አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ለእነ ንግስት ይርጋ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ታዘዘ::

​ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለአቶ ደመቀ መኮንን መጥርያ አልወጣም

ጌታቸው ሺፈራው 

የአማራ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር አቶ ሙሉጌታ ወርቁ፣ የጎንደር ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል እና ስለ ህዝባዊ አመፁ ማስረዳት ይችላሉ የተባሉ ባለስልጣናት እና የፖሊስ አዛዦች በእነ ንግስት ይርጋ ተፈራ ክስ መዝገብ ስር ለተከሰሱት 6 ግለሰቦች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት አዟል።

ባለስልጣናቱ ህዝባዊ አመፁ በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ ግጭት እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት በሚዲያ ቀርበው ያስረዱ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ህዝባዊ አመፁን ከ”ሽብር” ወንጀል ጋር በማገናኘት ተከሳሾቹ ላይ የ”ሽብር” ክስ መስርቶባቸዋል።

በተጨማሪም ተከሳሾች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሩ ሲሆን የሁለቱ ባለስልጣናት መጥርያ አልወጣም ተብሏል።

በእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ ስር የተከሰሱት ንግስት ይርጋ ተፈራ፣ አለምነህ ዋሴ ገ/ማርያም፣ ቴዎድሮስ ተላይ ቁሜ፣ አወቀ አባተ ገበየሁ፣ በላይነህ አለምነህ አበጀ እና ያሬድ ግርማ ኃይሌ ናቸው።

ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት በህዝባዊ አመፁ እጃቸው እንዳለበት እና የ”ሽብር ወንጀል” ፈፅመናል ብለው በሀሰት እንዲያምኑ ለማድረግ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ሲገልፁ የቆዩ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ንግስት ይርጋ ጥፍሮቿ እንደተነቀሉ በክስ መቃወሚያዋ ላይ ተገልፆአል። ሌሎች ተከሳሾችም ያልፈፀሙትን ፈፅማችሁታል ተብለው በደል እንደደረሰባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

ከባለስልጣናት ባሻገር የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ፕሮፌሰፈር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዶ/ር ያዕቆም ኃይለማርያም እና ሌሎች ምሁራንም በተከሳሾቹ በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረዋል። ምስክሮቹ ለታህሳስ 12/2010 ዓም ቀርበው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ ተፅፎ የነበር ቢሆንም መጥርያው ዘግይቶ በመውጣቱ አልደረሳቸውም። ታህሰስ 12/2010 ዓም ተከሳሾቹ ተነጣጥለን ወደ ችሎት አንገባም በማለታቸው ጉዳዩ ሳይታይ ቀርቷል።

One thought on “አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ለእነ ንግስት ይርጋ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ታዘዘ::

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