እነ ጌታሁን በየነ ተፈረደባቸው!

የፌደራል ከፍተኛ   ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል  ችሎት  በእነ ጌታሁን በየነ ክስ መዝገብ  በግንቦት 7 የተከሰሱት 9 ግለሰቦች ላይ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል። 1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ  9ኛ አመት ሲፈረድበት፣  2ኛ ተከሳሽ ዶ/ር አስናቀ አባይነህ እና  5ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ንጉሴ  16 አመት ከ6ወር፣ 4ኛ ተከሳሽ ብራዚል እንግዳ 15 አመት ተፈርዶባቸዋል። 2ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ   በዝቅተኛ ደረጃ ተይዞ እንደተፈረደባቸው ፍርድ ቤቱ  ተገልፆአል።
በተጨማሪም 7ኛ ተከሳሽ ያምላክነህ ገዛኸኝ፣ 8ኛ ተከሳሽ አብዱ  ሙሳ እና 14ኛ ተከሳሽ ደመላሽ ቦጋለ እያንዳንዳቸው በ5አመት፣ 12ኛ ተከሳሽ  መቶ አለቃ  ፍቅሬ እሸቱ  4 አመት ከአራት ወር እንዲሁም 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ 3አመት  ከ10 ወር ተፈርዶባቸዋል።
ተከሳሾቹ የተላለፈባቸውን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን “የታገልነው የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው፣ እናንተ ዳኞች ከእነ ሳሞራና አባይ ፀኃዬ በላይ ትጠየቃላችሁ፣ ወያኔ  አንድ አመት አይቆይም…የጫካ ውላችሁ አይሳካም፣ እኛ የታገልነው ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ ነው፣ ህወሓት ይቀበራል፣ነፃ እንወጣለን… ” ሲሉ ተሰምተዋል።  በተጨማሪም የተሰጠባቸውን ውሳኔ በመቃወም ችሎትና ዳኞቹን ዘልፈዋል።