ከግንባርነት ወደ ንቅናቄ፡ የኢሕአዴግ የግንባርነት ጉዞና ቀጣይ ፈተናዎቹ! 

በብንያም ነ. መንበረወርቅ

የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ የታወጀው የ«አዲሱን ሥርዓት» ቁልፍ የመጫዎቻ ሕጎችን በመቅረፅም ሆነ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ በዋነኝነት በመወሰን ረገድ ከኢሕአዴግ ጋር ለንፅፅር የሚቀርብ ሚና ቀርቶ፣ ትርጉም ባለው መልኩ አሻራውን መተው የቻለ የፖለቲካ ኃይል ነበረ ወይም አለ ብሎ በድፍረት ለመናገር ያስቸግራል። ኢትዮጵያ በይፋዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር ያካሄደቻቸውን አምስት አጠቃላይ ምርጫዎች በክልልም በፌዴራልም ደረጃ በሰፊ ልዩነት በማሸነፍ፣ አጋሬ ከሚላቸው ከሥጋው ሥጋ ከነፍሱ ነፍስ የእነሱ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር ከቀበሌ እስከ «ማዕከል» አገሪቱን በመቆጣጠር፣ በግዙፍ የመንግሥትና የፓርቲ የንግድ ተቋማት ላይ የያዘውን የበላይነት ሳያላላ በማስቀጠል፣ የአገሪቱ ልብና ነፍስ ሆኖ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት ዘልቋል።

ከዚህም ባሻገር ድርጅቱ በዘንድሮው ምርጫ በየሕገ መንግሥታቱ የመንግሥት ትልቁ ሥልጣን ባለቤት እንደሆኑ የተደነገገላቸው የአስፈጻሚው አካል የሥልጣን ምንጭ የሆኑት ምክር ቤቶችን መቀመጫ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን መቶ በመቶ በማሸነፍ ስላለፈው ብቻ ሳይሆን፣ በመጪውም ጊዜ የግንባሩ ፈርጣማ ጡንቻ ሳይኮማተር እንደሚቀጥል ፍንጭ ሰጥቷል። ግንባሩ አማራጭ የማይቀመጥላቸው ብቸኛ  የለውጥ መንገድ መሆናቸውን የሚገልጽ ታርጋ እየሰጠ የሚተልማቸው የረጅም ጊዜ ዕቅዶችም፣ ግንባሩ ከአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ጋር ራሱን አጣብቆ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ያለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመገንዘብ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም አቅም በፈቀደ መንገድ ለመፈተሽ የሚቻለው ከሌሎች መካከል «መሪ ተዋናይ» የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አደረጃጀት፣ አሠራር፣ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች በመመርመር ነው። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በመክተት በዚህ ጽሑፍ በቅርቡ አሥረኛ ጉባዔውን ያካሄደውን ኢሕአዴግ የግንባርነት ጉዞ በወፍ በረር በመዳሰስ፣ ግንባሩ በድርጅታዊ አወቃቀሩ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመንቀስ በዚሁ ረገድ የሚጠቀሱ ፈተናዎችን ለመፈተሽ ይሞክራል፡፡

የግንባሩ ዘፍጥረት

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በዚህ ቀን ተቋቋመ ተብሎ የሚታወቅ ቁርጥ ያለ ቀን ባይኖርም፣ የሁለት ፓርቲዎች ግንባር ሆኖ የመመሥረቱ ወሳኝ ሒደት የተከናወነው በ1980/1981 ዓ.ም. ነበር፡፡ የግንባሩ መሥራች አባላትም ሕወሓት (ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) እና ኢሕዴን/ብአዴን (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ነበሩ፡፡ በኢሕአዴግ በኩል የተዘጋጁ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፣ ድርጅቶቹ በ1980 ዓ.ም. ግንባር ለመፍጠር በመወሰን በ1981 ዓ.ም. የጋራ ፕሮግራም በማውጣት ለአባላት እንዲበተን ተደረገ።

ምንጫቸው ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የሚቀዳው የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች የግንባር ምሥረታ የፀረ ደርግ ካምፑን አስተባብሮ አምባገነናዊ ሥርዓቱን ማስወገድና በድኅረ ደርግ ኢትዮጵያም ቁልፍ ሚና መጫወት የሚችል ድርጅታዊ አቋም መገንባትን ዓላማው ያደረገ ነበር። የግንባሩ አንጋፋና ሰብሳቢ የሆነው ሕወሓት በ1967 ዓ.ም. ተመሥርቶ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚመራውን ወታደራዊ መንግሥት በትጥቅ ትግል ለመገርሰስ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ አካባቢ ያደረገው ተጋድሎ ፍሬ እያፈራ ወደ መሀሉ አገር የመግፋቱ ጉዳይ አይቀሬ እየሆነ ሲመጣ፣ ከትግራይ ክልል ውጪ ባለው የኢትዮጵያ ክፍል ተቀባይነት ሊኖራቸው ከሚችሉ ኃይሎች ጋር ግንባር መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡ ምንም እንኳ ድርጅቱ ሥልታዊም ሆነ ስትራቴጂካዊ ግንባር የመመሥረት አስፈላጊነት ላይ አዎንታዊ አቋም ከወሰደ ያረፋፈደ ቢሆንም፣ በወቅቱ  የተነሳው መሠረተ ሰፊ አገር አቀፍ ግንባር የመፍጠር ጉዳይ ግን ጊዜ የሚሰጥ አልነበረም። ለዚህ ዓላማ ስኬትም ሕወሓት ከአሕአፓ/ኢሕአሠ በተነጠሉ ጥቂት ግለሰቦች በነፃ አውጪ ንቅናቄው ድጋፍ ራሱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄነት ያደራጀውና በፕሮግራምም ተመሳሳይ ከሆነው ኅብረ ብሔራዊ ኃይል ጋር ግንባር ለመፍጠር በመወሰን የጋራ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ይፋ ሆነ፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች በኤርትራ ጥያቄ፣ በሕዝቦች «የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል» በሚለው መርህና በመሰል ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አንዱን ካንዱ ነጥሎ ማየት በማይቻልበት ሁኔታ ዓይነት አንድ አቋም ነበራቸው።

