ሁላችንም “የፖለቲካ እስረኞች” ነን!! ፍቱን-ተፋቱን!!

ዛሬ እየተሰማ ያለው ዜና ደስ ይላል። የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት መስማማቱ እየተገለፀ ይገኛል። ይህ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው። ለውጡ እንዴት መጣ ለሚለው “3ኛው ማዕበልና የልማታዊ መንግስት ፈተና” በሚለው ፅሁፌ በዝርዝር ገልጬዋለሁ። 

አሁን የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት የጀመረው በሌላ ምክንያት ሳይሆን በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል እንደ መንግስት ያለውን ቅቡልነት በማጣቱ ነው። ስለዚህ የኢህአዴግ መንግስት የለውጥ እርምጃ የጀመረው ሳይወድ በግድ – የሕልውና አደጋ ስላጋጠመው ነው። ሆኖም ግን፣ የለውጥ እርምጃ መጀመሩ በራሱ መልካም ነገር ነው። ከዚህ ቀጥሎ ሊነሳ የሚገባው መሰረታዊ ጥያቄ “ምን ዓይነት የለውጥ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ?” የሚለው ነው። 

የኢህአዴግ መንግስት ለውጥ ለማድረግ የተነሳበት ዋና ምክንያት ከሕዝቡ የሚነሱ የመብት፥ ነፃነትና ፍትህ ጥያቄዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ ስለተሳነው ነው። እነዚህ ጥያቄዎች በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ነው። ስለዚህ፣ ከኢህአዴግ መንግስት የሚጠበቀው የለውጥ እርምጃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ሥር-ነቀል ለውጥና መሻሻል ማድረግ ነው። 

ከፊል ተሃድሶ (partial reform) ለማድረግ መሞከር ችግሩን ይበልጥ ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ እንደ ኢህአዴግ ያለ ፈላጭ-ቆራጭ መንግስት ያለው ብቸኛ አማራጭ ሙሉ ተሃድሶ (full reform) ማድረግ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ሕልውናውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት “በየትኛው ዘርፍ ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል ማድረግ ይጠበቅበታል?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ 

በመጀመሪያ ደረጃ ከሕዝቡ እየተነሳ ያለው ጥያቄ የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የሚያስፈልጉት ለውጦች ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ በማለት ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ 

1ኛ፡- ፖለቲካዊ ተሃድሶ (Political reform)

የፖለቲካዊ ተሃድሶ መሰረታዊ ዓላማው የብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ሥርዓት – ዴሞክራሲን መገንባት ነው፡፡ ይህ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ምንም መሸራረፍ ማክበርና ማስከበር ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያየ ግዜ የወጡና የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድቡ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እንዲሁም ከሕገ-መንግስታዊ መርሆች ውጪ የሆኑ ሥራና አሰራሮችን በዘላቂነት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ሊያከናውናቸው የሚገቡ ዋና ዋና የለውጥ ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡- 

  1. የታሰሩ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣
  2. የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድቡ ለምሳሌ የፀረ-ሽብር አዋጁን መሻርና ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደገና ማርቀቅ፣ 
  3. የመንግስትና የግል ሚዲያ ተቋማትን ሥራና አሰራር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ማድረግ፣ ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነውን የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ እንደገና ማርቀቅ፣ 
  4. የሙያና ሲቪል ማህበራት በሀገሪቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ከዚህ አንፃር ለተቋማቱ አንቅስቃሴ ማነቆ የሆነውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ማዘጋጀት፣ 
  5. የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን “ፀረ-ስላም…ፀረ-ሕዝብ…ፀረ-ልማት” ብሎ በመፈረጅ የጠላትነት መንፈስ ከማዳበር ይልቅ መልካም ግንኙነት በማዳበር ለብሔራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣

2ኛ፡- አስተዳደራዊ ተሃድሶ (Administrative reform)

ከሕዝቡ እየተነሱ ያሉትን ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን በማከበር ብቻ ምላሽ መስጠት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም፣ ሕዝቡ ከመብትና ነፃነት በተጨማሪ በመልካም አስተዳደር እጦት ክፉኛ ተማሯል፡፡ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተነሱ ያሉት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ተሃድሶ በተጨማሪ በመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣት አለበት፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል በቅድሚያ ብቃት ያለው አመራር ሊኖር ይገባል፡፡ ነገር ግን፣ በመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር፣ እንዲሁም በሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ እና ልማት ተቋማት በሙያተኞች ሳይሆን በፖለተካ ተሿሚዎች የሚመሩ ናቸው፡፡ 

ይህ ከሙያዊ ብቃት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ አመራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ፖለቲካዊ መዋቅር ጥራት ያለው አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ዋና ማነቆ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ማድረግ ካልተቻለ ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም፡፡    

የኢህአዴግ የፖለቲካ ሹመኞች በተለይ ከሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ ማስወጣት አለበት፡፡ “ኢህአዴግ ቢሸነፍም-ባይሸነፍም ለውጥ አይመጣም” በሚለው ፅሁፍ በዝርዘር ለማሳየት እንደተሞከረው፣ የሀገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ መዋቅሩ በፖለቲካ ሹመኞች የሚመራ እስከሆነ ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግርን በፍፁም መቅረፍ አይቻልም፡፡

ከአመራር ብቃት ማነስ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ሹመኞች በአመራር ወጥመድ (leadership trap) የተጠለፉ እንደመሆናቸው ለለውጥና መሻሻል ዋና እንቅፋት ናቸው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ ተሃድሶ በተለይ የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ከታማኝ ፖለቲከኞች እጅ አውጥቶ ብቃት ላላቸው ሙያተኞች መስጠት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆነ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በመዘርጋት የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል፡፡ 

ከላይ በዝርዝር ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በቀጣይ ሥር-ነቀል የሆኑ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ለውጦችና መሻሻሎች ነፃና ገለልተኛ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ ገደብና ጫና በነፃነት ተንቀሳቅሰው ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁና መራጮችን እንዲቀሰቅሱ፣ የሲቪል ማህበራት በምርጫው ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ምርጫ ቦርድና የሚዲያ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ፣ እንዲሁም የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና በአደባባይ አቤቱታቸውን የመግለፅ መብታቸው እንዲከበር፣  የሀገሪቱ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ከገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ በፀዳ መልኩ ለሕዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይጠይቃል። 

የኢትዮጲያ ሕዝብ በሙሉ የፖለቲካ መብትና ነፃነቱን አጥቷል። ከዚህ አንፃር፣ “የሀገሪቱ ሕዝብ በሙሉ የፖለቲካ እስረኛ ነው” ማለት ይቻላል። ስለዚህ የኢህአዴግ መንግስት “ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ለመፍታት ከወሰነ የሀገሪቱ ሕዝብ እንዳለ መፈታት አለበት። አሁን የኢህአዴግ መንግስት “የፖለቲካ እስረኞች” የሚለው እስር ቤት ውስጥ የዘጋባቸውን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን፣ እንደ “Khalil Gibran” አገላለፅ፣ ሁላችንም የፖለቲካ እስረኞች ነን!!! ሁላችንንም ፍቱን-ተፋቱን