“በተፈናቃዮች ላይ ጉዳት ያደረሱት የፀጥታ ሃይሎች መሆናቸው ታውቋል” ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ 

  • በክልል አጥር ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆን አካል አይኖርም
  • ለሚዲያ ወይም ለሰፊው ህዝብ ለማቅረብ የሚያስቸግሩ ጉዳቶች ደርሰዋል
  • የሥርአቱ ጠበቆች እየመሰሉ ሥርዓቱን የሚያፈርስ ሥራ የሚሰሩ አካላት አሉ
  • በመሪው ፓርቲ በኩል የጤንነት ችግር የለም፤ በጣም ጤናማ ነው


         

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ከሰሞኑ በተለይ የኦሮሚያ- ሶማሌ አዋሳኝ ግጭት ያደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከአዲስ አድማስና ከሌሎች መገናኛ ብዙኃን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም
ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ሁሉንም እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡

በአሁን ወቅት በኦሮሚያና በኢትዮ-ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ግጭቱ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

በኦሮሚያና በኢትዮ-ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ቆሟል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በማይደርስባቸው አንዳንድ ራቅ ያሉ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር ግጭቱና መፈናቀሉ መቆሙን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በግጭቱ አካባቢዎች ማንኛውም ታጣቂ ኃይል እንዳይንቀሳቀስ፣ የግጭት ነፃ ቀጠናዎች /buffer zones/ ተከልለው ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በወጪ-ገቢ ንግድ መተላለፊያ መስመር ላይ አሁንም ቢሆን ችግር እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የንግድ ሚኒስቴርና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሁለቱ ክልሎች አካላት እየተነጋገሩ ቢሆንም ከመሃል አገር ወደ ኢትዮ-ሶማሌ፣ አሊያም ከኢትዮ-ሶማሌ ወደ መሃል አገር በሚገቡ ጭነቶች ላይ የሚደርስ ጫና አሁንም ቀጥሏል፡፡ 

በተለይም እንደ ጫት ያሉት የወጪ ምርቶች በማምረትና በመሸጥ በሚተዳደሩ አርሶ አደሮችና ላኪዎች ላይ ካሳደረው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተጨማሪ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና በአፋጣኝ መቆም የሚገባው በመሆኑ፣ የፌዴራሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት፣ ከአሁን በኋላ ችግሩ እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን በዚህ በኩል እንቅፋት በሚፈጥሩ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡ 

ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀረበው ሪፖርት መሰረት፣ አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋሉ ሥራ የተጀመረ ሲሆን በተለይም በኦሮሚያ ክልል አወዳይ አካባቢ ከባድ ሰብዓዊ ጉዳት በማድረስ ወይም ግድያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች፣ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል። በተመሳሳይ በኢትዮ- ሶማሌ ክልል፣ በወገኖቻችን ላይ ከባድ ሰብዓዊ ጉዳት በማድረስ ወይም ግድያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በክልሉ በኩል የተወሰደው እርምጃ አጥጋቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድ አሁንም የኢትዮ-ሱማሌ ክልል አመራሮች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የፌዴራል ፖሊስ አሳስቧል፡፡ 

በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉበትን ችግር ለመፍታት መንግስት ምን እየሰራ ነው?

በኦሮሚያና በኢትዮ-ሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም፣ ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሰው የአገር አቀፉ ግብረ ሃይል ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን፣ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን ጎብኝቶ ተመልሷል፡፡ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጡ ልዑካን ቡድን፣ ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖቻችን የሚገኙባቸውን በድሬድዋ፣ በሃረር ከተማ በአማሬሳና በባቢሌ የሚገኙ የመጠለያ ካምፖችን በመጎብኘት፣ ተፈናቃዮችን ከማነጋገሩ በተጨማሪ የደረሰውን ጉዳትና ለተፈናቃዮቹ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ ገምግሟል፡፡ ተፈናቃዮች ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በጥሞና በማዳመጥም፣ ችግሮቻቸው በጊዜያዊነት የሚፈታበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የፌዴራሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ለተጎጂዎች ቃል ገብቶላቸዋል፡፡