የግንባሩ ምሥረታ ቋንጣ ወሬ ሳይሆን ህልውና ያገኙት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኰንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአን) የግንባሩ አባል ወደ መሆን በመምጣታቸው፣ ኢሕአዴግ የመጀመሪያ ጉባዔው የካቲት 1983 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ቆላ ተምቤን ሲያካሂድ የአራት ድርጅቶች ግንባር ወደ መሆን ተሸጋግሮ ነበር (አቶ ገብሩ አሥራት ኢዴመአን ግንባሩ ጋር አብሮ ቢሠራም የግንባሩ አባል እንዳልነበር በመጽሐፋቸው ይጠቁማሉ)። ከድል በኋላ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኰንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአን) የተባለው ድርጅት ፈርሶ፣ አባላቱም በወታደራዊና በሲቪል አገልግሎት ላይ ተመድበው እንዲሠሩ ሲደረግ በእሱ ምትክ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢሕዴግ) የግንባሩ አባል ሆነ። ኢሕዴን ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተቀይሮ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባርም በሥሩ የሚገኙ «ሕዴዶችን» በአንድ አዋህዶ «ደኢሕዴን» ተሰኝቶና አጋር ፓርቲዎችም ከግንባሩ ተለይተው የማይታዩ አካል ሆነው፣ ኢሕአዴግ አሁን ያለውን መልክ ያዘ።

የግንባሩ ዕድገትና የአባል ድርጅቶች የኃይል ሚዛን

ጥምረት፣ ውህደት ወይም ግንባር የሚፈጥሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁሉም መመዘኛ እኩል የሚሆኑበት ሁኔታ በንድፍ ሐሳብ ደረጃ ብቻ የሚገኝ ሀቅ ነው። በተመሳሳይ የድርጅቶች አቅም ወይም ጥንካሬ በጊዜና በሁኔታ ውስጥ የሚዳብርና የሚኮማተር በመሆኑ አቅም ጥንካሬን የማይቀያየር አድርጎ መውሰድ አይገባም። የእነዚህን ጥምረቶች አወቃቀርና ግንኙነት ከሚበይኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው በተወሰነ ሁኔታና ጊዜ ውስጥ ያለው የአባል ወይም ተጣማሪ ፓርቲዎች ሁለገብ ጥንካሬ ነው። የፖለቲካ ማኅበራትን ጥንካሬ ለመለካት የሚያስችል ሁለንተናዊ መሥፈርት ባይኖርም ከሌሎች መካከል የሕዝብ ድጋፍ፣ የመሪዎች ችሎታና ተቀባይነት፣ የአባላት ብዛትና ጥራት፣ የፖሊሲና ስትራቴጂ ግልጽነትና ተቀባይነት፣ የውስጠ ፓርቲ አሠራር፣ በምርጫ ያገኙት የመቀመጫ ወንበር ቁጥርና ፓርቲዎቹ እንወክለዋለን የሚሉት የኅብረተሰብ ክፍል ስፋትን መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህ አኳያ ሲታይ ኢሕአዴግን በአባልነት የመሠረቱትና የተቀላቀሉት ድርጅቶች አቅማቸው ያልተመጣጠነና በዚህ ረገድ በመካከላቸው የነበረው ልዩነትም ከፍተኛ እንደነበር ዕሙን ነው። ሕወሓት ከኢሕዴን ጋር ግንባር ሲመሠርት በድርጅቶቹ መካከል የነበረው አለመመጣጠን አድበስብሰው ሊያልፉት ቢሞክሩ እንኳ የማይቻል ነበር። አቶ ገብሩ አሥራት በመጽሐፋቸው በግልጽ እንደጠቀሱት «በሁለቱ ድርጅቶች መሀል የነበረው የኃይል ሚዛን ልዩነት የሰማይና የምድርን ያህል የተራራቀ ነበር። … ሕወሓት ከፍተኛ ወታደራዊና ድርጅታዊ ዕድገት አሳይቶ በውጭም ቢሆን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በአንፃሩ ኢሕዴን ከበፊቱ የተሻለ የዕድገት አዝማምሚያ ቢያሳይም፣ ዝቅተኛ ዕድገት ደረጃ ላይ ነበር።» በመሆኑም ቢያንስ ግንባሩ በተመሠረተበት ወቅት ጋብቻውን የእኩዮች አድርጎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡ ይህ ማለት ግን ድርጅቶቹ የነበራቸው ግንኙነት አንዳንዶች እንደሚሉት የአዛዥና የተላላኪ ነበር እንደማለት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። የአቅም ልዩነቱ የሚፈጥረው የማይታለፍ የትልቅና የትንሽ ግንኙነት እንደጠበቀ ሆኖ፣ ይፋዊ በሆነው የኢሕአዴግ ትርክት በገደምዳሜ እንደሚጠቅሱትና ከሕወሓት ክፍፍል በኋላ ተነጥለው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ያሰፈሩ ጎምቱ የግንባሩ የቀድሞ መሪዎች እንደመሰከሩት፣ ኢሕዴን «ለድርጅታዊ ነፃነቱ» ቀናዒ የነበሩ አመራሮችን አቅፎ የያዘና በዚህም በውስጡና ከውጭም ከሕወሓት ጋር የነበረው ግንኙነት አልፎ አልፎ የሚሻክርበት ጊዜ ነበር። ሌሎቹ ግንባሩን የተቀላቀሉት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢሕዴግ/ደኢሕዴን) በወቅቱ የነበራቸው አንፃራዊ አቅም ደካማ የሚባል ነበር፡፡ ይህም ቀድሞም በግንባሩ ውስጥ የነበረውን አልተመጣጥኖ ማባባሱ ግልጽ ነው፡፡

