በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ መካከል ያለው ዋና “በሽታ” የፌደራሉ መንግስት ነው! 

ትላንት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የሕዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፌ ነበር። የስብሰባው ቦታ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር ፅ/ቤት አዳራሽ ነው። ተሰብሳቢዎቹ ደግሞ ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቭል ማህበራት እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ሲሆን የውይይቱ መሪዎች ደግሞ ከዞን አስተዳደር የመጡ ኃላፊዎች ናቸው። 

የውይይቱ መሪዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጡ መድረኩን ከፍት ሲያደርጉ ተሰብሳቢዎች እንዳለ እጃቸውን አወጡ። ከተቀመጥኩበት የፊት መስመር ወደኋላ ዞሬ ስመለከት ሁሉም ሁለት እጆቻቸውን ያወጡ ይመስላል። እጁን ያላወጣ ሰው ማየት ተሳነኝ። ፊቴን ወደ መድረኩ ሳዞር የስብሰባው መሪዎች ለማን የመናገር እድል እንደሚሰጡ ግራ ገብቷቸዋል። 

በእርግጥ የረቂቅ አዋጁ ይዘት ከወራት በፊት በማህበራዊ ሚዲያዎች አፈትልኮ ከወጣው ጋር ከተወሰኑ ቃላት በስተቀር ልዩነት የለውም። አዋጁ ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ለኦሮሚያ ክልል እንደ “ልዩ ጥቅም” አቅርቧቸዋል። “ልዩ ጥቅም” የተባሉት በሙሉ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 41፥ 89፥ 90፥ 91፥ 92፥… የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ብሔራዊ ዓላማዎች ናቸው። 

በዚህ ረገድ፣ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ሲሰጥ የነበረው ሃሳብና አስተያየት መሰረታዊና በጣም ጠቃሚ ነበር። ሆኖም ግን፣ የስብሰባውን ሂደት ለመዘገብ ሆነ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ የተሰጡትን ሃሳብና አስተያየቶች ለብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ በቦታው የተገኘ ጋዜጠኛ ወይም ሌላ አካል አልነበረም። በመሆኑም በውይይቱ ወቅት በግሌ የሰጠሁትን ሃሳብ ጠቅለል አድርጌ በምስል በማጠናቀር በፌስቡክ ገፄ ላይ ያወጣሁት ሲሆን ይህን ማያያዣ በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ።

በመሰረቱ የከተማ፥ የክልል፥ የፌደራል ወይም ሌላ ዓይነት መስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እስካለው ድረስ ተጠሪነቱ ለመረጠው ወይም ለወከለው ሕዝብ መሆን አለበት። የፌደራል መንግስት ተጠሪነቱ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) ነው። 

በአንቀፅ 49(2) መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር “ሙሉ” ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተጠሪነቱ በነዋሪዎች ለሚመረጠው የከተማዋ ምክር ቤት መሆን አለበት። ነገር ግን፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(3) “የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት” እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህ ምክንያት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተገፍፏል። በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በራሳቸው የመወሰን ስልጣናቸው በፌደራሉ መንግስት ተገፍፏል። 

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 (1) መሰረት የፌደራሉ መንግስት ርዕስ ከተማ አዲስ አበባ ነው። በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ሕገ-መንግስት ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) የክልሉ ርዕሰ ከተማ መሆኗን ይደነግጋል። በመሆኑም፣ የፌደራሉ መንግስትና የክልሉ መንግስት ከርዕሰ ከተማዋ ላይ እኩል መብትና ስልጣን ይኖራቸዋል። ሆኖም ግን፣ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የፌደራሉ መንግስት በአንቀፅ 49(3) መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተሰጠውን ያልተገባ ስልጣን በመጠቀም በከተማና በክልሉ መካከል አፍራሽ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዚህ መሰረት የፌደራሉ መንግስት፤ 

  • 1ኛ፡- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደ ርዕሰ ከተማ በአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ላይ ያለውን ስልጣንና መብት በአግባቡ እንዳይጠቀም አግዶታል፣ 
  • 2ኛ፡- በከተማ መስተዳደሩ እና በክልሉ መስተዳደር መካከል የተለያዩ ተግዳሮቶች በመፍጠር በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርጓል፣ 
  • 3ኛ፡- በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት የኦሮሚያ ክልል ከአገልግሎት አቅርቦት፥ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና ሁለቱን በሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው “ልዩ ጥቅም” ዝርዝሩ በሕግ እንዳይወሰንና ተግባራዊ እንዳይደረገ እንቅፋት ሆኗል፣
  • 4ኛ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ያልተገባ አስተዳደራዊ ስልጣን በመጠቀም በከተማዋ ላይ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ያካሂዳል፣ በመልሶ-ግንባታና ሕገ-ወጥ ግንባታ ስም የከተማዋን ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ያፈናቅላል፣ 
  • 5ኛ፡- “የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በሚል ሰበብ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ አርሶ አደሮችን ያለ በቂ ካሳና የማቋቋሚያ ድጋፍ ከመሬታቸው ያፈናቅላል። 

በአጠቃላይ፣ የፌደራሉ መንግስት በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ መካከል የችግሮች ሁሉ መንስዔ ነው፡፡ አሁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ” በሚል ከቀረበው ረቂቅ በስተጀርባ ያለው የፌደራሉ መንግስት ነው። አዋጁ ለማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን “ልዩ ጥቅም” በማለት ይዞ የቀረበ ነው። ይህ አዋጅ በማንኛውም መልኩ ፀድቆ ተግባራዊ ከተደረገ ለሌላ አመፅ፥ ተቃውሞ፥ ብጥብጥ፥ ሁከት መነሻ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