የፈሪዎች ዓለም፦ አስራኤላዊቷ ሴትዮ እና ህወሓት 

ባለፈው አሜሪካን ሀገር የሄድኩ ግዜ (አይዟችሁ ጉራ አይደለም)፣ … ከዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሆቴል በሚወስደኝ ታክሲ ውስጥ ተቀመጬ አንድ ሌላ ተሳፋሪ እስኪ መጣ እየጠበቅኩ ነው። አምስት ደቂቃ እንደጠበቅኩ አንዲት እስራኤላዊ ሴት አዛውንት መጥታ ከአጠገቤ ተቀመጠች። ከዚያ አድራሻዋን ለሹፌሩ ተናግራ ጉዞ ተጀመረ። 

ጉዞ እንደተጀመረ ከጎኔ የተቀመጠችው እስራኤላዊት ከየት፥ በየትና በየትኛው አየር መንገድ እንደመጣሁ ጠየቀችኝ። እኔም ኢትዮጲያ እንደሆንኩ፣ በ“Fly Emirates” የአየር መንገድ በዱባይ ትራንዚት አድርጌ እንደመጣሁ ነገርኳት። ፊቷን ጭፍግግ አድርጋ “እኛ በዚያ መሄድ አንችልምኧ” አለችኝ። “ለምን?” ስላት “ሁሉም ሙስሊሞች እኛን አይወዱንም! እስራኤሎችን ይጠሉናል” አለችኝ። ይሄን ግዜ የታክሲው ሹፌር “don’t say ‘All Muslims!’ … Say ‘Some Arabs!’” አላት። 

ለካስ ሹፌሩ በትውልድ ካሜሮናዊ ሲሆን የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኖሯል። ወዲያው ሴትየዋ ስትደናገጥ ተመለከተና “I am Muslim! But I don’t hate you!” ብሎ ሊያፅናናት ሞከረ። እሷ ግን አላረፈችም። ፊቷን ወደ እኔ አዙራ “አረቦች ይጠሉናል!” አለችኝ። እኔም ፊቴን ቅጭም አድርጌ “ሁሉም አረቦች እስራኤሎችን አይጠሉም!” አልኳት። 

ሴትየዋ “Look at Hamas, Hezbollah, Iran,…” በማለት፤ አረቦች እስራኤሎችን ይጠላሉ፣ በየግዜው የሽብር ጥቃት ይፈፅሙብናል፣ የኢራን መንግስት ሁሌም እስራኤልን ለማጥፋት ይዝታል፣…ወዘተ እያለች ማስረጃዎቿን መዘርዘር ቀጠለች። እኔም ዝም ብዬ ሳዳምጣት ቆየሁ። 

በመጨረሻ “አሁን የጠቀሻቸው አካላት ጥላቻ፥ ጥቃትና ዛቻ ከእስራኤሎች ፍርሃት አይበልጥም” ስላት ቆሌዋ ተገፈፈ። በድንጋጤ “እንዴት እንደዚህ ትላለህ?” ቅብርጥስ እያለች ስትንጣጣ በመሃል አቋርጬ “እስራኤሎች በፍርሃት ቆፈን ተይዘው በራሳቸውና በአረቦች ላይ የፈፀሙት ጥፋት ሁሉም አረቦች በእስራኤሎች ላይ ከፈፀሙት ጥፋትና ጥቃት ብዙ እጥፍ ይበልጣል” ብዬ እቅጩን ነገርኳት።

ሴትየዋ ግን ይበልጥ ስሜታዊ እየሆነች ሄደች። በአንድ በኩል፣ የእስራኤል ወታደራዊ ብቃት እና ከአረቦች ጋር ያደረጓቸውን ጦርነቶች በሙሉ በአሸናፊነት በመጥቀስ “እኛ ማንንም አንፈራም!” ትለኛለች። በሌላ በኩል፣ በሂትለር የተፈፀመባቸውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እና በአሸባሪዎች የተፈፀመባቸውን ጥቃት በመግለፅ “ከዚህ በፊት ተበድለናል፣ አሁንም ይጠሉናል፣ ወደፊት ይበድሉናል፥ ያጠቁናል፥ ያጠፉናል፥…” በማለት በውስጧ ያለውን ፍርሃት ትገልፃለች። 

በእርግጥ በወታደር ጉልበት ላይ የተመሰረተ የበላይነት የፈሪዎች ብልሃት ነው። ፈሪዎች ብቻ ናቸው ሌሎችን በማስፈራራት ነፃነት የሚሰማቸው። ስለዚህ የእስራኤል ወታደራዊ የበላይነት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት በፍርሃት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይጠቁማል። በሌላ በኩል፣ ወታደራዊ ጉልበትና የበላይነት የዜጎችን ፍርሃትና ስጋት አያስወግድም። 

