​የትግራይ ልሂቃን “ልሙጥ” የፖለቲካ አመለካከት መንስዔ ምንድነው? 

በተወሰነ ደረጃ የማክረር ዝንባሌ ካላቸው የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ጋር በማደርገው ውይይት በጣም አድካሚና አስቸጋሪ የሚሆንብኝ “የትግራይ ሕዝብን በጅምላ መፈረጅ የለበትም” ብሎ መከራከር ነው። በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሀገርና አከባቢ የሚገኝ ማህብረሰብን በጅምላ መፈረጅ ስህተት ነው። እንደ እኔ ደግሞ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አብሮ የኖረ ሰው የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በጅምላ ሲፈረጅ እያየና እየሰማ አምኖ መቀበል ይከብዳል። ሆኖም ግን፣ የማህብረሰቡን ስነ-ልቦና በጥልቀት መረዳት እስካልተቻለ ድረስ ለብዙ አመታትም ከሕዝቡ ጋር አብሮ የኖረ ሰው ማህብረሰቡን በጅምላ ሊፈርጅ ይችላል ወይም ደግሞ በሌሎች የሚሰነዘርን ጅምላ ፈረጃ በግልፅ መቃወም ይሳነዋል። ይህ ከትግራይ ህዝብ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ችግር ነው።  

ታዲያ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች በተለየ በጅምላ የሚፈረጅበት ምክንያት ምንድነው? አብዛኞቹ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የህወሓት ተቃዋሚ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ጭምር እንደሚሉት፣ በተለይ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ለትግራይ ሕዝብ የተለየ ጥላቻና ዘርኝነት ስላላቸው አይደለም። አብዛኞቹ ብዙሃኑን የትግራይ ሕዝብ ከፖለቲካ ልሂቃኑ ለመለየት ጥረት ያደርጋሉ። ነገር ግን፣ በዚህ ረገድ አንድ መሰረታዊ ችግር አለ። 
የኦሮማራ ልሂቃን የኢህዴድና ብአዴን አባላትና ደጋፊዎች፣ ትምክህተኞች እና ጠባብ ብሔርተኞች፣ ኪራይ ሰብሳቢ የሆኑ ተቃዋሚዎች፣ እንዲሁም ኦነግ እና አግ7 በማለት መከፋፈል ይቻላል። እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች በጭራሽ አንድ ዓይነት አቋምና አመለካከት ሊኖራቸው አይችልም። ነገር ግን፣ በተለይ የትግራይ ሕዝብን ጥቅምና ጉዳት በተመለከተ በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች መካከል ይቅርና በዓረና እና ህወሓት መካከል የሰናፍጭ ፍሬ የምታክል ልዩነት ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል።  

በትግራይ ተወላጆች ላይ የሆነ ችግር ሲደርስ “ሁሉም” እንኳን ባይሆን አብዛኞቹ ወይም የተወሰኑት የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ሁኔታውን ይቃወማሉ። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ለክልሉ ተወላጆች ድጋፍና አሌኝታነታቸውን ይገልፃሉ። ነገር ግን፣ ከህወሓት ደጋፊዎች እስከ ተቃዋሚዎች፥ ከሞላ-ጎደል “ሁሉም” የትግራይ ልሂቃን ችግሩን ከመጠን በላይ በማጉላት ያጋንኑታል፥ ያራግቡታል። በዚህ ረገድ በ2008 ዓ.ም በጎንደር የተከሰተው ችግርን ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በመቱና ወልዲያ የተፈጠሩትን ግጭቶች ማስታወስ በቂ ነው። 

በአንፃሩ በዋናነት በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች በሚመሩት የደህንነትና መከላከያ ሰራዊት በአማራና ኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ ግፍና በደል ሲፈፅሙ አብዛኞቹ የክልሉ ተወላጆች ምሬትና ተቃውሟቸውን ሲገልፁ፣ በጣት ከሚቆጠሩ ግለሰቦች በስተቀር የትግራይ ልሂቃን ዝምታን ይመርጣሉ። ፅንፈኛ የህወሓት ደጋፊዎች ደግሞ በሕዝብ ላይ በደልና ጭቆና የፈፀሙትን የፀጥታ ኃይሎች እና በጉዳዩ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በማወደስ፣ በሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ችግር ደግሞ በማጣጣል በቁስል ላይ እንጨት ይሰድዳሉ። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ብቻ በኦሮሚያ ክልል በአምቦና ጨለንቆ፣ በአማራ ክልል ደግሞ በወልዲያና ቆቦ ከተሞች የመከላከያ ሰራዊቱ የፈጸመውን ጭፍጨፋ መጥቀስ ይቻላል።  

