በኢትዮጵያ ብሔር ተኮር ግጭቶችና ጥቃቶች አሳሳቢ ሆነዋል (BBC)

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ለዜጎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እና ግጭቶች አፋጣኝ የፖሊሲ እና የአፈጻጸም መፍትሄ ያሻቸዋል ሲል የመብት ተሟጋቹ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ገልጿል።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብቶችን መከበር ለማረጋገጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ብሄር ተኮር ግጭቶችን ለማጣራት ዝግጅቴን እያጠናቀቅኩ ነው ብሏል።

ኮሚሽኑ ከድንበር ይገባኛል ጋር በተገናኘ በተለይም በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት መንስዔ እንዲሁም የደረሱ ጉዳቶችን በማጣራት ላይ መሆኑንም ለቢቢሲ አስረድቷል።

ሰመጉ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ጌዲኦ ዞን፤ እንዲሁም በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ ባለፈው ዓመት ተፈፅመዋል ያላቸውን የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው ልዩ መግለጫ ለብሔር ተኮር ጥቃቶች እና ግጭቶች በቂ ትኩረት አልተሰጠም፤ አስፈላጊው የህግ እና ተቋማዊ ስራም አልተከወነም የሚሉ ነቀፌታዎችን ማቅረቡ ይታወሳል።

የጉባዔው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብፅዐተ ተረፈ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መግለጫው ሲወጣ በአንድ በኩል በተጠቀሱት ስፍራዎች ላይ የተነሱት ችግሮች በራሳቸው መፍትሄ የሚያሻቸው መሆኑን በመጠቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እየተባባሱ የመጡትን ግጭቶች እና ጥቃቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አፅንዖት መስጠትን ታሳቢ አድርጓል።

“ሁለት ወገኖች እኩል የሚሳተፉባቸው በድንበር ይገባኛል፣ በግጦሽ መሬት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች አሉ፤ በፊትም ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ አቋም የሌላቸው አናሳ ብሔሮች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መበራከት ይዘዋል” ብለዋል አቶ ብፅዓተ።

ተፈናቃዮች በሐማሬሳ መጠለያ ውስጥ
አጭር የምስል መግለጫበኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ድንበር አቅራቢያ ተፈናቅለው በሐማሬሳ መጠለያ ውስጥ የነበሩ (ከአንድ ወር በፊት የተነሳ ፎቶ)

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች በርካቶች ሕይወታቸውን ባጡበትና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከሶማሌ ክልል በተፈናቀሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ፤ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን እንዲሁም በቤንሻንጉል ክልል ካማሺ ዞን የተከሰቱ ግጭቶች እና የተፈፀሙ ጥቃቶች ለሞት እና ለመፈናቀል ምክንያት መሆናቸው ይታወሳል።

“ሕይወቴን ብቻ ይዤ መውጣት ነው የምፈልገው”

ከዚህም በተጨማሪ በወርሃ መስከረም 2009 ዓ.ም በጌዲኦ ዞን እንዲሁም በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም በሐረር ከተማ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ የመብት ረገጣዎች ተፈፅመዋል የሚለው የሰመጉ መግለጫ፤ የብሔር ተኮር ግጭቶች እና ጥቃቶች “እየከፉና በአደገኛ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ ለመገኘታቸው አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል” ይላል።

በኢሰመኮ የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሃኑ አባዲ በበኩላቸው ከተለያዩ ስፍራዎች የመጡ ጥቆማዎችን በመከተል ብሔር ተኮር ግጭቶችን የሚያጣራ ቡድን በቅርቡ ይንቀሳቀሳል ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል፤ ቡድኑ ከሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች መካከል የኦሮሚያ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እንደሚገኙባቸውም ጨምረው ገልፀዋል።

አቶ ብርሃኑ “ከድንበር ጥያቄ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የደረሰውን ችግር የሚያጣራ ቡድን ግን ወደቦታዎች አምርቶ ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል” ብለዋል።