አብዛኞቹ እስራኤላዊያን እንደ ሴትዮ፤ “ትላንት ተበድለናል፣ ዛሬም ይጠሉናል፣ ነገ ያጠቁናል” በሚል እሳቤ የሚመሩ ናቸው። እስራኤል እንደ ሀገርና መንግስት የተመሰረተችው “ሂትለር ጨፍጭፎናል፥ ፍልስጤሞችና ሊባኖሶች ይጠሉናል፣ ኢራኖች በኒዩክለር ያጠፉናል፣…” በሚለው ሰቆቃና ፍርሃት ላይ ነው። ነገር ግን፣ ፍርሃት የነፃነት ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው። 

በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለ ሰው ወይም ማህብረሰብ ነፃነት ሊኖረው አይችልም። ነፃነት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ ሲሆን ፍርሃት ደግሞ የዚህ ተፃራሪ ነው። በግልፅ “እስራኤል የምትባል ሀገር ከምድረ-ገፅ መጥፋት አለባት” የሚል አቋም ከሚያራምዱት ሃማስ፥ ሂዝቦላህና የኢራን መንግስት በተጨማሪ ከ70 አመታት በኋላም አብዛኞቹ የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር ጤናማ ግንኙነት የላቸውም። 

በአጠቃላይ “ትላንት ተበድለናል፣ ዛሬም ይጠሉናል፣ ነገ ያጠቁናል” የሚለው እሳቤ ልክ እንደ ሴትየዋ የአብዛኞቹን እስራኤላዊያን ሕይወትና እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ እንዲሞላ አድርጎታል። ይህ በፍርሃትና ጥርጣሬ የተሞላ ሕይወት ጉዳት የሚያስከትለው በእስራኤላዊያን ላይ ብቻ አይደልም። የእስራኤላዊያን ፍርሃትና ጥርጣሬ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው ከራሳቸው ይልቅ በፍልስጤማዊያን ላይ ነው። 

በመሰረቱ ፍርሃትና ስጋት የሰው ልጅን ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ ይጋርዳል። ምክንያቱም በፍርሃትና ስጋት ውስጥ ያለ ሰው ነገሮችን በምክንያት መገንዘብና መረዳት ይሳነዋል። እንዲህ ያለ ሰው በተጨባጭ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ሊኖረው አይችልም። ከዚያ ይልቅ፣ በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ፣ በአለመተማመንና ጥርጣሬ የተሞላ የፖለቲካ አመለካከት ይኖረዋል። እንዲህ ያለ አመለካከት የራሳችንን ሕይወት በፍርሃትና ስጋት የተሞላ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በሌሎች ሰዎች ላይ እያደረስን ያለውን በደልና ጭቆና ከመገንዘብ ይጋርደናል። 

በመጀመሪያ ደረጃ አብዛኞቹ እስራኤላዊያን “ሙስሊሞች (አረቦች) ይጠሉናል” ከማለት በዘለለ “ለምን ይጠሉናል?” ብለው አይጠይቁም። በመቀጠል “ለምን ይጠሉናል?” ብለው ቢጠይቁ እንኳን ጥያቄውን በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመስርተው ለመመለስ ጥረት ለማድረግ ድፍረትና ነፃነት ሊኖራቸው አይችልም። 

አንድን ነገር በድፍረት ለማወቅና ለመጠየቅ በቅድሚያ ራስን ከፍርሃት ቆፈን ማላቀቅ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ግን በውስጣችን ያለው ፍርሃት በተጨባጭ ያለውን እውነታ ከመገንዘብ ይጋርደናል። ራሱን ከፍርሃት ቆፈን ማላቀቅ የተሳነው፣ በዚህም የአስተሳሰብ ነፃነት የሌለው ሰው “ለምን ይጠሉናል?” የሚለውን ጥያቄ ቢጠይቅ እንኳን “የሚጠሉን ስለሚጠሉን ነው!” ከሚለው ድምዳሜ ሊያልፍ አይችልም። በአጠቃላይ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለ ሰው የፖለቲካ አመለካከቱ ከጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ የዘለለ ሊሆን አይችልም። 

እንዲህ ያለ አመለካከት ልክ እንደ እስራኤላዊቷ ሴትዮ፤ “የሂትለር ናዚ ጨፍጭፎናል፣ ሙስሊሞች (አረቦች) ይጠሉናል፣ ሃማስና ሂዝቦላህ ያሸብሩናል፣ የኢራን መንግስት ሊያጠፋን ይዝታል” እያሉ ዘወትር ፍርሃትና ስጋትን ከመናዘዝ ያለፈ ፋይዳ የለውም። ነገሩን በጥሞና ካጤናችሁት፤ የሴትየዋ አመለካከት “የህወሓት የፖለቲካ አመለካከት” ነው። ሂትለር/ናዚ ጨፍጭፎናል – “መንግስቱ/ደርግ ጨፍጭፎናል”፣ ሙስሊሞች (አረቦች) ይጠሉናል – “አማራዎች (ኦሮሞዎች) ይጠሉናል”፣ ሃማስ – “ግንቦት7”፣ ሂዝቦላህ – “ኦነግ”፣ የኢራን መንግስት – “ኤርትራ መንግስት” ናቸው። የወታደር ጉልበት ስልቱ፣ ፍርሃትና ማስፈራራት የተግባር መርህና መመሪያው ናቸው።