ከተፈናቃዮች ጋር በተደረገው ውይይትም፣ ጉዳቱን ያደረሱባቸው የፀጥታ ኃይሎች እንጂ ህዝቦች እንዳልሆኑ፣ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በማድረግ በኩል የአገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ እገዛ ማድረጉን፣ በግጭቱ ወቅት የሁለቱንም ክልሎች ሕዝቦች፣ አንዱን ከሌላው ጥቃት በመከላከል መስዋዕትነት መክፈላቸውን፣ በተለይም ከምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ፣ የኢትዮ-ሱማሌዎች እንዳይፈናቀሉ የአካባቢው ሕዝብና አመራር ያደረገው ጥረት በአርአያነት ተጠቃሽ እንደሆነ፣ ከ30 ዓመት በላይ ከኖሩባቸው ቀዬዎች የተፈናቀሉ ወገኖቻችን፣ አሁንም ችግሩ ቶሎ ተፈትቶላቸው፣ ወደ ቀድሞ የመኖሪያ ሥፍራቸው የመመለስ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በተፈናቃዮቹ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ከፍተኛ መሆኑንም የልዑካን ቡድኑ ተጠቂዎችን በማነጋገርና በምልከታ መገንዘብ ችሏል፡፡ በተለይም አሁን ድረስ  ወላጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ህፃናትና ልጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ወላጆች መኖራቸውን፣ መደፈርን ጨምሮ ልዩ ልዩ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች መኖራቸውን፣ በነፍሰ ጡርነታቸው ጊዜ ላይ ሆነው ብዙ እንግልት የደረሰባቸውና በመጨረሻም በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ለመውለድ የተገደዱ፣ በድሬድዋና ሀረር ብቻ ከ100 በላይ አራሶች መኖራቸውን፣ ለጤና ችግር የተጋለጡና ከሁሉም በላይ በደረሰባቸው ከባድ ጥቃት የተነሳ የነገ ህይወታቸውን ጭምር በማሰብ፣ ለተስፋ መቁረጥና ለሌሎች ከባድ የስነ-ልቦና ጉዳቶች የተዳረጉ በርካታ ወገኖች እንዳሉ፣ ቤተሰቦቻቸው በመገደላቸው በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ የወደቁ፣ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ህፃናትና ወጣቶች መኖራቸውን ልዑካኑ ለማረጋገጥ ችለዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ወገኖች በሚፈልጉት ቦታ ተዘዋውረው በህይወት የመኖር፣ የመስራትና ሀብትና ንብረት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው መጣሳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ይህ ጉዳት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን የተገነዘበው የልዑካን ቡድን፣ የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን ለተፈናቃዮች የገለፀላቸው ከመሆኑም በላይ ለችግሩ መንስዔ የሆኑትን አካላት አጣርቶ፣ ለህግ እንደሚያቀርባቸው አረጋግጦላቸዋል፡፡ 

