አንዳንድ ነጥቦች በሥራ አስፈፃሚው መግለጫ ዙሪያ

  • 1 ጃንዩወሪ 2018

ኢህአዴግ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ቁልፍ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ በስፋት ስለተነገረ ሁሉም ውጤቱን ሲጠብቅ ነበር። ስብሰባው ከሁለት ሳምንታት በላይ በዝግ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ 2500 በሚጠጉ ቃላት የተዘጋጀ ሰፊ መግለጫ አውጥቷል።

የሥራ አስፈፃሚው መግለጫ በዋናነት ሕዝብን የሚያውኩ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን መመለስ፣ አባል ድርጅቶች ግልፅነትና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍኑ ማድረግ፣ በመንግሥታዊ አገልግሎት ላይ ለውጥ ማምጣት፣ ሕዝብን፣ ምሁራንን እነዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሳተፍ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበርን የመሳሰሉ ሰፊ ጉዳዮችን አካቷል።

መግለጫው ከወጣ በኋላ በርካቶች በይዘቱ ላይ ውይይቶች እያደረጉ ነው። አንዳንድ የመግለጫው ሃሳቦችም ጥያቄን ከማጫር ባሻገር የተለያዩ ትርጉሞችን እያስከተሉ ናቸው።

ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴው ያወጣው መግለጫ ሃገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ቁልፍ ነጥቦችን ያነሳ እንደሆነ የሚገልፁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የሚጠብቁትን ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳዮችን የያዘ አይደለም የሚሉ አሉ።

በተለይ ደግሞ ”መርህ አልባ ግንኙነት” በሚል የተጠቀሰው ሃሳብ በርካቶችን ግራ ያጋባና ለተለያዩ መላምቶች የተጋለጠ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

በተጨማሪም ”በአፍራሽ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የግልና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት አካሄዳቸውን የሚያስተካክሉበት ሁኔታ” ለመፍጠር የተቀናጀ እርምጃ እንደሚወሰድ መጠቀሱ ሌላኛው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው።

የመግለጫው ይዘት

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክና የሥነ-ጥበብ ታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው በተለያዩ ምክንያቶች ከመግለጫው የጠበቁትን አላገኙም።

ለምሳሌም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የመንግሥት ኃላፊዎች ኢትዮጵያዊነታችንን ትተን በአብዛኛው ልዩነታችን ላይ አተኩረናል የሚሉ አንድምታዎች ያሏቸው ንግግሮችን መስማታቸው ነበር።

“እነዚህ ሰዎች ይህንን ጉዳይ ከልባቸው ገዝተውት አንድ ነገር ላይ ይደርሳሉ ብዬ አስቤ ነበር” ይላሉ አቶ አበባው። መግለጫው ግን እንደውም ኢትዮጵያዊነትን ትቶ የብሄርን ጉዳይ የሚያጠናክር በድርጅቱ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ አግኝተውታል።

“የድርጅቱን ድክመት እንጂ ሀገሪቱ ወዴት ትሄዳለች የሚለውን አላሳየም” የሚሉት አቶ አበባው “እውነት ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ዳስሶ መፍትሄ ከማስቀመጥ ይልቅ በፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ግብግብ መፍታት ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኗል” ብለዋል።

ለፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም የኢትዮጵያ ህዝብ እየጠየቀ ያለው እና መግለጫው የተለያዩ ናቸው።

እየተጠየቀ ያለው የሕዝቦች ጥያቄ በአራት ነጥቦች ዙሪያ ነው የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ መግለጫው ግን እነዚህን ጉዳዮች ከመመልከት ይልቅ ሀገሪቱ ውስጥ ጥቃቅን ስህተቶች እና ችግሮች የተፈጠሩ ነው ያስመለሰው ይላሉ።

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህርና ጦማሪ የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ልክ እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ሁሉ የሥራ አስፈፃሚው መግለጫ የተለመደ የፓርቲው ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይናገራሉ።

