ሰሚ ያጣው አቤቱታ፦ በዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ የቀረበ “ሌላ” አቤቱታ! 

​”አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በተደጋጋሚ ጊዚያት በቂ ባልሆነ ምክንያት ቀጠሮ እየተሰጠብን እንደሆነ፣ በማዕከዊ( በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ) የደረሰበንን በደልና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመብን እንደሆነ አቤቱታ በምናቀርብበት ወቅት “ዝም በል፣ምን ታመጣለህ” በማለት መልስ የሚሰጡና ለአንድ በእስር ላይ ለሚገኝ ተከሳሽ የማይገቡ መልሶች የሚሰጡ ናቸው፡፡ በእኛ እምነተት እነዚህ ባለፉት ጊዚያት በነበሩን ቀጠሮዎች አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት የሚያደርጉት ድርጊት ገለልተኛ ዳኝነት እንደማይሰጡ ግልፅ ማሳያዎች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡”

ሕዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም

 የኮ/መ/ቁ 197775

ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት፣ ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት 

  • አ/አበባ
  • ከሳሽ፡- የፌደራል ጠ.ዐ.ህግ
  •  ተከሳሽ፡- እነ ክንዱ ዱቤ ደነቀው

ጉዳዩ:_ በ2ኛ እና 10 ተከሳሾች አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱልን የቀረበ አቤቱታ ነው

የፌደራል ጠቅላይ ዓ.ህግ ተከሳሾች የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል በመሆን የሽብር ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ክስ አቅርቦብንናል። በዚህ ክስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበን ባቀረብነው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጠን ነው፡፡ በዚህ ቅር በመሰኘት ሕዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከተመደቡት ዳኞች መካከል አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት የተባሉት
ዳኛ በተደጋጋሚ ጊዜ ቅሬታችንን እንድናቀርብ ሰንጠይቅ እያንገራጉን እንደሆነና በማህበራዊ ሚዲያ “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ በታሪክና በሕገ መንግስቱ” የሚል ርዕስ በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዘው አስተያየት ሲሰጡ የነበሩ በመሆናቸው ገለልተኛ ዳኝነት ሊሰጡ ስለማይችሉ ከችሎት እንዲነሱልን

በቃል በመጠየቃችን ፍ/ቤቱ አቤቱታችንን በጠበቃችን ታግዘን በፅሁፍ እንድናቀርብ ባዘዘው መሰረት እንደሚከተለው አቅርበናል። 

በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/88 አንቀፅ 27(1) በግልፅ እንደተደነገገው ተከራካሪ ወገኖች ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጥም ብለው ካመኑ ዳኛውን ከችሎት ለማስነሳት አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችሉና ይህም ዳኛን ለማስነሳት በቂ ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

የተጠቀሰው አዋጅ አንቀፅ 27(1) በፊደል ተራ (ሠ) ስር “ከዚህ በላይ ከ(ሀ) እስከ (መ) ከተመለከቱት ምክንያቶች ውጭ ትክክለኛ ፍትህ አይሰጥም የሚያሰኝ ሌላ በቂ ምክንያት ሲኖር” በማለት ዳኞች ከ(ሀ) እስከ (መ) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭ በተከራካሪ ወገን ተቃውሞ ከችሎት ሊነሱ እንደሚችሉ ይገልፃል። 

በጠቅላይ ዓ.ህግ በቀረበብን የሽብር ክስ ዝርዝር “በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ከተማና አካባቢው በሚገኙ የትግራይ ብሔር ተወላጆችና የአማራ ብሔር ተወላጅ የመንግስት አመራሮችና የመንግስት ደጋፊዎች እንዲገደሉ ቤት ንብረታቸው በእሳት እንዲቃጠል ጎንደር አካባቢ ሲንቀሳቀስ ለነበሩ የሽብር ቡድን አባላት ትዕዛዝ ሰጥቷል” የሚል ክስ አቅርቦብናል (በ10ኛ ተከሳሽ የክስ ዝርዘር ላይ ይገኛል)፡፡ በህዝባዊ እንቅስቃሴው ወቅት በተለያዩ ሚዲያዎች የትግራይ ብሔር ተወላጆች ተፈናቀሉ ቤት ንብረታቸው ተቃጠለ በማለት በመንግስት አካለት ተገልጧል፡፡

በዚህ መሰረት አቶ ዘርዓይ ወልደ ሰንበት የትግራይ ብሔር ተወላጅ በመሆናቸው ገለልተኛ ዳኝነት ይሰጡናል የሚል እምነት የለንም፡፡ ከላይ እንደገለፅነው አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በማህበራዊ ሚዲያ ሆርን አፊይርስ ለተባለ የግል የዜና ማሰራጫ “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ በታሪክና በሕገ መንግስቱ” በሚል ርዕስ በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ግልፅ የሆነ የፖለቲካ አቋም ይዘው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በዚሁ ጉዳይ ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች በምንም መልኩ የማንነት ጥያቄ የማቅረብ መብት የላቸውም በማለት የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 39(3)(5) እና 46(2) በመጥቀስ በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ገልፀዋል። በሌላ በኩል የቀረበብን ወንጀል ተመፀመ በተባለበት ቦታና ጊዜ ተነስቶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ መነሻው የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ በሚል ሽፋን ፀረ ሰላም ሃይሎች ያስነሱት ተቃውሞ እንደሆነ በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡

ስለዚህ ዳኛው እንዲህ አይነት ግልፅ የሆነ አቋም ከያዙበት ጉዳይ ጋር ተዛማጅ በሆነ ጉዳይ የቀረበብንን ክስ ሚዛናዊ ዳኝነት ይሰጣሉ የሚል እምነት የለንም። አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በተደጋጋሚ ጊዚያት በቂ ባልሆነ ምክንያት ቀጠሮ እየተሰጠብን እንደሆነ፣ በማዕከዊ( በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ) የደረሰበንን በደልና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመብን እንደሆነ አቤቱታ በምናቀርብበት ወቅት “ዝም በል፣ምን ታመጣለህ” በማለት መልስ የሚሰጡና ለአንድ በእስር ላይ ለሚገኝ ተከሳሽ የማይገቡ መልሶች የሚሰጡ ናቸው፡፡ በእኛ እምነተት እነዚህ ባለፉት ጊዚያት በነበሩን ቀጠሮዎች አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት የሚያደርጉት ድርጊት ገለልተኛ ዳኝነት እንደማይሰጡ ግልፅ ማሳያዎች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡

ስለዚህ ከላይ በዝርዝር ባቀረብነው መቃወሚያ መሰረት አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 27(2) መሰረት ከችሎት እንዲነሱልን አቤቱታችን እናቀርባለን። 

ተከሳሾች:- 

  • አቶ ዘመነ ጌቱ
  •  አቶ ለገሰ ወልደሀና

One thought on “ሰሚ ያጣው አቤቱታ፦ በዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ላይ የቀረበ “ሌላ” አቤቱታ! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