​የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት በዳኛ  ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ ያቀረቡት ተቃውሞ

“ዳኛው በእንዲህ አይነት ግልፅ የሆነ ተቃራኒ አቋም ውስጥ ሆነው ከዚህ ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለንን ተከሳሾች ጉዳይ ሚዛናዊ ዳኝነት ይሰጣሉ የሚል እምነት የለንም”

በእኛ በኩል  እንኳን ይህ ግልፅ ማስረጃ ባለበት ይቅርና እንዲሁ ጥርጣሬ ቢያድርብን እንኳን ተቃውሞ የቀረበባቸው ዳኛ ክርክሩን በግድ እዳኛለሁ እንደማይሉ እና በመቃወማችን ብቻ የአዋጁን አንቀፅ 27(2) መሰረት በማድረግ ተቃውሟችን በሌሎች ዳኞች ከመወሰኑ በፊት ራሳቸውን ከችሎት ያነሳሉ ብለን እንገምታለን። ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው ጉዳዩን በማየቱ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ ካልሆነ ወይም የተለየ አላማ ካልያዘ በቀር በግድ እዳኛለሁ ብሎ   እንደማይከራከር ይታመናል።  ከዚህ አጠቃላይ እውነት በመነሳት እኛ በዳኛው ላይ እውነተኛ ፍትህ አናገኝም የሚል ጥርጣሬ ካደረብን እውነተኛ ፍትህ ቢሰጡ እንኳን ከስነ ልቦና ጫና ነፃ እንደማንሆን መገመት አስቸጋሪ አይሆንም።”

አመልካቾች:_

  1. አቶ መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ
  2. አቶ ጌታሁን አደመ ሰረፀ
  3. አቶ አታላይ ዛፌ ገ/ማርያም
  4. አቶ አለነ ሻማ በላይ
  5.  አቶ ነጋ ባንተይሁን በራ

ጉዳዩ:_ አቶ  ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱልን ስለመጠየቅ

የቀረበብን ክስ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጠያቂ ኮሚቴ ነን በሚል ሽፋን የሽብር ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ነው። በዚህ ክስ በርካታ የክርክር ሂደቶች አልፈው የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች መርምሮ ተከሳሾችን ይከላከሉ ወይም በነፃ ይሰናበቱ በሚል ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከያዘ በኋላ ክርክሩን ከመጀመርያው ጀምሮ በአግባቡ ያጠኑትና የምስክሮችን ቃል አንድ በአንድ የሰሙት ዳኞች ሙሉ በሙሉ ከችሎት ተነስተው ሌሎች ጉዳዩን የማያውቁትና ያላጠኑት ዳኞች የተመደቡ ሲሆን ከተመደቡት ዳኞች መካከል አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት የተባሉት ዳኛ በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዘው ሚዲያ ላይ አስተያየት ሲሰጡ የነበረ እና ሆርን አፊየርስ ለተባለ የግል የዜና ማሰራጫ “የወልቃይት   የማንነት ጥያቄ በታሪክና በሕገ መንግስቱ” የሚል ርዕስ ባለው የፖለቲካ አቋም  ይዘው ፅሁፋቸውን ለሕዝብ ያሳወቁ  በመሆኑ ገለልተኛ ዳኝነት ሊሰጡ ስለማይችሉ  ከችሎት እንዲነሱልን ሕዳር 11/2010 ዓም በዋለው ችሎት የቃል አቤቱታ አቅርበናል። ችሎቱ አቤቱታችንን በጠበቃችን ታግዘን በፅሁፍ እንድናቀርብ ባዘዘው መሰረት እንደሚከተለው እናቀርባለን።

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/88 አንቀፅ 27(1) ላይ ዳኞች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ የሚቀርብባቸውን ምክንያት  ከ(ሀ)_ (መ) ከዘረዘረ በኋላ በፊደል ተራ (ሠ) ሥር “ከዚህ በላይ ከ(ሀ)  እስከ  (መ)  ከተመለከቱት ምክንያቶች ውጭ ትክክለኛ ፍትህ አይሰጥም የሚያሰኝ ሌላ በቂ ምክንያት ሲኖር” በማለት ዳኞች ከ(ሀ) እስከ (መ) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭም በተከራካሪ ወገን ተቃውሞ ከችሎት  ሊነሱ የሚችሉበት ሰፊ መብት ሰጥቷል።

ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለውም ተከራካሪ ወገኖች ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጥም ብለው መጠርጠራቸው ብቻ ዳኛን ከችሎት ለማስነሳት በቂ ምክንያት እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል።  እኛ የምናቀርበው አቤቱታ ግን በመጠራጠር ብቻ ሳይሆን ዓለም ባወቀው ማስረጃ የተደገፈ ሲሆን  ዝርዝሩን ከዚህ  በሚከተለው መልኩ አቅርበናል።

አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ስለ ወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በፃፉት ፅሁፍ በተለይ ስለ ብሔር ማንነት በሰፊው ከዘረዘሩ በኋላ እኛ በማስረጃነት ባቀረብነው ፅሑፋቸው  ገፅ 14፣  3ኛ አንቀፅ  “ስለሆነም እውቅና ይሰጠው የተባለው ማንነት በሀገሪቱ በየትኛውም ክፍል በሚገኝ መልክዓ ምድር ውስጥ የሰፈረ ማህበረሰብ ከሰፈረው መልክዓምድር ውጭ የሚገኝ ማናቸውም ማህበረሰብ ይህንኑ  ማንነት እንዳገኝ እውቅና ይሰጠኝ ብሎ የሚያቀርበው የማንነት ጥያቄ ሊኖር አይችልም” ይላል።

