​በፀረ ሽብር አዋጁ የተበተነ ቤተሰብ!

የፀረ ሽብር አዋጁ ሲወጣ በርካታ ትችቶች ቀርበውበታል። የመደራጀትና ሀሰብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚፃረር ገዳይ ሕግ ስለመሆኑ ብዙ ተብሎለታል። የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚረገጡበት ሕግ ስለመሆኑ ቀድሞ ተተንብዮለታል። በጭላንጭል ላይ ያለውን የተቃውሞ ጎራ በማዳፈን የሀገርን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ  ግብአተ መሬት እንደሚከት ታምኖበታል።  ይህ አዋጅ እንደተባለለትም  በርካታ ኪሳራዎችን አድርሷል። ለአሁኑ የቁልቁለት ጉዞ የፀረ ሽብር አዋጁ አይነት መግዢያ ሕጎች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው።

በሽብር ወንጀል የተከሰሰው የአቶ ባንተወሰን አበበ ባለቤት ወ/ሮ መስከረም ሣሙኤል እና የአንድ አመት ከ5 ወር ህፃን ልጁ

በፀረ ሽብር አዋጁ በርካታ ንፁሃን ሰለባዎች ሆነዋል። አካልና ሕይወታቸውን አጥተቃል። ቤተሰብ ፈርሷል። የአቶ አበበ አስፋው ቤተሰብ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።  አቶ አበበ አስፋው የአርባ ምንጭ ከተማ፣ ድል ፋና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እስከ 70 አመታቸው ድረስ   የአርባምንጭ አሳ አስጋሪዎች ማህበር አባል ሆነው ኑሯቸውን ሀይቁ በሰጣቸው ፀጋ ይመሩ ነበር። የሚኖሩባት ድል ፋና  ቀበሌ ህዝብ የኢህአዴግ ደጋፊ አይደለም ስለሚባል በክትትል ውስጥ ያለ ቀበሌ ነው። የዚህን ቀበሌ ህዝብ የኢህአዴግ ደጋፊ ለማድረግ በርካታ ስብሰባዎችን ይጠራሉ። ካድሬዎች ቤት ለቤት  እየዞሩ ይወተውታሉ። ኢህአዴግን ቢመርጡ፣ ከኢህአዴግ ቢጠጉ ወደፊት ኑሯቸው እንደሚቃና ተስፋ ይሰጧቸዋል።

ካድሬዎች አቶ አበበ አስፋውንም በየ ስብሰባው እንዲገኙ፣ ከኢህአዴግ እንዲጠጉ፣ ኢህአዴግን እንዲመርጡ ይወተውቷቸዋል። ሆኖም አቶ አበበ ከኢህአዴግ ይወርዳል ከተባለው መና ይልቅ ደካማ ጉልበታቸውን  ይተማመናሉ።  ያላመኑበትን ሀሳብ ተቀብሎ  የውሎ አበል ወደሚገኝበት ስብሰባ አዳራሽ ከመሄድ ይልቅ ሀቃቸውን ሳያጡ፣ እምነታቸውን ሳይጥሉ ደክመው አሳ ወደሚያሰግሩበት ሀይቅ ማምራትን ይመርጣሉ። አቶ አበበ በዚህ አቋማቸው  የካድሬዎች ጥርስ ውስጥ ገብተዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰባቸው የጥላቻው ሰለባ ሆኗል።  አርባምንጭ ከተማ ውስጥ በደኢህዴን ካድሬዎች በክፉ አይን የሚታየው ድል ፋና ቀበሌ ውስጥ የእነ አበበ አስፋው ቤተሰብ በቁጥር አንድ ጠላትነት ተፈርጇል።

