​አቶ ማሙሸት አማረ  ዐቃቤ ሕግ  ባቀረበባቸው  የሰነድ ማስረጃ ላይ ያቀረቡት ትችት 

“በደህንነት ሪፖርቱ ተዘጋጀ የተባለው፣ ተከሳሽ ሲጠቀምባቸው ነበሩ የተባሉ ሰባት የሚደርሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሮች ተጠልፈዋል በሚል ነው፤ ነገር ግን እነዚህ በማስረጃነት ቀረቡ የተባሉት ስልክ ቁጥሮች በእርግጥም በተከሳሽ ስም ስለመመዝገባቸው ከኢትዩ-ቴሌኮም ጋር የተደረገ የደንበኝነት ውል ማስረጃ አልቀረበም፣ የማን እንደሆኑም አይታወቅም፣ ይበልጡኑ ደግሞ፣ የደህንነቱ ሪፖርቱ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ የጸዳ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት እንዲቻል፣ ተደረገ የተባለው የተጠለፈው የስልክ ልውውጥ አብሮ ቀርቦ ተከራካሪ ወገኖች እንድንመለከተው ካለመደረጉም በላይ ፍ/ቤቱ እንኳን እንዲያዳምጠው ሳይደረግ በደፈናው የቀረበ ነው፡፡” 
“ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃውን ከተከሳሽ የስልክ ቁጥሮች አሰባሰብኩት ብሎ ከማቅረብ ባለፈ ይህ ማስረጃ ሕጉ ባስቀመጠው ግዴታ መሠረት በፍርድ ቤት ፈቃድ መሠረት ስለመሰባሰቡ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃ ሆነ ገለጻ የለም፡፡ ዐ/ሕግም ሆነ የደህንነት ተቋሙ፣ ስራቸውን ሲሰሩ፣ አገሪቱ ያወጣችውን ሕግ መሰረት አድርገው ስለማከናወናቸው ማስረጃ በማቅረብ ሊያረጋግጡ ይገባል እንጂ እርሱን ተከትለው ይሰራሉ ተብሎ ያለማስረጃ በፍ/ቤት ባለክርክር ላይ ግምት ሊወሰድበት አይችልም፡፡ የአገራችን ሕገ መንግስት በአንቀጽ 26 የዜጎች ግላዊ ህይወት የተጠበቀ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ግን ሊደፈር የሚችለው በአስገዳጅ ሁኔታ ሕግን ተከትሎ ብቻ እንደሆነ ንኡስ ቁጥር 3 አስቀምጧል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ያያያዘው ማስረጃ፣ የተከሳሽን ሕገ መንግስታዊ መብቱ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አስገዳጅ ድንጋጌ ተከትሎ በፍ/ቤት ፈቃድ ስላልተሰበሰበ፣ ሕገወጥ ማስረጃ ነው ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን እናመለክታለን፡፡”

(ሙሉውን የሰነድ ማስረጃ ትችት ከስር ይመልከቱ)

ቀን፡- 11/03/2010 ዓ.ም

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት

አዲስ  አበባ

  •  ከሳሽ ———-የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ  ሕግ 
  • ተከሳሽ ———-  አቶ ማሙሸት አማረ ድልነሴ

ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ በቀን 25/02/2009 ዓ/ም በቁጥር ፌ/ጠ/ዐ/ህግ/የተ/ድ/ተ/02/10 በተጻፈ ባቀረበው ክስ ላይ በቀረቡ ሰነድ ማስረጃዎች ላይ ከተከሳሽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 146 መሠረት የቀረበ ትችት፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ተራ ቁጥር 1ኛ ላይ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በቁጥር ደመ 42/119/09 በሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በተመለከተ፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃው ተራ ቁጥር 1 ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥር፡- ደመ 42/119/09 በሐምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በማያያዝ ተከሳሽ ህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንደ ሽፋን በመጠቀም እራሱን አርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር የነበረውን እንቅስቀሴ ያሳያል ሲል አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 14(1) ጠቅሶ በተከሳሽ ላይ ከስልክ ቁጥራቸው የተሰበሰበ ገጽ- 47 ማስረጃ አያይዟል፡፡ 

