የዓመታት አፈና ያስከተለው የፖለቲካ ቀውስ

በማህበራዊ ሚዲያዎች የፖለቲካ ጉዳዮችን በመሄስ፣ ጥናትን መነሻ ያደረጉ ፅሁፎችን በማቅረብ እንዲሁም ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመተንተን የሚታወቁት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመን፤ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንቅስቃሴና አካሄድ እንዲሁም የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሃሳብና ምልከታቸውም በየርዕሱ እንደሚከተለው ተቀናብሮ ቀርቧል፡፡ (አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

  መምህርና ጦማሪ ስዮም ተሾም

ድህረ ምርጫ 97 እና የድንጋጤ እርምጃዎች  
በ2008 ዓ.ም የተጀመረውን ሁኔታ ለመመልከት ወደ ኋላ ተመልሰን ምርጫ 97ን ማስታወስ አለብን። ለዚህ ደረጃ የበቃነው ከ1997 ምርጫ በኋላ በተፈጠሩ ፖለቲካዊ የለውጥ ሂደቶች ነው። በ97 በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ነበር። ገዥው ፓርቲም ስልጣኑን ህዝባዊ ቅቡልነት እንዳለው ለማስመሰል  ምርጫውን በአንፃራዊነት ነፃ ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ነፃ ነበሩ፡፡  ምሁራን፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎች የሀገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ፣ በግልፅና በድፍረት በሀገራቸው ጉዳይ እንዲነጋገሩ ዕድል ያገኙበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርጫው ተካሄደ፡፡ የምርጫው ውጤት ይፋ ሲደረግ ግን ኢህአዴግ ክፉኛ ነበር የደነገጠው፡፡ ያ ድንጋጤው ለተከታታይ አስራ ምናምን ዓመታትም አልለቀቀውም፡፡
 በዚህም የተነሳ ከምርጫው በኋላ ኢህአዴግ የአፈና እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ፡፡ በ2001 ዓ.ም የፀረ ሽብር አዋጅ ወጣ፡፡ በዚያው ዓመት የሚዲያ አዋጅ ወጣ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ወጣ። በቅርቡ ደግሞ የኮምፒውተር አዋጅ ወጥቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ የድንጋጤ እርምጃዎች ናቸው፡፡ የፍርሃት ውጤቶች የሆኑት እነዚህ አዋጆች፣ በህዝቡ ላይ የበለጠ ሸምቀቆውን የሚያጠብቁ ነበሩ፡፡ 
የፀረ ሽብር ህጉ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ጠንካራ ፖለቲከኞችን ከመድረኩ አግልሎ፣ አሁን የተቃውሞ ፖለቲካ የለም ከሚባልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ ፀረ ሽብር ህጉ ከወጣ በኋላ ከ60 በላይ ጋዜጠኞች ሃገር ጥለው ወጥተዋል፡፡ 10 ያህል እስር ቤት ገብተዋል፡፡ በርካታ ፖለቲከኞች እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅም በርካቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓል፡፡ የሚዲያ አዋጁም አማራጭ፣ ገለልተኛ ነፃ ሚዲያ እንዳይኖር ነው ያደረገው፡፡ ጋዜጦችና መፅሄቶች በጅምላ ተከስሰው እንዲዘጉ ሲደረግም አይተናል፡፡ ከዚያ በኋላ በ2002 በተደረገ ምርጫ፣ ገዥው ፓርቲ 99.6 በመቶ በሆነ ድምጽ አሸነፍኩ አለ፡፡ ቀጠለናም በ2007 በተደረገው ምርጫ፣ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ አረፈው፡፡ ይሄ እንኳን በማህበራዊ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስም እንኳን ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ እንዴት ተመሳሳይ ሀሳብ ሊኖረው ይችላል? በአጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ መዋቅሩ ነው የተሰባበረው፡፡ በዚህ ደግሞ ወደ ሁሉን ጠቅላይ መንግስትነት (Totalitarian state) ነው የተሸጋገርነው፡፡ በሂደትም ፈፅሞ አምባገነን የሆነ መንግስትን ነው እየገነባን የመጣነው፡፡  