በወቅቱ ሕወሓት ከሌሎች የግንባሩ አባላት ጠንካራ እንዲሆን ያበቃው ከሌሎች መካከል በተራዘመ ጊዜ የገጠሩን ሕዝብ ድጋፍና ቁጥጥር ማሳካቱ፣ በፀረ ደርግ ካምፕ ውስጥ በነበረው ትርምስ ሌሎችን አዳክሞና ደምስሶ በአካባቢው አሸናፊ ሆኖ በመውጣቱና በአንፃራዊነት ከደርግ ዕመቃ ራሱን ያተረፈ፣ በውጊያም ሆነ በአስተዳዳር የበለጠ ልምድ ያለው አመራሮችን አቅፎ በመገኘቱ ነው። ከድል በኋላም በአንድ በኩል ይህ ነው የሚባል ተገዳዳሪ የተቃውሞ ኃይል ባልበቀለበት ትግራይ በደምና በመስዋዕትነት ጭምር የተሳሰረ አንፃራዊ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘቱ፣ በሌላ በኩል በአካባቢው ልሂቃን መካከል ትርጉም ያለው ሽኩቻ አለመስተዋሉ ለድርጅቱ ጠንካራ ሆኖ መቀጠል የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱ ዕሙን ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ ከሕወሓት ውጭ ያሉት የግንባሩ አባላት (በመካከላቸው ያለው አልተመጣጥኖ እንደተጠበቀ ሆኖ) በወቅቱ በአመራር ጥንካሬ፣ በአባላት ብዛት፣ በሕዝብ ድጋፍ ረገድ የሚጠቀስ አንፃራዊ ድክመት ቢታይባቸውም እንወክላለን የሚሉት ሕዝብ ሰፊ መሆኑ ፖለቲካዊ ዋጋቸውን ያናረው ይመስላል።

ግንባሩ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሠራዊቱ የአገር ሠራዊት እንዲሆን በመደረጉ ግንባሩ ወታደራዊ ኃይል መሆኑ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ያበቃለት ጉዳይ ሆነ። በዚህም ወታደራዊ ጥንካሬ የአባል ድርጅቶቹ ጥንካሬ ወሳኝ መለኪያ የሚሆንበት ሁኔታ ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነሱ ግልጽ ነበር። ሲቋቋሙ ይህ ነው የሚባል የሕዝብ ድጋፍ ያልነበራቸው ድርጅቶች ቀስ በቀስ የሚወክሉትን ሕዝብ ምሁራንና ልሂቃን በዙሪያቸው በማሰባሰብ ራሳቸውን እያጠናከሩ ለመሄድ ሞክረዋል። በአንፃሩ በግንባሩ አንጋፋና ጠንካራ አባል ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል የተከሰተው ክፍፍል ትልልቅ አመራሮችን አስወግዶ መጠናቀቁ፣ ሕወሓት በግንባሩ ውስጥ የነበረውን የአመራር የበላይነት በእጅጉ የቀነሰ ነው። ክፍፍሉ ሕወሓትን በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይወክሉት ከነበሩት አምስት አባላት መካከል አራቱን ማሳጣቱን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። በተዋረድ በአንጃነት ከተወገዘው ቡድን ጋር ንኪኪ ያላቸው ሕወሓታውያን ምንጠራም ጉዳቱ ቀላል አልነበረም። ሌላው ክፍፍሉ ለሕወሓት ይዞበት የመጣው «ጣጣ» በተቃዋሚ ኃይሎች እምብዛም በማይደፈረው ትግራይ ከሕዝቡ ጎን ሆነው ለዓመታት አስፈላጊውን መስዋዕትነት በከፈሉና በየትኛውም መሥፈርት በትግራይ ሕዝብ ጠላትነት ተፈርጀው ሊጥላሉ በማይችሉ ግለሰቦች የሚመራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበር ብቅ ማለቱ ነው። ይህም ትግራይ ሕወሓት ያለረባ ተቃዋሚ ኃይል መቶ በመቶ የሚያሸንፍባት አካባቢ የመሆኗ ጉዳይ እንዲያከትም ያደረገ ነው። በአንፃሩ የክፍፍሉ መዘዝ ሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶችን ቢነካካም ትርጉም ያለው ዳፋ ሳያሳርፍባቸው ነበር ያለፈው።