በተለይ በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን በደልና ጭቆና በማውገዝ ወይም በመቃወም ረገድ በህወሓት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል ባለፉት ሦስት አመታት በጣም እየጠበበ ቢሄድም መጠንኛ የሆነ ልዩነት መኖሩ አይካድም። ሌላው ቢቀር የዓረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎች በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ማውገዝ ቢሳናቸው ልክ እንደ ህወሓቶች በሰው ቁስል ላይ እንጨት አይሰድዱም። የትግራይ ሕዝብን በተመለከተ ግን በህወሓት እና ዓረና አባላት መካከል ምንም ልዩነት የለም። ከላይ በተጠቀሱት ግጭቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከሞላ-ጎደል ሁሉም ልሂቃን ከመጠን በላይ ያራግቡታል። 

በተመሳሳይ ትግራይን በተመለከተ አንድ የተለየ መልካም ነገር ከተገኘ ለሌሎቻችን እስኪሰለቸን ድረስ ያለ-ቅጥ ያጋንኑታል። ለምሳሌ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት በሚወዳደሩበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ ይበቃል። በእርግጥ ዶ/ር ቴድሮስ ከአብዛኖቹ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በተሻለ በሌሎች ብሔር ተወላጆች ዘንድ ድጋፍና ተሰሚነት ነበራቸው። ሆኖም ግን፣ ዶ/ር ቴድሮስ በአንድ ግዜ ወደ መላእክትነት ተቀይሮ ከህወሓት ደጋፊዎች እስከ ተቃዋሚዎች በአንድነት ሲረባረቡ ማየት ነገሩን በጣም አሰልቺ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጲያዊያን በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። 

በመሰረቱ የትግራይ አርሶ-አደር ከሌሎች የኢትዮጲያ አርሶ-አደሮች ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም። እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አርሶ-አደሮች በላቡ ጥሮ-ግሮ የሚኖር ነው። በአጠቃላይ አብዛኛው የትግራይ ማህብረሰብ ከኑሮ ሩጫና ድካም የተረፈ ለፖለቲካ ቁማር ጨዋታ የሚሆን ግዜ የለውም። ጥቅምና ጉዳቱን ከማህብረሰቡ አባላት ጋር ተጋርቶ ይኖራል። አብዛኞቹ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚያደርጉት ጥቅምና ጉዳቱን ከመጠን በላይ አጋንኖ የሚያቀርብበት ምክንያትና መንገድ የለውም። 

የራስን ጥቅም ሆነ ጉዳት በአንድ ድምፅ ከመጠን በላይ ማጋነን፣ በአንፃሩ የሌሎች ጥቅምና ጉዳት ማጣጣል በትግራይ እና በኦሮማራ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ለሚስተዋለው ልዩነት እና አለመግባባት ዋና መንስዔ ነው። በዚህ መሰረት፣ የትግራይ ልሂቃን ስለራሳቸው ሕዝብና ስለ ሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ያላቸው የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ወጥና ተመሳሳይ ነው። የሁሉም የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የክልሉን ህዝብ ጥቅም በማስቀደምና ጉዳቱን ከመጠን በላይ በማጋነን፣ እንዲሁም የሌሎችን ጥቅም በማሳነስና ጉዳታቸውን በማጣጣል ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ከተቀሩት የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ጋር ዓይንና ናጫ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። 

ነገር ግን፣ የትግራይ ህዝብን ጥቅምና ጉዳት በማጋነን ሆነ የሌሎችን ጥቅምና ጉዳት በማጣጣሉ ተግባር የተሰማሩት የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው። እነዚህ ልሂቃን በጥሩም ሆነ በመጥፎ ሁኔታ ማህብረሰቡን ይወክላሉ። ምክንያቱም የልሂቃኑ ሃሳብና አመለካከት ከራሳቸው አልፎ የብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል አቋምና አመለካከት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። 

በዚህ መሰረት፣ የልሂቃኑ ልሙጥ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የትግራይ ሕዝብ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን በሕዝብ ስም የራሳቸውን ጥቅምና ጉዳት ከመጠን በላይ በማጋነናቸው እና የሌሎች ጥቅምና ጉዳት በማጣጣላቸው ምክንያት የተፈጠረው ቂምና ጥላቻ በብዙሃኑ የትግራይ ሕዝብ ላይ ያርፋል። ከዚህ በመነሳት የትግራይ ሕዝብን በልሂቃኑ ልክ ልሙጥ እንደሆነ ተደርጎ በጅምላ ይፈረጃል። የፖለቲካ ሁከትና ብጥብጥ በተነሳ ቁጥር ያለ አግባብ ተጠቂ ይሆናል። በክልሉ ተወላጆች ላይ ከሚደርሰው የአካልና ንብረት ጉዳት በተጨማሪ፣ በሥነ-ልቦና ረገድ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።   

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚስተዋለውን ጅምላ ፍረጃና ጥላቻ፣ ብሎም ጥቃት ለማስቀረት፣ “የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ለምን ልሙጥ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ኖራቸው?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። የዚህ ችግር መሰረታዊ መንስዔ መለየትና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት በክልሉ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መገለል ለማስቀረት፣ እንዲሁም በአንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ እየተጠራቀመ ያለውን ቂምና ጥላቻ ለማስወገድ ያስችላል። ስለዚህ የትግራይ ልሂቃን ልሙጥነት ከምን የመነጨ ነው? 