ተቃዋሚ ከጠፋ፣ ነፃ ሚዲያ ከጠፋ፣ እያንዳንዱ ጉዞ የጨለማ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ እንኳን ሌላውን ገዥውን መንግስትም ሳይቀር ያስፈራዋል። ሲፈራ ደግሞ በጨለማው ውስጥ ከፊቱ ያለውን ነገር ሁሉ እየደነበረ፣ በኃይል ለመድፈቅ መሞከሩ የግድ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ነው እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰን፡፡ የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ  ሲነሳ የመጀመሪያ እርምጃው ሃይል ነበር፡፡ ሰልፍና ስብሰባም በገዥው ፓርቲ ፍቃድ ብቻ የሚሰጥ ሆኖ ነው ያየነው፡፡ ህዝብ ደግሞ በታፈነና ጫና በበዛበት ቁጥር ብሶቱ እየተባባሰ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ከ2008 ጀምሮ እስካሁን የምንመለከተው፣ ከ1997 ምርጫ በኋላ የተፈጠረው የ10 ዓመታት የአፈና እና ህዝብን አማራጭ የማሳጣት ውጤት ነው፡፡ 
የለውጥ ፍላጎትን ማስቆም ይቻላል? 
አሁን ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ላይ ተደርሷል፡፡ ይሄ ተፈጥሯዊም ሆኗል፡፡ ይሄን ተፈጥሮአዊ የሆነን ጉዳይ ለማስቆምና እንደ በፊቱ ለመቀጠል መፈለግ የትም አያደርስም፡፡ አሁን ያለው የለውጥ ፍላጎት ደግሞ በህዝቡ፣ በፖለቲካ ልሂቃኑና በገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ውስጥ ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ኦህዴድና ብአዴን ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ፀረ-ለውጥ የሆነ እንቅስቃሴ በዚያው በኢህአዴግ ውስጥ ይታያል፡፡ ይሄ የፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴ ቡድን፣ ነገሮችን አሁንም በኃይል፣ በጡንቻ ለማፈን የሚፈልግ ነው፡፡ ህወሓት እና ደኢህዴን በተግባር ከለውጥ አራማጆቹ ጋር ሲላተሙ እያየን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለውጥ የሚመጣው ዝም ብሎ የለውጥ ኃይል ስላለ ብቻ አይደለም፡፡ ለውጡን የሚቀበል ሌላ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ አክቲቭና ፓሲቭ ብለን ልንመድባቸው እንችላለን፡፡ አክቲቭ የሆነው ለውጡን የሚመራው ነው፡፡ ፓሲቭ የምንለው ደግሞ የሚመጣውን ለውጥ ተቀብሎ ለማስተናገድ የተዘጋጀው ኃይል ነው፡፡ አሁን ፀረ ለውጥ የሆኑ ኃይሎች አስቀድሜ እንደገለፅኩት መሃል ላይ አሉ፡፡ የእነዚህ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ለሚለው እንግዲህ፣ እሳት ወርቅን የማቅለጥ ኃይል አለው፡፡ ወርቅም ይሄን ኃይል ተቀብሎ በማስተናገድ ወደ ፈሳሽነት ተቀይሮ፣ እንደገና ጠጥሮ፣ አብረቅርቆ አምሮ ይወጣል፡፡ ይሄ የሆነው ለውጡን ለመቀበል ፍቃደኛ ስለሆነ ነው። በአንፃሩ ድንጋይ ደግሞ በእሳት ቢቃጠል በቀላሉ ለውጡን ተቀብሎ ወደ ፈሳሽነት አይለወጥም። ተቃጥሎ መፈረካከስ ነው ዕጣ ፈንታው፡፡ ተፈጥሮአዊ ለውጥን ለመቀበል ፍቃደኛ የማይሆን፣ ዕጣ ፈንታው ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ ይሄ ሲሆን ደግሞ በሃገር ላይም ጉዳት ያስከትላል፤ ሀገርንም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ስለዚህ ለውጥን ተቀብሎ ማስተናገድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡   

በኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል  
ከ1997 በኋላ ኢህአዴግን በሰላማዊ መንገድ ተደራጅቶ መታገል አልተቻለም፡፡ ጠንከር ብሎ የተቃወመ ወይ ግንቦት 7 አሊያም ኦነግ ተብሎ በመፈረጅ ይታሰራል፡፡ ፍፁም ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ እነ በቀለ ገርባ፣ እነ ዮናታን ተስፋዬ፣ እነ እስክንድር ነጋና  ሌሎችም ታስረዋል፡፡ ይሄ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ሌላው አማራጭ በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ መታገል ነው፡፡ ከ1997 በኋላ አብዛኛው የኦሮሚያና የአማራ ክልል ወጣቶች፣ በየዩኒቨርሲቲው በነበረው ምልመላ፣ ኢህአዴግ ውስጥ ነው የገቡት፡፡ እነዚህ ወገኖች እንግዲህ አሁን የህዝብን ጥያቄ መስማት እየጀመሩ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ማስተጋባትና ኢህአዴግን ከውስጥ ሆነው ለመቀየር ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ 

በ2007 ዓ.ም መቀሌ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በቀረበ አንድ ጥናት፣ ወደ 16 ሺህ አካባቢ በዝቅተኛና በመካከለኛ የአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙት የተሃድሶ ስልጠና ቢሰጣቸውም ጠባብነትና ትምክህተኝነትን መቋቋም አልቻልኩም፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አጀንዳ ነው የሚያራግቡት ብሎ ነበር፡፡ ይሄ የለውጥ ኃይል ገና በ2007 ዓ.ም ኢህአዴግ ውስጥ መግባቱን ያሳየናል፡፡ እነዚህን አመራሮች ኢህአዴግ መከታተል ቢጀምርም ውጤት ያመጣበት ግን አይመስልም። እዚህ ላይ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ የማስተር ፕላኑ አጀንዳ ዋነኛው ነው፡፡ ኦህዴድ ውስጥ ያሉ እነዚህ አመራሮች ናቸው አጀንዳውን ወደ ህዝቡ ያወረዱትና ለህዝብ ያሳወቁት፡፡ ተቃውሞውም የጀመረው ከእነሱ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ከተካሄዱ ውይይቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በጎንደርና በባህርዳር የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችም ሊካሄዱ የቻሉት የእነዚህ አመራሮች ይሁንታ ታክሎበት ነው። መጨረሻ ላይ በኦህዴድ ውስጥ ይህን የለውጥ መንገድ ከህዝብ ጋር ሲያቀነቅን የነበረው ኃይል፣ የህዝቡን ጫና ተጠቅሞ ወደ ስልጣን መጣ። የዚህ አመራር አመጣጥ ከተለመደው አካሄድ ውጪ ነበር፡፡ ይህ አመራር ወዲያው ነው የለውጥ እንቅስቃሴ የጀመረው፡፡ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ በቀጥታ ሄዶ የተላተመው ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ ተቃዋሚዎች እንደሌሉና ሃሳቡን ሊያስተጋቡለት እንደማይችሉ ስለተረዳ፣ ተስፋ ያደረገው በዚህ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የለውጥ ኃይል ላይ ነው፡፡ አሁን ባለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ የተደራጀ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል ስለሌለ፣ ለውጡ ሊመጣ የሚችለው፣ኢህአዴግ ውስጥ እየተደረጉ ባሉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ነው፡፡ 
የህዝብ ጥያቄና የኢህአዴግ መርህ 
ለኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለምና መርህ ተገዢነታቸው እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ኦሮሚያ ውስጥ የመጣው ለውጥ እንዴት ሆኖ መጣ የሚለውን ያለመረዳት ችግር በአብዛኞቻችን ዘንድ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሄን ለውጥ እነዚህ አመራሮች ያመጡት ከድርጅታቸው በላይ የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ውጪ አማራጭ ስላልነበራቸው ነው፡፡ እነሱ ከዲሞክራሲ ማዕከላዊነት ወጡ አልወጡ ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ እየተቀበሉና እያስተናገዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በ2008 ላይ ባቀረበው ሪፖርት፣ ከታህሳስ እስከ መጋቢት ወር ብቻ ኦሮሚያ ውስጥ 14 የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን፣ 101 ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም 14 አመራሮች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ቤቱ የተዘረፈ፣ የተቃጠለ አመራር  በርካታ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ይሄ ከሆነ እያንዳንዱ የኦህዴድ አባል ህይወቱ አደጋ ላይ እንደወቀደ አመላካች ነበር፡፡ በጣም አደገኛ እንቅስቃሴ እንደነበር ተረድተው ነው፣ ተሰብስበው አሁን ያለውን አመራር ወደ ስልጣን ያመጡት፡፡ ይህ አዲስ ኃይል ደግሞ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ከመቀበል ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም፡፡ አዲሶቹ አመራሮች፤”አለቃችን ህዝቡ ነው፣ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ተቀብለን ከማስተናገድ ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም” ብለው ነው መንቀሳቀስ የጀመሩት፡፡ ይህን ሁኔታ የኢህአዴግ መርህና ደንብ የሚያስቆመው አይደለም፡፡ ይህን ለውጥ ለማድረግ አመራሩ ሲወስን ፍላጎቱን ማስተናገድ የማያስችል መርህና ደንብ ይወገዳል ማለት ነው፡፡
 አሁን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አካሄድም ያንን ነው እያመጣ ያለው፡፡ ከኢህአዴግ መርህ ውጪ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ፖለቲካው የሚገባው ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምደባ ጉዳይ፣ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ለምን እኔ ሳልጠይቅ ወደ ክልሌ ገቡ የሚለው ተቃውሞ፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠር፣ በኦሮሞና አማራ ህዝቦች መካከል ግንኙነት መፍጠርና የመሳሰሉት ከኢህአዴግ መርህ ውጪ ናቸው። አሁን በኦህዴድና በብአዴን መካከል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ተቀብሎ ማስተናገድ እንጂ እንቅስቃሴውን በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት መርህ ውስጥ ለማስገባት መሞከር ድርጅቱን በማፍረስ ነው የሚጠናቀቀው። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው፣ ከእንግዲህ አሁን ያለው የኦህዴድ አመራር አንዲት ኢንች እንኳ ወደ ኋላ መመለስ እንደማይችል ነው፡፡ ምክንያቱም እንዴት ሆኖ ወደ ስልጣን እንደመጣና ቅቡልነት እንዳገኘ ያውቀዋል፡፡ ይሄ አካሄድ ደግሞ የኢህአዴግን በርካታ መርሆዎች እንደሚቀይር ጥርጥር የለውም፡፡ 

