መሆኑ በራሱ ትልቅ ስድብና ንቀት ነው እንዴት በዚህ ክፍለዘመን እንደ ቅኝ ገዢዎች ዘመን ከእኛ በምንም ባልተሻሉ ወሮበሎች ጠመንጃ በመያዛቸው ብቻ እራሳቸውን እንደ ምጡቅ ሳይንቲስት በሚያመፃድቁ አላዋቂዎች እስከመቼ እንሸወዳለን

  አሁን በእስርና በስደት ያሉት የኦሮሞ ህዝብ ትግል መሪዎች የትኛውን የኦሮሞ ህዝብ ትግል ነበር የመሩት ? የታሰሩትስ ለማን ነው ? ደርግ በገዳይነቱ ዓለም ያወቀዉ መንግስት ቢሆንም ጊዜዉ እንዳበቃ እንደመሸበት ሰለገባዉ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የተወገደዉ ምድራችንም የተፈራዉ መከራ ያለደረሰባት በእዉነት የደርግ መንግስት ሼም ያዉቃል እነዚህ ሼም የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸዉ ነብሰ በላ ከአንድ ተራ ማጅራት መቺ ያነሰ የወረደ አስተሳሰብ ያላቸዉ ዛሬን ብቻ አልፈን የሚሉ ነገን የማያዩ ሆዳሞች አሁን እያየን ያለነው እና ሁኑ እየተባለ ያለው ቪቫ ለማ መገርሳ ቪቫ አባዱላ ነው ዛሬም በምድራችን ግለሰብን የማግነን በሽታ ይታያል ጉዳዩ ይህን ትልቅ ህዝብ ትልቋን ኢትዮጵያ የማዳን እንጂ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ኮከብ የማውጣት ጉዳይ አይደለም ዛሬ ያሰቃዩን አሰቃዮች በይቅርታ ሰበብ የይቅርታ መንገዱን እነሱ በፈለጉት መንገድ ይዘዉ ተከስተዋል በበኩሌ የይቅርታ ችግር ኖሮብኝ ሳይሆን ይቅር ለፈጣሪ ሲባል መርህ አለዉ በዳይም በዳይነቱን አምኖ ተበዳይም ልቡ ተቀብሎ ወደፊትም ይህ ላይደገም መማሪያ ትምህርት ለበዳዮች ተሰጥቶ ሊከወን ሲገባ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የኔ ነው በማለት ሁሉን ተቆጣጥሮ መመፃደቅ የትም አያደርስም ነገ ሌላ ቀዉስ ይጠብቀናል በዉጭ ያላችሁ ሚዲያዎች እና ፀሀፊዎች ከፈረሱ በፊት ጋሪዉን አታስቀድሙ ህዝቡን ወገቡን አታስፈቱት ለምስጋናም አትቸኩሉ ስታስቡት የትልቋ ኢትዮጵያ ችግር በአንድ ወገን አሺታና እምቢታ ይፈታል ? የግድ ሁሉንም ሊያሳትፍ ይገባል ። ኢትዮጵያ አሁን ምድሪቷን አየገዙ ካሉት ሰዎች ሌላ ሰው የላትም ወይስ ጉልበተኛ ባለ ጠመንጃ ስለሆኑ ምን ይደረግ እየተባለ ለመገዛት ወስነናል ማለት ነው ? ህዝብን ሲገደሉ ሲያወርዱ ሲያስሩ ከሀገር ሲያሳድዱ አብረው የህወሓት ቀኝ እጅ የነበሩ በህዝባቸዉ ደምና ዕንባ የነገዱ በሙሉ በመዉደቂያቸዉና ለፍርድ በመቀረቢያቸዉ ዘመን ዛሬ በለመደባቸዉ አድርባይነት ባህሪያቸዉ ማሊያ ቀይረው በአዲስና በተለወጠ በሚመስል ማንነት ወደተሻለ ሥልጣን ዳግም ለማንገስ በህወሓት የተጠነሰሰው የቤት ሥራ እየያዘ እየሰመረ ያለ ይመስላል። መቼ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ወይም የኦሮሞ ህዝብ ከወያኔ አዉቅልአለሁ አገዛዝ ነፃ የሚሆነው ? ኢትዮጵያ ከወያኔዊ አመለካከት በተለየ ሀሳብ የምትመራዉ መቼ ነው የተለየ አማራጭ ወደ ህዝብ የሚደርሰው መቼ ነው ከእስር ከስደት ህዝባችን የሚገላገለዉ ??? እየሆነ ያለው ትናንት ሲታገሉ እና ሲያታግሉ የነበሩ የህዝብ ልጆች ወደጎን ተደርገው እነ ገዱ እነ ለማ እነ አባዱላ እነ ኢህአዴጎች በሙሉ አሁን በተያዘዉ አዲስ የተሃድሶ መንገድ በመራራው የህዝብ ትግል ላይ ቀዝቃዛ ዉሀ ሊቸልሱበት ነገር ሁሉ በደጅ ነው ። ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ የህዝቡ ጥያቄ ተመለሰ የሚባለው እንዴት ሲሆን ነው ?? የታገሉለትን መሪዎች አስበልቶ ወህኒ እየማቀቁ ነው ??? ይህ ከሆነማ ታሪክ ራሷን ደገመች ይሉሀል ይህኔ ነው የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ እንደተባለው ሆነ ማለት ነው የመጨረሻው ሃሳቤ ይህን ዳር የደረሰ የህዝብ ትግል ዳር ቆመን የምንመለከት እንዲሁም ህዝቡን ስታታግሉ ብዙ ዉጣ ወረድን ያለፋችሁ በነዚህ አስመሳይ ተለዋዋጭ ነብሰበላዎች አትፈቱ ምንም ቢሆን ከእባብ እንቁላል የዶሮ ጫጩት አይገኝም

