በ1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተው “አለ በጅምላ” ድርጅት የለም ተባለ!

መንግስት ዋጋን ለማረጋጋት ከ3 ዓመት በፊት “አለ በጅምላ” በሚል ስያሜ የተቋቋመው ድርጅት ያለበት የእዳ ጫና እና የካፒታል እጥረት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰራ እንዳደረገው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መረጃ አግኝቷል።

በ1 ቢሊየን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው ድርጅቱ፥ ከ3 ዓመት በኋላም ከተወዳዳሪነትና ለሸማቾች በሚፈለገው ደረጃ ከመድረስም አንጻር ጥያቄ ይነሳበታል። ምርቶችን ከአለ በጅምላ እየገዙ የሚቸረችሩ ነጋዴዎች፥ ድርጅቱ የብዙ ምርቶች የአቅርቦት እጥረት እንዳለበትና በሚፈልጉት ልክ እቃዎችን እንደማያገኙ፤ አንዳንድ ምርቶች ከመርካቶ ይልቅ በአለ በጅምላ የዋጋ ጭማሬ እንደሚያሳዩ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ስር በፍጆታ እቃዎች ንግድ ዘርፍ ተጠቅልሎ ያለው ተቋም ከተወዳዳሪነትና ከተደራሽነት አንጻር ስላሉበት ችግሮች ማሳያዎች አሉ። በ3 ዓመት ውስጥ ከ25 በላይ መሸጫዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል እከፍታለሁ ያለው ተቋም ከ7 መሸጫዎች ማለፍ ያልቻለ ሲሆን፥ 26 በመቶ የጠቅላላ ሀገሪቱ የጅምላ ንግድ ድርሻ ይኖረኛል ቢልም እዛ መድረስ አልቻለም።

የእዚህ ነገር መነሻ ምን እንደሆነ ለማወቅ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ጥረት አለ በጅምላ አሁንም ተወዳዳሪነቱ ችግር ውስጥ የገባው ቀድሞ የተገባለት 1 ቢሊየን የተፈቀደ ካፒታል ስላልተሰጠውና ስራውን የጀመረው ራሱ በብድር ስለሆነ መሆኑን መረዳት ችሏል። በ2006 ዓ.ም ሲቋቋም አለ በጅምላ ከመንግስት በጥሬ የተሰጠው ገንዘብ 50 ሚሊየን ብር ብቻ ሲሆን፥ ተመናቸው ወደ ገንዘብ ተሰልቶም የመነገጃ መጋዘኖች ተሰጥተውታል። ከዚያ ውጭ ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ9 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ 596 ሚሊየን ብር እንዲበደር ተደርጎ ነው።

ድርጅቱ ውስጥ መስራትን ጨምሮ በቅርበት የሚያውቁትና ግለሰቦችም የገበያ ማረጋጋት ስራን እንዲሰራ በመንግስት የተቋቋመ ድርጅት በዚህ የእዳ ጫና ውስጥ ከሆነ እንዴት ተወዳዳሪ መሆን ይችላል የሚል ጥያቂ የሚያነሱ ሲሆን፥ ተገቢም እንዳልነበር ተናግረዋል። በ2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ስር ሲሆንም ይህንን እዳ ይዞ ነው።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ከበደ፥ አለ በጅምላ ወደ ኮርፖሬሽኑ ከመጠቃለሉ በፊት የነበረበት የመነገጃ ካፒታል ችግር እንደሚፈለገው እንዳላስኬደው፤ ይህም ለመጠቃለሉ ምክንያት እንደነበር ያነሳሉ። የነበረው ችግር አለ በጅምላ በ2006 አ.ም ሲቋቋም በብድር እንዲሰራ መደረጉ ብቻ አልነበረም ።

ከተበደረው 596 ሚሊየን ብር ውስጥ ለስራው 367 ነጥብ 5 ሚሊየን ብሩን ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች ወጭዎች ከተጠቀመ በሁዋላ 256 ነጥብ 4 ሚሊየን ብሩን ለውጭ አማካሪ እንዲከፈል እንደተደረገ ጣብያችን መረጃ አለው። ይህ ክፍያም የአለ በጅምላ የብድር አካል ነው የተደረገው። የዚህን ጉዳይ ተገቢነት ያነሳንላቸው አቶ መንግስቱ፥ ይህ የተፈጸመው ኮርፖሬሽኑ ከመመስረቱ በፊት በመሆኑ በእኔ የሚመለስ አይደለም ብለዋል። ኢቲ ካርኒ የተባለው የውጪ አማካሪ ያጠናው ጥናትም ቢሆን አተገባበር ላይ ሊሆን ይችላል እንጂ ጥናቱ ችግር የለውም አንብቤዋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

አለ በጅምላ አሁን ካጋጠመው ችግር መውጣት አለበት ያሉት አቶ መንግስቱ፥ ከችግሩ እንዲወጣ ላምደረግ ካፒታሉን መደገፍ አስፈላጉ ነው ብለዋል። ይህ ከተደረገም ከውጪም ይሁን ከሀገር ውስጥ ምርቶችን ገዝቶ በማከፋፈል የታለመለትን ስራ መስድራትና ትርፋማ መሆን ይችላል ሲሉም ተናግረዋል። ከ2009 አ.ም ጀምሮ አለ በጅምላ የተጠቃለለበት የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አለ በጅምላ ተበድሮት የነበረውን ብድር እየከፈለ ሲሆን፥ በየ3 ወሩም 69 ሚሊየን ብርን ይከፍላል።

የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ፥ “አሁን ኮርፖሬሽኑ እየከፈለ ያለው እዳ ከመቋቋሙ በፊት ያለ እንደመሆኑ መንግስት እዳውን ሸፍኖለት ምርቶችን በስፋት ወደ ማከፋፈል እንዲገባ ለመንግስት ጥያቄ ቀርቧል፤ እዳው እንደሚሸፈንም እምነት አለን” ብለዋል።

በዚህ ላይ ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግስት ሀላፊዎችን ለማነጋገር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።


ምንጭ፦ Fana Broadcasting Corporate