እውን የህወሓት የበላይነት አለ?  ይህ ሃገር የሚመራው በህገ መንግስቱ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ደግሞ የህወሓት ሙሉ ፕሮግራምና የፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እዚህ ጋ ዋናው ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ጨዋታውን ማን ተጫወተ የሚለው ሳይሆን የጨዋታውን ህግ ማን አስቀመጠ የሚለው ነው፡፡ ይህ የጨዋታውን ህግ ያስቀመጠ ቡድን፣ በጨዋታው ሜዳ ላይ ራሱ ተጫወተም ሌሎች ተጫወቱም አሸናፊው ራሱ ነው። ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ “ህገ መንግስቱ በህወሓት ልክ የተሰፋ ጥብቆ ነው” ይሉታል። ሌሎች ሲለብሱት ወይ ይጠባል ወይ ይሰፋል። ህገ መንግስቱ በህወሓት ልክ የተሰፋ ጥብቆ ከሆነ፣ ብአዴን ወይም ኦህዴድ ሲለብሰው ወይ ይሰፋል አሊያም ይጠባል፡፡ ይህ ነው እየሆነ ያለው፡፡ የኦህዴድ ሰዎች ትንሽ ዝንፍ ካሉ፣ ኦነግ ይባላሉ፡፡ የብአዴን ሰዎችም ከተዛነፉ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ይባላሉ፡፡  ለዚህ ማጫወቻው ደግሞ የፀረ ሽብር ህጉ ነው፡፡ አሁን በፀረ ሽብር ህጉ ተከስሰው ከሚገኙ 1400 ያህል ሰዎች መካከል 412 በኦነግነት፣ 415 ያህሉ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሽብር ከተከሰሱት ሁለት ብቻ ናቸው ከትግራይ ክልል ያሉት፡፡ ይሄን አሃዛዊ መረጃ የጠቀስኩት፣ የፀረ ሽብር ህጉ እንዴት የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል እያገዘ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ የአንድ ድርጅት የበላይነት የሚረጋገጥበት ሌላው ማሳያ በፖለቲካ ልሂቃን እንቅስቃሴ ነው። አንዳንዶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ 3 ህወሓት ብቻ ናቸው ያሉት በማለት ይሞግታሉ። ይሄ ግን ሁነኛ መከራከሪያ አይደለም፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚለካው በባለስልጣናት ብዛት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ልሂቃኑ ቁጥርም ነው፡፡ እዚህ ሃገር ዛሬም ለፖለቲካ ለውጥ ማነቆ የሆነው ይህ የህወሓት የበላይነት ነው፡፡ 
ሌላው እዚህ ጋ ላነሳው የምፈልገው፣ አንድ የህወሓት አመራር፣ አይጋ ፎረም ላይ ያሰፈረውን ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ አመራር “አዲሱ የኦህዴድ አመራር ጤናማ አይደለም፣ መመርመር ያለበት ነው” ይላል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው፡፡ እኔ ጠፍጥፌ ልስራህ ማለት ነው? እሱ የምን ቴርሞ ሜትር ሆኖ ነው ጤንነቱን የሚመረምረው? በምን አግባብ ነው በኦሮሚያ ውስጥ የሚሰራን ፓርቲ፣ ህወሓት የሚመረምረው? እኒህን የማያቸው፣ የህወሓትን የበላይነት ያለማስደፈርና ያለማስነካት እንቅስቃሴ አድርጌ ነው፡፡ 