“እነዚህ የሥራ አስፈፃሚ አባላት በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የለውጥ ፍላጎት ለማፈን አላማ አድርገው እስከተሰበሰቡ ድረስ ምንም ነገር አልጠብቅም” የሚሉት አቶ ስዩም “ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማፈን የሚፈልግ ኃይል 17 ቀን አይደለም 17 ዓመት ቢሰበሰብ ለውጥ አያመጣም ምክንያቱም ለውጡ የተፈጥሮ ሂደቱን ተከትሎ የመጣ ነው” ይላሉ።

የመድረክ ሥራ አስፈፃሚና የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹም የስራ አስፈፃሚው መግለጫ ሕዝባችን የሚጠብቀው አይደለም ብለዋል።

ሕዝቡ እያለ ያለው የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል ሆኖ ሳለ መግለጫው ግን ስለጥገናዊ ለውጥ ያወራል።

ከዚያ ይልቅ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ሀገሪቱ ያለችበት ችግር እንዲፈታ ከመምከር ይልቅ፤ ጠቡን ከግለሰቦች ጋር ያለ በማስመሰል ስህተታችንን ተቀብለናል እንዲህ አይነት ማስተካከያ እናደርጋለን ማለት መፍትሔ አይሆንም። የህዝባችን የትግል እንቅስቃሴንም አይመልስም ሲሉ ያስረዳሉ።

ኢህአዴግ 26 ዓመት ሙሉ አጥፍቻለሁ በሚል የህዝቡን ይሁንታ ለማግኘት ይጥራል። ነገር ግን ይህን እንደ ስልት በመጠቀም ለውጥ አለማምጣት ለህዝባችንም ሆነ ለሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጠቃሚ አይሆንም ሲሉ ይናገራሉ።

https://emp.bbc.com/emp/SMPj/2.16.27/iframe.html

አቶ አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር)

ከዚያ ይልቅ ሀገሪቱንም ሆነ ፓርቲያቸውን ለማዳን ህዝቡ የጠየቀውን ጥያቄ መመለስ ነበረባቸው። ይህ ካልሆነ የህዝብ ጥያቄ መቀጠሉ አይቀርም ብለዋል። ያ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር እንዳይኖር በር ይዘጋል ሲሉ ያክላሉ።

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሚሳተፉ እና በብዛት መንግሥትን በመደገፍ ሃሳቡን በማካፈል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ ዘርአይ ኃ/ማርያም የኢህአዴግ መግለጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ በባዶ ቃላት የተሞላ እና የሀገሪቱን ችግሮች በተጨባጭ ያላገናዘበ ሳይሆን ሀገሪቷና ህዝቦቿ የገቡበትን አዘቅት ፍንትው አድርጎ ያሳየ በመሆኑ “ረክቼበታለሁ” ይላል።

ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ መሰረት ለሀገሪቱ ቀውስ ናቸው የሚላቸውን የራሱ ከፍተኛ አመራሮች ላይም እርምጃ ወስዶ ወደ ተግባር ካልገባ ግን መግለጫው ከወረቀት በዘለለ ትርጉም ሊኖረው አይችልም ይላል።

“መርህ አልባ ግንኙነቶች”

እንደ አቶ ዘርአይ መርህ አልባ ቡድነኝነት ማለት በአስተሳሰብና በዓላማ የማይናኙ ቡድኖች ለጊዜያዊ ጥቅም ሲወዳጁ የሚፈጠረው ግንኙነት ነው። የኢህአዴግ ብሄራዊ ድርጅቶችም የእዚሁ ሰለባ ሆነው መቆየታቸውን የአባል ፓርቲዎቹ መሪዎች በሚያስተዳድሯቸው ሚዲያዎች ሲሰጡት የነበረውን መግለጫ ያስታውሳል።