ኢሕአዴግ ምርጫ 97ን በምጥ ካለፈ በኋላ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የአባላት ምልመላን ማፋፋም ነበር። ይፋዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግንባሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአባል ድርጅቶችን የአባላት ቁጥር በአንድ ሺሕ እጥፍ በማሳደግ ከሰባት መቶ ሺሕ አባላት ሰባት ሚሊዮን አባላት ያቀፉ ድርጅቶች ግንባር ወደ መሆን ተሸጋግሯል። ይህም የግንባሩን የአባላት ስብጥር በእጅጉ የቀየረ ክስተት ሲሆን፣ የግንባሩ አባል ድርጅት ያላቸው የአባላት ቁጥር የሰማይና የምድር ያህል እንዲራራቅ ያደረገ ነበር።

ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ የግንባሩ የመተካካት ፖሊሲ ነው። የመተካካቱ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን፣ በአባል ድርጅቶቹ ላይ ያሳረፈው ውጤቱ ተመሳሳይ አልነበረም። አንዳንዶቹ አባል ድርጅቶች ቁልፍ አመራሮቻቸውን እያጡ ሲሄዱ፣ ቀድሞውንም በአንፃራዊነት ወጣት አመራር የነበራቸው አባል ድርጅቶች ፖሊሲው የረባ መዘዝ አላስከተለባቸውም። በዚሁ ፖሊሲ ብዙ አመራሮቹን ከግንባሩ የአመራር መዋቅር የገፋው ወይም የተካው ሕወሓት ባልተጠበቀው የአቶ መለስ ሞት በብቸኝነት ይዞት የነበረው የሊቀ መንበርነት ቦታ ከእጁ ያፈተለከበት ሁኔታ ተፈጠረ። የሕወሓት፣ የግንባሩና የአገሪቱ ቁልፍ ሰው ሆነው የቆዩት የአቶ መለስ ሕልፈት የሕወሓትን አቅም የቀነሰ ከመሆኑም ባሻገር፣ በግንባሩ ውስጥ የነበረውን የኃይል ሚዛን ትርጉም ባለው መልኩ ያናጋ አድርጎ መውስድ ስህተት አይሆንም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ ውስጥ በትግል የተሳተፉ ስለኢሕአዴግ ለመናገርም ሆነ ኢሕአዴግን ለመምራት የበለጠ የሞራል የበላይነትና ተሰሚነት ያላቸው አመራሮች በመተካካት፣ በዕድሜና በጤና እንዲሁም በተፈጥሮ ሞት ከፖለቲካው ሜዳ ባፈገፈጉ ቁጥር በፓርቲዎቹ መሪዎች መካከል በዚህ ረገድ ያለው ልዩነት እየተዳከመ መሄዱ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ በእሳት ተፈትነው ያለፉ አመራሮችን ተፅዕኖ በመቀነስ ከሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች የተወጣጣው አዲስ ትውልድ አመራር በእኩልነት ራሱን የሚያቀርብበት ዕድል ይሰጠዋል። ይህም የግንባሩን የኃይል ሚዛን በመወሰን ረገድ የተወሰነ ሚና አይጠፋውም።

በግንባር ውስጥ ስላለው የኃይል ሚዛን ሲነሳ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ የአባል ድርጅቶቹ የኢኮኖሚ አቅም ነው። ግንኙነታቸው በግልጽ ባይቀመጥም በእኛ አገር ሁኔታ በፓርቲ ቁጥጥር ሥር ያሉ የኢኮኖሚ ተቋማት በመኖራቸው፣ የፖለቲካ ድርጅቶቹ የገንዘብ አቅም በአባላት መዋጮና በደጋፊዎች ችሮታ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዚህ ረገድ ያሉ ልዩነቶች በጣም ከፍተኛ በመሆናቸው በኃይል ሚዛኑ ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ መንኳሰስ የለበትም። ከሌላ አኳያ ሕወሓት በወታደራዊ፣ በመረጃና በደኅንነት ተቋማት ላይ አለው የሚባለውን ላቅ ያለ ቁጥጥርና ይህንንም የራሱ የ«በላይነት» ለመጠበቅ ይጠቀምበታል የሚለውን የሚያነሱ አሉ። በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ መረጃዎች ቢኖሩም ጉዳዩን በተጨባጭ ማስረጃ እያስረዱ ማብራራት ከባድ መሆኑን በማመን ጠቅሶ ከማለፍ ባሻገር፣ በዚህ ጽሑፍ ጠንከር ያለ ክርክር ማቅረብ አልተሞከረም።

