“ህዝብ በቋንቋና በጎሳ እንዲለያይ በማድረግ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም ኢ-ሰብአዊነት ነው!”

“የቱንም ቋንቋ ብንናገርና ከየትኛውም ጎሳ ብንመጣ ህልማችን ለሁሉም ኬኒያውያን የምትመች የተባበረች አንዲት ሀገር መፍጠር ነው!”

“ህዝብ በቋንቋና በጎሳ እንዲለያይ በማድረግ የሚገኝ የፖለቲካ ጥቅም ኢ-ሰብአዊነት ነው!” ዛሬ የኬኒያው ፕሬዚዳንት ይህን ሲናገሩ ሀይለማሪያም በዚያ ነበሩ።


ዛሬ የምስራቅ አፍሪካዋ ብቸኛ የዴሞክራሲ መገለጫ ተብላ የምትሞካሸው በተለይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለዜጎቿ በማስተዋወቅና በአንጻራዊ የሚዲያ ነጻነት የምትታወቀው ኬኒያ የነጻነት አርበኛ የጆሞ ኬኒያታ ልጅ የሆኑትን ኡሁሩ ኬኒያታን ለሁለተኛ ጊዜ በመሪነት ቃል አስገብታለች።

ከ45 ሀገራት በመጡ መሪዎችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከ40 ሺህ በላይ በሚቆጠሩ ኬኒያውያን ፊት ሀገሪቱን በዴሞክራሲና በልማት ለመምራት ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን የሀገራቸውን የፖለቲካ ሂደት እየተፈታተነ ያለውን “ዘረኝነትና ጎሰኝነት” ለመዋጋት ቆርጠው መነሳታቸውን ይፋ አድርገዋል።

“የሀገራችን ህዝቦች በሰውነታቸው ብቻ ተከብረውና በዜግነታቸው የሚገባቸውን መብትና ግዴታ እያሟሉ የሚኖሩባት እንጂ በጎሳ ፖለቲካ ተተብትበው የሀገራችን ህገ መንግስትና አንድነታችንን እንዲፈታተኑት መፍቀድ የለብንም።” በማለት “ዘረኝነትና ጎሰኝነትን ጥፍሩን እየነቀልን እንጥለዋለን።” ሲሉ ተናግረዋል።

ኡሁሩ ኬኒያታ አክለውም “የምንገነባት ሀገራችን ኬኒያ እንኳን ለራሷ ዜጎች ይቅርና ለሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች የሚመች መልካም የንግድና የመኖሪያ አካባቢ ነች” በማለት የምስራቅ አፍሪካ ዜጎችን በኬኒያ ውስጥ የመኖር፣ ከኬኒያውያን ጋር የመጋባት፣ የመማርና የመስራት ሙሉ ነጻነት አውጀዋል።

ይህ ሁሉ ሲባል ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ከፊት ለፊት ከተደረደሩት የክብር ወንበሮች በአንዱ ቁጭ ብለው የኡሁሩን ንግግር በሚገባ አድምጠዋል።

አቶ ሀይለማሪያም የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲና የሚያስተዳድሩት የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ከዚህ ከኡሁሩ አስተሳሰብ በሚሊየን ማይልስ የራቀ እንደሆነ እያሰቡ እጃቸውን በአገጫቸው ላይ አስደግፈው በአንክሮ አድምጠዋል።

የእርሳቸው ኢህአዴግ ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ ህልሙና ሀሳቡ ኢትዮጵያ የምትባል አንዲት ስመ ገናና ሀገር ሳትሆን ብሄር ብሄረሰብ የተባሉ በፖለቲካ አስተምህሮ ብቻ የተቀናበሩት ቡድኖች ብቻ ናቸው።

ኬኒያና ፕሬዚዳንቱ የሚጠየፉት ይህ “የብሄር አስተሳሰብ ፖለቲካ” ኢትዮጵያ ውስጥ መብት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በግዴታ ሊሰባሰቡበት የሚገባ የአኗኗር ዘይቤ ነው።

ኢትዮጵያ ያለ ጎሳ ፖለቲካ ያለ ብሄር አደረጃጀት የሚተነፍስ መንግስትም የፖለቲካ ድርጂትም መሪም የላትም።

ኡሁሩ ይህንኑ ንግግራቸውን ሲያጸኑ “እዚህ የደረስነው ለኬኒያውያን ሊደርግ ስለሚገባ መሰረተ ልማትና ነጥሮ ሊወጣ በሚችል የፖለቲካ አስተሳሰብ እንጂ በብሄርና በጎሳ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ አይደለም።” በማለት ላለፉት አምስት አመታት በነበራቸው የመሪነት ቆይታ ለእያንዳንዱ ኬኒያዊ ያደረጉትን ከምስራቅ እስከ ምእራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ በስም እየጠቀሱ ያስረዱ ሲሆን ወደፊትም አንዲት ኬኒያና አንድ ኬኒያዊ ህዝብ በየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ቢዋቀር በእኩልነት እንደሚያስተዳድሩት አስረድተዋል።

ይህን ሁሉ በሚናገሩበት ወቅት ግን አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ እያዳመጡ ነው።

በድጋሚ የተመረጡት የኬኒያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሀይለማሪያም ደሳለኝን ሲገልጹ “የኬኒያ ጓደኛ የሆነው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር” ብለዋቸዋል።

እናስ ኢትዮጵያ ከኬኒያ ጋር ያላት ጓደኝነት ትናንት አጼ ሀይለስላሴ ለሀገሪቱ የነጻነት ትግል ለጆሞ ኬኒያታ ባደረጉት አስተዋጽኦ ነው ወይስ አንዲት ለምትባል ሀገርና አንድ ለሚባል ህዝብ በሚደረግ ትግልና መስዋእትነት?

ይህን ጥያቄ ዛሬ በናይሮቢ ካሳራኒ ስታዲየም የተገኘውና የኬኒያውን ፕሬዚዳንት ንግግር የሰማው የጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጆሮና ልብ ይመልሰው!!

****

ምንጭ፦ Mereja.com