ይህ ማለትም በኢትዮጵያ አማራ የሚባል እውቅና የተሰጠው ብሔር ስላለ በአማራ ክልል ውስጥ የማይኖር ሰው አማራ ነኝ ማለት አይችልም፣ ቢልም እውቅና ሊሰጠው አይገባም የሚል ግልፅ ትርጉም መያዙን ተገንዝበናል።

ከዚህ በመቀጠልም ሌሎች ሰፊ ትንተናዎችን ከሰጡ በኋላ በገፅ 15፣ 2ኛ አንቀፅ ላይ “የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ የጥያቄ አገላለፅ እንደሚያሳየው የወልቃይት ሕዝብ የማንነት እውቅና ሊሰጠው የሚችል ልዩ ማንነት የለውም” በማለት ግልፅ የፖለቲካ አቋማቸውን አስፍረዋል። ከዚህ በመቀጠል እኛ በማስረጃነት ባቀረብነው ፅሑፋቸው ገፅ 16፣ 2ኛ አንቀፅ  ” በትግራይ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ተወካዮች ነን ባዮች በምንም መልኩ የማንነት ጥያቄ የማቅረብ መብት የላቸውም” በማለት እኛ የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ተብለን የተከሰስነውን ግለሰቦች በግልፅ በመንቀፍ   አቋማቸውን ለህዝብ አሳውቀዋል።

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ  “የወልቃይት መልክዓ ምድር ውስጥ የሰፈረው ሕዝብ  በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 39(3)(5)  እና 46(2)  መሰረት የትግራይ ማንነት ባህርይ የሚያሳይ መሆኑ ታምኖበት ከሽግግር ዘመኑ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ለግማሽ ክፍለ ዘመን በትግራይ ክልል ውስጥ ተከልሎ የሚገኝ ምድር ነው።  በመሆኑም  በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች በፌደራሉ ህገ መንግስት ሆነ በትግራይ ህገ መንግስት መሰረት የአማራ ማንነት እውቅና ብለው የመጠየቅ ህገመንግስታዊ መብት የላቸውም” በማለት አሁንም በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ያላቸውን ተቃራኒ አቋም ገልፀዋል።

አሁን ላቀረብነው  አቤቱታ ከዚህ በላይ የተገለፁት በቂ ናቸው እንጅ በፅሑፋቸው የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄን እንደሚቃወሙ  ከዚህ የበለጡ በርካታ ነጥቦችን አንስተው አቋማቸውን  በግልፅ አንፀባርቀዋል።  ከላይ እንደጠቀስነው እኛ ወንጀል ፈፀማችሁ የተባልነው የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ የኮሚቴ አባል በመሆናችን ስለሆነ ክሱ በግልፅ ያስረዳል። 

ከችሎት እንዲነሱልን የምንጠይቀው ዳኛ ደግሞ በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄን ሕጋዊ ነው ብለው እንደማይቀበሉ ጥቂት ምክንያቶች ከላይ የተገለፁ ሲሆን ባቀረብነው 46 ገፅ ያለው ፅሑፋቸው ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ድረስ በወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት ጥያቄ  እና በእኛ  በኮሚቴዎቹ ላይ  የተዘጋጀ ከመሆኑ በላይ የዳኛው የፖለቲካ አቋምም እጅግ ግልፅ ሆኖ የወጣ ነው። 

ዳኛው በእንዲህ አይነት ግልፅ የሆነ ተቃራኒ አቋም ውስጥ ሆነው ከዚህ ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለንን ተከሳሾች ጉዳይ ሚዛናዊ ዳኝነት ይሰጣሉ የሚል እምነት የለንም።

በእኛ በኩል  እንኳን ይህ ግልፅ ማስረጃ ባለበት ይቅርና እንዲሁ ጥርጣሬ ቢያድርብን እንኳን ተቃውሞ የቀረበባቸው ዳኛ ክርክሩን በግድ እዳኛለሁ እንደማይሉ እና በመቃወማችን ብቻ የአዋጁን አንቀፅ 27(2) መሰረት በማድረግ ተቃውሟችን በሌሎች ዳኞች ከመወሰኑ በፊት ራሳቸውን ከችሎት ያነሳሉ ብለን እምገምታለን። ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሰው ጉዳዩን በማየቱ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ ካልሆነ ወይም የተለየ አላማ ካልያዘ በቀር በግድ እዳኛለሁ ብሎ   እንደማይከራከር ይታመናል።  ከዚህ አጠቃላይ እውነት በመነሳት እኛ በዳኛው ላይ እውነተኛ ፍትህ አናገኝም የሚል ጥርጣሬ ካደረብን እውነተኛ ፍትህ ቢሰጡ እንኳን ከስነ ልቦና ጫና ነፃ እንደማንሆን መገመት አስቸጋሪ አይሆንም።

ስለዚህ ከላይ በዝርዝር ባቀረብነው መቃወሚያ መሰረት አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 27(2) መሰረት ከችሎት እንዲነሱ እንዲወሰንልን አቤቱታችን እናቀርባለን።  ለአቤቱታችን ማስረጃ ይሆን ዘንድ በአቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት የተፃፈ 46 ገፅ የአማርኛ ፅሑፍ  አቅርበናል።

(ኮሚቴዎቹ ከማረሚያ ቤት  የፃፉት አቤቱታ  ሲሆን  በፅሑፍ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ የአምስቱም ፊርማ አርፎበታል)

One thought on “​የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት በዳኛ  ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ ያቀረቡት ተቃውሞ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