የፖለቲካ ማኅበራትን የሕዝብ ድጋፍ በሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መንገዶች መመዘን የተለመደ ቢሆንም፣ በእኛ አገር እንዲህ ዓይነቱን መረጃ የሚያቀብል እምነት የሚጣልበት ተቋምና አሠራር የለም። በአገራችን ይፋ የሚደረጉት የምርጫ ውጤቶችም ከውዝግብ ፀድተው የማያውቁ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግን የመሠረቱ የፖለቲካ ማኅበራትን የሚያገኙትን የፓርላማ ወንበርና የሕዝብ ድምፅ ተጠቅመን ያላቸውን የሕዝብ ድጋፍ ብንመዝን የምናገኘው ልዩነት ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም። ለምሳሌ በዚህ ዓመት በተካሄደው ምርጫ አራቱም ፓርቲዎች ያሰማሯቸው ሁሉም ዕጩዎች በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት አሸናፊ መሆናቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል። በመሆኑም የሕዝብ ድጋፍን በተመለከተ የሚነሱ አንዳንድ ተገቢ ጥያቄዎችን ቀምሮ ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ ለመድረስ ብዙ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ ጉዳዩን ማቅለል ቢመስልም፣ ከላይ በቀረበው መልኩ አስቀምጦ ከማለፍ ሌላ አማራጭ ለጊዜው የለም።

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ኢሕአዴግ ከጥንስሱ አንስቶ የእኩዮች ግንባር አልነበረም። ከምሥረታው ጀምሮ በብዙ መልኩ ጠንካራ የነበረው ሕወሓት መሪነቱን ይዞ ለበርካታ ዓመታት ዘልቋል። የግንባሩ ምክትል ሊቀ መንበርነትም ከብአዴን ሳይወጣ ቀላል ለማይባል ጊዜ ቀጥሏል። ይኼ ነባሩ የኃይል ሚዛን ግን ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መምጣቱን ቀደም ሲል ለማሳየት ተሞክሯል። ይሁንና በሌላ በኩል የግንባሩ አወቃቀርና አደረጃጀት የአባል ድርጅት ጥንካሬና በመካከላቸው ያለውን የኃይል ሚዛን ሳያገናዝብ ለአባል ድርጅቶች እኩልነት ቅድሚያ የሰጠ ይመስላል። የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የሰሞኑን ጉባዔ አስመልክቶ በድረ ገጹ ያተመው ጽሑፍ እንዳመለከተው ግንባሩ ሲዋቀር የሁለቱ ፓርቲዎች በግንባሩ አመራር ያላቸው ውክልና እኩል ነበር። በሁለቱ ቀዳሚ የግንባሩ ጉባዔዎች የግንባሩን አወቃቀርና በተለያዩ አደረጃጀቶች (ጠቅላላ ጉባዔ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴና ፖሊት ቢሮ) ያላቸውን ውክልና በተመለከተ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ መረጃ ማግኘት ባይችልም፣ በ1990 ዓ.ም. በጅማ ከተካሄደው ሦስተኛ ጉባዔ ያለው የግንባሩ አወቃቀር በአባል ድርጅት እኩልነት ላይ የተመሠረተ ነበር። የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብም የአባል ድርጅት እኩልነት መርህን የሚያረጋግጥ ነው። በስድስተኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የፀደቀው መተዳደሪያ ደንብ የግንባሩን የአደረጃጀትና አሠራር መርሆች ባስቀመጠበት አንቀጽ 7/1/መ ላይ እንደደነገገው፣ «ኢሕአዴግ እኩልነታቸው የተጠበቀ ድርጅቶች ግንባር ነው፤» በመሆኑም ለድርጅቶቹ ጥንካሬ፣ ላገኙት የሕዝብ ድምፅና የፓርላማ ወንበር፣ ለአባላት ቁጥርና ለመሰል ጉዳዮች ቁብ የሚሰጥ አደረጃጀትና መዋቅር ኢሕአዴግ አላበጀም።

ከሰንጠረዥ ማየት እንደሚቻለው አሁን ባለው አወቃቀር ሁሉም አባል ድርጅቶች በጠቅላላ ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ምክር ቤትና በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ያላቸው ውክልና «ተመጣጣኝ» ሳይሆን ተመሳሳይ ነው። የአገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች የሚወሰኑትም ሆነ የሚመከሩበት በፓርቲው ላዕላይ መዋቅሮች መሆኑን ለሚገነዘብ ሰው፣ የአባል ፓርቲዎች በጠንካራው የፓርቲ አወቃቀር ላይ ያላቸው ውክልና ጉዳይ እንደ ቀልድ የሚታለፍ አለመሆኑ ይገባዋል።

ውክልና ከተነሳ አይቀር ሊነሳ የሚገባው አንኳር ነጥብ አጋር የሚባሉት ፓርቲዎች በግንባሩ አወቃቀር ያላቸው ቦታ ነው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው የግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ድርጅቱ ከአጋር ፓርቲዎቹ በጋራ እንደሚሠራ፣ በጋራ አመራር እንደሚሰጥና የግንኙነቱ ዝርዝር አፈጻጸም በኢሕአዴግ ምክር ቤት በኩል እንደሚወጣ ከተቀመጠው ባሻገር፣ በተግባር ፓርቲዎቹ ግንባሩ በማዕከል ደረጃ በሚወስናቸው ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ የለም ማለት ይቻላል። ከኢሕአዴግ የተለየ ቋንቋ ሲናገሩ የማይደመጡት፣ በአፍም በግብርም ከኢሕአዴግ የማይለዩትና በኢሕአዴግ ጉባዔ የአጋርነት መልዕክት ሲያስተላልፉ በይፋ አባል ለመሆን እስከመጠየቅ የደረሱት አጋር ፓርቲዎች አባል ያልሆኑበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።

