​የሰውነት ክብርን ማስከበር፥ ውርደትን ማዋረድ – በአደዋ! 

እንደ ምክንያታዊ ፍጡር ነፃነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ማሰብና መወሰን፣ በራሱ ሃሳብ እና ፍቃድ መመራት ይችላል። “ነፃነት” ማለት በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል ነው። በመሆኑም እንደ ምክንያታዊ ፍጡር ነፃነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። 

ነፃነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደመሆኑ የእያንዳንዱ ግለሰብ እንቅስቃሴ የሌሎች ሰዎችን ነፃነት መገደብ የለበትም። እያንዳንዱ ግለሰብ የሌሎችን ፍላጎትና ምርጫ በማይገድብ መልኩ የሚንቀሳቀስ ከሆነ የሁሉም ሰዎች ነፃነት ይከበራል። ስለዚህ የሁሉም ሰዎች ነፃነት የሚከበረው የእያንዳንዱ ግለሰብ እንቅስቃሴ በእኩልነት መርህ የሚመራ ከሆነ ነው። እኩልነት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ የመነጨ የተግባራዊ እንቅስቃሴና ግንኙነት መርህ ነው። 
እያንዳንዱ ሰው በእኩል ዓይን መታየት ይፈልጋል። “እኩልነት” የሰው ክብር (human dignity)፤ የሰውነት ማዕረግ፥ ወግ ነው። “አዋረደ” ማለት ከሰው ክብር፥ ከሰውነት ማዕረግ፥ ወግ፣ ከእኩልነት ደረጃ ዝቅ አደረገ ነው። “ውርደት” (humiliation) ከሰውነት ከብር ዝቅ ማለት፥ ቅሌት፥ መቅለል፥ በሚያሳፍር ሁኔታ መገኘት ነው። 

በዚህ መሰረት፣ “እኩልነት” የሰው ክብር፥ የሰውነት ማዕረግ፥ ወግ ሲሆን “ውርደት” ደግሞ ከእኩልነት ደረጃ መውረድ፥ የሰውነት ክብርን ማጣት፥ በእኩል ዓይን አለመታየት፥ ከሌሎች በታች መሆን ነው። የአንድ ወገን የበላይነት (domination) ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት የሰውነት ክብርን በመግፈፍ በሌሎች ሰዎች ላይ ውርደት ያስከትላል። 

“The historic man would appear to be a product of a choice between abject submission or bondage on the one hand, for the sake of self-preservation and, on the other, a quest for dignity, even if this leads to death. In one form or the other, the quest for human dignity has proved to be one of the most propulsive elements for wars, civil strife and willing sacrifice… [The] loss of dignity would affirm the nullification of human status” Reith Lectures 2004: Climate of Fear by Wole Soyinka, Lecture 4: The Quest for Dignity: 28 April 2004 

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የአንድ ወገን የበላይነት የሌሎችን የሰውነት ክብር በመግፈፍ ለውርደት ይዳርጋል። በመሆኑም የአንድ ወገን የበላይነትን መከላከል እኩልነትን ማረጋገጥ ነው። በእኩልነት ሰው-መሆን ይረጋገጣል፣ የሰውነት ክብርን ማጣት ከሚያስከትለው ውርደት ይታደጋል። በዚህ ረገድ “Evelyn Waugh” የተባለው እንግሊዛዊ ፀኃፊ ኢትዮጲያ ከነጮች እኩል በራሷ መቆም ሆነ ምንም ነገር ማድረግ የማትችል ስለሆነ ለነጮች ተገዢ መሆን እንዳለባት የገለፀበት ሁኔታ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡-

“Abyssinia could not claim recognition on equal terms by the civilized nations and at the same time maintain her barbarous isolation; she must put her natural resources at the disposal of the world; since she was obviously unable to develop them herself, it must be done for her, to their mutual benefit, by a more advanced power.” Evelyn Waugh, Waugh Abroad: Collected Travel Writing/Evelyn Waugh (New York: Everyman’s Library)

በአጠቃላይ የቅኝ-ግዛት ኃይሎች በኢትዮጲያ ላይ ወረራ የፈፀሙበት ምክንያት የነጮችን የበላይነት እና ኢትዮጲያዊያን የበታችነት ለማረጋገጥ ነው። በአንፃሩ ኢትዮጲያዊያን ወደ አደዋ የዘመቱት ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር በማሸነፍ የነጮች የበላይነትን ለማክሸፍና የጥቁሮችን እኩልነት ለማረጋገጥ ነው። 

በዚህ መሰረት፣ “የአደዋ ጦርነት” የሰው ልጆችን እኩልነት ለማረጋገጥ፣ የጥቁሮችን የሰውነት ክብርና ማዕረግ ለማስከበር፤ ኢትዮጲያዊያንን ከሽንፈት፥ ውርደት፥ ሃፍረት፥ ባርነት ለመታደግ ጀግኖች የተፋለሙበት፥ የተዋደቁበት ነው። በደምና አጥንታቸውን የጥቁሮችን ነፃነትና እኩልነት ያረጋገጡበት፣ የሰውነት ክብርና ማዕረግ ያስከበሩበት፣ ትውልድን ከአሳፋሪ ሽንፈት፥ ሃፍረትና ውርደት የታደጉበት ነው። ስለዚህ “አደዋ” ማለት የሰው ልጅ ክብር የተከበረበት፣ የሰው ልጅ ውርደት የተዋረደበት ነው። 

የአደዋ ጦርነት የኢትዮጲያኖች ነፃነትና ሉዓላዊነት የተከበረበት ብቻ አይደለም። በእርግጥ የአደዋ ድል ከኢትዮጲያዊያን አልፎ ለአፍሪካዊያን የእኩልነትና ነፃነት ትግል ፈር ቀዳጅ ነው። ለአፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች የእኩልነትና ነፃነት ተምሳሌት ነው። የአደዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለም ክፍልና የታሪክ ዘመን በባርነትና ጭቆና ስር ለሚገኙ ሕዝቦች የድል ተስፋና የፅናት ምልክት ነው።