እንደ አባታቸው ሁሉ የአቶ አበበ ልጆች ገዥዎቹ ከሚያቀርቡላቸው  ማባበያ ይልቅ ጉልበታቸውን ተማምነው ይኖራሉ። በፍቃዱ አበበ እንደ አባቱ አሳ እያሰገረ ልጁን ያሳድግ ነበር። እናትና አባቱን ይደጉማል። እንግዳ አበበ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ብሎኬት ያመርታል። አየለች አበበ ታስተምራለች። ታናሹ ባንተወሰን አበበ ደግሞ ከትምህርት ውጭ ባለው ጊዜ ያገኘውን ስራ ሰርቶ ደካማ ቤተሰቦቹን ያግዛል። በስብሰባ ከሚገኝ አበልና ኢህአዴግ ከሚሰጣቸው ተስፋ ይልቅ ጉልበታቸውንና የራሳቸውን እውነት ያመኑት የአበበ አስፋው ቤተሰብ አባላት ጥቅምህን አልፈልግም ያሉት ኢህአዴግ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው። በቀበሌው ውስጥ ጥብቅ ክትትል ይደረግባቸዋል። ከ2006 ዓም በኋላ ደግሞ የፀረ ሽብር አዋጁ ሰለባ ሆኑ።  የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የታወጀው ለእነሱ ቤተሰብ እስኪመስል ድረስ!

አቶ አበበ አስፋው

በፍቃዱ አበበ በአርባ ምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ነው። በዛች የተጠላች ቀበሌ፣ ከኢህአዴግ የማይቀርቡት፣ እውነትና ጉልበታቸውን አምነው የሚኖሩት የአቶ አበበ ቤተሰብ ውስጥ በከተማው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆነው በፍቃዱና ቤተሰቡ ላይ ያለውን ክትትልና ጥላቻ የባሰ አድርጎታል።

በድል ፋና ቀበሌ የተቃዋሚ ፓርቲ ቢሮዎች ሲከፈቱ የቀበሌዋ ነዋሪዎችም በጅምላ የጥቃት ሰለባ ሆኑ። ከእስር እና ማስፈራሪያ ባሻገር  ተደራጅተው የሚሰሩባቸውን መሳርያዎች፣ ቦታና ፕሮጀክቶች ተቀምተዋል። ለአብነት ያህል የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆነው በፈቃዱ ታናሽ ወንድም እንግዳ አበበ ከጓደኞቹ ጋር ብሎኬት የሚሰራበት መሳርያ ተነጥቆ ገዥዎቹን ለሚደግፉት ወጣቶች ተሰጥቷል። ብሎኬት እያመረቱ ቤተሰብ ሲያስተዳድሩ የነበሩት የቀበሌው ወጣቶች ስራ አጥ ሆነው ለችግር ተጋልጠዋል። ወጣቶቹ ይህን ስራ ከተነጠቁ በኋላ አንዳንዶቹ ሀገር ጥለው ተሰደዋል። እንግዳ አበበ ከሚያዝያ 13/2006ዓም ጀምሮ ደብዛው ጠፍቷል። የልጃቸው መጥፋት ያሳሰባቸው እነ አቶ አበበ   እንግዳ ኤርትራ እንደገባ  ያወቁት ዘግይተው ነው።

እንግዳ ኤርትራ መግባቱ ሲሰማ የከተማው ካድሬዎች የአቶ አበበን ቤተሰብ ደብዛ የሚያጠፉበት ተጨማሪ ሰበብ አገኙ።  እንግዳ አበበ ደካማ እናትና አባቱን ጥሎ ከጠፋ 4ወር ሳይሞላ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሆነው ታላቅ ወንድሙ መጥለፊያ ሰበብ ተበጀለት። አንድ ወር በላይ አርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አስረው ከገዥዎቹ ጎን እንደማይቆም፣ ተቃውሞውን እንደማይተው ሲያውቁ ወደ ማዕከላዊ ላኩት። ማዕከላዊ የግንቦት 7 አባል ነኝ ብሎ በግድ እንዲያምን ብዙ በደል ደረሰበት።  ይህ አልሆን ሲል አርባ ምንጭ ውስጥ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና ጓደኛው በሀሰት እንዲመሰክርበት ተደረገ። ተደብድቦ በግድ የመሰከረው የበፍቃዱ ጓደኛ በሀሰት መመስከሩ እንደ ውለታ ተቆጥሮለት ከእስር ሲፈታ በጓደኛው ላይ በሀሰት በመመስከሩ ባደረበት ፀፀት አርባ ምንጭ መቀመጥ አልቻለም። በሀሰት መስክር ተብሎ በደረሰበት ድብደባ፣ በጓደኛው ላይ በግድ በሀሰት በሰጠው ምስክርነት ተገፍቶ እሱም ወደ ኤርትራ አቀና።

