አብዮታዊ ዴሞክራሲ፤ የኅብረ-ብሔር ፖለቲካ መልሕቅ ወይስ የአኃድ ድርጅት ግልቢያ?

በመንግሥቱ አሰፋ (ዶ/ር)

ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን መጠበቅ የማይገረሰስ የኢህአዴግ መርህ ነው“::
ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር

መግቢያ
ታሪካዊ ዳራ

አብዮታዊ ዴሞክራሲ በብዙ ነገሩ ከማርክሲስት-ሌኒኒስት አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ መሰረታዊ የፖለቲካ ጽንሰ-ሐሳብ ያለው መሆኑን ብዙ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያን እየመራት ያለው ድርጅት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ይህን የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ተቀብሎ ያራምዳል፡፡ ወደ ሥልጣን ከመዉጣቱ በፊት ኮሚዩኒዝምን ሲያራምድ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ኮሚዩኒዝምን የተወዉ በርዕዮተ-ዓለሙ ማመን ስላቆመ ሳይሆን በጊዜው የነበረው የዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ስላስገደደው ነው፡፡ ልምሳሌ የሶቪዬት ኅብረት መፈረካከስ እና ከነፃ ገበያ አራማጅ ሀገሮች በተለይ ከአሜሪካ መጠነኛ ድጋፍ ማግኘቱና ሌሎች የጊዜው የዓለም የፖለቲካ ሁኔታዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ኢህአዴግ ብዙም የርዕተ-ዓለም ለውጥ አደረገ ለማለት ያዳግታል፡፡

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለም መሠረታዊ እሶቶች

የኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አስተሳሰብ መሠረቱ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም-ማዖዒዝም ጋር ቅርብ ቁርኝት ያለው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑትም ህዝብን ለአስተዳደርና ብቻ ሳይሆን ለራሱ ርዕዮተ-ዓለም ማስፋፊያና ማስቀጠያ በሚያመች መልኩ መከፋፈሉ ነው፡፡ ከሚከፋፍላቸው ህዝብ ክፍል በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው አርሶ አደሩ ሲሆን መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በቁጥር ማነሳቸው በፖለቲካና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ድርጅቱን የሚደግፍም ሆነ በተሻለ ሁኔታ የሚገዳደረው አለመኖሩን ሳሙኤል ሀንቲንግተን የተባሉ ምሁር ይናገራሉ (Huntington 1993: 271):: ሀንቲንግተን እ. አ. አ. በ1993 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጥተው ስለ ፌደራል ህገ-መንግሥቱ ጽንሰ-ሐሳብ የሰጡና የአዉራ ፓርቲ ምስረታ ላይ ኢህአዴግን አማክረዋል የሚባሉ ምሁር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት አንድ አዉራ ፓርቲ ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍልን ተዓማኒነት ይጎናጸፋል፡፡ ትናንሽና በፖለቲካ ተደራሽነታቸው ብሔር-ተኮር የሆኑ፣ ደካማና ለተወዳዳሪ የሀሳብ ምንጭ የማይሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች ይኖራሉ፡፡ ይህ ለሁለት ነገር ይጠቅማል ፡:

  1. ኢህአዴግን (አውራውን ድርጅት አማራጭ የሌለውና ብቸኛ ተወዳዳሪ ያደርገውና በተከታታይ ምርጫን በማሸነፍ የስልጣን እድሜውን ያራዝማል፡፡
  2. ሌላው ደግሞ ትናንሽ የፖለቲካ ድርጅቶች መቼም ቢሆን መንግሥትን የሚያስመሠርታቸው ድጋፍና ተደራሽነት አይኖራቸው፡፡ ይህ ደግሞ የብዙሃን የፖለቲካ መስተጋብር (Multiparty Political atmosphere) እንዳለ በማስመሰል ኢህአዴግ በውጪ በተለይ የምዕራቡን ዓለም ከላይም ቢሆን የሚያሳየውን የኅብረ-ፓርቲ ፖለተካ እንዳለ ያስመስልለታል)2፡፡ ይህ በመርህ ደረጃ ቀላል ይምሰል እንጂ ሚስተር ሳሙኤል ሃንቲነገተን ያላስተዋሉት ነገር አለ፡፡ እሱም “ኢህአዴግ ይህን መርህ ተግባራዊ የሚያረግበት ፍትሓዊ ነው ወይ?” የሚለው ነው፡፡ በሚቀጥሉት የጽሁፉ ከፍሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያመጣውን ውጤት ለማየት እንሞክራለን፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና ፌዴራሊዝም

ፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥርዓት በማእከላዊ መንግሥትና በክልሎች መሃከል የሚደረግ የሥልጣን ክፍፍል ላይ የሚመሠረት ሲሆን በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው የሥልጣንና የሥራ ክፍፍል መሠረት የሚተዳደሩ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የመንግሥት አካላትም ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት የሚከፋፈል እና የሚሠራ ይሆናል፡፡ አንዱ አካል በ “Check and Balance” ሕግን በተከተለና ግልጽ በሆነ አሠራር እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመርህ ደረጃም ከፌዴራሊዝም ጋር የሚጋጭበት ነገር አለው፡፡ ይህም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስልጣን ወደ ገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ያከማቻል፡፡ በዚህ መሠረት በየክልሉና ሌሎች መካከለኛና ዝቅተኛ የድርጅቱ አመራሮች እጅግ የተገደበ የዉሳኔ ሰጪነትና የሐሳብ አመንጪነት ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ማለት ባጠቃላይ የመንግሥቱ ሥርዓት ውስጥ ከመጠን በላይ የሥልጣን ማዕከላዊ ክምችት (Power Over centralization )ይኖራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ማለት ይኸ ነው፡፡ይህ ደግሞ ከፌዴራሊዝም መሠረታዊ እሴት ጋር የሚጋጭና ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢዴሞክራሲያዊ ነው::

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ሥርዓት ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የክልሎች ክፍፍል ስለሆነ ከሌሎቹ ሀገሮች ፌዴራል ሥርዓት በእጅጉ ይለያል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ሥርዓት የሚመራው በተለመደው የዴሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት መርሆች ሳይሆን በገዢዉ ፓርቲ ርዕዮተ-ዓለምና የአመሪር መርሆች ነዉ፡፡ ሀገሪቱን እየመራት ያለው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ከ1980ዎቹ መጨረሻ የዓለም የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁኔታ መለወጥ በተለይ የቀዝቃዛው ጦርነት መገባደድን ተከትሎ የተወሰኑ ህገ መንግሥታዊና የይስሙላ ርዕዮተ-ዓለማዊ ለዎጦችን አድርጓል፡፡ ቢሆኖም ግን መሠረታዊ ለውጥ አላደረገም፡፡ የሀገሪቷን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጤን ካስፈለገ በህገመንግሥቱና በሌሎች ሆጎች በጽሑፍ ደረጃ የተቀመጡትን ከማጥናት (De jure) በተጨማሪ በተግባር መሬት ላይ የሚታየው ነገር ማጥናት (de facto study) ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢህአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርሆዎችና አሠራሮችን በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የኢህአዴግ ፌዴራል ሥርዓት መሠረታዊ መርሆው የሶሻሊስት ፌዴራሊዝም ነው፡፡ የጆሴፍ ስታሊንን “የብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን” መሠረት ያደረገ የክልሎች ክፏፍፍልን ይከተላል፡፡
ሥርዓቱ የ”Bourgeoise” ጠላት ሲሆን ማለትም
1. የግለሰብ ተሳትፎዎችንና
2. የመድበለ-ሐሳብ ፖለቲካን አያበረታታም፡፡ በዚህ መሠረት ራሱን አውራ ፓርቲ የማድረግ ዕቅዱን ያሳካል ማለት ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ እንደሚያወራው የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በህገመንግሥቱ በተቀመጡለት ዴሞክራሲያዊ መርሆችን ማለትም ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል፣ የዜጎች መብቶች መጠበቅ እና ድሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባትን መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ ነዉ፡፡ መሬት ሌይ የሚታየው እውነታ ግን የዚህ ፍፁም ተቃራኒ ነው፡፡ ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ከትክክለኛው ፌዴሬላዊ ዴሞክሬሲ መርሆዎች ይልቅ በራሱ አምባገነናዊ መርህ ማለትም “ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” ነው እያስተዳደረ ያለው፡፡ ደዚህም መገለጫዎች፡