ለተፈናቃዮች በጊዜያዊነት እየተሰጠ ያለው እርዳታ ምን እንደሚመስልም የልዑካን ቡድኑ ገምግሟል፡፡ በዚህም ተፈናቃዮች አስፈላጊውን የዕለት ደራሽ እርዳታ፣ በፌዴራሉ የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን እንዲሁም በሁለቱ ክልሎች በኩል እየቀረበላቸው መሆኑን ተመልክቷል፡፡ ጉብኝቱንም ተከትሎ በመጠለያዎቹ ውስጥ ሆነው ለወለዱ አራሶች፣ ፍራሾች እንዲቀርቡላቸውና ለህፃናቱም አልሚ ምግቦች እንዲሰጧቸው ማድረግ መጀመሩን፣ ከአደጋ መከላከያ ዝግጁነት ኮሚሽን ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት፣ 24 የህክምና ባለሙያዎችን በሰባት ቡድኖች በማሰማራትና ከክልል የጤና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት፣ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይዛመቱ እንዲሁም የመደፈር አደጋ ለደረሰባቸው፣ በመጠለያ ለወለዱ ሴቶችና ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን የመድኃኒትና ሕክምና አቅርቦት እንዲያገኙ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ህፃናት፣ በያሉባቸው የመጠለያ አካባቢዎች በጊዜያዊነት ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትና በዘለቄታው ወደ ቀያቸው ሲመለሱም ትምህርታቸውን የሚያካክሱበት ዕድል እንዲመቻችላቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ 
ተፈናቃዮችን በጊዜያዊነት የመደገፉ ስራው እንዳለ ሆኖ፣ በዘላቂነት ለማቋቋም በሚቻልበት ላይ ሁለቱ ክልሎች የሚያደርጉት ጥረት አሁንም የቀጠለ ሲሆን የፌዴራል መንግስቱ ያቋቋመው አገር አቀፍ ግብረ ሃይልም ከክልሎቹ ጋር በመተባበር፣ ተፈናቃዮቹን በዘለቄታው መልሶ ለማቋቋም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን በሁለቱ ህዝቦች መካከል እርቅና ሰላም የማስፈን ስራው ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ያለበት ሲሆን ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ የሚጠበቅባቸውን ትልቅ ኃላፊነት እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ 

በሁለቱ ክልሎች በተፈጠረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሰባሰበው ገንዘብ ለአንድ ወገን በተለይም ለኦሮሚያ ክልል ብቻ ነው የሚሉ መረጃዎች አሉና ይህ በራሱ ሌላ ችግር አያስከትልም? በሌላ በኩል፣ ጅግጅጋ ላይ “የኦሮሞ ብሄርን ትደግፋላችሁ” የተባሉ የአማራና ጉራጌ ተወላጆች ላይ ጫና እየተፈጠረባቸው መሆኑ እየተነገረ ነው —

መታወቅ ያለበት ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ለመደገፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሁለት በኩል ነው መታየት ያለበት፡፡ አንደኛው በተናጠል በየክልሎቹ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የባንክ ሂሳብ ከፍቶ ድጋፍ እያሰባሰበ ነው፤ በተመሳሳይ የኢትዮ- ሶማሌ ክልልም ተጎጂዎችን ለመርዳት የራሱን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት ደግሞ የራሱን የድጋፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት የባንክ ሂሳብ ከፍቶ ገንዘብ እየሰበሰበም ሆነ ለአንድ ወገን እየሰጠ አይደለም፡፡ አሁንም ብሄርን፣ ሃይማኖትንና አካባቢን እየለዩ በማናቸውም መልኩ ጥቃት ማድረግ፣ የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ከዚህ በፊት ከሚወሰደው እርምጃ በተለየ ሁኔታ እርምጃ እየተወሰደም ማስተካከያ ይደረጋል፡፡ በክልል አጥር ውስጥ ወንጀል ሰርቶ ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆን አካል አይኖርም፡፡ የፌደራል መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ 

ይህ ዓይነቱ ግጭት በድጋሚ እንደማይከሰት፣ አጥፊዎችም እንደሚቀጡ ተገልጾ ነበር፡፡ እስካሁን ምን እርምጃ ተወሰደ?

መንግስትም በተደጋጋሚ እንደገለፀውና በገሃድም እንደታየው፣ በእርግጥም ይህ የአሁኑ ግጭት የከፋ ግጭት ነው፡፡ ጋዜጠኞች ደግሞ ወረድ ብላችሁ ሁኔታውን ብታዩ፣ የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ከሚነገረውም በላይ የከፋ መሆኑን ትረዳላችሁ። ለሚዲያ ወይም ለሰፊው ህዝብ ለማቅረብ የሚያስቸግሩ ጉዳቶች ናቸው የደረሱት፡፡ ይሄ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ሲናገሩ የስርአቱ ጠበቆች እየመሰሉ በተግባር ግን ሥርዓቱን የሚያፈርስ ሥራ የሚሰሩ አካላት አሉ፡፡ በሚናገሩበት ጊዜ ለሀገር አንድነት እንደኖሩ፣ የሀገር አንድነት ጠበቃ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ፣ በተግባር ግን ለዜጎች ክብር የሌላቸው አካላት ተፈጥረዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የግል ጥቅምን መሰረት አድርጎ በህዝብ ስም መነገድ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ ይሄን መንግስት ጊዜ ወስዶ በማጣራት እርምጃ ይወስዳል፡፡ ይሄ በሁሉም አካባቢዎች ነው ያለው፡፡ የማጣራት ስራውም እየተሰራ ያለው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ 

