በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እየተፈፀሙ ያሉ በደሎች፡ ከታራሚዎች የቀረበ አቤቱታ

ቀን 23/02/2010 ዓ/ም

የመ/ቁ 200109

ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ልደታ ም/19ኛ ወ/ችሎት

   አ/አበባ

አመልካቾች፡- 

  •                   1ኛ) ኦሊያድ በቀለ
  •                    2ኛ) ኢፋ ገመቹ
  •                    3ኛ) ሞይቡል ምስጋኑ
  •                    4ኛ) ባይሉ ነጮ
  •                    5ኛ) ኤሊያስ ክፍሉ

ጉዳዩ፦ በማረሚያ ቤቱ እየደረሱብን ያሉት የተለያዩ ችግሮች እንዲቆምልን ትዕዛዝ እንዲሰጥልን የቀረበ አቤቱታ ነው፡፡

አመልካቾች ዐ/ህግ ባቀረበብን የሽብር ወንጀል ክስ ምክንያት ከሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምረን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነን ጉዳያችንን እየተከታተልን እንገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ በማረሚያ ቤቱ ሰብዓዊ እና ድሞካራሲያዊ መብታችን ተከብሮልን ጉዳያችንን በአግባቡ መከታተል ሲገባን የተለያዩ ችግሮች እየደረሱብን ይገኛሉ፡፡ ይሄውም፡-

1ኛ) በማረሚያ ቤቱ የሚቀርብልን ውሃ የጉድጓድ ውሃ ሲሆን ውሃው የደፈረሰ ( ንጹ ያልሆነ)፣ ጠጠር እና ሌሎች ባዕድ ነገሮች ያሉበት፣ እንዲሁም በጣም የሚያቃጥልና ለመጠጣት በጣም አስቸጋሪ የሆነ ውሃ ነው፡፡ በአጠቃላይ በማረሚያ ቤቱ የሚቀርብልን ውሃ ችግር ያለበት ሲሆን በዚህ ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን በመሆኑ ለወደፊት ህይወታችን ችግር ፈጥሮብናል፡፡

2ኛ) የማረሚያ ቤቱን መኝታ ክፍል በተመለከተ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 150 ( አንድ መቶ ሃምሳ ) ሰው ሆነን የሚንተኛ ሲሆን የምንተኛውም ስፋቱ 80 ሴንት ሜትር(80 cm) በሆነ ፍራሽ ላይ በ 2 (ሁለት) ሰው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሌሊት ሌሊት የንጹ አየር ችግር ( safocation) እያጋጠመን በመሆኑ ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረግን እንገኛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሊቱን ሙሉ በአንድ ጎን ብቻ ተኝተን የሚናድር በመሆኑ ለከፋ ችግር ተጋልጠናል፡፡

3ኛ) በአሁኑ ጊዜ በማረሚያ ቤቱ የተለያዩ አድስ የቤቶች ግንባታ እየተከናወኑ ሲሆን የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን እንዲንሰራ እየተገደድን እንገኛለን፡፡ በተለይም የኦሮሞ ተወላጆች የሆን እስረኞች የጉልበት ስራውን እምቢ በምንልበት ጊዜ የኦህዲድ (የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት) ባለስልጣናት የሚታሰሩበት ቤት ነው እየተባልን በአንዳንድ የማረሚያ ቤቱ የፖሊስ አባላት አስጸያፊ ስድቦችን እየተሰደብን እንገኛለን፡፡

4ኛ) ማረሚያ ቤቱ የኦሮሚኛ መጽሐፍቶችን እያስገባልን አይደለም፡፡ አመልካቾች የምንፈልገውን መጽሐፍ የማንበብ መብት ያለን ሲሆን ቤተሰቦቻችን ከዚህ በፊት የተለያዩ የኦሮሚኛ መጽሐፍቶችን አምጥተውልን የኦሮሚኛ መጽሐፍ በመሆኑ ብቻ አናስገባም በሚል ምክንያት መልሰውብናል፡፡ ይህም በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የቋንቋ እኩልነትን በእጅጉ የሚጣረስ ነው፡፡ በአጠቃላይ በማረሚያ ቤቱ የተለያዩ ችግሮች እየደረሱብን ስለሆነ ማረሚያ ቤቱ እነኝን ችግሮች እንዲያስተካክልልን ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡   

ከ5ኛ አመልካች ለብቻው የቀረበ የጤና ችግር፡-

5ኛ አመልካች ከዚህን በፊት የነርቭ የጤና ችግር ያለብኝ መሆኑን በመግለጽ አቤቱታ ካቀረብኩኝ በኋላ ፍ/ቤቱ ረጅም ኮሌታ ያላቸውን ልብሶች መጠቀም እንዲችል ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠልኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ማረሚያ ቤቱ እስካሁን ይህንን በፍ/ቤቱ የተሰጠውን ትዕዛዝ አልፈጸመልኝም፡፡ ከዝህም በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ህመሙ ተባብሶብኝ ግማሽ አካሌን ሙሉ በሙሉ እያመመኝ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ራሴን አየሳትኩ በየቦታው እወድቃለሁ፡፡ የማረሚያ ቤቱ ህክምናም ምንም ሊጠቅመኝ አልቻለም፣ በተቃራኒው በማረሚያ ቤቱ በየጊዜው እየተሰጡኝ ያሉት መድኃኒቶች ለሌላ በሽታ (የጨጓራ በሽታ) እያጋለጡኝ ይገኛሉ፡፡ በዝህ ምክንያት የተሻሌ ህክምና በራሴ ለመታከም ማረሚያ ቤቱን ብጠይቅም አልፈቀዱልኝም፡፡ እንዲሁም ከህክምናው ጎን ለጎን የተስተካከለ አለባበስ እና ጫማን ጨምሮ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ራሴን እንዳላንከባክብ ማረሚያ ቤቱ ከልክሎኛል፡፡ የመኝታ ቦታዬም ቢሆን ሁለት ሰው ሆነን ስፋቱ 80 ሴንት ሜትር የሆነውን ፍራሽ ስለምንጠቀም ሌሊቱን ሙሉ በአንድ ጎን ብቻ እየተኛው ለከፋ ችግር እየተጋለጥኩ እገኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ ህይወቴ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም በህክምናውም ሆነ በአለባበስ እንዲሁም ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ያለብኝን የጤና ችግር እንዳከባክብ ለማረሚያ ቤቱ ጥብቅ የሆነ ትዕዛዝ እንዲሰጥልኝ አመለክታለሁ፡፡             

One thought on “በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እየተፈፀሙ ያሉ በደሎች፡ ከታራሚዎች የቀረበ አቤቱታ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