በቅድሚያ አንድ ማስረጃ ከላይ ዐ/ሕግ በጠቀሰው ሕግ አንቀጽ 14(1) ስር እንዲቀርብ ማስረጃው ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ መሰባሰብ እንዳለበት ሕጉ ግዴታን እንደሚከተለው በማለት ጥሏል፣” የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ…..” ማስረጃዎች ማሰባሰብ እንደሚችል ገልጿል፡፡ 

ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃውን ከተከሳሽ የስልክ ቁጥሮች አሰባሰብኩት ብሎ ከማቅረብ ባለፈ ይህ ማስረጃ ሕጉ ባስቀመጠው ግዴታ መሠረት በፍርድ ቤት ፈቃድ መሠረት ስለመሰባሰቡ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃ ሆነ ገለጻ የለም፡፡ ዐ/ሕግም ሆነ የደህንነት ተቋሙ፣ ስራቸውን ሲሰሩ፣ አገሪቱ ያወጣችውን ሕግ መሰረት አድርገው ስለማከናወናቸው ማስረጃ በማቅረብ ሊያረጋግጡ ይገባል እንጂ እርሱን ተከትለው ይሰራሉ ተብሎ ያለማስረጃ በፍ/ቤት ባለክርክር ላይ ግምት ሊወሰድበት አይችልም፡፡ የአገራችን ሕገ መንግስት በአንቀጽ 26 የዜጎች ግላዊ ህይወት የተጠበቀ መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ግን ሊደፈር የሚችለው በአስገዳጅ ሁኔታ ሕግን ተከትሎ ብቻ እንደሆነ ንኡስ ቁጥር 3 አስቀምጧል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ያያያዘው ማስረጃ፣ የተከሳሽን ሕገ መንግስታዊ መብቱ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን አስገዳጅ ድንጋጌ ተከትሎ በፍ/ቤት ፈቃድ ስላልተሰበሰበ፣ ሕገወጥ ማስረጃ ነው ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን እናመለክታለን፡፡

ፍ/ቤቱ ይሄን ከላይ ያቀረብነውን ክርክር አያልፈውም እንጂ የሚያልፍበት በቂና ሕጋዊ ምክንያት ካለ ደግሞ በአማራጭ የሚከተለውን ክርክር እናቀርባለን፡፡ የደህንነት ሪፖርቱ ተዘጋጀ የተባለው፣ ተከሳሽ ሲጠቀምባቸው ነበሩ የተባሉ ሰባት የሚደርሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሮች ተጠልፈዋል በሚል ነው፤ ነገር ግን እነዚህ በማስረጃነት ቀረቡ የተባሉት ስልክ ቁጥሮች በእርግጥም በተከሳሽ ስም ስለመመዝገባቸው ከኢትዩ-ቴሌኮም ጋር የተደረገ የደንበኝነት ውል ማስረጃ አልቀረበም፣ የማን እንደሆኑም አይታወቅም፣ ይበልጡኑ ደግሞ፣ የደህንነቱ ሪፖርቱ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ የጸዳ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ መስጠት እንዲቻል፣ ተደረገ የተባለው የተጠለፈው የስልክ ልውውጥ አብሮ ቀርቦ ተከራካሪ ወገኖች እንድንመለከተው ካለመደረጉም በላይ ፍ/ቤቱ እንኳን እንዲያዳምጠው ሳይደረግ በደፈናው የቀረበ ነው፡፡ 

የፀረ ሽብርተኝነት አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 14(1)(ሀ) የሚለው ” በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የስልክ… ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል ይችላል” ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ መሠረትም፣ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከተከሳሽ የስልክ ግንኙነቶች ላይ ተከታትሎ የጠለፋቸውን ልውውጦች፣ ከሪፖርቱ ጎን ለጎንም ቢሆን አላቀረበም፡፡ ይህን ሕግ መሠረት አድርጎ የሰበሰበውን የስልክ ግንኙነት ለፍ/ቤቱ ካላቀረበ ደግሞ ተከሳሽ እነዚህን ስልክ ቁጥሮች ተጠቅሞ የሽብር እንቅስቃሴ ማድረግ አለማድረጉን በእርግጠኝነት ለመደምደም የማያስችል ስለሆነ ማስረጃው ውድቅ ሊደረግ ይገባዋል፡፡