  Like

 4. የድኩማን ጦር አይወጉበት ወይ አያስፈራሩበት
  የምትለዉ አባባል ትመቸኛለች በአንድ ፅሁፍ ላይ ለአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ የሚመጥን ርዕሰ ነበር ሁልጊዜ በስብሰባ ማብቂያ ላይ አቋማቸው ወሬ ብቻ ጉራ ብቻ ስለነበረ ዛሬም ታዲያ ሰሞነኞቹ የለዉጥ ሃዋርያት እነ ሆድአደር
  ለማ መገርሳ አዲሱ አረጋ ለኦህዴድ ሆዳሞች እና ባህር ዳርም ላይ ላሉት የእነዚህ ቢጤዎች በሙሉ ይድረስልኝ

  ሀገርና ዘር አሰዳቢዎች በምንም መንገድ የኦሮሞን ህዝብ አትወክሉም ሰሞኑን አምቦ ላይ በቄሮዎች ለአድማ መንገድ የተዘጋበትን ድንጋይና እንጨት የወያኔ አግዓዚ ጦር የኦህዴድን ፖሊሶችን ሰብስቦ ቆመህ መንገድ እንዳዘጋህ ትጥቅህን ፍታና ጥረግ አያሉ እየገረፉ በህዝብ ፊት ሲዋረዱ የሞት ሞት ነዉ ። እናንተን ብሎ ባለሥልጣን ከሆድ ያላለፈ ሃሳብና ህልም የሌላችሁ ምድረ ሆዳም በእናንተ ዘራችን ህዝባችን ይሰደባል ። የእስከዛሬ ትርፋችሁ አዳማ ላይ እየተሰበሰባችሁ በየልኳንዳ ቤት ሆዳችሁን ከመሙላት ያለፈ ታሪክ የሌላችሁ ። መግለጫ ስታወጡ እንኳ የምትጠቀሙበት አማርኛ የወያኔያ የገደል ማሚቱ የሆነ ወደፊት ከህዝብ ድል በኋላ ይሄ የምታደነቁሩን ወያኔ የፈጠራቸዉ ሌባ ቃላቶች ከሥርዓቱ ጋር ይቀበራሉ ፀረዴሞክራሲያዊ ፣ፀረሰላም፣ተሞክሮ፣ሁከት ፈጣሪ ኪራይሰብሳቢ። የዚያ የደንቆሮ ፓርላማ ስብስብ አማርኛ ሰልችቶናል 26 ዓመት አንገሽግሾናል በኢትዮጵያ ዉስጥ በኦሮሞ ህዝብ ይሁን በሌላ አካባቢ በህዝብ መካከል ምንም የምትሉት በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ ህዝብን ከህዝብ የሚያጫርስ የተደረጀ ኃይል የለም ቢኖርም በወያኔ አደራጅነት በኦህዴድ አስፈፃሚነት የተቀናጀ የሰወ ዘር ፍጅት እየፈበረከ በሰዉ ልጅ መከራና ሞት ስልጣን ላይ ለመቆየት እየሰራ ያለዉ ዛሬ ጫንቃችሁ ላይ ቀንበር ጭኖባችሁ በፍርሀትና ለሆዳችሁ ብላችሁ የምታደገድጉለት ነብሰ በላዉ ቡድን ወያኔ ነው። ይህን ልባችሁ ያውቀዋል ለምን ይዋሻል ይህን ምስኪን ህዝብ አታጨናብሩት እነዚህ ቦንብ ሽጉጥ ይዘዉ ተገኙ የሚባሉት ግለሰቦች ከተያዙ በኋላ ይህን ዓመት ተፈረደባቸዉ ብቻ ነዉ መጨረሻዉ ? በማን እንደተላኩ የማን ተወካዮች እንደሆኑ ለምን አይገለፅም አህያዉን ፈርቶ አሉ ። በማን እንዴት አንደሚቀነባበር ታውቃላችሁ በመጀመሪያ ይህን ሥርዓት ልታገለግሉ ስትወስኑ የማላችሁት መሀላ ወይም ከወያኔ ጋር የገባችሁት ኪዳን የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ሣይሆን ልጅህንም ቢሆን ለማስገደል ወስነህ ነው ለባርነት ራስህን የሰጠኸዉ። ሲጀመር በዚህ እድሜአችሁ የወያኔን ቡድን የተቀላቀላችሁት ምን አስገድዷችሁ ነዉ? አባዱላና ኩማ የሻዕቢያ ምርኮኞች መቃብር ቆፋሮ አስመርሮአቸዉ ነው ለዚህ ማረጋገጫ የቀደሙት መሪ ተብዬዎቹ እነ ኩማ ደመቅሳ ፣አባዱላ ገመዳ ፣ ግርማ ብሩ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል እስቲ የነዚህን ሰዎች ሰብዕና አስተዉል ምን ዓይነት ሆዳሞች ህሊናቸውን የሸጡ እንደ አህያ የወያኔ ሸቀጥ መጫኛ አጋሰስ ሆነው በራሳቸው አህምሮ ሳይሆን እንደ አንድ ግዑዝ እቃ የወያኔ ሀሳብ እየተጫነባቸዉ ዘመናቸውን የፈጁ ወራዶች ዛሬ እድሜያቸው እንኳን ገፍቶ የማይፀፀቱ ሆዳቸው አምላካቸው ክብር የሚገኘው በወያኔዊ ባርነት ሥር ብቻ ነው ብለዉ ሰዉነታቸዉን ማንነታቸውን እንደ አንድ ምናምንቴ የሸጡ የለወጡ ባሪያዎች ያሉበትን ቴረሪስት ግሩፕ ነዉ ጆይን ያደረጋችሁት ታዲያ ከዚህ ፈጣሪ አምላኩ ወያኔ ከሆነ ማንነት ምን ይጠበቃል ?ሲጀመር አንድ ኢትዮጵያዊ የማንም ብሄር ተወላጅ ይሁን እንዴት የኢህአዴግ አባል ይሆናል ምን ለመሥራት ምን ለማድረግ ምንስ ለዉጥ ለህዝብ ለማስገኘት በምንስ ሞራልና አቅም እስቲ አጠገብህ ያሉትን የቀደሙት እና አዳዲስ የኦህዴድ አባላትን አስተዉል በአብዛኛው ምግባረ ብልሹ የገጠር አስተማሪነት የመረረዉ በየወሩ የአረቄና የጫት እዳ ያንገሸገሸዉ በዱቤ ምግብ ፈርሞ የበላበትን ዕዳ መክፈል ያቃተው ሀገርና መንደር ሲያምታታ የኖረ ሌባ ጥርቅም ብቻ ነው ለዚህም ማረጋገጫ ፓርላማው በቂ ነው የሰዉን ልጅ በአደባባይ የሚያሳርድ አዋጅ ወያኔ ሲያዘጋጅ እየሳቀ ያፀድቃል ኸረ ለመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ወይም የኦሮሞን ይሁን የአማራን ህዝብ ለማታገል በወያኔ ሰር መደራጀት ምን የሚሉት የሂሳብ ድምር ነው የወያኔ አላማ ወይም አልቲሜት ጎል ምንድነዉ ? ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ለነገሩ ብታስቡ ነዉ የሚገርመው ዛሬ በስደት በሰዉ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እናንተ አሽከር የሆናችሁበት ወንበር ተሸካሚነት ተጋብዘው ነበር ነገርግን እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ ሙሴ ከግብፅ ወርቅና ብር ይልቅ ከኩሩዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መከራ መቀበል ይሻላል ብለው ተሰደዉ ወይም በሀገር ዉስጥ የዝምተን ፖዝሽን መርጠዉ ወይም በወያኔ ማጎሪያ ወህኒ ተወርዉረዉ እግዚአብሔር የሰጣቸውን አህምሮ ሳያሳድፉ ስጋቸውን እንጂ ነብሳቸውን ምንም ሊያደርጉ ለማይችሉ ምናምንቴዎች ህሊናቸዉን አሳልፈው አላቀረቡም የህዝብ ልጆች በዚህ መከራ ዉስጥ አልፈው ነገ የድል ብርሀን ያያሉ በዚህ አቋማቸዉ ቢሰዉም እንኳ ከፀፀት በፀዳ ህሊና ህዝባቸውን እና ይህችን ዓለም ይሰናበታሉ።

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