ያላጠፋ ይቅርታ አይጠይቅም  
ለእኔ በመንግስት መዋቅርና በፓርቲው መካከል እየተደረገ ያለው እየተቃረነ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይቅርታ በተጠየቀ ማግስት ቄሮ ላይ ምርመራ እጀምራለሁ ማለት የዚህ ተቃርኖ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል ይቅርታ ከተጠየቀ፣ ጥፋተኛ ነበርኩ ማለት ነው አንድምታው፡፡ ያላጠፋ ይቅርታ አይጠይቅም። ታዲያ ጥፋቱ በይቅርታ ብቻ የሚታለፍ ነው የሚለው ደግሞ ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ለኔ ግን የይቅርታ ጥያቄው ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በ2008 ዓ.ም ተጠይቋል፡፡ እንዲያውም ተደጋግሞ ተጠይቋል፡፡ የይቅርታ ጥያቄ ተደጋግሞ ሲቀርብ ደግሞ ትርጉም ያጣል፡፡ ለኔ የሰሞኑ የይቅርታ ጥያቄ የሚታየኝ በዚህ መልኩ ነው፡፡ 
ህዝብን አንድ የማድረግ አጀንዳ ማራመድ 
አንድ ፈረንሳዊ ምሁር “ዲስትኒክሽን” በሚል ባወጣው ጥናታዊ ፅሁፍ፤ በህዝብ፣ በሰዎች ውስጥ ልዩነትን በመፍጠር፣ ልዩነትን በማስፋት የማይለያዩትን የአንድ ሀገር ህዝብ በመለያየት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቡድን የመጨረሻ ዓላማና ግቡ በመለያየት ኃይል (separative power) የራሱን መሰረት ማደላደል ነው ይላል፡፡ አሁን በኛ ሀገር የተካሄደውም ይሄው የመለያየት ሃይልን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከአንድነት ይልቅ ልዩ የሚያደርገን ነገር በህዝቦች መካከል ሲሰበክ ነው የኖረው። እንዲህ አይነት ባህሪ ያለው ኃይል፤ በሰዎች መቆራቆዝና መለያየት የራሱን ስልጣን ማደላደል ሁነኛ ተግባሩ ነው፡፡ ለምሳሌ የቆየ የአብሮነት ታሪክ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ህዝብ፣ ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸውን አጉልቶ ማንፀባረቅ፣ አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ አድርጎ ማቅረብ —- እነዚህ ሁሉ ሲደረጉ ተመልክተናል፡፡
በአጠቃላይ የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄን ዜጎች በዜግነታቸው ብቻ እንዳያነሱ እንቅፋት የሆነ ስርአት ነው ሲገነባ የቆየው፡፡ ህዝብን በመለያየት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተሳሰብን ማፍረስ የሚቻለው በተቃራኒው ህዝብን አንድ የማድረግ አጀንዳ በማራመድ ነው፡፡ በዚህ ላይ የተመሰረተ አንድነት በማምጣት ነው፣ ይሄን የመለያየት አካሄድ ማፍረስ የሚቻለው፡፡ አቶ ለማ ባህር ዳር መሄዳቸው ምሳሌያዊ እርምጃ ነው፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመማር ማስተማር ከ16 ዓመት በላይ ቆይቻለሁ። ብዙ ጊዜ የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ሲጋጩ እታዘብ ነበር፡፡ አቶ ለማ ባህር ዳር ከሄዱ በኋላ ግን መተሳሰቡ መተዛዘኑ ሲበረታ ነው ያየሁት፡፡ ይሄ ደግሞ ወረት አይደለም፡፡ ፅኑ መሰረትና መነሻ የነበረውና እንደገና የታደሰ ስለሆነ ከዚህ በኋላ አይናድም፡፡          
*** 

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ 

2 thoughts on “የዓመታት አፈና ያስከተለው የፖለቲካ ቀውስ

  1. TPLF leaders and their Ideology since 1978 anti religion, anti Amhara/Oromo, anti Imperialism, and against basic principles of gender equality, rule of law and freedom of press. We are mot expecting any thing good from TPLF leaders they are discarding democracy; a return to the Iron fist. Since 2014 an explosion of terrorist violence, Autocrats use of more brutal tactics, and the state of freedom worssened significantly in nearly every part of Ethiopian region. TPLF no willing ro change ita policy and no longer official government leader. The group secret plan is to promote Terrorism through out the region and inciting genocide. Amhara and Oromo people are fighting for their existence, they knew the plan of TPLF. Regional strong leaders are the one kept the nation’s together for now so far TPLF plan failed. It is time to promoting democratic development through independent Truth and Reconciliation commission for betterment of future Ethiopia. Gi. Haile( Voice of peace Democracy and Freedom.)

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