  1. ህዝብ የበላይ ፍፁም የሥልጣን ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የገዢዉ ፓርቲ ጥቂት ከፍተኛ መሪዎች “ራዕይ” አስፈጻሚ ሆኖኣል፡፡ የህዝቡ ተሳትፎ ውጥት የሚለካው ከላይ የድርጅት መሪዎች የሚሰጡትን ቀጭን ትዕዛዝ በመፈጸም እና ባለመፈጸም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህዝብ የሥልጣን ምንጭ መሀኑ ቀርቶ ራሱን አውራ ፓርቲ ያደረገው ድርጅት ባሪያ ይሆናል፡፡
  2. የዜጎች መብት አለመጠበቅ ና እኩልነት አለመረጋገጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ የመብትና ነጻነት ጥያቄዎች በየጊዜዉ ይነሳል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የቀጠለው የኦሮሞ ተቃውሞ እንዲሁም የአማራ ተቃውሞኖ መጥቀስ ይበቃል፡፡ መንግሥት የተለመደውን ሰላማዊ ተቃውሞን በጠብመንጃ ዝም ከማሰኘት ውጪ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መልስ መስጠትን አልፈለገም፡፡ ይህ የሆነው ባለማወቅ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ለህዝቡ መብትና ጥያቄ ደንታ የሌለውና ራሱን ሥልጣን ላይ ለማስቆየት ምንም ነገር ማድረግ እንደሚችል በተግባሩ በተደጋጋሚ እያሳየን ነው፡፡
  3. የሲቪክ ማኅበራት፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እና ነጻ ሚዲያ በተደጋጋሚ የፖለቲካ ጫና ይደረግባቸል፡፡ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አማራጭ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሐሳቦችን የሚያመነጩትን ግለሰበችና ድርጅቶች እንዲንኮታኮቱ በማድረግ ራሱን አውራ ድርጅት ያደርጋል፡፡

የልማታዊው መንግሥት ንግር

በ1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ ከፍተኛ የፖለቲካ ሽንፈት እና የህዝብ ተቃውሞ ሲያጋጥው ሁለት ወሳኝ እርምጃዎችን ነው የወሰደው፡፡
1. የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ከፍተኛ አመራሮችና አባላትን ማሰርና ማንገላታት፡፡
2. ከ1998 ጀምሮ ደግሞ አዲስ የድስኩር ርዕስ “ኢምፖርት” አደረገ፡፡ እሱም “የልማታዊ መንግሥት” ንግር ነው፡፡ ህዝቡ የመብት፣ የነጻነትና የፍትሕ ጥያቄ ሲያቀረብ በጠብመንጃ ኃይል በማፈን በምትኩ በ”ልማት በመካስ” እንዲሁም የህዝብን መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ አቅጣጫ እንዲቀይር በማድረግ የራሱን የአውራ ፖርቲ ምስረታ ፕሮጀክት ያጠነክራል፡፡

የኢህአዴግ ግምገማ መርህና ዴሞክራሲ

ፓርቲው ከሚታወቅባቸው አሠራሮችና መርሆዎች አንዱ የግምገማ ሥርዓቱ ነው፡፡ ይህ አሠራር የድርጅት/የሀገር መሪዎችና አባላት በየጊዜዉ ግለ-ሂስና ሂስ በሚባሉ ህደቶች ያሳየው መሰጠትና የሠራው ነገር ይገመገማል፡፡ ግምገማ በመሠረቱ ጥሩ ነው፡፡ የአመራር ብቃትንና የመሪዎችን ቁርጠኝነት ኦንደሚያጎላ ይታመንበታል፡፡ ነገር ግን ከዝጎች የተሰወረ፣ አሠራሩም በውል ያልታወቀ ከመሆኑም በላይ ከመሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ አሠራር ሥርዓት (ግልጽነት (transparency )፣ ተጠያቂነትና(accountability) ተገቢ የመንግሥት አሠራር (due process) ጋር በእጅጉ ይጣረሳል፡፡ መሪዎች አሠራራቸው ግልጽ፣ ህግና ደንብን የተከተለ እና ጥፋታቸው በህግ በይፋ መታየት ሲገባው የኢህአዴግ ግምገማ ግን ከዚህ ሁሉ ይልቅ መሪዎች ከድርጅቱ ጋር በየጊዜዉ ራሳቸውን እየቃኙ ስለሚያጠፉት ነገር ሳይጠየቁ “እንዲስተካከሉ” የሚያደርግ ኢዴሞክራሲያዊ አሠራር ነው፡፡

ማሳረጊያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሲሰጡ ከተናገሩአቸው ሁለት ዐረፍተ-ነገሮችን ለዚህ ጽሁፍ መቋጫ እናድርጋቸው፡፡

“ዲሞክራሲያው ማዕከላዊነትን መጠበቅ የማይገረሰስ የኢህአዲግ መርህ ነው”::

“አቶ አባዱላ ሥልጣን መልቀቁን በቴሌቪዢን ለህዝብ መናገሩ ስህተት ነበር….. እኛው በውስጥ መፍታት እንችል ነበር”::

በዚህ መሠረት ኢህአዴግ መቼም አቋሙን ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የማያመቻችና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የብቻው ሜዳ ለማድረግ ቆርጦ መነሳቱን ከራሱ በግልጽ ደጋግሞ አሰምቶናል፡፡