​በእነ ክንዱ ዱቤ ክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 5 ተከሳሾች ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት እንዲነሱ ያቀረቡት አቤቱታ

“…………በችሎት ላይ በደላችንን እና አቤቱታችንን እንዳናቀርብ፣ ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት እየዘለፉ ጭምር፣ ሙሉ በሙሉ የመናገር መብታችንን ገድቧል፡፡ ከዚህም ባለፈ፣ ክልከላው ተገቢ አይደለም ብሎ በደሉን በሚናገር ተከሳሽ ላይ፣ ታስረን ለምንገኝበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ተልዕኮ በመስጠት እያስወጡ እንዲያስፈራሩን እና ለወደፊቱ ችሎት ስንቀርብ ዝም ብለን እንድንመለስ ተፅኖ እያሳደሩብን ስለሚገኙ፤

………… ጉዳያችንን ለመከታተል የሚመጡ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች አሉን፡፡ ሆኖም፣ ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት እነዚህን ችሎት ተከታታዮች የማስፈራራት ተግባር በመፈጸማቸው፤

…………በስተመጨረሻም፣ ግለሰቡ ከዳኝነት አቅማቸው ባሻገር፣ ትግሬ ማንነታቸው በመመካት፣ በችሎት ላይ እኛን ተከሳሾችን፣ ምንም አትፈጥሩም በማለት እየዛተብን ስለሚገኝ፤”

 • ቀን   18/03/2010 ዓ.ም
 • ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
 • ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት
 • አዲስ  አበባ            

 ከሳሽ –  የፌዴራል ጠቅላይ   ተከሳሾች

 በእነ ክንዱ ዱቤ ደነቀው መዝገብ(10 ሰዎች)

 •   3ኛ. አቶ ደበበ ሞገስ
 •    4ኛ. አቶ ዘርዓይ አዝመራው ጎለንታው
 •    5ኛ. አቶ ገብረስላሴ ደሴ አሰግድ
 •    6ኛ. መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረ
 •    7ኛ. አቶ ሀብታሙ እንየው ፈረደ

በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 28(1) መሠረት ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱ የቀረበ ማመልከቻ

ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ አምሓራዊ ማንነታችንን መሠረት አድርጎ የሽብር  ክስ በ06/10/2009 ዓ.ም. በተጻፈ አቅርቦብን ክሱን በመከታተል ላይ እንገኛለን፡፡

ሆኖም፣ ክሳችንን በዚህ 2010 ዓ.ም በግራ ዳኛነት ተሰይመው በማየት ላይ የሚገኙት ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ ጉዳያችንን በገለልተኝነት ወይም ገለልተኛ በመምሰል(He is not impartial or does not appear to be impartial in the discharge of his judicial functions) አይተው ፍትህ ይሰጡናል ብለን ስለማናምን እንዲነሱልን እናመለክታለን፡-

1ኛ. ተከሳሾች የታሰርነው በአምሓራ ክልል በ2008 ዓ.ም. የወልቃይት ህዝብ አምሓራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ ነው፡፡ ክሱም የቀረበብን የሽብር ተግባር ስለፈጸምን ሳይሆን አምሓራ በመሆናችን ብቻ ነው፡፡ ጉዳያችንን በማየት ላይ የሚገኙት ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ደግሞ በዚህ ላይ ከተከሳሾች እምነት እና አቋም ጋር የሚለያየውን አቋማቸውን ግልጽ ባለ ሁኔታ በጽሁፍ እና በተለያየ የሚዲያ ተቋማት ገልጸዋል፤ ለማስረጃነት በእንግሊዘኛ አጠራሩ “Horn Affairs – Amharic” ተብሎ የሚጠራው ጦማር ላይ “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ – በታሪክና በህገ መንግስቱ” የሚለው ገጽ- 46 ከዚህ አቤቱታ ጋር አያይዘን አቅርበናል፡፡ ዳኛው ሃሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ቢሆንም ይህ አቋቸው ከያዙት የዳኝነት መዝገብ ጋር ቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ፤

2ኛ. ተከሳሾች ቀደም ሲል በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በነበርንበት ጊዜ ከፍተኛ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰብን መሆኑ የሚታወቅ ነው፤ እንደዚሁም፣ አሁን ባለንበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተለያየ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በየጊዜው ይደርስብናል፡፡ እነዚህን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ ጉዳያችንን ለሚያየው ፍ/ቤት እንደየመዝገባችን እና በግላችን ለመናገር እና እርምጃ እንዲወሰድልን ያስፈልገኛል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በችሎት ላይ በደላችንን እና አቤቱታችንን እንዳናቀርብ፣ ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት እየዘለፉ ጭምር፣ ሙሉ በሙሉ የመናገር መብታችንን ገድቧል፡፡ ከዚህም ባለፈ፣ ክልከላው ተገቢ አይደለም ብሎ በደሉን በሚናገር ተከሳሽ ላይ፣ ታስረን ለምንገኝበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ተልዕኮ በመስጠት እያስወጡ እንዲያስፈራሩን እና ለወደፊቱ ችሎት ስንቀርብ ዝም ብለን እንድንመለስ ተፅኖ እያሳደሩብን ስለሚገኙ፤

3ኛ. ችሎቱ የሚያስችለው በግልጽ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ጉዳያችንን ለመከታተል የሚመጡ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች አሉን፡፡ ሆኖም፣ ዳኛ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት እነዚህን ችሎት ተከታታዮች የማስፈራራት ተግባር በመፈጸማቸው፤

4ኛ. በስተመጨረሻም፣ ግለሰቡ ከዳኝነት አቅማቸው ባሻገር፣ ትግሬ ማንነታቸው በመመካት፣ በችሎት ላይ እኛን ተከሳሾችን፣ ምንም አትፈጥሩም በማለት እየዛተብን ስለሚገኝ፤

ስለዚህ፣ ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች በአ/ቁ. 25/1988 27(2) መሠረት ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ራሳቸውን ከችሎት እንዲያነሱልን እንጠይቃለን፤ በዚህ ፈቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 28(4) መሠረት በሌሎች ዳኞች ማመልከቻችን ውሳኔ እንዲሰጥልን ስንል በትህትና እናመለክታለን፡፡
****

ተከሳሾች

 •   3ኛ. አቶ ደበበ ሞገስ
 •    4ኛ. አቶ ዘርዓይ አዝመራው ጎለንታው
 •    5ኛ. አቶ ገብረስላሴ ደሴ አሰግድ
 •    6ኛ. መሪጌታ ዲበኩሉ አስማረ
 •    7ኛ. አቶ ሀብታሙ እንየው ፈረደ

(ተከሳሾቹ ዛሬ ህዳር 18/2010 አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት ይነሱ አይነሱ የሚለውን ለመበየን ለታህሳስ 3/2010 ቀጠሮ ተይዟል)

One thought on “​በእነ ክንዱ ዱቤ ክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 5 ተከሳሾች ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት እንዲነሱ ያቀረቡት አቤቱታ

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