“የህወሀት እና ብአዴን አመራሮች በግላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት፤ የህወሀት አመራሮች የአማራ ህዝብን እንደእራሳቸው ህዝብ አድርገው አለመውስድ እንዲሁም የብአዴን አመራሮች የትግራይን ህዝብ እንደእራሳቸው ህዝብ አድርገው እስካለመውሰድ ደርሰዋል” ይላል።

በተጨማሪም አቶ ዘርአይ በተመሳሳይ የኦህዴድ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ አመራሮች በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን የድንበር ግጭት ከኢህአዴግ መርህ ውጭ የሁለት ሃገራት ጦርነት እስኪመስል ድረስ ነበር በሚዲያዎቻቸው ሲያሰራጩ የነበረው፤ በማለት የግንባሩ ብሄራዊ ድርጅቶች በመርህ አልባ ግንኙነት ተጠቅተው እንደነበር ያብራራል።

ለአቶ አበባው ግን መግለጫው መርህ አልባ ግንኙነቶች ሲል በሁለት ብሄራዊ ድርጅቶች መካከል የሚኖር ማንኛውም ግንኙነት ያለ ኢህአዴግ እውቅና ሊካሄድ አይችልም የሚል ነው።

እነዚህ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል የተካሄዱ ህዝባዊ ግንኙነቶች በበጎ አልታዩም። እንዲሁም እነዚህ በክልላዊ ወይም በብሄራዊ ፓርቲዎች መካከል በራስ ተነሳሽነት የተካሄዱ ግንኙነቶች የፖለቲካ ጫና ያሳድርብኛል ብሎ የሚፈራ ወገን መኖሩን ያሳያል ይላሉ።

“በእነዚህ ህዝቦች መካከል የሚደረግ የጎንዮሽ ግንኙነት የሚከለከልበት መንገድ የለም። ይህ ለ25 አመታት ሲሰራበት ከነበረው መንገድ በወጣ መልኩ የድርጅቱን አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ስጋትም የፈጠረ ይመስለኛል” ሲሉ ያክላሉ አቶ አበባው።

መግለጫው በኦሮሞና በአማራ ሕዝቦች ግንኙነት ላይ ውሃ የቸለሰ ነው ያሉት ደግሞ ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው። ከዚህ በፊት በውጊያ የተገኘውን መርህ ያለው ግንኙነት ተብሎ አሁን ህዝቦች በሰላም እንቀራረብ፣ እንተሳሰብ በአንድ ጎዳና እንሂድ ሲሉ አንድ መንግሥት ጥሩ አደረጋችሁ ማለት ሲገባው ለጠባብ ጥቅም ሲባል ብሎ እንዴት ይኮንናል ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ ስዩም ልክ እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ሁሉ ይህንን ሃሳብ በጥያቄ ይሞግታሉ።

“በአንድ ሃገር ውስጥ በጋራ ሥርዓት የሚተዳደሩ የጋራ ታሪክ ያላቸው፣ የወደፊት አብሮነት ባላቸው ህዝቦች መካከል በጋራ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው እና የተሻለ ግንኙነት እና ጥምረት መፍጠራቸው በምን መስፈርት ነው መርህ አልባ የሚሆነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል” ይላሉ።

እንግዲያውስ መርሁ ምንድን ነው ብለን ስንል ይህ ግንኙነት እንዳይፈጠሩ ከዚህ በፊት የተቀመጠ የመለያየት፣ ልዩነትን የማጉላት መርህ ነበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ የፓርቲው መርህ እንደሆነ ያሳየናል ይላሉ።

ለአቶ ስዩም ልዩነትን በማጉላት በሁለት ህዝቦች መካከል ቁርሾ እና ቂምን መሰረት ያደረገ ሥርዓት የሚገነባ የአፓርታይድ ሥርዓት ነው።

