የማዕከላዊ ሰቆቃ፦ የሸጊቱ ስቃይ፥ የደስታ መከራ!

​ሸጊቱ ነገዎ፦ 

“2009 ዓም ሻሸመኔ ከተማ ነው የተያዝኩት። ሻሸመኔ ፓራዳይዝ ቫሊ ኮሌጅ ውስጥ ነበር የምሰራው። ሌላ ድርጅት ውስጥ አልሰራም። የተከሰስኩት ግን ሌላ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን ሰብስበሽ ትሰሪያለሽ ተብዬ  ነው።  ……ማዕከላዊ በማላውቀው ጉዳይ ላይ ነው ተገድጄ የፈረምኩት። ጆሮዬ እስኪደማ ድረስ ተደብድቤ ተጎድቷል።ግራ እጄ ታሟል። በእግራቸው ነበር የሚረግጡኝ። ፀጉሬን እየጎተቱ ነበር የሚደበድቡኝ። ይደበድቡኝ የነበረው ያልሰራሁትን ነገር ሰርተሻል እያሉ ነው። እኔ ምንም የሰራሁት ነገር የለም። የሰጠሁት ቃል የለም። በግድ ነው የፈረምኩት። የደበደቡኝን መርማሪዎች ስማቸውን አላውቅም። ከቤ፣ ከቤ ነው የሚባባሉት። “

(በእነ ሀጅ ሁሴን ኬሶ መዝገብ  2ኛ ተከሳሽ ሸጊቱ ነጋዎ ህዳር 20/2010 ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የሰጠችው ቃል ሲሆን ንግስት ይርጋ እና ቀነኒ ታምሩም በማዕከላዊ ስለደረሰባት በደል የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተውላታል።)

ደስታ በሪሶ፦ 

“ማዕከላዊ የገባሁት መስከረም 6/2009 ዓ.ም ነው።  ጠዋት 2 ሰዓት ወደ ምርመራ ክፍል ይወስዱኝና እስከ ምሳ ሰዓት ይደበድቡኛል።  ከምሳ ሰዓት በኋላም ወስደው ይደበድቡኛል።  ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ ወስደው እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ይደበድቡኛል። የኦነግ አባል ነህ እያሉ ነበር የሚደበድቡኝ። በድብደባው ምክንያት በእጆቼ፣ በእግሮቼና በጀርባዬ ላይ ጉዳት ደርሶብኛል። በድብደባው በደረሰብኝ ጉዳት ምክንያት  በሌሎች ድጋፍ ነበር  ሽንት ቤት የምሄደው። አሸናፊ የተባለው ምስክሬ ነበር ተሸክሞ ሀኪም ቤት የሚወስደኝ።

ይደበድቡኝ የነበረው የማላውቀውን ነገር ፈርም ሲሉኝ አልፈርምም በማለቴ ነበር። አስገድደው አስፈርመውኛል። የህይወት ታሪክ ተብሎ በቃሌ   የቀረበው የሌላ ሰው ነው።  የልጆቼና የባለቤቴ ስም ተብሎ በህይወት ታሪኬ ላይ የተፃፈው የእኔ አይደለም። ………በቃሌ የተጠቀሰችው የእኔ ባለቤት አይደለችም፣ ልጆቹም የእኔ ልጆች አይደሉም። ይረጋገጥል………”

(በእነ ሀጅ ሁሴን ኬሶ የክስ መዝገብ 13ኛ ተከሳሽ ደስታ በሪሶ ህዳር 20/2010 ዓ•ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ከሰጠው ቃል የተወሰደ ነው)

One thought on “የማዕከላዊ ሰቆቃ፦ የሸጊቱ ስቃይ፥ የደስታ መከራ!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