የተወሰደ እርምጃ የታለ? ለተባለው፣ ምርመራና ማጣራት እየተደረገ ነው፡፡ ያ የምርመራ ውጤት፣ ጊዜውን ጠብቆ ለህዝብ ይገለፃል፡፡ አሁንም ቢሆን በቁጥጥር ስር የዋሉ አካላት አሉ፡፡ በአወዳይ ከተማ በግድያ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በተመሳሳይ በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ጉዳት ያደረሱ በቁጥጥር ስር መዋል አለባቸው። ለዚህም ፌደራል ፖሊስ ስራውን እየሰራ ነው የሚገኘው። የሚወሰደው እርምጃም በቂ ነው፤አልቋል ተብሎ አልተደመደመም፡፡ መንግስት እያጣራ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል፡፡ አሁን ትልቁ ትኩረት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋም ላይ ይሆናል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ስጋት ላይ መውደቃቸውን ይገልፃሉ፡፡ በመታወቂያ ብሄር እየተለየ ጥቃት ይደርሳል የሚል አቤቱታ ያቀርባሉ። መንግስት በዚህ ላይ ምን እየሰራ ነው? 

እውነት ነው፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን፣ ጥቃት ደርሶብናል ብለው ለትምህርት ሚኒስቴር አመልክተዋል። እንደተባለው መታወቂያ እየታየም ልዩነት ተደርጓል። ጥቃትም ደርሶባቸዋል፡፡ ይሄ መረጃ አለን፡፡ ይሄ ግን በተለይ አወዳይ ላይ ሰዎች ተገደሉ የሚል መረጃ ከወጣና ገፅታው የብሄር ግጭት ተደርጎ ከተወሰደ በኋላ በቁጣ መነሳሳት የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በገፍ የተፈናቀሉትም ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ግድያው መፈፀሙን ተከትሎ መረጃ ሲሰራጭ፣ ቅስቀሳ መደረጉ ነው ትልቁን ችግር ያመጣው። አሁን ግን የተቀመጠው አቅጣጫ፣ ይሄን ችግር በአጭሩ ፈትቶ፣ የኦሮሚያ ተማሪዎች ወደ ጅግጅጋ፣ የሶማሌ ተማሪዎች ወደ ኦሮሚያ እንዲሄዱ ካልተደረገ፣ ለወደፊት የማንወጣበት ችግር ውስጥ ስለሚከተን አደገኛ ነው ተብሎ በአፋጣኝ እንዲስተካከል ነው፡፡ 

የክረምት ተማሪዎች በጅግጅጋ የተባለው ደርሶባቸዋል፡፡ በብሄር ልዩነትም የታሰሩ አሉ፡፡ ይሄ ማናችንንም አይወክለንም በሚል በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች ክልሎች በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። ይህ አይነቱ አመለካከት ትርጉሙ ጥሩ አይደለም። የከፍተኛ የትምህርት ተቋም በብሄር፣ በሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ፣ ተማሪዎችን ማስተማር ግዴታው ነው፤ ካልሆነ መንግስት ያንን ዩኒቨርሲቲ የመዝጋት መብት አለው፡፡ የተማሪዎችን ስጋት እንጋራለን፤ ስለዚህ በቅድሚያ ችግሩን ለመፍታት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው የሚገኘው፡፡ ስጋቱ ስጋት ሆኖ አይቀጥልም። መንግስት ኃላፊነቱን ወስዶ ችግሩን መፍታት አለበት፤ ያንንም ያደርጋል፡፡ 

መንግስት “የታጠቁ አካላት” ሲል የሚገልፃቸውን ምን ያህል ለይቷል?