ህዝቦች እንዲለያዩ እንዳይተባበሩ መስራት እና ከሆነም እርምጃ እወስዳለሁ ማለት ጤናማነት አይደለም ይላሉ አቶ ስዩም።

እንደ አቶ ሙላት ደግሞ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ቦታ የታየውን ከሕዝብ ጋር የመወገን እና ሕዝብ ላይ አናስተኩስም ያሉትን በጎሪጥ የሚያይ ሃሳብ ነው።

https://emp.bbc.com/emp/SMPj/2.16.27/iframe.html

አቶ ስዩም ተሾመ መምህር እና ጦማሪ

“አፍራሽ ዘገባ ያቀረቡ የመገናኛ ብዙሃን”

ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ወደ ጎን ትተው በብሄሮች መካከል ጥርጣሬን በመፍጠር ሲሳተፉ የነበሩ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ከእርምት ጀምሮ፤ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን ጋዜጠኞችም ሆኑ አመራር አካላት ወደ ፍርድ ቤት እስከ መውሰድ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ዘርአይ ያስረዳሉ።

እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ማስተካከያ እናደርጋለን የሚለው ሃሳብ ላይ ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር እና መልሶ የራሱን ድምፅ ብቻ የሚሰማበት ልሳኑ ሊያደርጋቸው ማሰቡን ያሳያል።

ከአሁን በኋላም እያንዳንዱ ዘገባ ርእዮተ አለሙ ልክ መሆኑን እንደሚያረጋግጡ እና ከፈት ብሎ የነበረውን የመገናኛ ብዙሃኑን ነፃነት እንዘጋለን ማለቱ እንደሆነ ያስቀምጡታል።

አቶ ስዩምም ከዶ/ር ዳኛቸው ሃሳብ ጋር ይስማማሉ “ኢህአዴግ የተለየ ሃሳብ ለመስማት ዝግጁ አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ጥያቄ የሚያራምዱ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ደስተኛ አለመሆኑንም ማሳያ ነው” ብለዋል።

ሃሳብ በራሱ የአመፅ እና የብጥብጥ ምክንያት ሊሆን አይችሉም የሚሉት አቶ ስዩም፤ ይልቁንም ክፍተቶችን ለማየት እና ለማስተካከል በር ከፋች ናቸው ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህ ወቅት አንዳንድ የክልል መገናኛ ብዙሃን የፓርቲያቸው ልሳን ከመሆን ወጥተው የሕዝቡን ብሶት ማሰማት ጀምረዋል የሚሉት አቶ አበባው፤ ያንን ያሰሙበት መንገድ ምን ያክል ትክክል ነው የሚለው ሊያጠራጥር ይችላል ብለዋል።

ምናልባት ግን ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ የሚፈልገውን ነገር ብቻ የሚያቀነቅኑ ይሆናል ማለት ነው ይላሉ።

ለአቶ ሙላቱ የሚዲያ ተቋማቱ ውስጥ ውሃ ቀጠነ የሚል የተለመደ ግምገማ ማካሄድ እና በግምገማው ጋዜጠኞቹ ላይ እንደተለመደው አንተ የዚህ ድርጅት ተላላኪ ነህ አንተ ደግሞ ከዚህኛው ወገን ጋር ትሰራለህ በሚል ለማዋከብ እንጂ የሚመጣ ለውጥ የለውም ይላሉ።

ለአቶ ሙላት ከሥርዓቱ ጋር አልወገኑም የሚባሉ ሰራተኞች ከሥራቸው እና ከሃላፊነታቸው መነሳት የሚጠበቅ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች


ምንጭ:- BBC|አማርኛ 

One thought on “አንዳንድ ነጥቦች በሥራ አስፈፃሚው መግለጫ ዙሪያ

  1. Eventhough I did’t expect much from the unjuist, this one is low. Any party against public unity has definitely reached to the climax of fear of loosing it’s power. Because after this point, it is obvious that public trust on the government will never be the same and tough to restor it back.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