ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የህወሓትን ባለስልጣን አስጠነቀቁ!

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የህወሓትን ባለስልጣን አስጠነቀቁ፡፡ ሚኒስትሩ የመስሪያ ቤታቸውን የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ አንዳንድ ባለስልጣናት በእሳቸው እና በመስሪያ ቤታቸው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡ የህወሓት አመራር የሆኑት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም፣ ከዚህ ቀደም ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ መንግስታቸውን እና መስሪያ ቤታቸውን ወክለው የሰጡትን መግለጫ ‹‹የግል አስተያየታቸው ነው›› ሲሉ አጣጥለውት ነበር፡፡

ሚኒስትሩ በወቅቱ የሰጡት መግለጫ ዛሚ የተባለው እና ለስርዓቱ በተለይም ለህወሓት የሚያጎበድደው ሬድዮ ጣብያ እያቀረበ ከሚገኘው አጋጭ ዘገባ እንዲታቀብ የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም የህወሓት አመራር እና የብሮድካስት ባለስልጣኑ የዶ/ር ነገሪ ሌንጮን መግለጫ በማጣጣል ለሬድዮ ጣብያው ድጋፍ የሚሰጥ አስተያየት ነበር የተናገሩት፡፡ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመስሪያ ቤታቸውን የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ለፓርላማው ሲያቀርቡ፣ ‹‹በስም ማጥፋት ተግባር ውስጥም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች እየተሳተፉ የሚገኙ ዕድሜያቸውን ለማሳጠር እየጣሩ ያሉ አካላት ናቸው፡፡›> ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከዚህ ቀደም በህወሓቱ አመራር በአቶ ዘርዓይ አስገዶም የደረሰባቸውን ስም ማጥፋት በተመለከተ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ሪፖርቱ በሚቀርብበት ወቅት አንድ የፓርላማ አባል በበኩላቸው ‹‹ተቋሙም ሆነ ሚኒስትሩ የሚወክሉት መንግስትን፣ የሚያንጸባርቁትም የመንግስትን አቋም ስለመሆኑ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል፡፡›› ብለዋል፡፡

የህወሓቱ አመራር ከዚህ ቀደም በሰጡት መግለጫ ላይ፣ የዶ/ር ነገሪ ሌንጮችን መግለጫ ሲኮንኑ ‹‹ሚኒስትሩ የግል አስተያየት ነው የሰጡት፤ እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም፡፡›› ብለው ነበር፡፡ የፓርለማው አባል ለዚህ ምላሽ በሚመስል መልኩ፣ ዶ/ር ነገሪም ሆኑ መስሪያ ቤታቸው የሚወክሉት መንግስትን እንዲሁም ተጠሪነታቸውም ለፓርላማ መሆኑን በመግለጽ፣ አንዳንድ አመራሮች ጎጠኝነትን እያራመዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው እንዲህ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እያከናወኑ ያሉ አካላት ዕድሜያቸው እንደሚያጥር ዝተዋል፡፡ አቶ ዘርዓይ በመቀሌ እየተካሔደ ባለው የህወሓት ማዕከላዊ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ሂስ ከተሰነዘረባቸው አመራሮች መካከል አንዱ መሆናቸውን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

Source BBN news November 22, 2017

3 thoughts on “ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የህወሓትን ባለስልጣን አስጠነቀቁ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