በመጋቢት 1999 ዓ.ም. «የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግልና አብዮታዊ ዴሞክራሲ» በሚል ርዕስ የታተመ የግንባሩ ኅትመት፣ አጋር ፓርቲዎች አባል ያልሆኑበት ምክንያት፣ «በአካባቢያቸው ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማኅበራዊ መሠረት የሌለ በመሆኑ የተሟላ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ መያዝ ባለመቻላቸው» መሆኑን ያትታል። የቀረበው ምክንያት መፍታታት የሚያሻው በመሆኑ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያስፈልገው ማኅበራዊ መሠረት ምን እንደሆነ? የግንባሩ አባል ድርጅቶች ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማኅበራዊ መሠረት ማግኘት ሲችሉ አጋሮቹ ያንን ማሳካት ሳይችሉ የቀሩበት ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ? ይህ ነገር እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል? እና ተያያዥ ጥያቄዎችን በሚገባ አይመልስም። አጋር ፓርቲዎቹ የበቀሉበት ማኅበራዊ ዓውድ አንዱ ከአንዱ ልዩነት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ እነሱን እንደ ቡድን ከአባል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዓውድ የሚለያቸው ነገር መኖሩ ያጠራጥራል። በተግባር ከድርጅቱ ጋር ተባብረውና በወሳኝ ይፋዊ መስመሮችም ግልጽ የድጋፍ አቋም ወስደው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ድርጅቶችን ውኃ በማያነሳ ምክንያት ከአባልነት ያነሰ ደረጃ ሰጥቶ ከውሳኔ መስጫ ማዕቀፉ መግፋት ተቀባይነት የለውም። በፌዴራሉ የአስፈጻሚ አካል ውስጥ የእነዚህን ድርጅቶች ውክልና ያስተዋለ ሰው ከግንባሩ የኃይል ማዕከል መራቃቸው በጋራ አስተዳደሩ ላይ እንዳይሳተፉ እንቅፋት እንደሆነባቸው ቢገምት ስህተት አይመስልም።

ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የኢሕአዴግ መዋቅር ከአባል ድርጅቶቹ ድርጅታዊ ጥንካሬ የሚመነጨውን በድርጅቶቹ መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን ግምት ውስጥ የሚከት አይደለም። የድርጅቱ አሠራር እኩልነትን ብቻ የሚያሰፍን ነው። (በእርግጥ ይኼ ሁኔታ በአገሪቱ ፌዴራል ሥርዓት ፍፁም ባልተመጣጠነ ሁኔታ ክልሎች በሕዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት፣ በሀብትና በኢኮኖሚያዊ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተለያይተው ከተቀረፁበት ሁኔታ የሚመነጨውን ፖለቲካዊ አልተማጣጥኖ ‘Political Asymmetry’ በማለስለስና በማቀዘቀዝ፣ በሌሎች ፌዴራል ሥርዓቶች ሁለተኛዎቹ ምክር ቤቶች የሚጫወቱትን ሚና እንዲጫወት አስችሎታል። ይህ ዓይነቱ አሠራር ግን ከመዋቅሩ የጎላ አስፈላጊነት አንፃር በመደበኛው ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሊፈታ የሚገባው እንጂ፣ በምርጫ ሊወጣና ሊወርድ በሚችል ፓርቲ ውስጥ መንጠልጠል እንደሌለበት ጸሐፊው ያምናል።) የተለያየ አቅም ያላቸው ፓርቲዎች መካከል የሚጫን እኩልነት ለግዙፎቹ ፓርቲዎች የተሰጠን ውክልና የሚያንኳስስ ከመሆኑም ባሻገር፣ በዚህ አቅማቸውን ባላገናዘበ መዋቅር ሥር ለመቀጠል የወሰኑበትን ምክንያት ለግምት ክፍት በማድረግ ተዓማኒነታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጋል። በሌላ በኩል አጋር የተባሉት የፖለቲካ ኃይሎችን የሚያሳትፍ ለታዛቢም የሚታይ መደበኛ መዋቅር ኢሕአዴግ የለውም። ይህም ሌላው መዋቅራዊ ክፍተቱ ተደርጎ ሊወስድ ይገባል።

የወደፊቱ መንገድ

ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ የአብሮነት ቆይታም በኋላ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ማኅበራት ግንባር ነው። በአሠራሩ እንኳን በጥምረት የተሰባሰቡ ቀርቶ አንድ ወጥ ፓርቲዎች አልፎ አልፎ ብቻ የሚያሳኩትን ውህደትና ማዕከላዊነት ያሳካ ቢመስልም፣ አሁንም ከግንባርነት ወደ ላቁ አደረጃጀቶች ሲያማትር አይታይም። ውህደትን በተመለከተ አንዳንድ አፈተለኩ የተባሉ ወሬዎች የወጡ ቢሆንም፣ ግንባሩ በዚህ ረገድ ይፋዊ የአቋም ለውጥ እንደሚያደርግ ጠቁሞ አያውቅም። እንደ እኔ እምነት ድርጅቱ ከላይ የጠቆምኳቸውን የመዋቅር ግድፈቶች ያለከፋ መንገራገጭ በሚገባ ሊፈታቸው የሚችለው ውህደት በመፈጸም ነው። በተግባር እኩል ያልሆኑትን አባል ድርጅቶች አጣቦ በተመሳሳይ በር የሚያስገባውን የእኩልነት መርህ ተፃረው «ለእኔ ይኼ ያንሰኛል» የሚል ጥያቄ ሳያነሱ፣ ጉዳዩም የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ በደጋፊም በነቃፊም ሳይነሳ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃ መውስድ ብልህነት ነው።

በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ያስቀመጣቸው ኢሕአዴግ ከእንዲህ ዓይነቱ አደረጃጃት ይልቅ ግንባርነትን የመረጠበት ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም። መተዳደሪያ ደንቡ እንደሚያትተው «ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር እንደመሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስቡ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን፣ የድርጅቶችን በተለይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት አማካይነት ነው፤» ይህም አወቃቀር ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንደሚመልስ መተዳደሪያ ደንቡ ያስቀምጣል። የመጀመሪያው ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥቅማቸውንና መብታቸውን ለማስከበር፣ የተሻለ ድርጅታዊ አመራር ለማግኘትና በፖለቲካ ሒደቱ በበለጠ ለመሳተፍ የብሔር ድርጅቶች ተመራጭ እንደሆኑ በተግባር መታየቱ ነው። ሁለተኛው ምክንያት እነዚህ የብሔር ድርጅቶች በተናጠል ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ዓላማዎች የሚመራ ኅብረ ብሔር የጋራ ግንባር መንቀሳቀሳቸው በኢትዮጵያ «ብሔር ብሔረሰቦች ሰፊ ሕዝብ መካከል ፅኑ ወንድማማችነትና አንድነት ለማዳበር» አስፈላጊ መሆኑ ነው።

ከላይ በቀረበው አቀራረብ በሕገ መንግሥቱ በቀላሉ እንዳይሸራረፍ ሆኖ ዕውቅና ያገኘን መብት ተግባራዊ ለማድረግ የብሔረሰብ ድርጅቶች የበለጠ ምቹ የሆኑበት ምክንያት በግልጽ አልተቀመጠም። ለብሔረሰቦች መብት ቁርጠኛ የሆነ አገር አቀፍ ድርጅት በየትኛውም አደረጃጃት ቢዋቀር ግልጽ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን ከመተግበር የሚያፈገፍግበት ምክንያት አይኖርም። የዕይታው መነሻ ተግባራዊው ተሞክሮ ከሆነ ይኼኛው አማራጭ ተሞክሮ ድክመት ስላላሳየ አንዱ ካንዱ ይሻላል ማለት አያሳምንም። ክርክሩ ከተወሳሰበው የግንባር አወቃቀር ይልቅ በተዋሀደ ንቅናቄ ማዕቀፍ የብሔረሰብ መብቶች ተግባራዊነትን የሚያሳልጡ መዋቅራዊ ፈጠራዎችን መቀየስ የሚቻልበትን አማራጭ ፉርሽ አያደርግም። በተግባር እንደታየው የግንባሩ አባል የሆነው ደኢሕዴን የብሔረሰብ ድርጅቶችን አዋህዶ አንድ ንቅናቄ መሥርቶ የተንቀሳቀሰበት አግባብ የቀደመውን ክርክር የሚያጣጥል ነው። በዚህ መልኩ የሚታየው የተወሰኑ ግንባር የነበሩ አጋር ፓርቲዎች ከግንባርነት በውህደት ራሳቸውን የቀየሩበት አንዱ ምክንያት፣ በግንባር መሥራት ውስጥ ያሉ ውስብሰብ ችግሮችን በቀላሉ ለመሻገር ነው። የቀረበው ክርክር በመጠኑ ሲለጠጥ በብአዴን የታቀፉ የዋግ ኽምራ፣ የኦሮሞ፣ የአዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊያን የራሳቸውን ፓርቲ ማቋቋም ይገባቸዋል እንደማለት ነው። በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኩናማዎችም እንደዚያው። በመንግሥት አወቃቀር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ያለ ገደብ ተረጋግጧል። በዚህ ረገድ የሚነሱ ሥጋቶች በመደበኛው አሠራር መፍትሔ አላቸው። ኢሕአዴግ በምርጫ ተወዳድሮ የመንግሥትን ሥልጣን የሚይዝ ድርጅት እንጂ መንግሥትን የሚተካ ተቋም ባለመሆኑ፣ ሁሉንም ሥጋቶች በድርጅታዊ አወቃቀሩ እንዲፈታ አይጠበቅበትም። ስለዚህ ኢሕአዴግ አወቃቀሩን ሲወስን ራሱን እንደ ድርጅት መመልከት ይገባዋል።

ሌላው የተነሳው ነገር የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር መሆንና የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት ሰብስቦ ለማታገል የሚቻለው በብሔር ድርጅቶች ግንባር መሆን ነው። ሲጀምር ኅብረ ብሔራዊ አገር ለመሆን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ አገር አይደለችም። በምናልባት ከሚጠቀሱት ጥቂት አገሮች ውጪ የብሔረሰቦች ስብጥርና ታሪካዊ ግንኙነት የተለያየ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የዓለም አገሮች ኅብረ ብሔራዊነት መገለጫቸው ነው። ይሁንና የብሔረሰብ ጉዳይ ወሳኝ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ለአሥርት ዓመታት በዘለቀበት፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም ጉዳዩ ቁልፍ የማጠንጠኛ ማዕከል ሆኖ በተቀመጠበት ሁኔታ የብሔረሰብ ጉዳይን የፖለቲካ ማነሳሻነት ወይም ማታገያነት አቅም ማጣጣል አይቻልም። ይህ ማለት ግን ማታገልና ማነሳሳት በአጀንዳ ዙሪያ እንጂ በመዋቅር መደገፉ የግድ አይደለም። የብሔረሰቦችን መብት ወደ ፖለቲካ መድረኩ ያመጣ፣ የብሔረሰቦችን መብት በማክበርና በማስከበር ከእኔ በላይ ላሳር የሚል ድርጅት ኅብረ ብሔራዊም ሆኖ ምልዓተ ሕዝቡን በዚህ ደረጃ ማነሳሳት ወይም ማታገል ይችላል ብሎ ማሰብ ትክክል ነው። ይህ ውሳኔ የፖለቲካ ዋጋ ያስከፍላል ተብሎ ከተሰጋም የሚመሠረተው ንቅናቄ ክልላዊ ቅርንጫፎች የተወሰነ ነፃነት እንዲኖራቸው በማድረግ ለጉዳዩ እልባት መስጠት ይቻላል። በዚህ ረገድ የደኢሕዴንን ተሞክሮ በሚገባ መርምሮ በተግባር የተፈተሹ ትምህርቶችን መቅሰም ይመከራል።

ኢሕአዴግ የአገሪቱን አብዮታዊ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊያን ግለሰቦችን አስተባብሮ የሚመራ ንቅናቄ ወደ መሆን ቢሸጋገር በግንባርነት መቀጠል ሊፈጠር ከሚችለው ውስብሰብ አሠራርና አይቀሬ ውጥረት ተላቆ፣ አንደኛ የአባላትን ስብጥርና የሕዝብ ውክልናን የሚያንፀባርቅ አመራር እንዲኖረው ያስችላል። ሁለተኛ የእኩልነቱ ገደብ ሳያግዳቸው ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚወከሉ አመራሮች እንደ ብቃታቸው ተፎካክረው ወደ አመራር የሚመጡበትን አግባብ ይፈጥራል። ይህ የተሻለ አመራር ነጥሮ የሚወጣበትን ሁኔታ ክፍት ለማድረግ የሚያግዝ አሠራር የብሔረሰቦችን ውክልና ጨርሶ እንዳያጠፋ ገዳቢ አሠራሮች በማስቀመጥ ከብቃቱም ከውክልናውም አቀናጅቶ እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል። ንቅናቄው የተጠናከረ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ መገንባት ከቻለ አንዳንድ አካባቢዎች በአመራሩ ሳይወከሉ የሚቀሩበትን አግባብ መቀነስም ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም ለአመራርነት የሚበቁ ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የተወሰነ አነስተኛውን ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር ከአንድ አካባቢ ብቻ በሚያገኙት የተከማቸ ድምፅ ወደ አመራር የማይመጡበትን አሠራር በመዘርጋት፣ አንድም በብዙኃን ቁጥጥር ሥር የመውደቅ ሥጋትን ማስወገድ፣ በሌላ በኩልም ከሁሉም አካባቢ ድጋፍ ለማግኘት ለሁሉም አካባቢ የሚበጁ ሐሳቦች የበላይ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። ሦስተኛው የተወሰነ ዓይነት ልዩነት በውስጡ እንዲንሸራሸር ሆኖ፣ በሚደራጀው ንቅናቄ ውስጥ አባላት በይነ ብሔረሰብ የሆነ የማይሰበር ትብብርና ግንኙነት እንዲመሠርቱ በማድረግ ድርጅቱ «ትምክህተኝነትና ጠባብነት» የሚላቸው አመለካከቶች ተዳከመው፣ ዴሞክራሲያዊ አገራዊ አመለካከት ጎልቶ እንዲወጣ ያግዛል። ለማጠቃለል ኢሕአዴግ ራሱን ወደ ንቅናቄነት አሸጋግሮ ለመቀጠል ካልወሰነ ግንባሩና አባል ድርጅቶቹ በጋራና በተናጠል በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የአወቃቀር ክፍተቶች የሚመነጩ ፈተናዎች ጋር መጋፈጣቸው አይቀሬ ይመስላል።

******

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም በፌዴራል ጥናቶች ሁለተኛ ዲግሪ ሲኖራቸው፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው yambinimw@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 ***

ምንጭ:- ሪፖርተር 

2 thoughts on “ከግንባርነት ወደ ንቅናቄ፡ የኢሕአዴግ የግንባርነት ጉዞና ቀጣይ ፈተናዎቹ! 

  1. “ኢትዮጵያ በይፋዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር ያካሄደቻቸውን አምስት አጠቃላይ ምርጫዎች በክልልም በፌዴራልም ደረጃ በሰፊ ልዩነት በማሸነፍ፣ …” ይሄን እውነት ንው ብሎ ለምጽፍ ስው እውቀት ምን ዋጋ አለው?

    Like

  2. “ኢትዮጵያ በይፋዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሥር ያካሄደቻቸውን አምስት አጠቃላይ ምርጫዎች በክልልም በፌዴራልም ደረጃ በሰፊ ልዩነት በማሸነፍ፣….” ይሄን እውነት ንው ብሎ ለምጽፍ ስው እውቀት ምን ዋጋ አለው?

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