​የፓርላማው የመመርመር ስልጣን (ከ”anonymous”)

ጥር 22 ቀን 2010 የጉምሩክ ባለስልጣናት ተወካዮች ምከር ቤት (ፓርላማ) ቀርበው የመስሪያ ቤታቸውን የግማሽ አመት ሪፖርት አቅርበው ከምከር ቤት አባላቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። በጥያቄና መልሱ ወቅት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከመጉዳት አልፈው የፖልቲካ ቀውስ እየፈጠሩ ናቸው፣ በእነዚህ ሀይሎች ጡንቻ የጉምሩክ ባለስልጣን ራሱ ታስሯል፣ ለብሄር ግጭት ምክንያት ሆነዋል፣ ወዘተ የሚባልላቸው “ኮንትሮባንዲስቶች” ማንነት ይገለጽልን ብለው የምከር ቤት አባላቱ ቢጠይቁም የባለስልጣኑ ሀላፊዎች በጥያቄው መሰረት ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የባለስልጣኑ ሀላፊዎች የኮንትሮባንዲስቶቹን ማንነት እንደሚያውቁ አምነው፣ ነገር ግን ስማቸውን ለምን እንደማይናገሩ የሰጡት ምክንያት “ቀንደኞቹን ለይተን በመንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው ግብረሀይል ስላቀረብን የሚወሰደውን እርምጃ በጋራ ብናይ ይሻላል” የሚል ነበር። ፓርላማውም እምቢተኛነታቸውን አክብሮ ጉዳዩን በዝምታ አልፎታል። ይህ አሳዛኝም አስገራሚም ነው።


ህገመንግስቱ አንቀፅ 55(17) እና አንቀፅ 55(18) ላይ ምክር ቤቱ የፌደራል የመንግስት ባለስልጣናትንና የህግ አስፈጻሚውን አካል (እንደ ጉምሩክ ባለስልጣን ያሉትን ማለት ነው) የመመርመርና እርምጃ የመውሰድ ስልጣን አለው ይላል። የተሻሻለው የኢ.ፊ.ድ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት የስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 470/1997 ደግሞ በአንቀጽ 7 ስር ምክር ቤቱ የፌደራል የመንግስት አካላትን የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት ዋና አላማ ናቸው ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ የዜጎች መብት፣ ሰላምና ፀጥታ መከበሩን፤ እንዲሁም ፍትሀዊና ፈጣን የልማት አቅጣጫ መኖሩን ማረጋገጥ ነው የሚሉት ይገኝበታል።

እንግዲህ “ኮንትሮባንዲስቶች” የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጎድተዋል፣ የፖለቲካ ቀውስ እየፈጠሩ ነው፣ የጉምሩክ ባለስልጣንን አኮላሽተዋል፣ ለብሄር ግጭት ምክንያት ሆነዋል፣ የሀገርና የህዝብን ፀጥታ አናግተዋል፣ ወዘተ እየተባለ የባላስልጣኑ ሀላፊዎች ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱና ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ የተሰጠውን ስልጣን ተንተርሶ በምርመራው ወቅት ላቀረበው ጥያቄ መልስ አንሰጥም ሲሉ ምክር ቤቱም አቅም የሌለው ይመስል ዝም ብሎ አልፏቸዋል። በዚህም ምክንያት ህዝብ የጣለበትን አደራና በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት ሳይወጣ ቀርቷል። የስም ዝርዝሩ በኮንትሮባንዲስቶቹ ላይ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት ለህዝብ ይፋ መደረግ የለበትም ቢባል እንኳ ለምክር ቤቱ አባላት በጽሁፍ ወይም በዝግ ስብሰባ እንዲነገር መደረግ ነበረበት። የመንግስት አስፈጻሚ አካል ጥያቄዎችን የሚመልሰው እርሱ መመለስ ሲፈልግ ብቻ ከሆነማ ምኑን ምርመራ ሆነ? 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወካዮች ምክር ቤት ትንሽ መነቃቃት እየታየበት መሆኑ አበረታች ነው። ነገር ግን በህግ የተሰጠውን ስልጣን አሁንም በተገቢው መጠን እየተጠቀመበት አይደለም። ፍርድ ቤቶቻችን ገና በህገ መንግስቱ መሰረት ነጻነታቸውን ያላወጁ ስለሆነ ለጊዜውም ቢሆን የአስፈፃሚውን አካል መቆጣጠር የሚቻለው በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ብቻ ነው። ስለዚህ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እባካችሁ በህግ የተሰጣችሁን ስልጣን በቅጡ ተረድታችሁ ህዝብ የጣለባችሁን ሀላፊነት በአግባቡ ተወጡ።