ህወሓት አዲስ ሊቀመንበር መረጠ! 

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲያካሂድ የነበረውን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አዳዲስ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመሾም አጠናቀቀ፡፡
በዚህም መሠረት የመገናኛ፣ ኮሙዩኒኬሽና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) ሊቀመንበርና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔርን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ፡፡ 

ሕወሓት በስብሰባው አቶ ጌታቸው አሰፋን፣ አቶ ዓለም ገብረዋህድን፣ አዲስ ዓለም ባሌማን (ዶ/ር)፣ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴን፣ አቶ ጌታቸው ረዳን፣ ወ/ሮ ኬሪያም አብራሐምንና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አብራሐም ተከስተን (ዶ/ር) በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት መርጧቸዋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ከትናንት ወዲያ ባስተላለፈው ውሳኔ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከማዕከላዊ ኮሚቴ ሲያግድ፣ የቀድሞው የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሰብሳቢና የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ወልዱንና የኤፈርት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ በየነ ምክሩን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ ግምገማ ቀጥሎ የሚጠበቀው የሕወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ሲሆን፣ ከሥራ አስፈጻሚው የታገዱት የወ/ሮ አዜብ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የህወሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴ በጥልቀት ሲያካሂድ የቆየውን የሂስና ግለ ሂስ መድረክ እና የድርጅቱን ቁልፍ አመራር መልሶ ማደራጀት ዛሬ አጠናቋል፡፡


የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዲስ መልኩ የተደራጀ ሲሆን በዚህም መሰረት 

  • 1. ጓድ ደብረፂዮን ገብረሚካኤል  (ዶ.ር)
  • 2. ጓዲት ፈትለወርቅ ገ/እግዛብሄር
  • 3. ጓድ ኣለም ገ/ዋህድ
  • 4. ጓድ ኣስመላሽ ወ/ስላሴ
  • 5. ጓድ ጌታቸው ረዳ
  • 6. ጓድ ኣዲስዓለም ባሌማ (ዶ.ር)
  • 7. ጓዲት ኬርያ ኢብራሂም
  • 8. ጓድ ኣብራሃም ተከስተ (ዶ.ር)
  • 9. ጓድ ጌታቸው ኣሰፋ የህወኃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነዋል፡፡

ጓድ ደብረፂዮን የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡ ሲሆን ጓዲት ፈትለወርቅ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።

***

ምንጭ:- ሪፖርተር  እና EPRDF Official

One thought on “ህወሓት አዲስ ሊቀመንበር መረጠ! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