ነገር ግን ፍ/ቤቱ  ብይን ከመስጠቱ በፊት እነዚህን በደህንነት መስሪያ ቤቱ የተጠለፉ የስልክ ልውውጦችን አስቀርቦ መመርመሩ ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት እና እውነት ላይ ለመድረስ ወሳኝ በመሆኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ወይም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በትእዛዝ ቀርበው ሊመረመሩ ይገባልናል ስንል እናመለክታለን፡፡

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃ ዝርዝር ተራ ቁጥር 2ኛ ላይ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቋም በቁጥር ደመ 42/229/09 በሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በተመለከተ፤

ዐቃቤ ሕግ በሰነድ ማስረጃው ተራ ቁጥር 2 ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቁጥር፡- ደመ 42/229/09 በሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ቀረበ ያለውን የቴክኒክ ማስረጃ በማያያዝ ተከሳሽ ህጋዊ ፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እንደ ሽፋን በመጠቀም እራሱን አርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ ከሚጠራው የሽብር ቡድን ጋር የነበረውን እንቅስቀሴ ያሳያል ሲል አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 23(1) ጠቅሶ በተከሳሽ ላይ የተሰበሰበ ገጽ- 11 ማስረጃ አያይዟል፡፡ 

ይህ ማስረጃ ሲመዘን በአዋጁ አንቀጽ 23(1) መሠረት ተቀባይነት አለው ከሚባል ባሻገር፣ በምን አይነት ሁኔታ እና እንዴት እንደተገኜ የማይታወቅ፣ አንዳንድ ግዜም ተአማኒነቱ በእጅጉ አጠራጣሪ ስለሆነ ፍ/ቤቱ በተከሳሽ ላይ ሊያስረዳ ይችላል ብሎ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ማስረጃ አይደለም፡፡ ማስረጃው በየአንቀጾቹ መጨረሻ ላይ በመረጃ ተረጋግጧል እያለ ድምዳሜ ለመስጠት ቢሞክርም በምን አይነት መረጃ ተረጋገጠ፣ መረጃውስ ትክክል ነው ወይስ አይደለም? ብሎ ተከሳሽ እራሱን እንዲከላከል የማያስችል በመሆኑ የደህንነት መስሪያ ቤቱ የፈጠራ ማስረጃ ከመሆን ባለፈ አንድ የተከሰሰ ሰው ላይ ክብደት ተሰጥቶት ሊቀርብ የሚችል ማስረጃ አለመሆኑን ፍ/ቤቱ በማስረጃ ምዘና ወቅት የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት አያይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ የሚከተሉት ነጥቦች አለመሟላታቸው ማስረጃውን ጎዶሎ/ደካማ(weak probative value) በማድረግ ክሱን እንዳላስረዳ የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ሽመልስ ለገሰ በተባለ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ተመልምሏል ቢልም፣ የትና እንዴት? እንደተመለመለ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነቱን፣ አመራርነቱን እንደሽፋን ተጠቅሟል፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ተልዕኮ ተሰጠው፣ እርሱም ስምምነት አድርጓል ቢልም፣ የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ፣ ተልዕኮ የተቀበለው በምን እንደሆነ፣ ስምምነቱን በምን? እንዳስታወቀ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በሚያዝያ/2007 ዓ.ም ለሽብር ቡድኑ አባላትን ከአዲስ አበባ መልምሎ ልኳል ቢልም፣ እነማንን፣ ብዛታቸው ስንት እንደሆነ፣ እንዴት? እንደላካቸው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ታህሳስ/2008 ዓ.ም ከተለያዩ አካባቢዎች የመለመላቸውን 11 የሽብር ቡድን አባላትን ቦሌ ክፍለ ከተማ ሰብስቦ አንዱን ብሄር በሌላኛው ብሄር እንዲነሳሳ ተልዕኮ ሰጥቷል ቢልም፣ ከየት አካባቢ እንደተመለመሉ፣ አነማንን መመልመሉን፣ የተሰበሰቡት ቦሌ ክ/ከተማ የት ቦታ እንደሆነ እና የትኛውን ብሄር በየትኛው ብሄር ላይ? እንዳነሳሳ አይገልጽም፣

