​አርባምንጭ አካባቢ የአግ7 ወታደራዊ ቤዝ አቋቁመዋል ከተባሉት 14 ተከሳሾች ውስጥ በ8ቱ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ተላለፈ

የግንቦት 7 አመራር እና አባል በመሆን አርባምንጭ አካባቢ  የድርጅቱን ወታደራዊ ቤዝ በመመስረት፣ ከፀጥያ ኃይሎች ጋር ተኩስ በመግጠም የሰራዊቱን አባል ገድለዋል፣ የግንቦት ሰባት ታጣቂዎችን አግዘዋል እንዲሁም በማንኛውም መንገድ በድርጅቱ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ 14 ተከሳሾች ዛሬ ህዳር 4/2010 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ብይን ተሰጥቶባቸዋል። 

በእነ ጌታሁን በየነ የክስ መዝገብ ስር ከተከሰሱት መካከል 1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ ሰው በመግደልና በድርጅቱ በአመራርነት በመሳተፍ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ዶክተር አስናቀ አባይነህ፣ 3ኛ ተከሳሽ ሰይፉ አለሙ፣ 4ኛ ተከሳሽ ብራዚል እንግዳ እና  5ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ንጉሴ በድርጅቱ ውስጥ በአመራርነት በመሳተፍ ክስ ቀርቦባቸዋል። 6ኛ ተከሳሽ ኪሩቤል ግርማ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጣቂዎች ድጋፍ በማድረግ፣ 7ኛ ተከሳሽ ያምላክነህ ገዛኸኝ፣ 8ኛ ተከሳሽ አብዱ ሙሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ  ለገሠ ኃ/መስቀል፣10ኛ ተከሳሽ   አስፋው አበላ፣ 11ኛ ተከሳሽ ታከለ ተሸመ፣ 12ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ፍቅሬ እሸቱ፣ 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ እና 14ኛ ተከሳሽ  ደመላሽ ቦጋለ በማንኛውም መንገድ ድርጅቱ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 7/1 ስር የተጠቀሰው ክስ ቀርቦባቸዋል።

1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ ተከሶበት ከነበረው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 3(1) እና 7(2) ስር የተጠቀሰው ክስ በአንቀፁ 7(1) እንዲከላከል ክሱ ሲቀየርለት ቀሪዎቹ ተከሰውበት በነበረው አንቀፅ ስር የተጠቀሰውን እንዲከላከሉ ተበይኖባቸዋል። 

ከ14ቱ ተከሳሾች መካከል  1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ፣ 2ኛ ተከሳሽ አስናቀ አባይነህ፣4ኛ ተከሳሽ ብራዚል እንግዳ፣ 5ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ንጉሴ፣  7ኛ ተከሳሽ ያምላክነህ ገዛኸኝ፣ 12ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ፍቅሬ እሸቱ፣ 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ እና 14ኛ ተከሳሽ  ደመላሽ ቦጋለ ተከላከሉ የሚል ብይን በተሰጠባቸው ወቅት እንደማይከላከሉ በመግለፃቸው የጥፋተኝነት ብይን ተሰጥቷቸዋል።

13ኛ ተከሳሽ ባንተ ወሰን አበበ  የቀበሌ ካድሬዎች በሀሰት እንዳሳሰሩት፣ የአቃቤ ህግ ምስክሩም ጋር ጠብ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ቢያስረዳም ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክር እንደፈቀደ፣ እሱ ብቻ ሳይሆን ወንድሙ በፍቃዱ አበበ በሀሰት ክስ ቀርቦበት 7 አመት  እንደተፈረደበት፣ እህቱ አየለች አበበ በአባቱ ላይ አርባምንጭ ቀርቦ የነበረ ክስ ቀርቦባት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት እየተከታተለች እንደምትገኝ ገልፆ፣ በእሱና በቤተሰቡ ላይ እየቀረበ ያለው ክስ በሀሰት በመሆኑ የማይከላከልበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ  አቅርቧል። 

ባንተ ወሰን አበባ መንግስት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሰራው ዶክመንተሪ አርባምንጭ ላይ በአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎችና በመንግስት የፀጥታ ኃይል መካከል በተደረገ ውጊያ እንደተሰዋ የተገለፀው እንግዳ አበበ ታናሽ  ወንድም ነው። ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ብይን በተላለፈባቸው  ተከሳሾች ላይ ፍርድ ለማሰማት ከህዳር 26/2010 ቀጠሮ ይዟል።