የታጠቁ አካላት የተባሉት በመንግስት ይታወቃሉ፤ ነገር ግን ማጣራቶች ተደርገው ይቀርባሉ፡፡ ያንን መጠበቅ አለብን፡፡ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች ቁጥርም ተጣርቶ ሲያበቃ የሚገለፅ ይሆናል፡፡ 

የአቶ አባዱላ ገመዳና የአቶ በረከት ስምኦን  ከስልጣን መልቀቅ በገዥው ፓርቲና በመንግስት  መዋቅር ውስጥ ችግር መኖሩን ያመላክታል የሚሉ ወገኖች  ተበራክተዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም የሀገሪቱ እጣ ፈንታ አስጊ መሆኑን የሚተነብዩ አሉ። በአጠቃላይ የፖለቲካው ሁኔታ ምን ላይ ነው ያለው?

በመሪው ፓርቲ በኩል የጤንነት ችግር የለም፤ በጣም ጤናማ ነው፡፡ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ይታወቃል። እንደተባለው አቶ በረከትም የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል። ይሄ እንግዲህ ሊኖር የሚችል ነገር ነው። በእርግጥ እነዚህ አንጋፋ መሪዎች ምክንያታቸው ሲገልፁ፣ መንግስት ጋር ጤንነት ስለመኖር አለመኖሩ የምንሰማ ይሆናል። መታወቅ ያለበት እነዚህ አንጋፋ መሪዎች በመሪው ፓርቲ ውስጥ ዋጋ የከፈሉ ናቸው፤ እስካሁንም ለህዝብ አገልግሎት ህይወታቸውን በሙሉ ሰጥተው የሰሩበት የመሩበት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ይሄ ድርጅታቸው ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋሉ ብሎ መገመት፣ የድርጅቱን ባህል ካለማወቅ የሚመነጭ ነው የሚሆነው። በድርጅቱ ጤንነት ላይ ግን ምንም ጥርጣሬ የለንም፡፡ እነዚህ አንጋፋ መሪዎች አሁን ካሉበት ሃላፊነት ቢለቁም ህዝባቸውን በሚችሉት የስራ መስክ እንደሚያገለግሉ ደግሞ እንጠብቃለን። አንድ ነገር መገንዘብ ያለብን፣ በምንወስዳቸው እርምጃዎች የውጤቱ ተጠቃሚ ህዝቡ ከሆነ ስራ መልቀቅ ቀላል ነው፡፡ 

በአንድ በኩል ገዥው ፓርቲ ጥልቅ ተሃድሶ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል በኦሮሚያ ተቃውሞ እንዲሁም የድንበር ግጭቶች ተከስተዋል። እኒህን ጉዳዮች እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው? 

ጥልቅ ተሃድሶ የራሱ ዓላማ ነበረው፤ ዓላማውን አሳክቷል፡፡ ነገር ግን ጥልቅ ተሃድሶው አሁንም በሂደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ ሌሊት የሚያበቃ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተሃድሶ በሰዎች አመለካከት፣ ተግባርና አሰራር ላይ ነው፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው አሁንም ውጤት ያሳየበት ሁኔታ አለ። በቀጣይ ደግሞ ውጤት የሚያሳይ ይሆናል። ግጭቶችን ከጥልቅ ተሃድሶው ጋር ማያያዝ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከጥልቅ ተሃድሶ በፊትም እነዚህ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የተከሰተው ግጭት፣ ከ20 ዓመት በላይ የቆየ ችግር ነው፡፡ ይሄን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ብቻ ማያያዝ ተገቢ አይሆንም፡፡


ምንጭ:- አዲስ አድማስ