የዓረና ፓርቲ አባላትና አመራሮች በመቀለ ያደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ (2010 ዓ.ም)

የትግራይ ልሂቃን ልሙጥነት የህወሓት ጭቆና እና አፈና ምክንያት የተከሰተ ችግር ነው። ምክንያቱም የህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የራሱ የሆነ መጀመሪያና መጨረሻ አለው። የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል ማለት የድርጅቱን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት መጨረሻ ላልተወሰነ ግዜ ማራዘም ወይም ማስቀጠል ነው። በዚህ መልኩ፣ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በዘላቂነት ለማስቀጠል አዲስ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳይፈጠር ማድረግ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ የህወሓት የበላይነትን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻለው በማህብረሰቡ አባላት ላይ ከፍተኛ ሽብርና ፍርሃት በመፍጠር የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችን በማጥፋት ነው። 

እንደ ምክንያታዊ ፍጡር እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ ግንዛቤና አመለካከት አለው፤ በራሱ ሃሳብና ፍላጎት፣ ምርጫና ፍቃድ መንቀሳቀስ ይችላል። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ አዲስ የሕይወት ጅማሬ ነው። ስለዚህ የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል የሚቻለው በትግራይ ሕዝብ ስም የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች በማጥፋት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ተገዢ የሆነ ልሙጥ የፖለቲካ ማህብረሰብ በመፍጠር ነው። እንደ “Hanna Arendt” አገላለፅ፣ እንደ ህወሓት ያለ አምባገነን ፖለቲካዊ ቡድን በትግራይ ሕዝብና በሰማዕታት ሰበብ የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች ከማህብረሰቡ ውስጥ ጨርሶ ያጠፋል፡-  

“Terror eliminates individuals for the sake of the species—not only those who eventually become the victims of terror, but in fact all men insofar as this movement, with its own beginning and its own end, can only be hindered by the new beginning and the individual end which the life of each man actually is. With each new birth, a new beginning is born into the world, and a new world has potentially come into being.”  On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የህወሓት የፖለቲካ ስልጣንና የበላይነት የተመሰረተው ከማህብረሰቡ ውስጥ “ግለሰቦችን” (individuals) በማጥፋት አዲስ የፖለቲካ ጅማሬን በማስወገድ ነው። የህወሓት የበላይነት እንዲቀጥል አዲስና የተለየ ሃሳብ የሚያፈልቁ ግለሰቦች በነፃነት መንቀሳቀስ፥ ማሰብ፥ መናገርና መፃፍ የለባቸውም። ለዚህ ደግሞ የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን የሚገድቡ የሕግ አዋጆችን በማውጣት የሕግ-የበላይነትን መናድ፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነትን መጣስ፣ ተጠያቂነትና የሕግ-የበላይነት የጎደለው ሥራና አሰራር መዘርጋት፣ በዚህም የክልሉ ሕዝብ በፍርሃት ቆፈን እንዲያዝ ያደርጋል። 

በአጠቃላይ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ልሙጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት እንዲኖራቸው የተደረገው ህወሓት በፈጠረው የፍርሃት ቆፈን አማካኝነት ነው። ግለሰቦች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በመተው፣ በአንድም ሆነ በሌላ በመልኩ የህወሓት የአቋምና አመለካከት እንዲያራምዱ ተደርገዋል። በዚህ መሰረት፣ ለህወሓት ሽብርና ፍርሃት ተገዢ ሆነዋል። ስለዚህ የትግራይ ልሂቃን ራሳቸውን ከልሙጥ የፖለቲካ አመለካከት ለማውጣትና ከሌሎች የኢትዮጲያ ልሂቃን ጋራ ለመግባባት፣ ራሳቸውን ከህወሓት አምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን ከተቀረው የኢትዮጲያ ሕዝብ እየተነጠሉና እየተገለሉ በመሄድ በመጨረሻ የራሳቸውን ሆነ የሕዝቡን ጥቅምና ተጠቃሚነት ማረጋገት ይሳናቸዋል።  

3 thoughts on “​የትግራይ ልሂቃን “ልሙጥ” የፖለቲካ አመለካከት መንስዔ ምንድነው? 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