አርባምንጭ ከተማ ውስጥ በካድሬዎች በጠላትነት የተፈረጁት ወጣቶች ወደ ኤርትራ ማቅናታቸው ቀበሌዋ፣ በተለይም የአቶ አበበ ቤተሰብ ላይ ቁጥጥሩ ጠብቋል።  ወንጀል የሚባል ሲያጡባቸውም  የሀሰት ምስክርና የሀሰት ማስረጃ እያቀረቡ ከመወንጀል ወደኋላ አላሉም።  በፈቃዱ ከታሰረ አመት ሳይሞላው፣ ግንቦት 14/2007 ዓም የ70 አመቱ አቶ አበበ አስፋው ግንቦት 16 የሚካሄደውን ምርጫ ሊያደናቅፉ ነው ተብለው ቤታቸው ተበረበረ። የጦር መሳርያ ባይገኝባቸውም ካድሬዎቹ ተገኝቶባቸዋል ብለው በትዕዛዝ  አንድ አመት ከስድስት ወር አስፈርዱባቸው።  በኋላ ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት የአይን እማኝ የሆኑ የከተማው ነዋሪዎች የአቶ አበበ ቤት ውስጥ ምንም አይነት መሳርያ እንዳልተገኘ መስክረው በይግባኝ ሊፈቱ ችለዋል። አቶ አበበ ቤት ውስጥ መሳርያ እንዳልተገኘ ካድሬዎች ታዛቢ ያደረጓቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በመሰከሩት መሰረት አቶ አበበ ነፃ የሆኑበትን ክስ አሁን ለልጃቸው ለአየለች አበበ ተሰጥቷል።

አየለች አበበ ካድሬዎች “የትም አንጥለውም!” ብለው ከአባቷ ለእሷ በሀሰት ከሰጧት  ክስ በተጨማሪ የሽብር ክስ ቀርቦባት ቃሊቲ ትገኛለች። በአየለች ላይ የመሰከረችው አርባምንጭ ውስጥ የምትኖር ካድሬ ነች። ምስክሯ አየለች አበበ ማታ ማታ ለወንድሟ እንግዳ አበበ እየደወለች በርታ እንደምትለው ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች። አንድ ቀን  ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ጨለማ ውስጥ ሆና ደውላ ስታበረታታው ሰምቻለሁ አለች። በጨለማ እንዴት አየሻት ስትባል የአየለችን ድምፅ አውቀዋለሁ አለች። አራት ሆነው አየለችን ሲከታተሏት እንደነበር የገለፀች ካድሬ አብረውሽ የነበሩትን ሶስት ሰዎች ስም ጥቀሽ ስትባል አላስታውስም ነበር ያለች።  ከአየለች ቤተሰብ ጠይቄ እንደተረዳሁት መስካሪዋና አየለች የተለያየ ሰፈር ነው የሚኖሩት። ሆኖም ይች ካድሬ የአየለችና የእሷን ቤት የሚለየው ግድግዳ እንደሆነ፣ ማታ ማታ ወደ ኤርትራ ደውላ ከወንድሟ ጋር ስታወራ እንደምትሰማት ነው የመሰከረችው።

አየለች አበበ በታሰረችበት ወቅት የ63 አመት ደካማ እናቷም አብረው ታስረው ነበር። በወቅቱ እየተፈለገ የነበረው የአቶ አበበ የመጨረሻው  ልጅ ባንተ ወሰን አበበ ባለፈው ክረምት ለእስር ተዳርጓል። ትናንት ህዳር 6/2010 ዓም ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ተብሏል። ባንተ ወሰን አበበ ትናንት ለፍርድ ቤት እንዳስረዳው እሱ ቃል ባይሰጥም የሌላ ግለሰብ ቃል ከመዝገቡ ጋር ተያይዞበት የሌላ ሰው መሆኑ በመረጋገጡ ተነስቷል። ጥፋተኛ ከመባል አላዳነውም እንጅ።  ከባንተ ወሰን ጋር ጠብ የነበረው ግለሰብ በምስክርነት ሲቀርብ ለፍርድ ቤት ጠበኞች መሆናቸውን ቢገልፅም ፍርድ ቤት ባንተወሰን ያቀረበውን ማስረጃ ወደ ጎን ብሎ እንዳስመሰከረበት ጥፋተኛ ላለው ችሎት አስታውሷል።

