​“አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና መሆኗ አግባብ ነው?”…ተው ባክህ! 

ባለፈው ሳምንት፥ እሁድ ዕለት የቢቢሲ ቴሌቪዥን የአፍሪካ ፕሮግራም አዘጋጅ ስልክ ደውሎ በአፍሪካ ሕብረት እና ሙስና ዙሪያ ሊያናግረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። ፍቃደኝነቴን ስገልፅለት ስለ ኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ሙስና እና የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ. በ2018 ሙስናን ለመታገል መወሰኑን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች አነሳልኝ። በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት በሙስና የተዘፈቀ ከመሆኑም በተጨማሪ በማህብረሰቡ ሥነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ገለፅኩለት። ምክንያቱም የመንግስት ባለስልጣናት ሙስናን የተለመደ ተግባር አድርገውታል። ይህ በቁሳዊ ሃብትና ንብረት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይልቅ በሕብረተሰቡ ማህብራዊ እሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። 

የአፍሪካ ህብረት 

ከዴሞክራሲ አንፃርም ቢሆን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚጥስ ፍፁም ጨቋኝ እንደሆነ እየተናገርኩ ሳለ በመሃል ጋዜጠኛው አንድ ጥያቄ ጣል አደረገ። “የኢትዮጲያ መንግስት በሙስናም ሆነ በዴሞክራሲ ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት “በሞዴልነት” የሚጠቀስ አይደለም። ታዲያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ‘አግባብ ነው’ ትላለህ?” አለኝ። በጋዜጠኛው ጥያቄ ተናደድኩኝ፣ ለዚህ ዓይነት የሞራል ኪሳራ የዳረጉንን የኢህአዴግ መሪዎች ረገምኩኝ። 

ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንዲህ አልኩት፡- “የተባበሩት መንግስታት (UN) መቀመጫ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ የተደረገው ሀገሪቱ በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመዘርጋቱ ረገድ በዓለም ግንባር ቀደም ሚና ስላላት ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጲያ መላው ጥቁር ሕዝቦች ለነፃነትና እኩልነት የሚያደርጉትን ትግል ከፊት ሆና የመራች ሀገር ናት። የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ የሆነው በዛሬ መሪዎች የዘቀጠ ስብዕና አመለካከት ሳይሆን ኢትዮጲያ የአፍሪካዊያን የነፃነትና እኩልነት ትግል ከፊት ሆና የመራች በመሆኗ ነው። 

እርግጥ ነው አሁን ያሉት የኢትዮጲያ መሪዎች ሙሰኛና ጨቋኝ ናቸው። በተመሳሳይ የአሁኑ የአሜሪካ ፕረዜዳንት በታሪክ ከታዩት የአሜሪካ መሪዎች የለየለት ዘረኛና ፅንፈኛ ነው። የአሜሪካ መንግስት ዘረኞች እና ፅንፈኞች በተሰበሰቡበት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚመራ እንደመሆኑ “የአሜሪካ መንግስት በዴሞክራሲ ረገድ ለሌሎች የዓለም ሀገራት “በሞዴልነት” የሚጠቀስ ስላልሆነ የተባበሩት መንግስታት መቀመጫ ኒውዮርክ መሆኑ ‘አግባብ ነው’ ትላለህ? ጨቋኝና ሙሰኛ መንግስት ከዘረኛና ፅንፈኛ መንግስት በምን ይለያል?” እያልኩ ጋዜጠኛውን ወጥሬ ያዝኩት።

ጋዜጠኛው በሰጠሁት በምላሼ ተገርሞ እየሳቀ “በል እሺ… ነገ ጠዋት 2፡30 ላይ በ“BBC World Service” ቀጥታ ስርጭት ላይ ለመቅረብ ተዘጋጅ” አለኝ። ሃሃሃ…እኔ እኮ የምንጣጣው ኢንተርቪው እያደረገኝ መስሎኝ ነው። ለካስ እሱ “’እንዲህ ብዬ ብጠይቀው ምን ብሎ ይመልሳል?’ እያለ እየገመገመኝ ኖሯል። በማግስቱ በቀጠሮ ሰዓት ደውሎ በሰሜን ወሎ አከባቢ በዜጎች ላይ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ ለአንዲት ደቂቃ ያህል እንዳወራሁ የስልክ መስመሩ ጥራት ስለሌለው ቃለ-ምልልሱ ተቋረጠ። 

ለማንኛውም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አዲስ አበባ የሆነው በወቅታዊ በኢትዮጲያ መሪዎች ማንነት ወይም በመንግስታዊ ስርዓቱ ዓይነት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ኢትዮጲያ መላው የጥቁር ሕዝቦች፣ በተለይ ደግሞ አፍሪካዊያን ለነፃነትና እኩልነት ያደረጉትን ትግል ከፊት ሆና የመራች ሀገር በመሆኗ ነው። የኢትዮጲያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዕዋት ለሆኑ ጀግኖች ክብር ሲባል የተሰጠ ገፀ-በረከት ነው። አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የሆነችው በአጋጣሚ አይደለም። ወዳጄ ይሄ የአደዋ ድል ቱርፋት ነው! ካላመንከኝ ቀጥሎ ያለውን ፅሁፍ በጥሞና አንብበው፡- 

“As the sovereignty and national will of African communities became gradually subsumed into a Europe’s orbit, Ethiopia emerged as the romantic beacon of independence and dignity for those who aspire for change in these African societies. Ethiopian defeat of Italy at Adowa in 1896 had also helped redefine the modern Euro-African relationship with the West. Based on the fact that the United States and Europe were extending the reach of “white authority” around the globe, this first modern military defeat of Europeans by non-Europeans preserved Ethiopian independence, and out of Africa came hope for blacks around the world, especially in areas where racial discrimination and inequality was most extreme. …Ethiopia [is] the anchor upon which the idea of the common African struggle against European colonial powers was drafted within Africa and across the African Diaspora. The significance of Ethiopian civilization and independence led to its description in the twentieth century as “the black man’s last citadel,” which must be protected at all costs from European colonial designs.” Adejumobi, Saheed A. (2007), The history of Ethiopia: The Greenwood histories of the modern nations, ISSN 1096–2905)