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በየካቲት/2008 ዓ.ም አዲስ አበባ ያደራጃቸውን 12 አባላት ሰበሰበ፣ በየቀጠና አከፋፍሎ ልኳል ቢልም፣ እነማንን፣ የት እንዳደራጀ፣ ቀጠናዎቹ ስንትና እነማን እንደሆኑ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በግንቦት/2008 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ቤዝ መረጠ፣ ዘጠኝ አባላትን ለወታደራዊ ስልጠና ላከ ቢልም፣ ሰሜን ሸዋ የት ቦታ፣ ዘጠኝ አባላቱ እነማን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደላካቸው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በግንቦት/2008 ዓ.ም ውጪ ከሚገኙ አመራሮች ደጋፊዎች 80ሺ ብር ተላከለት፣ መሳሪያ ገዛ፣ አውግቼው በተባለ ሰው ልኮ አስታጠቀ ቢልም፣ አመራሮቹ ደጋፊዎቹ እነማን እንደሆኑና የት እንደሚገኙ፣ ገንዘቡ በማንና እንዴት ተልኮለት እጁ እንደገባ፣ መሳሪያ የታጠቁት እነማን እንደሆኑ፣ አውግቸው የተባለው ሙሉ ስሙን አይግልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በሰኔ/2008 ዓ.ም ዘመነ ምህረት፣ ለገሰ ወልደሃና ከተባሉ የሽብር ቡድኑ አመራር/አባል ጋር አዲስ አበባ ተሰብስቦ ተልዕኮ ሰጥቷል ቢልም፣ አዲስ አበባ የት እንደተሰበሰበ እና ጊዜውን? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በህዳር/2009 ዓ.ም የመለመላቸውን፣ ያደራጃቸውን አባሎች/አመራሮች ጠርቶ ተልዕኮ ሰጠ ቢልም፣ እነማን እንደሚባሉ፣ የት አካባቢ እንደጠራቸው፣ በምን ጥሪ እንዳደረገላቸው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በተለያዩ ስልክ ቁጥሮች በመጠቀም ከውጭ 100 ሺ ብር በህዳር/2009 ተላከለት፣ በ50 ሺ ብር ጥይት ገዛ ቢልም፣ አመራር/አባላት የተባሉት እነማን እንደሆኑ፣ የተላከለትን ገንዘብ በምን አይነት ሁኔታ እንዲደርስ እንዳደረገ፣ ከየት አገርና በምን አይነት መንገድ እንደተላከለት፣  ገንዘቡን ለማን ሰሜን ሸዋ ውስጥ እንደሰጡ፣ ታጣቂዎቼ እነማን እንደሆኑ፣ ገንዘብና ስንቅ የሰጠው ማን እንደሆነ አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በታህሳስ/2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባ የተመለመሉትን 6 ሰዎች በገዛኸኝ በኩል ላከ ቢልም፣ የተላኩት እነማን እንደሆኑ፣ የሄዱበት ቦታ ሰሜን ሸዋ የት እንደሆነ፣ በምን እንደላካቸው፣ ገዛኸኝ የተባለውን ሙሉ መጠሪያው አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በጥር/2009 ዓ.ም ውጭ ካሉ አመራሮች ስለአደረጃጀት መመሪያ፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አመጽ ጽሁፍ ተልኮለት በህቡ አወያይቷል ቢልም፣ ከየት አገር እንደተላኩለት፣ አመራሮቹ ማን እንደሚባሉ፣ በምን አይነት መልኩ እንደተላከለት፣ የት እንዳወያየ፣ ማንን እንዳወያየ? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በታህሳስ/2009 ዓ.ም ለመሳሪያ መንዣና ትጥቅ ብር 80ሺ ብር ተልኮለት ከስልጠና ለተመለሱት አስታጠቀ ቢልም፣ እነማን እንዳስታጠቀ፣ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የገለጸው ለማን እንደሆነ፣ ከየት አገር ገንዘብ እንደተላከለት፣ በምን አይነት መንገድ ግንኙነት እንዳደረገ፣ ገንዘቡ በምን አይነት መንገድ እንደተላከለት፣ ጥይት የትና መቼ እንደገዛ? አይገልጽም፤

