​ትምህርት ሚኒስቴር መስማት ወይም መስራት አቁሟል! 

ባለፈው ሳምንት በዶችቬሌ ራዲዮ ላይ በፖለቲካ አለመረጋጋትና ትምህርት በሚል ርዕስ ዙሪያ በት/ት ሚኒስቴር የኮሚኑኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረግን ጨምሮ ከሌሎች ሁለት ተሳታፊዎች ጋር በስልክ ውይይት አድርገን ነበር። በውይይቱ ላይ በት/ት ተቋማት ውስጥ ለሚከሰቱ ግጭቶችና ተያያዥ ችግሮች በዋናነት ተጠያቂው የትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። 
ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት የፌደራል መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የክረምት የትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎች መታወቂያቸው እየታየ ልዩነት ሲደረግባቸው እንደነበር ገልፀዋል። ከዚህ አልፎ ተርፎ መታወቂያቸው እየታየ ጥቃት የተፈፀመባቸው ተማሪዎች እንዳሉ ገልፀዋል። 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ 60 መምህራን የትምህርት ሚኒስቴርን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው አዲስ አበባ ድረስ መጥተው አመልክተዋል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቁበትን ምክንያት በድህረ-ገፃችን ማውጣታችን ይታወሳል። 

ከውይይቱ በፊት ከተጠቀሱት መምህራን ወደ አንዱ ስልክ በመደወል ሁኔታውን ለማጣረት ሞክሬ ነበር። ነገር ግን፣ የትምህርት ሚኒስቴር ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው ከጠየቁት 60 መምህራን ውስጥ አሁን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የቀሩት ከአራት እንደማይበልጡ ለማወቅ ችያለሁ። የተቀሩት መምህራን እንደ አዲስ ሥራ ፍለጋ በየዩኒቨርሲቲው በመንከራተት ላይ ናቸው። 

ከላይ በተጠቀሰው የራዲዮ ውይይት ይህን መረጃ በመጥቀስ የትምህርት ሚኒስቴር እንኳን የተማሪዎቹን የመምህራኑን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደተሳነው ገልጬ ነበር። የሚኒስቴሩ ቃል-አቀባይ የሆኑት ወ/ሮ ሐረግ የተሰጡኝ ምላሽ ግን እጅግ በጣም አስገራሚ ነው። ወ/ሮ ሐረግ የሰጡት ምላሽ “አራቱ መምህራን እስካሁን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ያሉት ደህንነታቸው ስለተጠበቀ ነው” የሚል ነበር። 

ሰሞኑን ደግሞ “ከቀጣዩ የ2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የመጀመሪያ ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና (Exit-Exam) መውሰድ አለባቸው” የሚለውን የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ በመቃወም የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጧል። ለምሳሌ እኔ በማስተምርበት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች መመሪያውን በመቃወም ትምህርት ካቆሙ ሁለተኛ ሳምንታቸውን ይዘዋል። በተመሳሳይ የጅማና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ግቢውን ለቀው እየወጡ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተገለፀ ይገኛል። 

በእርግጥ እያንዳንዱ ተመራቂ ተማሪ በተማረበት የሞያ መስክ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ሊኖረው ይገባል። ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁሉም ተመራቂዎች ወጥ የሆነና ደረጃውን የጠበቀ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወይም የመውጫ ፈተና (Exit-Exam) መስጠቱ መልካም ነው። ነገር ግን፣ ከእንዲህ ያለ ፈተና በፊት ወጥ የሆነና ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ሊኖር ይገባል። 

የትምህርት ጥራትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት እንዲኖር ደግሞ እኩል የሆነ የትምህርት ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች አቅርቦት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የትምህርት ጥራትን ማዕከል ያደረገና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እኩል ተግባራዊ የተደረገ ስርዓተ-ትምህርት፣ በተግባር የተደገፈ የመማር-ማስተማር ሂደት፣ አስፈላጊው ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣… ወዘተ ያስፈልጋሉ። 

እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከተሟሉ በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፥ መምህራንና ሰራተኞች፣ እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ ወጥና ደረጃውን የጠበቀ የብቃት ማረጋገጫ ወይም የመውጫ ፈተና (Exit-Exam) ለመስጠት በሁሉም አካላት ዘንድ አስፈላጊው ግንዛቤና ዝግጅት መደረግ አለበት። 

ሰሞኑን በትምህርት ሚኒስቴር የወጣው “ከቀጣዩ የ2011 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የመጀመሪያ ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና (Exit-Exam) መውሰድ አለባቸው” የሚለው መመሪያ ግን ከላይ ከተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ እንዱን እንኳን አያሟላም። ይህ መመሪያ ፍፁም ግልብና በተጨባጭ እውነታ ላይ ያልተመሰረተ፤ የተማሪዎቻችንን አቅምና ፍላጎት፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትምህርት አሰጣጥ ሂደትና አደረጃጀት ከግንዛቤ ያላስገባ፣ የአተገባበር ሂደቱ ግልፅነት የጎደለው፣ ዝም ተብሎ በማን-አለብኝነት የተላለፈ ነው። 

በመግቢያው ላይ በተጠቀሰው የራዲዮ ውይይት ፕሮግራም ላይ መመሪያው በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ሌላ አመፅና ተቃውሞ እያስነሳና በዚህ ምክንያት የመማር-ማስተማር ሂደቱን እያስተጓጎለ እንደሆነ ተናግሬ ነበር። ሆኖም ግን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳሬክተሯ ወ/ሮ ሐረግ የተጠቀሰው ችግር የተለየ እንደሆነ እና በቀጣይ ሊታይ እንደሚችል ገልፀዋል። ነገር ግን፣ ባለፈው የክረምት የትምህርት ፕሮግራም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው፣ በዚህ ወር መጀመሪያ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው፣ እንዲሁም ሰሞኑን እንደ አምቦ፥ ጅማና ሀሮማያ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እየታዩ ያሉት ችግሮች በትምህርት ሚኒስቴር ስራና አሰራር ክፍተት ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው። 

በሌላ በኩል፣ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንት ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ማድረግ ያለበት ምንድን ነው? እንደ ኃላፊ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ደውሎ “ይህን መመሪያው ተግባራዊ ማድረግ አንችልም” ብሎ እቅጩን መናገር፤ ወይም “መመሪያው በዚህ መልኩ መለወጥና መሻሻል አለበት” ብሎ ሃሳብና አስተያየት መስጠት፣ … የትምህርት ሚኒስቴርን ኃላፊዎች እና በስሩ ያሉ ሰራተኞችና ተማሪዎችን ማሳመን፣ በዚህም የመማር-ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል ይጠበቅበታል። 

ፕረዜዳንቱ ይሄን ከማድረግ ይልቅ፣ ትምህርት አቋርጠው ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ተማሪዎችን መንገድ ላይ ቆሞ የሚለምን ከሆነ አሁንም ችግሩ የትምህርት ሚኒስቴር ነው። ምክንያቱም፣ ወይ የዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንቶችን መስማት አቁሟል፣ አሊያም በዩንቨርሲቲዎቻችን ላይ የአመራር ብቃት የሌላቸው ሰዎችን መድቧል። ስለዚህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትምህርት ተቋማቱን በበላይነት ከመምራትና ማስተዳደር አንፃር ስራውን መስራት ተስኖታል። ያም ሆነ ይህ፣ ትምህርት ሚኒስቴር መስማት ወይም መስራት አቁሟል! 

One thought on “​ትምህርት ሚኒስቴር መስማት ወይም መስራት አቁሟል! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