በአሁኑ ወቅት በፍቃዱ አበበ 7 አመት ተፈርዶበት ዝዋይ ይገኛል።አየለች አበበና ባንተወሰን አበበ በዚህ ወር ፍርድ ቤት ቀርበው  በተከሰሱበት የ”ሽብር ክስ” የሚጠራባቸውን ቁጥር እየተጠባበቁ ነው። ኤርትራ የነበረው እንግዳ አበበ ሚያዝያ 28/2008 ዓም አርባ ምንጭ አካባቢ በግንቦት7 እና በመንግስት የፀጥታ ሀይል መካከል ተደረገ በተባለ ውጊያ መሰዋቱን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተሰራ ዶክመንተሪና ዜና ተገልፆአል። በፍቃዱ አበበና አየለች አበበ በመታሰራቸው ከደካማ እናትና አባታቸው በተጨማሪ ልጆቻቸውም ለችግር ተጋልጠዋል። የአየለች አበበ ልጅ አጋዥ ከሌላቸው አበበ አስፋውና አልማዝ ካሳሁን ጋር ይኖራል። የባንተወሰን ጓደኛ ልጇን ለማሳደግ ስራ ፈልጋ ስትገባ የተፈረጀው ቤተሰብ አባል ነችና ወዲያውኑ ያባሯታል።

አቶ አበበ አስፋው 73ኛ አመታቸው ይዘዋል። እንደድሮው ወደ ሀይቁ ሄደው ለማስራት ጉልበታቸው ደክሟል። የሚጦሯቸው ልጆቻቸው የሉም።  አልፎ አልፎ የልጆቻቸውን የፍርድ ቤት ውሎ ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። አየለችን ለማየት ቃሊቲ፣ ባንተወሰንን ለመጠየቅ ቂሊንጦ፣ እንዲሁም ፍርደኛውን በፈቃዱን ለመጎብኘት ወደ ዝዋይ ይከላተማሉ። ሲታመሙ፣ ለትራንስፖርት ሲያጡ እና ሲደክማቸው   ልጆቻቸው ሳያዩ የሚሰነብቱበት ጊዜ ብዙ እንደሆነ አጫውተውኛል። ክልትሙና ችግር የሚፈራረቅባቸው አቶ አበበ አይናቸው ደክሟል። ከባለፈው ክረምት ወዲህ ጤናቸውም እየታወከ እንደሆነ ገልፀውልኛል። ከእሳቸው በበሳ የ65 አመቷ ባለቤታቸው አንድ አይናቸው አጥተዋል። ቀሪው አይናቸውም ከመዳከሙ በተጨማሪ የአልጋ ቁራኛ ከሆኑ ሰነባብተዋል።

የፀረ ሽብር አዋጁ እንደ መግዢያ፣ የስልጣን ማራዘሚያ……የገዥዎች ሕግ ዴሞክራሲ ሊያሰፍኑ የሚችሉ ተቋማትና ሂደቶችን በመደፈቅ የሀገርን ህልውና እንደሚፈታተን ብዙዎች ጩኸታቸውን አሰምተዋል።  የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንደሚያፍን ይህም ሀገርን ለባሰ አደጋ፣ ህዝብን ለስቃይ እንደሚዳርግ ብዙ ምክሮች ተሰጥተው ነበር።  ገዥዎች  በሕግ  ሰበብ ተቋማትን አፍርሰው፣ ዜጎችን አሳራቸውን አሳይተው በስልጣን መክረም ነው የሚፈልጉትና ምክሩን አላዳመጡም።

በአቶ አበበ ቤተሰብ ላይ የተፈፀመው በበርካታ ቤተሰቦች ላይ ደርሷል። በእነ አቶ አበበ ቤተሰብ ላይ የደረሰው መከራ እንደሚያሳየው የፀረ ሽብር አዋጁ የታወጀው የሀገር መሰረት በሆኑት መሰረታዊ ተቋማት  ላይ ነው። ይህ አዋጅ ተቃዋሚ ፓርቲና ጋዜጣን ከማዘጋት በላይ ቤተሰብ እያፈረሰ ነው። ዋነኛ የሀገር መሰረት የሆነው!

3 thoughts on “​በፀረ ሽብር አዋጁ የተበተነ ቤተሰብ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