ዐቃቤ ሕግ በክስ ማስረጃነት አይይዞ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ላይ ተከሳሽ በመጋቢት/2009 ዓ.ም ውጭ አገር ሄዶ የሽብር ተግባር እንዲመራ ተልዕኮ ተሰጥቶት ኬንያ ሊሄድ ሞያሌ ላይ ተያዘ ቢልም፣ ተልዕኮ ማንና እንዴት እንደተሰጠው አይገልጽም፤ 

ዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃ አድርጎ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተከሳሽ ሙሉቀን ተስፋው እና ሸንቁጥ አየለ ከተባሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ያለ ቢሆንም መቼ፣ በምን አይነት መንገድ እና ለምን አላማ እንደተገናኘ አያስረዳም፡፡ 

ስለሆነም ይህ ሪፖርት ክሱን አስረጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር አለመገናኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋው እና አቶ ሸንቁጥ አየለ የተባሉት ግለሰቦች የአርበኞች ግንቦት ሰባት የተባለው ድርጅት አባል ካለመሆናቸውም ባሻገር የዚህን ድርጅት አመለካከት የማያራምዱ እና በአብዛኛው “የአምሓራ ብሔርተኝነት” አራማጆች መሆናቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በራሳቸው ገጾች ላይ የሚገልጹት አቋም(በተለጠይም አቶ ሙሉቀን ተስፋው “የጥፋት ዘመን” እና “አገር አልባ ባላ’ገር” የሚለውን አሳትመው በገበያ ላይ በመሸጥ የሚገኘውን የመጽሐፍ ስራቸውን ሊመለከተው ይችላል) መሆኑን መገንዘብ መቻሉ፣ የደህንነት ተቋሙ ማስረጃዎቹን ሰበሰብኩ ከማለት ባለፈ ስራውን ባግባቡ እንዳልሰራ ፍንትው አድርጎ  ለፍ/ቤቱም የሚያስረዳ ነው፡፡

በደህንነት ሪፖርቱ ላይ ተከሳሽ ቅንነት፣ አምባሰል፣ ራስ ዳሽን፣ ሀብታሙ፣ አለምፀሀይ፣ ታምርነሽ እና ከሌሎች የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት እና አመራሮች ጋር ግንኙነት ፈጥሯል ያለ ቢሆንም በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ግለሰቦች በእርግጥ በህይወት ያሉ ግለሰቦች ናቸው ወይ? ካሉስ የት ነው ያሉት? መቼስ ነው ግንኙነት የፈጠሩት? ግባቸውስ ምንድን ነው? የሚለው ባልታወቀበት ሁኔታ በደህንነት ሪፖርት ላይ ስለተጻፈ ብቻ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡

ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የደህንነት ሪፖርት ማስረጃ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ስለመሆኑ፤

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በዋናነት ተከሳሽ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል እና አመራር በመሆኑ የተለያዩ ተልዕኮዎችን ተቀብሏል በማለት ክስ ያቀረበ ቢሆንም የሰነድ ማስረጃው በማድረግ ባቀረበው የደህንነት ሪፖርት ገጽ 16 እና 17 ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባት አማራን የሚፈልገው ጉልበቱን ብቻ እንጂ ከዛ ባለፈ ድርጅቱ ለአማራ ህዝብ እንደማይጠቅም ተከሳሽ ገልጿል በማለት ያስቀምጣል፡፡ ይህም፣ ተከሳሽ የአምሓራን ጉልበት እንጂ ጥቅም በዘላቂነት አያስጠብቅም የሚሉት የሽብር ድርጅት አባል እንዳልሆኑ እና ሊሆኑም እንደማይችል ከማረጋገጥ አልፎ አቃቤ ሕግ ያቀረብኩትን ክስ ያስረዳልኛል በማለት ያቀረበው ሪፖርት እርስ በእርሱ የሚጣረስ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ስለሆነም ፍ/ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ላይ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ከላይ ባነሳነው ምክንያት እንደ ክሱ ያላስረዳ በመሆኑ የቀረበብንን ክስ ውድቅ በማድረግ መከላከል ሳያስፈልገን ከክሱ እንዲያሰናብተን ስንል በትህትና እናመለክታለን፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