ለመፈንቅለ መንግስት እንኳን “ያልታደለች” ሀገር! 

ባለፈው አንድ የውጪ ሀገር ጋዜጠኛ በዚምባብዌ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት አስመልክቶ “የሮበርት ሙጋቤ ከስልጣን መወገድ በሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ፖለቲካ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል?” የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። በእርግጥ ሮበርት ሙጋቤ ለረጅም አመታት በስልጣን ላይ እንደመቆየቱና “እስከ እለተ-ሞቴ ድረስ ስልጣን አለቅም” ማለቱ ይታወሳል። 

የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በጉዳዩ ጣልቃ-ገብቶ ሙጋቤን የሙጥኝ ካለበት ስልጣን ማስወገዱ የዩጋንዳው ዮሪ ሙሰቬኒ፣ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና የመሳሰሉት የአፍሪካ መሪዎች ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ምክንያቱም እነዚህ መሪዎች የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ የሀገሪቱን ሕገ-መንግስት “ያሻሻሉ” ናቸው። በዚህም ልክ እንደ ሙጋቤ ከሕግ አግባብና ከሕዝቡ ፍላጎት ውጪ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ያሉ መሪዎች ናቸው። 

ስለዚህ ዚምባብዌው የጦር አዛዥ ሙጋቤን ከስልጣን ሲያስወግደው የዩጋንዳና ሩዋንዳ የጦር መሪዎች ሌላው ቢቀር “ይሄም አለ ለካ!” ማለታቸው አይቀርም። አያ ጅቦ “ይዘገያል እንጂ አህያ የእኔ ናት” እንዳለው፣ ይዘገያል እንጂ ሙሰቬኒና ፖል ካጋሜ ልክ እንደ ሙጋቤ በመፈንቅለ መንግስት ይወገዳሉ።

በመቀጠል ጋዜጠኛው “የሙጋቤ ከስልጣን መወገድ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ላይ ምን ዓይነት አንድምታ ይኖረዋል?” በማለት ጠየቀኝ። በእርግጥ ማንም፥ መቼምና የትም ይሁን፣ ከሕዝብ ፍቃድና ምርጫ ውጪ የሆነ መሪ የተከበረበት ስልጣን ያዋርደዋል። ምክንያቱም በክብር ተጠይቆ አልወርድም ያለ መሪ ሁሉ በግድ ተገፍትሮ ይወድቃል። ከሮበርት ሙጋቤ ይህን ልንማር እንችላለን። ነገር ግን፣ እሱ ራሱ ከመንግስቱ ኃይለማሪያም አልተማረም። የእኛ ሀገር መሪዎችም ከሙጋቤ የሚማሩ አይመስለኝም። 

ከዚህ በተረፈ በኢትዮጲያና ዚምባብዌ መካከል የምድርና ሰማይ ያህል ልዩነት አለ። ልክ እንደ ኢትዮጲያ በዝምባብዌም የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ እርግጥ ነው። ልክ እንደ ሮበርት ሙጋሜ የእኛ ሀገር መሪዎችም የስልጣን ሱሰኞች ናቸው። ከቀበሌ ሊቀመንበር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን መውርድ “መዋረድ” ይመስላቸዋል። 

ልክ እንደ ሮበርት ሙጋቤ አፄ ኃይለስላሴም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን መወገዳቸው ይታወሳል። በመንግስቱ ኃይለማሪያም ላይም ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል። እንደሚታወቀው ጓድ መንግስቱ የመፈንቅለ ሙከራ ያደረጉትን የጦር መሪዎች፤ “ቂጣቸውን በሳንጃ ወጋናቸው?” ይሁን “ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው!” ብሎ ፎክሯል።

ነገር ግን፣ አሁን ያሉት የጦር ጄኔራሎች የመፈንቅለ-መንግስት ቢያደርጉ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚያመጡት ለውጥ የለም። ምክንያቱም፣ የመከላከያ ሰራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ያላቸው የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ከህወሓቱ ሊቀመንበር ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። ከታች በፎቶው ላይ እንደሚታየው የኢትዮጲያ የጦር አዛዥ የህወሓትን አርማና ዓላማ ይራምዳሉ። 

ጀ/ል ሳሞራ ዬኑስ

የጦር አዛዡ ሲገርመን ከሰሞኑ ደግሞ የሀገሪቱ የመረጃና ደህንነት ባለስልጣን ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌታቸው አሰፋ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነዋል። አቶ ጌታቸው የሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊ እንደመሆናቸው መጠን በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉ ይገመታል። ይህን የማድረግ ስልጣን የተሰጣቸው የሀገርና ሕዝብን ደህንነት ለማስከበር እንጂ የህወሓትን የፖለቲካ አጀንዳ እንዲያስፈፅሙ አልነበረም። 

ይህን የዊኪሊክስ መረጃ ማንበብ ስለ አቶ ጌታቸው የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ጥሩ ምልከታ ይሰጣል። እንዲህ ያለ የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን እንደ ወንጀል የሚቆጥር ግለሰብ የአንድ ሀገር የመረጃና ደህንነት ኃላፊ መሆኑ በራሱ ያሳቅቃል። በዚህ ላይ አንድን ብሔር የሚወክል የፖለቲካ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባል መሆናቸው ደግሞ እጅግ በጣም ያስገርማል። አንዳንድ የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎች የአቶ ጌታቸው አሰፋ የፎቶ ምስል “የላቸውም” ብለው ሲለጥፉ ማየት ደግሞ የባሰ ያስቃል። 

አቶ ጌታቸው የህወሓት ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል ነው። ስለዚህ ህወሓቶች የሚያውቁት እኛ የማናውቀው ሰው በሁላችንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ይወስናል። እንበልና በህወሓትና ኦህዴድ ወይም ብአዴን መካከል አለመግበባትና ልዩነት ቢፈጠር፣ እንደ ድርጅቱ አባል የህወሓትን አጀንዳ ለማስፈፀም ይስራል። 

ልክ ጉዳዩ እየከረረ ሄዶ የህወሓትን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚነካ ሆኖ ሲገኝ የሀገርና ህዝብን ደህንነት እንዲያስከበር የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት የድርጅቱን ጥቅምና የበላይነት ለማስከበር ይጠቀምበታል። ከመረጃና ደህንነቱ ኃላፊ ጎን ደግሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ዋና አዛዥ ይከተላል። በዚህ መልኩ የሀገሪቱ የደህንነትና መከላከያ መዋቅርና የሰው ኃይል የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ ይውላል። 

የህወሓት/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባላት

መቼም ከሀገሪቱ የመከላከያና ደህንነት መዋቅር ውጪ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ አይታሰብም። እነዚህ ሁለት መስሪያ ቤቶች አደረጃጀት ደግሞ የህወሓትን የበላይነት በማስቀጠል ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ መፈንቅለ መንግስት እንኳን ቢደረግ በእነዚህ ሁለት አካላት ፍቃድና ድጋፍ እንደመሆኑ ዓላማው የህወሓት የበላይነት ማስቀጠል ይሆናል። በአጠቃላይ፣ የአሁኗ ኢትዮጲያ ለሰላማዊ ለውጥ ቀርቶ ለመፈንቅለ መንግስት እንኳን ያልታደለች ሀገር ናት። 

One thought on “ለመፈንቅለ መንግስት እንኳን “ያልታደለች” ሀገር! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