ዚምባብዌ የካቲት 14ን የሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ ብሔራዊ የወጣቶች ቀን በማለት ሰየመች! 

የሃገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙጋቤ የልደት ቀን ብሔራዊ የህዝብ በዓል እንዲሆን ታወጇል።

ሙጋቤ የሃገሪቱ ሠራዊት ጣልቃ መግባቱን እና ለቀናት የዘለቀ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

‘ዘ ሄራልድ’ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የቀድሞው ፕሬዝዳንት የልደት ቀን ብሔራዊ በዓል እንዲሆን የፓርቲያቸው ዛኑ-ፒፍ የወጣት ሊግ ከፍ ያለ ግፊት ሲያደርግ ቆይቶ ተቀባይነት ያገኘው ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር።

ውሳኔው ግን በይፋ እንዲመዘገብ የተደረገው አርብ ዕለት እንደሆነ ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እንደተናገሩት፤ ሙጋቤ ከሃገሪቱ መስራቾች እና መሪዎች መካከል አንዱ እንደመሆናቸው ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።

“በግሌ ሙጋቤ አባት፣ መምህር፣ የትግል ጓድ እና መሪ እንደሆኑ ይቆያሉ” ሲሉ ምናንጋግዋ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ገልፀው ነበር።

ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን እንዲለቁ ለማግባባት 10 ሚሊዮን ዶላር ተሰጥቷቸዋል የሚለውን ሪፖርት እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማዋ ሐራሬ ውስጥ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን ሃገራቸውን ለቀው የመውጣት ዕቅድ የላቸውምም ተብሏል።

***

ምንጭ:- BBC|አማርኛ