የሰመጉ መግለጫ በቀጥታ ተጎጅዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦች በማነጋገር፤ የምስክሮችን ቃል በመቀበል እና ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉትን አካባቢዎች በአካል በመጎብኘት ባደረግኩት ማጣራት በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም በደረሰ ብሔር ተኮር ጥቃት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ደርሼበታለሁ ይላል።

መግለጫው ጨምሮም በ2009 ዓ.ም የሰኔ ወር መገባደጃ ላይ የአፍረን ቀሎ የባህልና የታሪክ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ መጣል ጋር ተያይዞ ብሔር ላይ ያነጣጣረ ማዋከብ፣ እስራት እና ድብደባ ተፈፅሟል ይላል።

መንግስት ለመሰል ግጭቶች እና ጥቃቶች መንስዔ የሆኑት “ጥቅማቸው የተነካባቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች” እና “የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች” ናቸው ሲል ይወነጅላል።

በኢትዮጵያ ብሔር ተኮር ግጭቶችና ጥቃቶች አሳሳቢ ሆነዋልImage copyrightPAUL SCHEMM

በቅርቡም የብሔር ይዘት ያላቸውን ግጭቶችን የማባባስ ሚና ያላቸው የአመራር አባላት እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተናገሩ ሲሆን፤ እነዚህ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸው ይታወሳል።

“በድንበር ይገባኛል ሰበብ የከፉ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋርም በመመካከር አስቸኳይ መፍትሄ ይስጥ” በሚል ርዕስ ኢሰመጉ ባለፈው ጳጉሜ መግለጫ አውጥቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ መንግሥት ለጥቃት እና ግጭቶቹ የሚሰጠውን ምላሽ “የዘገየ” ከመሆኑም ባሻገር ችግሮቹን ከስር መርምሮ ሲቀርፍ አይስተዋልም ሲል ይወቅሳል።

እንደ አምቦ ዩኒቨርስቲ መምህርና ጦማሪው ስዩም ተሾመ ግን የጥቃቶቹ እና ግጭቶቹ መሰረታዊ መነሻ ላለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ስራ ላይ ካለው ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ስርዓት የሚዘል አይደለም።

መንግሥት ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች፣ ሕዝባዊ ሰልፎች እና አድማዎች ብሔር ተኮር ብሔርተኝነት ካልተጨመረባቸው በስተቀር ወደ ብሔር ግጭትነት አይቀየሩም ሲል የሚከራከረው ስዩም “የብሔር ተኮር ስርዓት መጥፎ መልክ የሚገለጠው የብሔር ልዩነቶችን በሚያገን ስርዓት ያለመተማመን የተዘራበት ማሕበረሰብ በፖለቲካዊ ያለመረጋጋት ሲናጥ ነው” ይላል።

“ያኔ የዘር ግጭት ተባብሶ የዘር ማጥፋት ሊከሰት ይችላል” ሲል ስዩም ለቢቢሲ ያስረዳል።

ባለፉት 26 ዓመታት ኢሰመጉ ካወጣቸው ወደ አንድ መቶ ሰማንያ የሚጠጉ በመብት ጥሰት ዙርያ የሚያጠነጥኑ መግለጫዎች መካከል ከአርባ በላይ የሚሆኑት የብሔር ጥቃቶችን ወይንም የብሔር ተኮር ግጭቶችን ተከትሎ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን የሚመለከቱ ናቸው።

አቶ ብፅዓተ የግጭቶቹና ጥቃቶቹ መደጋገም በተመለከተ “አንድም ትምህርት እንዳልተወሰደ ያሳያል፤ ከዚህ በባሰም የታጠቁ አካላት ጭምር ወዲያና ወዲህ ተቧድነው ወገኔ ከሚሉት ጋር አብረው በግጭት እና ጥቃቶች መሳተፋቸው የችግሩን መጠንከር ያሳያል” ሲሉ ይደመድማሉ።

***

ምንጭ፦ BBC|አማርኛ