​ባለስልጣናቱ ለእነ ጉርሜሳ አያኖ  ምስክርነት እንዲቀርቡ በድጋሜ ታዘዘ

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ በምስክርነት የተቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣  አቶ አባዱላ ገመዳ፣  አቶ ለማ መገርሳ፣  ዶ/ር አብይ አህመድ እና ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ቀርበው እንዲመሰክሩ በዛሬው ዕለት  ትዕዛዝ ሰጥቷል።  ከአሁን ቀደም ጉዳዩን ይዘውት የነበሩት የ4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ባለስልጣናቱ  ቀርበው እንዲመሰክሩ መጥሪያ እንዲፃፍ አዘው የነበር ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን የያዙት አዲስ ዳኞች  የባለስልጣናቱን በምስክርነት መቅረብ አግባብነት መዝገቡን አይተን እንበይናለን በማለት ቀጠሮ ሰጥተው  እንደነበር ይታወሳል።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ህዳር 6/2010 ቀጠሮ ይዞ የነበረው ከአሁን ቀደም ለባለስልጣናቱ እንዲደርስ የተፃፈው  መጥሪያ ለምን ወጭ እንዳልሆነ  የሚመለከተውን አካል በችሎት ቀርቦ እንዲያስረዳ፣ እንዲሁም በመዝገቡ ስለ ምስክሮቹ የተሰጠውን ትዕዛዝ መርምሮ የተቆጠሩት ምስክሮች መቅረብ አግባብ ነው አይደለም የሚለውን ለመበየን ነው።

 ፍርድ ቤቱ መጥሪያው ያልወጣበትን ምክንያት “በሪጅስትራል አካባቢ ትኩረት ስላልተሰጠው” መሆኑንና ለዚህም ሌላ ቀጠሮ ሰጥቶ የሚመለከተውን አካል ለመጠየቅ እንደማያስፈልግ ገልፆ፣ ምስክሮችም መቅረብ እንዳለባቸው ብይን ሰጥቷል። 

 ከባለስልጣናቱ በተጨማሪ የአቶ በቀለ ገርባ ምስክር የሆነው አቶ አንዱዓለም አራጌ  ያልቀረበ ሲሆን በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ  ለፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተላልፏል።  ለአቶ አንዱዓለም አራጌ የተፃፈው መጥሪያ ለማረሚያ ቤቱ መድረሱ ቢገለፅም ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት አልቀረበም።

በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ  ከ1ኛ እስከ 4ኛ ካሉት ተከሳሾች  ውጭ ያሉት 13 ተከሳሾች ጥቅምት 28 በነበረው ችሎት መከላከያ አናሰማም በማለታቸው፣ እንዲሁም ጥቅምት 27፣28 እና 29 በነበረው ቀጠሮ ምስክሮቻቸው ሳይሰሙ ስለተመለሱ ለማሰማት ፍላጎት እንደሌላቸው ስለሚያሳይ ምስክር የማሰማት መብታቸው እንዲታለፍ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። 

የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው ተከሳሾቹ ምስክር አናሰማም አለማለታቸውን፣ በቀጠሮዎቹም አሰምተው ጊዜ ስላልበቃ ቀሪ ምስክሮች እንደተመለሱ በመግለፅ ለዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ መልስ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱም  ከ1ኛ እስከ 4ኛ ካሉት በተጨማሪ ዐቃቤ ሕግ ምስክር የማሰማት መብታቸው ይታለፍ ብሎ የጠየቀባቸው 13 ተከሳሾችም ለታህሳስ 17፣ 18 እና 19/2010 ዓም  መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያሰሙ ቀጠሮ ይዟል።